Friday, November 22, 2013

መከራችንን ያረዘሙ ነገሮች (ክፍል ሁለት )


በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ 



 ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር፥ ኢትዮጵያ የነፃነት ሃገር፥ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ታሪክ ነች። ይህች የብዙዎች የነጻነት ዓርማ የሆነች አገር፥ ዛሬ ዓይነቱ ብዙ በሆነ የመከራ ቀንበር ውስጥ ናት። የመከራችን ብዛቱና ስፋቱ የት እንዳደረሰን ነጋሪ አያስፈልገንም። መከራው ከመርዘሙ የተነሣ ከመከራው የምንወጣበትን በር ለማየት ተስኖናል። በክፍል አንድ ጽሑፋችን  ከዚህ ካለንበት የመከራ ማጥ እንዳንወጣ መከራችንን ያረዘመው ምንድነው የሚለውን መመልከት ጀምረናል። 
ወደ ሁለተኛው ክፍል ከመሄዳችን በፊት በተነሣንበት ርእስ ላይ ሊሰነዘሩ ከሚችሉ ጥያቄዎች ውስጥ አንደኛውን ገለጥ አድርጌ ማለፍ እፈልጋለሁ። ጥያቄውም በችግር ውስጥ ያለውንና በብዙ መንገድ የተጠቃውን ሕዝብ ለችግሩ ምክንያት አንተ ነህ ማለት ይቻላልን? የሚል ነው።  በሕዝባችን ላይ የደረሰውን ወይም እየደረሰ ያለውን ዓይነቱ ብዙ የሆነውን መከራ መካድ ማለት ከእውነት ጋር መታገል ነው፤ ሆኖም ግን የሕዝባችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመከራችን ምክንያት በሆኑት እጅ ልናስቀምጥ አይገባም። መፍትሔውን መፈለግ ያለብን ከራሳችን ነው። መከራችን እንዲህ የረዘመው፥ የመከራችን ምክንያቶች ከመፍትሔ ባሻገር ሆነው ሳይሆን፥ መከራችንን ሊያረዝሙ የሚችሉ ነገሮች በእኛ መካከል መገኘታቸውና እነርሱን ለማየት ድፍረት ማጣታችን ነው። 
የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፥ በችግሮቻችንናን የኢትዮጵያን መልካምነት በማይፈልጉ አካላት እጅ ሳይሆን በእኛ እጅ ነው። ይህን እውነታ ከልብ ከተቀበልነው፥ እኛ ደግሞ አሁን ያለንበትን ሁኔታ፥ የደረሰብንን  እየሆንን ያለነውን በእርጋታ በመመርመር መፍትሔ መፈለግ ይኖርብናል። በመሆኑም ባለፈው ጽሑፌ መከራችንን ካረዘሙት ነገሮች አንዱ ባለፈው ታሪካችን እሥረኛ መሆናችን መሆኑን ገልጬ  ነበር። በዚሁም ውስጥ የተመለከትነው የትላንቱ ማንነታችን ውስጥ እስረኞች በመሆናችን አንደኛችን ለትምክህታችንና የዛሬን ኃላፊነት ላለመቀበላችን ምክንያት ስናደርገው ሌሎቻችንን ደግሞ ለዛሬው ጥላቻችን እና ክፋታችን ምንጭ አድርገነዋል። ዛሬ ወደ ሁለተኛው እንሄዳለን። 
2. ልዩነታችንን ለዕድገታችን መሣሪያ ልናደርገው አለመቻላችን  

