እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ
ተወዳጅዋ ኦርቶዶክሳዊት ደራሲና ጋዜጠኛ ፥ ፍሬድሪካ ማቲውስ ግሪን በመጽሐፉዋ ላይ ሪቻርድ ኡምብራንድ የተባሉ የሩሜንያ የሃይማኖት መሪ ፥ በኮሚኒስት ሩሜንያ ዘመን አብረዋቸው ታስረው ስለነበሩ ኦርቶዶክሳዊ ካህን የጻፉትን ተርካ ነበር። በዚያን ወቅት የአንድ ገዳም አበምኔት የነበሩት አባ ኢስኩ በኮሚኒስቶች እጅ ብዙ ስቃይና ድብደባ ደርሶባቸው ስለነበር ከስቃዩና ከድብደባው የተነሣ ለሞት ቀርበው ነበር። ከእርሳቸው ራቅ ብሎ ደግሞ አንድ የኮሚኒስት ባለስልጣን የነበረ እንዲሁ ከደረሰበት ድብደባና ግርፊያ የተነሳ ለሞት ያጣጥራል። ሰውየው በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ አባ ኢስኩን ብዙ ስቃይና ድብደባ ያደረሰባቸው ነው፤ አሁን ግን እርሱም በተራው ከኮሚኒስት ፓርቲው ተወግዶ ለሥቃይና ለግርፋት እስር ቤት የተጣለ ነው። ነገር ግን ይህ ኮሚኒስት በዚያ ጻእር ላይ እያለ በአጠገቡ ያሉትን ሪቻርድ ኡምብራንድን ደግሞ ደጋግሞ << ይህን የመሰለ አጸያፊ ድርጊት ፈጽሜ (ንስሐ ሳልገባ) መሞት የለብኝም፥>> በማለት እንዲጸልዩለት ይነግራቸዋል።
ራቅ ብለው በታላቅ ሕመም ውስጥ ያሉት ኦርቶዶክሳዊው አበ ምኔት ከተኙበት አልጋ ላይ ሆነው ንግግሩን ይሰማሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአጠገባቸው የሚገኙትን ሌሎች እስረኞች ግራና ቀኝ እንዲደግፉአቸው አድርገው እየተጎተቱ ያ የገረፋቸው ያ ያሰቃያቸውን ለሞት ያደረሳቸው ሰው ዘንድ ደረሱ፤ ከዚያም በአባታዊ ፍቅር ግንባሩን ዳሰሱት፤ እናም ተናገሩት፤
<< ወጣት ነህ፤ ታደርገው የነበረውን አታውቅም ነበር፤ እኔ ይቅር ብዬሃለሁ ከልቤ እወድሃለሁ፤ እኔ ኃጢአተኛ የምሆን አንተን መውደድ ከቻልኩ፥ ራሱ ፍቅር ሆኖ ሰው የሆነው ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚያፈቅርህ አስብ። አንተ ያሰቃየሃቸው ክርስቲያኖች በሙሉ ፍጹም ይቅርታ አድርገውልሃል፥ ደግሞም ይወዱሃል፥ ክርስቶስ ይወድሃል። አንተ ደህንንነት ለማግኘት ከምትመኘው በላይ፥ ክርስቶስ እንድትድን ይወዳል። አንተ ኃጢአትህ ይቅር ይባል እንደሆነ አስበህ ይሆናል፤ አንተ ኃጢአትህ ይቅር እንዲባል ከምትመኘው በላይ ኃጢአትህን ይቅር ሊል እርሱ ይፈልጋል።አንተ ከእርሱ ጋር በሰማያት ከእርሱ ጋር ለመሆን ከምትመኘው በላይ ከእርሱ ጋር በሰማያት እንድትሆን ይመኛል፤ እርሱ ፍቅር ነው። አንተ የሚያስፈልግህ ወደ እርሱ መመለስና ንስሐ መግባት ነው።>> አሉት። ንግግራቸውን እንደጨረሱ ያ የተኛው የቀድሞ ገራፊ ኮሚኒስት በእንባና በብዙ ስቃይ ሆኖ ኃጢአቱን ሲናዘዝ፥ ገዳማዊው ኦርቶዶክሳዊ አባት ደግሞ የኃጢአት ሥርየትን ያውጁለት ነበር። ሪቻርድ ኡምብራንድ እንደነገሩን፥ ንስሐ የገባው ሰውና ኦርቶዶክሳዊው አባት በዚያው ምሽት አርፈው ወደሰማያዊ አባታቸው ዘንድ ሄደዋል።
ይህን ታሪክ ያነሳንበት ምክንያት እኒያ ኦርቶዶክሳዊ አባት ለዚያ በጸጸት እሳት ለተለበለበው ነፍስ በወቀሳ ቀስት ለተወጋው ሕይወት የሰበኩለት በመስቀል ያሸበረቀ የፍቅርና የተስፋ መልእክት፥ ዛሬም ለእኛ የመድኃኔ ዓለምን ጥንተ ስቅለቱን ለማክበር ለተሰበሰብን ሕያው የሆነ መልእክት ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ይወደናል፤ ከታላቅ ፍቅሩም የተነሣ፥ በእኛ ፈንታ፥ ለኃጢአታችን ሥርየት ይሆን ዘንድ፥ አንድ ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል። ይህ ለእርቅ የሆነው ሞቱ ይህ ለድል አድራጊነት የሆነው የመስቀል ጉዞ የብሉይ ኪዳን መስዋዕቶችን በብዙ መንገድ የፈጸመ ስለሆነ ነው ዮሐንስ መጥምቅ << እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ>> በማለት የአዳኙን መምጣት ያወጀው። ዮሐ 1፥29 ።