Saturday, November 23, 2013

በዓለት ላይ የተሠራው ቤት

በዓለት ላይ የተሠራው ቤት
ዶክተር ሊሊያን አልፊ 
ትርጉም ቀሲስ መልአኩ ባወቀ   

ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ማቴ 7፥25 
አንድ ቀን ማለዳ፥ ከእንቅልፋችሁ ስትነሱ፥ በዓለም ላይ እጅግ የጸና መሠረት ያለው ነገር ከቦታው ጠፍቶ ልታገኙት ትችላላችሁ። ሂሮሺማ እንዳልነበረ ሆኖአል። የሶቪየት ኅብረት ተበታትኖአል። የበርሊን ግንብ ተደርምሶአል። የኒው ዮርኩ መንታ ሕንፃ ፈርሶአል። ብዙ ከተሞች በእሳተ ገሞራ፥ በውኃ መጥለቅለቅና በመሬት መንቀጥቀጥ እንዳልነበሩ ሆነዋል። የምንወዳቸውን ባልጠበቅነው መንገድ አጥተናቸዋል። 
ነገር ግን አንድ ቀን ማለዳ፥ ከእንቅልፋችሁ ስትነቁ ኢየሱስ የሌለበት ቀን አጋጥሞአችኋል? በጭራሽ!! እርሱ በዘመናት የሸመገለ ዓለታችን ነው። መንግሥታት ይጠፋሉ፤ እርሱ ግን « ትናንትና፥ ዛሬም፥ ለዘላለም ያው ነው» እርሱ ቀናችንን ሁሉ ከእኛ ጋር ነው፤ ፀሐይ ይሁን ዝናብ፥ በጎ ይሁን ክፉ፥ በጤና ይሁን በሕመም፥ በሠርግ ይሁን በቀብር፥ በደስታ ይሁን በሐዘን፥ በቀን ይሁን በሌሊት፥ በዚህ ሕይወት ይሁን በሚመጣው ሕይወት እርሱ ይመጣል። ልንገፋ እንችላለን፤ የምንወዳቸውን ልናጣ እንችላለን፤ ነገር ግን « በሚነደው የእቶኑ እሳት» ውስጥ እንኳ እርሱ ከእኛ ጋር ነው። 

ብዙ ቤቶችን በአሸዋ ላይ ገንብተናል። ብዙ ቤቶችን በአሸዋ ላይ መገንባታችንን ቀጥለናል። ለእነዚህ ቤቶች የተጠበቀላቸው አጠቃላይ ጥፋትና ውድመት ነው። በቅጽበት ሕይወት ሊለወጥ ይችላል፤ በዚያን ጊዜ የሚቀረው በዓለት ላይ የተሠራው ቤት ነው።  

Friday, November 22, 2013

መከራችንን ያረዘሙ ነገሮች (ክፍል ሁለት )


በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ  ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር፥ ኢትዮጵያ የነፃነት ሃገር፥ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ታሪክ ነች። ይህች የብዙዎች የነጻነት ዓርማ የሆነች አገር፥ ዛሬ ዓይነቱ ብዙ በሆነ የመከራ ቀንበር ውስጥ ናት። የመከራችን ብዛቱና ስፋቱ የት እንዳደረሰን ነጋሪ አያስፈልገንም። መከራው ከመርዘሙ የተነሣ ከመከራው የምንወጣበትን በር ለማየት ተስኖናል። በክፍል አንድ ጽሑፋችን  ከዚህ ካለንበት የመከራ ማጥ እንዳንወጣ መከራችንን ያረዘመው ምንድነው የሚለውን መመልከት ጀምረናል። 
ወደ ሁለተኛው ክፍል ከመሄዳችን በፊት በተነሣንበት ርእስ ላይ ሊሰነዘሩ ከሚችሉ ጥያቄዎች ውስጥ አንደኛውን ገለጥ አድርጌ ማለፍ እፈልጋለሁ። ጥያቄውም በችግር ውስጥ ያለውንና በብዙ መንገድ የተጠቃውን ሕዝብ ለችግሩ ምክንያት አንተ ነህ ማለት ይቻላልን? የሚል ነው።  በሕዝባችን ላይ የደረሰውን ወይም እየደረሰ ያለውን ዓይነቱ ብዙ የሆነውን መከራ መካድ ማለት ከእውነት ጋር መታገል ነው፤ ሆኖም ግን የሕዝባችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመከራችን ምክንያት በሆኑት እጅ ልናስቀምጥ አይገባም። መፍትሔውን መፈለግ ያለብን ከራሳችን ነው። መከራችን እንዲህ የረዘመው፥ የመከራችን ምክንያቶች ከመፍትሔ ባሻገር ሆነው ሳይሆን፥ መከራችንን ሊያረዝሙ የሚችሉ ነገሮች በእኛ መካከል መገኘታቸውና እነርሱን ለማየት ድፍረት ማጣታችን ነው። 
የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፥ በችግሮቻችንናን የኢትዮጵያን መልካምነት በማይፈልጉ አካላት እጅ ሳይሆን በእኛ እጅ ነው። ይህን እውነታ ከልብ ከተቀበልነው፥ እኛ ደግሞ አሁን ያለንበትን ሁኔታ፥ የደረሰብንን  እየሆንን ያለነውን በእርጋታ በመመርመር መፍትሔ መፈለግ ይኖርብናል። በመሆኑም ባለፈው ጽሑፌ መከራችንን ካረዘሙት ነገሮች አንዱ ባለፈው ታሪካችን እሥረኛ መሆናችን መሆኑን ገልጬ  ነበር። በዚሁም ውስጥ የተመለከትነው የትላንቱ ማንነታችን ውስጥ እስረኞች በመሆናችን አንደኛችን ለትምክህታችንና የዛሬን ኃላፊነት ላለመቀበላችን ምክንያት ስናደርገው ሌሎቻችንን ደግሞ ለዛሬው ጥላቻችን እና ክፋታችን ምንጭ አድርገነዋል። ዛሬ ወደ ሁለተኛው እንሄዳለን። 
2. ልዩነታችንን ለዕድገታችን መሣሪያ ልናደርገው አለመቻላችን  

 የኢትዮጵያን ማኅበራዊ ሕይወት በተለይም ያለፉትን ስልሳ የፖለቲካ እሰጥ አገባ ዓመታትን ስንመለከተው፥ ስለ አንድነት ብዙ የተናገርንበት፥ በዚያው መጠን ደግሞ በብዙ የተለያየንበት ዓለም ነው። በረባ ባልረባው የፈጠርነው ልዩነት መንፈሳዊውንም ሥጋዊውንም ክፍል ከመሠረቱ አናግቶታል። በልዩነት የተፈጠሩት ክፍተቶች እጅግ አሳዛኝ የሆኑ ድርጊቶች እንዲታዩባቸው ምክንያት ሆነዋል።  ለምሳሌ እኔ አካል የሆንኩባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌነት እናንሳ፤ ባለፉት አርባ አመታት ውስጥ አንደኛውን ፓትርያርኳን አስገድላ፥ አራተኛዋን ፓትርያርክ አሳድዳ ዛሬ ከሦስት በላይ በሆኑ አካላት ተከፋፍላ የምትገኝ ተቋም ናት። 
በዚህ ራሱን ንጹሕ አድርጎ ጣቱን የሚቀስርና በምጽድቅነት የሚቆም አንድም አካል የለም። በፖለቲካውም ያለው ይኸው በመንፈሳዊው ተቋም ላይ ያየነው ነገር ነው። ደም አቃብቶን እርስ በእርሳችን ያጋደለን ልዩነት ብለን በመካከላችን ያመጣነው ነገር ነበር። ለአገር ለወገን በአንድነት ተነሣሥተው  በመገዳደል የጨረሱ ስንቶች ናቸው? በዚህ ያጣናቸውን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን እናስባለን? ለታላቅ ሀገራዊ ራዕይ በአንድነት ተቀምጠው፥ በራዕያቸው ሳይሆን በስብሰባ ሥርዓት «ጨዋታቸው ፈርሶ» የሕዝባቸውን አንገት ያስደፉ ስንቶች ናቸው? 
የአገራችንን ባሕል ያጠኑ የማኅበራዊ ኑሮና የሥነ ሰብዕ ጥናት  ጠበብቶች ከሙያቸው አንጻር የሚሉትን እንዲያካፍሉን እየለመንን እኛ ግን በመንፈሳዊ እይታ ራሳችንን የመረመርንበትን ስናቀርብ የሚከተሉት ዋና ዋና ነገሮች ልዩነታችን እንዲጎላና አንድነታችን እንዲደበዝዝ አድርጎታል። 

