Tuesday, May 22, 2012


የቅዱስ ጳውሎስ አጭር ታሪክ 

ስለ ጳውሎስ ማንነት በጥልቀት የምናገኘው ሉቃስ ከጻፈልን ከሐዋርያት ሥራ እና ከራሱ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ነው።
1. በጠርሴስ ተወለደ 
ቅዱስ ጳውሎስ በአሁኑ ዘመን በደቡብ ምሥራቅ ቱርክ በምትገኘውና በዚያን ዘመን የትምህርት ማዕከላት ከሆኑት ከአቴንስ እና ከእስክንድርያ ጋር በእኩልነት ከምትጠራው ታዋቂ ከተማ በጠርሴስ ተወለደ። ወላጆቹ ከብንያም ነገድ ወገን የፈሪሳውያን ወገን ሲሆኑ ልጃቸውንም ከብንያም ወገን ታዋቂ በሆነው በንጉሥ ሳኦል ሰይመውታል። ምንም እንኳ የጳውሎስ ወላጆች አጥባቂ ፈሪሳውያን ቢሆኑም በዜግነት ሮማውያን እንደሆኑ በሐዋ ሥራ 21: 39 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ጠቅሶአል። ሐዋ ሥራ 16:37፤ 22:25፤ 25:11። 
2. በገማልያል እግር ሥር ተማረ:: 
የተወለደባት የጠርሴስ ከተማ በግሪክ ፍልስፍና በተለይም በስቶይክ ፍልስፍና ትምህርት ማዕከልነትዋ የታወቀች ቢሆንም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ እንደነገረን የተማረው በገማልያል እግር ሥር ነው። ሐዋ ሥራ 22:3። ገማልያል ታዋቂ የሆነው የሂለል የረበናት ትምህርት ቤት መሪ የነበረ ሲሆን በጥበቡና በአስተዋይነቱ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በረበናት ትምህርቱ ከብዙዎች ጓደኞቹ የበለጠ ዕውቀት እንደነበረው በዚሁ በምናጠናው መልእክቱ ውስጥ ገልጦልናል። ገላ 1:14። 
3. ክርስቲያኖችን አሳዳጅ ነበረ ::
ምንም እንኳ በገማልያል እግር ሥር ሆኖ ቢማርም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሕጉና ስለሃይማኖቱ እጅግ ቀናኢና ከገማልያል ይልቅ የክርስትና መልእክትን ተጽዕኖ የተረዳ ይመስላል። ሐዋ ሥራ 5:34-39። በመሆኑም ገና የተመሠረተችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ ያሳድዳት ነበር። ገላ 1:13። በሐዋ ሥራ ላይ የምናየው ደብዳቤም ይህ ክርስቲያኖችን ማሳደዱ በኢየሩሳሌም ባሉት የአይሁድ መሪዎች ይሁኝታን ያገኘ ነበር። ሐዋ ሥራ 8:3። 
4. ለሐዋርያነት መጠራቱ:: 
ከሊቀ ካህናቱ ተልእኮ ተቀብሎ በኢየሱስ የሚያምኑትን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ በጉዞ ላይ ሳለ ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ለጳውሎስ እንደተገለጠለት በሐዋ ሥራ 9 ላይ እናገኛለን። ጌታ ኢየሱስ በደማስቆ ላይ የጳውሎስን ሕይወት መቀየር ብቻ ሳይሆን ለታላቅ የወንጌል አገልግሎትም ነበር የጠራው። እስከዚያች ሰዓት ድረስ እንደመልካም የኦሪት ተማሪ ጳውሎስ የሚያምነው በእንጨት የሚሰቀል ሰው የተረገመ እንደሆነና በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሞተ ሰው መሲህ (ክርስቶስ) መሆን እንደማይችል ነበር። ነገር ግን የተሰቀለውን ኢየሱስ ፊት ለፊት ተገናኘው። የኢየሱስ ተከታዮች የሚሉትም እውነት እንደሆነ ተመለከተ። ጳውሎስን ከሁሉ በላይ ያስደነገጠው ነገር ቢኖር እየተከተለው ያለው መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ያ ሕይወቱን የሰጠለት የኦሪቱ ሕግ አለማሳየቱ ነበር። ከዚያ ይልቅ ወሰን የሌለው የክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ በምህርቱ እንደጠራው አስተዋለ። በመሆኑም ለእርሱ ከዚያች ቀን ጀምሮ << ሕይወት ክርስቶስ >> እንደሆነ አወጀ። ፊል1:21። ሕይወቱን ሁሉ ለክርስቶስ ለመስጠት ወሰነ።
5. የአሕዛብ ሐዋርያ መሆን 