 የኢትዮጵያን ማኅበራዊ ሕይወት በተለይም ያለፉትን ስልሳ የፖለቲካ እሰጥ አገባ ዓመታትን ስንመለከተው፥ ስለ አንድነት ብዙ የተናገርንበት፥ በዚያው መጠን ደግሞ በብዙ የተለያየንበት ዓለም ነው። በረባ ባልረባው የፈጠርነው ልዩነት መንፈሳዊውንም ሥጋዊውንም ክፍል ከመሠረቱ አናግቶታል። በልዩነት የተፈጠሩት ክፍተቶች እጅግ አሳዛኝ የሆኑ ድርጊቶች እንዲታዩባቸው ምክንያት ሆነዋል።  ለምሳሌ እኔ አካል የሆንኩባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌነት እናንሳ፤ ባለፉት አርባ አመታት ውስጥ አንደኛውን ፓትርያርኳን አስገድላ፥ አራተኛዋን ፓትርያርክ አሳድዳ ዛሬ ከሦስት በላይ በሆኑ አካላት ተከፋፍላ የምትገኝ ተቋም ናት። 
በዚህ ራሱን ንጹሕ አድርጎ ጣቱን የሚቀስርና በምጽድቅነት የሚቆም አንድም አካል የለም። በፖለቲካውም ያለው ይኸው በመንፈሳዊው ተቋም ላይ ያየነው ነገር ነው። ደም አቃብቶን እርስ በእርሳችን ያጋደለን ልዩነት ብለን በመካከላችን ያመጣነው ነገር ነበር። ለአገር ለወገን በአንድነት ተነሣሥተው  በመገዳደል የጨረሱ ስንቶች ናቸው? በዚህ ያጣናቸውን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን እናስባለን? ለታላቅ ሀገራዊ ራዕይ በአንድነት ተቀምጠው፥ በራዕያቸው ሳይሆን በስብሰባ ሥርዓት «ጨዋታቸው ፈርሶ» የሕዝባቸውን አንገት ያስደፉ ስንቶች ናቸው? 
የአገራችንን ባሕል ያጠኑ የማኅበራዊ ኑሮና የሥነ ሰብዕ ጥናት  ጠበብቶች ከሙያቸው አንጻር የሚሉትን እንዲያካፍሉን እየለመንን እኛ ግን በመንፈሳዊ እይታ ራሳችንን የመረመርንበትን ስናቀርብ የሚከተሉት ዋና ዋና ነገሮች ልዩነታችን እንዲጎላና አንድነታችን እንዲደበዝዝ አድርጎታል። 