የአሳብ ልዩነት ጠላትነት መሆኑ 
በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል በመፈጠራችን፥ እኛ ሰዎች ስንባል ካገኘነው ታላቅ ስጦታ መካከል አንዱ ውስጣዊ ነጻነት ነው። ስሙን የዘነጋሁት አንድ የክርስትና ጸሐፊ ሲናገር « አብዮት የሚፈጠረው ሰው ሰውን ሊገዛው ሲሞክር ነው። ምክንያቱም ሰው በማንም እንዳይገዛ ሆኖ የተፈጠረ ነው» ብሎአል። ይህ ውስጣዊ ነጻነት ደግሞ በማንም እንደ ሮቦት ከመመራት ይልቅ ውስጣዊ ራዕያችንን ግባችንን እንድንፈልግ ይገፋፋናል። በአንድ በኩሉ የውስጣዊ ወይም ግላዊ ነጻነት፥ በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ወይም የወል ግብ አንዳንድ ጊዜ ውጥረት መፍጠሩ አይቀርም። 
በውስጣችን ካለው ነጻነት የተነሣ፥ አዲስ አስተሳሰብ ወይም አዲስ አመለካከት ይዘን ወደ ማኅበረሰባችን እንቀርባለን። ይህ አዲስ አስተሳሰብ ለውይይት፥ ለክርክር፥ እንዲሁም ደግሞ ለአስተሳሰብ እድገት በር መክፈቻ ሊሆን ሲገባ፥ ለልዩነታችን ግንባር ቀደም ችግር ሲሆን በተደጋጋሚ እንመለከታለን። ችግሩ በሦስት መንገድ ይከሠታል። 
በመጀመሪያ ያን አዲስ አሳብ ያፈለቀው ሰው ስለ አመነጨው አዲስ አሳብ የሚኖረው አስተሳሰብ ለችግሩ ምንጭ ሲሆን ይስተዋላል። አዲሱ አሳብ ከአንደበቱ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፥ ሰሚዎቹ አሳቡን እንደአሜሪካ ሕገ መንግሥት ወይም እንደ ሮማው ፓፓ ሃይማኖታዊ መልእክት (encyclical)  እንዲቀበሉት ይፈልጋል። የረሳው ነገር ቢኖር  የአሜሪካ ሕገ መንገሥት በየትውልዱ ብዙ ጭማሪዎች ( amendements) የተደረገበት ሰነድ መሆኑን ነው። የሮማው ፓፓ ያን የሃይማኖታዊ መልእክት (encyclical) ለመላው ዓለም ከመላካቸው በፊት በብዙ ሊቃውንት ተመክሮበትና ተዘክሮበት የተዘጋጀ መሆኑን። እንደዚያም ሆኖ ከትችት አያመልጥም።  የእኔ አሳብ በእነእገሌ ዘንድ ተቀባይነት ካላገኘ እነርሱ ጠላቶቼ ናቸው የሚለው  አመለካከት ተዘውትሮ የሚታየው፥ የራስ  አሳብ እንደወረደ ተቀባይነት እንዲኖረው ሰዎች ከመፈለጋቸው የተነሣ ነው። 
