Thursday, November 14, 2013

በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ


እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፤ ፊልጵስዩስ 2፥6 

« በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ» የሚለውን የግእዙ ዘር « ዘውእቱ አርአያሁ ለእግዚአብሔር» እርሱ የእግዚአብሔር አርአያ መልክ ነው ይላል። አማርኛችን « መልክ» ግእዙ « አርአያ» ግሪኩ « ሞርፌ» የሚለውን ቃል በዚህ ንባብ ውስጥ ቁልፍ ቃል ነው። መልክ ወይም አርአያ ተብሎ የተተረጎመው ቃል  አንዳንዶች ለመተርጎም እንዳሰቡት ውጫዊ ቅርጽን ሳይሆን ውስጣዊ ባህርይን ወይም እውነተኛ ማንነትን የሚያመለክት ነው። ሐዋርያው ይህን ቃል የተጠቀመው የክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት ግልጥ አድርጎ ለማሳየት የሚጠቅም ቃል ስለሆነ ነው። ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለዚህ ሲናገር «  ልክ በእግዚአብሔር ምሳሌ እንደተፈጠረው ሰው « እንደ እግዚአብሔር የመሰለ ባሕርይ ይዞ» አላለም። ነገር ግን ጳውሎስ « በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ አለ»  ይህም [የሚያመለክተው] አብ በወልድ ውስጥ ህልው መሆኑን ነው።» ይኸው ጎርጎርዮስ ስለእግዚአብሔር መልክ ሲናገር   « የእግዚአብሔር መልክ (አርአያ) ፍጹም ከባሕርዩ ( essence ) ጋር አንድ ነው። ነገር ግን በባርያ መልክ ይሆን ዘንድ በመጣ ጊዜ፥ [ሰው በሆነ ጊዜ] አንዱን ባሕርይ ብቻ አልወሰደም። ከእግዚአብሔርነቱ ባሕርይም አልተለየም።  ም 
ቅዱስ ጎርጎርዮስ በሚገባ እንዳሳየን ጳውሎስ በዚህ « በእግዚአብሔር መልክ»  በሚለው ቃል ክርስቶስ ቅድመ ሥጋዌ በአምላክነቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሲመለክ መኖሩን ካመለከተን በኋላ በሥጋዌው ወራት ግን ይህን አምላክነቱን በንጥቂያ አልወሰደም።  መከራ ለመቀበል የመጣ ስለሆነ በአምላክነቱ መከራ የሚያሳዩትን ለማጥፋት አልሞከረም።  የአምላክነቱን ባሕርይ ለማዳን ሥራው አቋራጭ መንገድ አድርጎ በንጥቂያ ወይም በሥርቆት ( መቀማት የሚለው የግሪኩ ቃል የሚያመለክተው ይህን ነው) አልሄደበትም።  
እዚህ ላይ ይህ ንባብ የሚያሳስበን የቀደመው አዳምን ነው።  እግዚአብሔር በመልኩ በአምሳሉ የፈጠረው ቢሆንም ትእዛዙን እንዲፈጽም ነግሮት ነበር ሆኖም ግን የእባቡን ቃል በመስማት ለእግዚአብሔር አልታዘዝም አለ። የእባቡ የማታለያ ቃል « እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ የሚል ነበር። ዘፍጥረት ም. 2 እና 3ን ተመልከቱ።
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
ባሪያ የሚለው ቃል በመጀመሪያ ለተጻፈላቸው ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ከዚህ በፊት እንዳመለከትነው ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ነው። ባሪያ ማለት ምንም ነፃነት የሌለው በጌቶቹ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚደገፍ ማለት ነው። « ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በክብር በባሕርይ የሚተካከለው በከፍታ ያለው አምላክ የሮም ዜጎች እጅግ የሚጸየፉትን እጅግ ዝቅ ያለውን ሕይወት ባርነትን መረጠ። ባሪያ ሆነ። የኛ አባቶች በትርጓሜያቸው እንዳመለከቱን እርሱ እግዚአብሔርነት ሳይኖረው እግዚአብሔርነትን የፈለገ አይደለም፥ ነገር ግን ለባሕርዩ የማይስማማና የሌለውን የባርያን መልክ ወሰደ። 

አምላክ ሰው ሰው የሆነበት ምሥጢር ከመዳን ነገር ጋር የሚያያዘው ለዚህ ነው። ሰው ሆነ ስንልም ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ ነው። ሐረገ ትውልድ ተቆጥሮለት ነው። ከመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ዘመን ጀምሮ የተነሡ የስህተት ትምህርቶች በዋናነት የሚክዱት በመጀመሪያ አምላክነቱን ሲሆን በሁለተኛ ሰውነቱን ነው። ይህ ንባብ ግን ቀደም ሲል ዮሐንስ አፈወርቅ እንደጠቀሰው የክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት የሚክዱትን መናፍቃን አፍ የሚያዘጋ ነው። ለምሳሌ በእግዚአብሔር መልክ ሳለ የሚለውን « መልክ» የሚለውን ቃል በሌላ ለመተርጎም የሚፈልጉ አርዮሳውያን አሉ። ስለሆነ የምንጠይቃቸው ጥያቄ ይህ ነው። በእግዚአብሔር መልክ ሳለ የሚለው ቃል እግዚአብሔርነቱን የማይገልጥ ከሆነ በባሪያ መልክ  የሚለውስ ቃል ምንነቱን ይገልጣል?  በእግዚአብሔር መልክ ሳለ ሲል በእግዚአብሔርነቱ ወይም በመለኮትነቱ ሳለ ማለቱ ነው። ልክ እንደዚሁ የባሪያን መልክ ያዘ የሚለው ቃልም ፍጹም ሰውነቱን የሚያመለክት ነው። ይህም « ቃል ሰው ሆነ» ከሚለው የወንጌል ቃል ጋር ይስማማል። 

1 comment:

  1. መተካከልን መቀማት* እንደሚገባ =ይህ ቃል ብዙ ያወዛግበኝ ነበረ..ትክክለኛው -ቀ* ጠብቆ ሲነበብ ነው ወይስ ላልቶ እያልኩኝ..ምክንያቱም የትርጉም ልዩነት አለውና.. ቀሲስ ስለዚህ ትርጉም አንድ ሙሉ ጽሁፍ ብትጽፍልን ደስ ይለኛል

    ReplyDelete