የአሳብ ልዩነት ጠላትነት መሆኑ 
በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል በመፈጠራችን፥ እኛ ሰዎች ስንባል ካገኘነው ታላቅ ስጦታ መካከል አንዱ ውስጣዊ ነጻነት ነው። ስሙን የዘነጋሁት አንድ የክርስትና ጸሐፊ ሲናገር « አብዮት የሚፈጠረው ሰው ሰውን ሊገዛው ሲሞክር ነው። ምክንያቱም ሰው በማንም እንዳይገዛ ሆኖ የተፈጠረ ነው» ብሎአል። ይህ ውስጣዊ ነጻነት ደግሞ በማንም እንደ ሮቦት ከመመራት ይልቅ ውስጣዊ ራዕያችንን ግባችንን እንድንፈልግ ይገፋፋናል። በአንድ በኩሉ የውስጣዊ ወይም ግላዊ ነጻነት፥ በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ወይም የወል ግብ አንዳንድ ጊዜ ውጥረት መፍጠሩ አይቀርም። 
በውስጣችን ካለው ነጻነት የተነሣ፥ አዲስ አስተሳሰብ ወይም አዲስ አመለካከት ይዘን ወደ ማኅበረሰባችን እንቀርባለን። ይህ አዲስ አስተሳሰብ ለውይይት፥ ለክርክር፥ እንዲሁም ደግሞ ለአስተሳሰብ እድገት በር መክፈቻ ሊሆን ሲገባ፥ ለልዩነታችን ግንባር ቀደም ችግር ሲሆን በተደጋጋሚ እንመለከታለን። ችግሩ በሦስት መንገድ ይከሠታል። 
በመጀመሪያ ያን አዲስ አሳብ ያፈለቀው ሰው ስለ አመነጨው አዲስ አሳብ የሚኖረው አስተሳሰብ ለችግሩ ምንጭ ሲሆን ይስተዋላል። አዲሱ አሳብ ከአንደበቱ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፥ ሰሚዎቹ አሳቡን እንደአሜሪካ ሕገ መንግሥት ወይም እንደ ሮማው ፓፓ ሃይማኖታዊ መልእክት (encyclical)  እንዲቀበሉት ይፈልጋል። የረሳው ነገር ቢኖር  የአሜሪካ ሕገ መንገሥት በየትውልዱ ብዙ ጭማሪዎች ( amendements) የተደረገበት ሰነድ መሆኑን ነው። የሮማው ፓፓ ያን የሃይማኖታዊ መልእክት (encyclical) ለመላው ዓለም ከመላካቸው በፊት በብዙ ሊቃውንት ተመክሮበትና ተዘክሮበት የተዘጋጀ መሆኑን። እንደዚያም ሆኖ ከትችት አያመልጥም።  የእኔ አሳብ በእነእገሌ ዘንድ ተቀባይነት ካላገኘ እነርሱ ጠላቶቼ ናቸው የሚለው  አመለካከት ተዘውትሮ የሚታየው፥ የራስ  አሳብ እንደወረደ ተቀባይነት እንዲኖረው ሰዎች ከመፈለጋቸው የተነሣ ነው። 
የአዲስ አስተሳሰብ መሆናችን ከስህተት የጸዳን አያደርገንም። በብዙ ያልተፈተነ መሣሪያ ለተጠቃሚው አደጋ እንደሚሆን ሁሉ በአሳብ ፍጭት፥ በትችና በክርክር ያልዳበረ አስተሳሰብ ለሕዝብ ጉዳት ይሆናል። አንዳንድ መንግሥታት እነርሱ የሚሉትን ያለምንም ክርክር የሚያጸድቅላቸው ፓርላማ ስላላቸው ምቾት ሊሰማቸው ይችላል። ነገር ግን እየበደሉት ያሉት ራሳቸውንና እንመራዋለን የሚሉትን ሕዝብ ነው።  
ሁለተኛው ችግር የሚመጣው ደግሞ አዲሱ አሳብ ከሚቀርብለት ክፍል የሚመነጭ ነው። እኛ ባልለመድነውና ባላሰብነው መንገድ የመጣን አሳብ ለመቀበል ጊዜ ጊዜ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህም የተገባ ነገር ነው። በብዙ ቦታ የሚታየው ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማጣጣልና ማናናቅ፥ አዲስ የቀረበውን አሳብ ውድቅ ማድረግ ነው። ተቃውሞው ደግሞ በቀረበው አሳብ ላይ አያቆምም። አሳቡን ያቀረበው ሰው ጠንከር ብሎ ባቀረበው አሳብ ላይ ከጸና ፥ የእኛን አሳብ ሊጥልና ሊያጠፋ እንደመጣ ሰው ቆጥሮ ሌሎችን በዚያ ሰው ላይ ማሳደም፥ ስሙን ማጥፋት የተለመዱ የአሠራራችን ዘይቤዎች ናቸው። ፥ 
እዲስ አስተሳስብን ፈርተን ወይም ወደ እኛ ዘንድ እንዳይደርስ ረጅም ግንብ ሠርተን ብንቀመጥ፥ ጊዜያዊ ምቾት ይስጠን እንጂ እድሜንና ጊዜን ተከትሎ ከሚመጣ ጥያቄ አያድነንም።  አንድ የስፔይን ጸሐፊ የተረከው ታሪክ አለ። ሴትዮዋ ዓይነ ሥውር የሆነ ልጅ ትወልዳለች። ልጇ እንደሌሎቹ ፍሬያማ የሆኑ ዓይነ ሥውራን ልጆች፥ በፊቱ ላለው ኃላፊነት እንዲዘጋጅ እንደመርዳት ፈንታ፥  ለቤተሰቦቿ አንድ የሚገርም ትዕዛዝ ሰጠች። ይኸውም በልጇ ፊት እርሱን ስለ ዓይነ ሥውርነቱ ሊያሳስቡ ይችላሉ ብላ የምታስባቸውን ቃላት ለምሳሌ፦ «ብርሃን» «ቀለም» « ማየት» የሚሉትንና የመሳሰሉትን እንዳይናገሩ አዘዘች፤  በልጇ ፊት ሰዉ የሚናገረው ተጠንቅቆ ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን አንዲ የጎረቤት ልጅ መጥታ ይህ ልጅ ሰምቶት የማያውቃቸውንና በዚያ ቤተሰብ ተነግሮ የማያውቀውን አስደናቂ ቃላት መናገር ጀመረች። ልጁ ሁሉ ነገር አዲስ ሁኖበት ግራ ተጋባ። እናቱ በጥንቃቄ የገነባችለት ዓለም በእንድ ጊዜ ትርምስምሱ ወጣ። 

