የአሜሪካንን የመካከለኛ መደብ ማኅበረሰብን እግር ከወርች ቀይዶ የያዘው የዕዳ ጉዳይ ነው። ሕይወት ማለት ለብዙ አሜሪካውያን የባንክ ወለድ መገፍገፍ ሆኖአል። የክሬዲት ካርድ ያላማረረው ማን ነው? ከመካከለኛ መደብ እጅግ በባሰ ሁኔታ ደግሞ መጤውንና ( immigrants) ደኃው ኅብረተሰብ በሆነ ባልሆነው እያባበሉት ከማይወጣበት የዕዳ ሐዘቅት ውስጥ እያስገቡት ነው።
ሆኖም ግን የ2011 ዓም በባንኮች ላይ የተካሄደውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ የመራው አካል ( Occupy Wall Street) ይህን የባንኮች በስስት ላይ የተመሠረተ አይጠግቤነትና ኅብረተሰቡን በወለድ አግድ በዕዳ መያዙ አምርሮ መቃወሙ ይታወቃል። በመሆኑም ይህ እንቅስቃሴ የወለደውና የግለሰቦችን ዕዳ በማስወገድ ላይ በዋናነት ያተኮረው Rolling Jubilee ተባለው ቡድን የግለሰቦችን ዕዳ ከባንኮች እጅግ በቅናሽ ዋጋ በመግዛት ከ15 ሚሊዮን በላይ የግለሰቦችን ዕዳ ለማስወገድ ችሎአል።
ዕዳውን ከባንኮች እጅግ በቅናሽ ዋጋ ስለሚገዛው ቡድኑ የ14,734,569.87 ዶላር የግለሰቦችን ዕዳ 400,000 ዶላር በማውጣት ማቃለል ችሎአል። እንደ አንድሪው ሮስ የቡድኑ አባልና በኒዮርክ ዩንቨርስቲ የማኅበራዊና ባህላዊ ትንታኔ ፕሮፌሰር ገለጻ ከሆነ ዕዳው እንደዚህ ሊቀል የቻለው የሁለተኛ ዕዳ ገበያ ካለው ባህርይ የተነሣ ነው። ባለዕዳዎች ብዙ ጊዜ ስለማይከፍሉ፥ ባንኮች ዕዳውን ለሌላ ሦስተኛ ወገን የሚሸጡት እጅግ ርካሽ በሆነ ሁኔታ በአብዛኛው ለአንድ ዶላር ዕዳ እምስት ሳንቲም ያህል በመጠየቅ ነው። በመሆኑም የዕዳ አስወጋጁ አካል ዕዳውን በርካሽ ከባንኮች በመግዛት ግለሰቦችን የዕዳ ኪሳራ ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል። ዕዳ አስወጋጁ አካል በዋናነት ያተኮረው የሕክምና ዕዳ ላይ ነው።
ሮስ እንደሚለው ከሆነ ዕዳቸው በዕዳ ሰብሳቢዎች (debt collectors) ምን ያህል በርካሽ እንደተገዛ የሚያውቁ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ሲሆን ይህን ማወቅ ደግሞ ስለ ዕዳ ሥነ ልቡናዊ ለውጥ ይሰጣል ። በመሆኑም ዕዳ ሰብሳቢዎች ሲደውሉና ዕዳችሁን በሙሉ እንድትከፍሉ ሲጠይቁ፥ ዕዳ ሰብሳቢዎች ዕዳችሁን እጅግ በጣም በጣም ርካሽ በሆነ መንገድ ገዝተውት እንደሆነ ታውቃላችሁ ማለት ነው። ይህም ከዳ ሰብሳቢዎች ለምታደርጉት ንግግር የሞራል ብርታት ይሰጣችኋል
በመልካም ነገር ሕዝቡን የሚያስተምርና ነጻ የሚያወጣ አዎንታዊ ተቃውሞ ማለት ይህ ነው።
ምንጭ፦ ዘጋርዲያን
No comments:
Post a Comment