ቅዱስ ጳውሎስ ለሐዋርያነት ከጌታ ኢየሱስ የቀረበለትን ጥሪ ምላሽ የሰጠው ወዲያው ነበር። መጀመሪያ ወደ አረቢያ (ገላ 1:17) በመቀጠልም ወደ ደማስቆ  ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ በመሄድ በዚያም ጴጥሮስን እና የጌታ ወንድም ያዕቆብን አግኝቶአል። (1ቆሮ 15:5) ወደ ተወለደበት ወደ ተርሴስ በመሄድም ሊያጠፋው የሞከረውን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ሰብኮአል። (ገላ 1:21-24)  ቀድሞ ወደ ሐዋርያት ያመጣው በርናባስ እንደገና ወደ አንጾኪያ ሄደው በዚያ እንዲያገለግሉ ጋበዘው።ሐዋ 11:19-26። የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች በብዛት ያሉባት ነበረች። 
6. የኢየሩሳሌም ጉባኤ 
የአንጾክያ ምዕመናን በሃይማኖት የበረቱና ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተብለው የተጠሩ ነበሩ። አገልግሎታቸውም በአሕዛብ መካከል ወንጌልን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን መርዳት ነበር። ይህን እርዳታ ለማድረስ ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጡበት ወቅት በኢየሩሳሌም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ይመሩ የነበሩት ጴጥሮስ ዮሐንስና የጌታ ወንድም ያዕቆብ በአንጾኪያ ያለውን አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ለበርናባስና ለጳውሎስ ድጋፋቸውን ገለጡ። (ቀኝ እጃቸውን ሰጡ።) ሐዋ 11:27-30። ገላ 2:1-10። ሆኖም በኢየሩሳሌም በአይሁድ መካከል ያለችው ቤተ ክርስቲያን እና በአንጾኪያ በአሕዛብ መካከል ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሊከተሉት ስለሚገባቸው መንገድ የተለያየ አቀራረብ ነበራቸው። በመሆኑም ከኢየሩሳሌም ወደአንጾኪያ የሚሄዱ አንዳንዶች ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የገቡትን የኦሪትን ሥርዓት መቀበል እንዳለባቸው ማስገደድ ስለጀመሩ በኢየሩሳሌም እንደገና ወንጌልን በአሕዛብ መካከል እንዴት መስበክ እንደሚገባ የሚወስን የሐዋርያት ጉባኤ ወይም የሐዋርያት የመጀመሪያው ሲኖዶስ ተካሄደ። ሐዋ 15:1-29። ቅዱስ ጳውሎስ ከጉባኤው በኋላ አገልግሎቱን በማስፋት በብዙ ቦታዎች ላይ አብያተ ክርስቲያናትን የመሠረተ ሲሆን ከኢየሩሳሌሙ ጉባኤ በኋላ ለሁለት ጊዜ ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶአል:: በመጨረሻም የተያዘውና በእሥር ወደሮም የተወሰደው ከኢየሩሳሌም ነው።
ጳውሎስ በዘመናት ውስጥ 
33    ለሐዋርያነት ተጠራ:: ወደ ዓረብ ምድር ሄደ 
35    ወደኢየሩሳሌም ለአጭር ጉብኝት ሄደ 
35-45 ኪልቅያ ሶርያ አንጾኪያ 
46    ከአዕማድ" መሪዎች ጋር  በኢየሩሳሌም መገናኘቱ (ገላ 2:1-10) 
       ከአንጾኪያ ይዞት የሄደውን እርዳታ ለኢየሩሳሌም ቅዱሳን ማድረሱ (ሐዋ ሥራ 11:27-30) 
47-48 ጳውሎስ እና በርናባስ የመጀመሪያውን ሕዋርያዊ ጉዞ ማድረጋቸው (ሐዋ 13:4-14:28)
48/49 የሐዋርያት ጉባኤና ውሳኔ 
49-51/52  ጳውሎስና ሲላስ በመቄዶንያና በአካይያ:: የፊልጵስዩስ በተሰሎንቄ በቤሪያ እና በቆሮንቶስ 
                አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ:: (ሐዋ ሥራ 16:9-18:18) 
51/52 ጳውሎስ በኢየሩሳሌም አስቸኳይ ጉብኝት አደረገ 
52-55 ጳውሎስ በኤፌሶን (ሐዋ ሥራ 19:1-20:1) 
55-57 ጳውሎስ በመቄዶንያ በእልዋሪቆን እና በቆሮንቶስ 
57      ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ኢየሩሳሌምን መጎብኘቱ::መያዙ እና መታሠሩ:: 
57-59  በቂሳርያ መታሠሩ (23:35-26:32) 
59-60 ወደኢጣሊያ ጉዞ 
60-62 በቁም እስር በሮም መቀመጡ 
62      ጳውሎስ በቄሳር ፊት 
64      የሮም መቃጠል 
65      የጳውሎስ ሰማዕትነት 

No comments:

Post a Comment