« የኑፋቄ ፓለቲካ»  
በፖለቲካውም ሆነ በመንፈሳዊ ዓለም የ«ኑፋቄ ፖለቲካ» ብለን የምንጠራውን አካሄድ በየቦታው ተንሰራፍቶ ይታያል። « ኑፋቄ» የሚለው ቃል ነፈቀ ተጠራጠረ፥ ከፈለ፥ ገሚስ አምኖ ገሚስ ተወ ማለት ነው። በክርስትናው ለምሳሌ በኦርቶዶክሱ ዓለም ኑፋቄን ለመለየት ቅዱስ መጽሐፍና የአባቶች ጉባኤያት ወሳኝነት አላቸው። « የኑፋቄ ፖለቲካ» ማለት ግን፥ በልዩነታችን ውስጥ ድል አድራጊ ለመሆን፥ አንድን ሰው በኑፋቄ መክሰስን ነው። ይህም ብዙ ጊዜ ለአዲስ አሳብና አመለካከት ካለን ፍርሃት ጋር የተያያዘ ነው። 
ለምሳሌ ከመስከረም አንዱ የኒዮርኩ የሽብር ጥቃት በኋላ፥ « ሽብርተኝነት» የሚለው ቃል የኑፋቄ ፖለቲካም ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖአል።  በብዙ መንግሥታት ዘንድ ሥልጣኔን ይቀናቀናል የሚሉትን በሽብርተኝነት መክሰስ የተለመደ ነገር ሆኖአል። ድጋዜጠኞች፥ ጸሐፊዎች፥ የፖለቲካ ተንታኞች በሽብርተኝነት ሲከሰሱ እናያለን። በእኛው አገር እንኳ በሽብርተኝነት የተከሰሱትን ጋዜጠኞችን እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢ ነው። የሚያስከስሳቸው ነፍጥ አንግበው ወይም ሽብር ፈጥረው ሳይሆን አዲስ አሳብ ይዘው መገኘታቸው ነው። 
  በእምነት አደባባዮቻችንም በየጊዜው አንዱ ወገን ሌላውን ለማጥቃት የኑፋቄ ፖለቲካን እንደ መሣሪያ ሲጠቀምበት ይታያል።  ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያኔ ታሪክ « ካቶሊክ» የሚለው ቃል የኑፋቄ ፖለቲካ መሣሪያ ነበር። ስለ ሳይንስ ሰው ቢጠይቅ፥ ወይም ለመመርመር ልቡናውን ቢከፍት የሚሰጠው መልስ « አንት ኮተሊክ» የሚል ነበር። በሊቅነታቸው ሰፋ ያለ አሳብ በማቅረባቸው  « እርሳቸው ኮተሊክ ናቸው» ተብለው መቆሚያ መቀመጫ አጥተው የተሰደዱ መምህራን ጥቂት አይደሉም። የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና የመምህራቸው የመምህር ክፍሌ ታሪክ ለዚህ ማስረጃ ነው።   
የኑፋቄ አሳብ የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆን ማናቸውም ነገር መክሰሻ ይሆናል። በእምነቱም ሆነ በፖለቲካው አደባባይ በአሁኑ ወቅት የማያስወግዝ ምንም ነገር የለም።  ሁሉም ነገር ዶግማ ሲሆን ሁሉም ነገር የሚያስወግዝ ይሆናል። በእኛ ታሪክ በአጠቃላይ አዲስ አሳብ እጅግ በጥርጥር የሚታይበት ባሕል ውስጥ ስለኖርን ፥ ሊቅ የሚባለው የመምሕሩን ጭነት እንዳለ ሳየለውጥ ይዞ የተገኘ ሰው ነው። አተነፋፈሳቸውን  ሳይቀር። ከዚህ የተነሣ መምሕራን « በኑፋቄ» ጥላሸት እንዳይቀቡ ወይም በውግዘት ነፋስ እንዳይመቱ የተጫኑትን ነው ለትውልድ አስተላልፈው የሚሄዱት፤ ለየት ያለ ምዕላድ ቢኖራቸውም ለታማኝ ተማሪያቸው ካልሆነ በስተቀር በጉባኤ አያስተምሩትም። ለትውልድ ብዙ ማስተላለፍ የሚችሉ ሊቃውንት « ከምወገዝ» በማለት ዝምታን መርጠው መቃብር ወርደዋል። 
አዲስ አሳብን እጅግ የምንፈራ ከመሆናችን የተነሣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳ የኢንኵዝሽን ዘመንን ሕግ ይዘን አፍንጫ ብንፎንን፥ ምላስ ብንቆርጥ፥ መጻሕፍት ብናቃጥል ደስ የሚለን ብዙ ነን። በዚህ በአሜሪካ የቤተ መጻሕፍት ማኅበር ( America Library Association) በየዓመቱ የታገዱ መጻሕፍትን የሚያስብበት ሳምንት አለው። ይህ ሳምንት የሚታሰበው የአስተሳሰብ ነጻነትን ለማዳበር አንባቢው የምርጫ ነጻነት እንዲኖረው ነው። እዚህ ላይ አዲስ አሳብ ሁሉ መልካም ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን ያን አሳብ ወደ ሕዝብ ዘንድ ሳይደርስ ማፈኑ ግን አደገኛ ወደሆነ ነገር ያደርሰናል። 

የመሪዎች ኃላፊነት 
ይህ ወደ ሦስተኛው ነገር ያመጣናል።   በአዲሱ አሳብና በነባሩ አሳብ መካከል ያለውን አስታርቆ ለአሁን ዘመን ወይም በፊታችን ላለው ችግር የሚበጀውን ማዘጋጀት አንዱና ዋናው ችግራችን ነው። ምክንያቱም ልዩነታችንን አቻችለንና አቀራርበን ወደ አንድነት የምናመጣበት ችሎታችንን ልናዳብር አለመቻላችን ነው።  ጥቂቱ ልዩነታችን ታላቁን ሥራችንን ሲያበላሸው አይተናል። ልዩነትን ለማጥበብና ወደ አንድነት ለማምጣት በሁለቱም ወገን ባሉት አሳቦች ውስጥ ዋጋ ያለውን ነገር ማየት ያስፈልጋል። ሁለቱም ወገኖች የኔ የሚሉትን ወደ አንድ ጠረጴዛ ላይ እንዲያመጡትና ከግል አንጻር ያቀረቡትን አሳብ ከሕብረት አንጻር እንዲከልሱት  ማድረግ ይኖርብናል። 
ይህ የመሪዎች ተግባር ነው። የእውነተኛ መሪ ችሎታ ሕዝብን በአንድ ታላቅ ተልእኮ ወይም ራዕይ ዙሪያ ማሰባሰብና በእነርሱ ተሳትፎ ውጤታማ ወደ ሆነ ግብ እዲደርሱ ማድረግ ነው። የእውነተኛ መሪ ችሎታ ሕዝብን መንዳት ሳይሆን ሕዝብን ማሳተፍ ነው።  በእኛ ዘንድ ግን መሪ ማለት እርሱ ያመነጨውን እሳብ የሚንከባከብ ነው። የመሪነቱ ኃይልም የሚገለጠው ከእርሱ አሳብ ለየት ያለ አሳብ ይዘው የሚነሡትን በማጥቃት ነው። መሪ የምንላቸው የአሽከር ያለህ የሚሉ እንጂ በራዕያቸው ዙሪያ የሚያሰባስቡ ወይም ራዕያቸውን በማካፈልና የሌሎች አሳብ ታክሎበት እንዲያድግ የሚፈልጉ  አይደሉም። ዛሬ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ በትንሹም በትልቁም እንዳንታረቅ ሆነን የተለያየነው ከዚህ የመሪነት እጦት ነው። የተለያየንበት ነገር ጥቂት ብዙ ነገር ከመሆኑ የተነሣ፥ የተለያየንበትን ነገር ረስተን እንድ ነገር ብቻ ይዘን ተቀምጠናል። ጠላት መሆናችንን። 
በብዙ ነገሮች እየተጯጯህን ነን እንጂ ገና መነጋገር አልጀመርንም።  የራሳችንን አሳብ ምሬታችንንና ብስጭታችንን ስለተወጣን፥ ልባችን ላይ ያለውን ስለተነፈስን፥ ከሌላው ጋር ተነጋግረናል ማለት አይደለም። እውነተኛ ንግግር የራስን አሳብ ለማካፈል በሚደረገው ጥረት ትይዩ ሌላውን ሰው ለመረዳት ለማድመጥ የሚኖረንን ፈቃደኝነት ይጨምራል።  መደማመጥ ማለት ድምጽ መስማት ማለት አይደለም። ማድመጥ ማለት ኢንፎርሜሽን መሰብሰብም አይደለም። ማድመጥ ማለት ራስን መስጠት ማለት ነው። ማድመጥ ማለት ከፊታችን ለተቀመጠው ሰው ዋጋ መስጠት ማለት ነው። ልዩነታችንን ማጥበብ የምንችለው አንዳችንን አንዳችን ማድመጥ ስንችል ነው። 
(ይቀጥላል።) 

1 comment:

  1. Dear Kesis:
    May God Almighty bless you even more for bringing this piece of light to those of us who are in total darkness when it comes to nation building. Awoke

    ReplyDelete