የአዲስ አስተሳሰብ መሆናችን ከስህተት የጸዳን አያደርገንም። በብዙ ያልተፈተነ መሣሪያ ለተጠቃሚው አደጋ እንደሚሆን ሁሉ በአሳብ ፍጭት፥ በትችና በክርክር ያልዳበረ አስተሳሰብ ለሕዝብ ጉዳት ይሆናል። አንዳንድ መንግሥታት እነርሱ የሚሉትን ያለምንም ክርክር የሚያጸድቅላቸው ፓርላማ ስላላቸው ምቾት ሊሰማቸው ይችላል። ነገር ግን እየበደሉት ያሉት ራሳቸውንና እንመራዋለን የሚሉትን ሕዝብ ነው።  
ሁለተኛው ችግር የሚመጣው ደግሞ አዲሱ አሳብ ከሚቀርብለት ክፍል የሚመነጭ ነው። እኛ ባልለመድነውና ባላሰብነው መንገድ የመጣን አሳብ ለመቀበል ጊዜ ጊዜ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህም የተገባ ነገር ነው። በብዙ ቦታ የሚታየው ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማጣጣልና ማናናቅ፥ አዲስ የቀረበውን አሳብ ውድቅ ማድረግ ነው። ተቃውሞው ደግሞ በቀረበው አሳብ ላይ አያቆምም። አሳቡን ያቀረበው ሰው ጠንከር ብሎ ባቀረበው አሳብ ላይ ከጸና ፥ የእኛን አሳብ ሊጥልና ሊያጠፋ እንደመጣ ሰው ቆጥሮ ሌሎችን በዚያ ሰው ላይ ማሳደም፥ ስሙን ማጥፋት የተለመዱ የአሠራራችን ዘይቤዎች ናቸው። ፥ 
እዲስ አስተሳስብን ፈርተን ወይም ወደ እኛ ዘንድ እንዳይደርስ ረጅም ግንብ ሠርተን ብንቀመጥ፥ ጊዜያዊ ምቾት ይስጠን እንጂ እድሜንና ጊዜን ተከትሎ ከሚመጣ ጥያቄ አያድነንም።  አንድ የስፔይን ጸሐፊ የተረከው ታሪክ አለ። ሴትዮዋ ዓይነ ሥውር የሆነ ልጅ ትወልዳለች። ልጇ እንደሌሎቹ ፍሬያማ የሆኑ ዓይነ ሥውራን ልጆች፥ በፊቱ ላለው ኃላፊነት እንዲዘጋጅ እንደመርዳት ፈንታ፥  ለቤተሰቦቿ አንድ የሚገርም ትዕዛዝ ሰጠች። ይኸውም በልጇ ፊት እርሱን ስለ ዓይነ ሥውርነቱ ሊያሳስቡ ይችላሉ ብላ የምታስባቸውን ቃላት ለምሳሌ፦ «ብርሃን» «ቀለም» « ማየት» የሚሉትንና የመሳሰሉትን እንዳይናገሩ አዘዘች፤  በልጇ ፊት ሰዉ የሚናገረው ተጠንቅቆ ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን አንዲ የጎረቤት ልጅ መጥታ ይህ ልጅ ሰምቶት የማያውቃቸውንና በዚያ ቤተሰብ ተነግሮ የማያውቀውን አስደናቂ ቃላት መናገር ጀመረች። ልጁ ሁሉ ነገር አዲስ ሁኖበት ግራ ተጋባ። እናቱ በጥንቃቄ የገነባችለት ዓለም በእንድ ጊዜ ትርምስምሱ ወጣ። 

« የኑፋቄ ፓለቲካ»  
በፖለቲካውም ሆነ በመንፈሳዊ ዓለም የ«ኑፋቄ ፖለቲካ» ብለን የምንጠራውን አካሄድ በየቦታው ተንሰራፍቶ ይታያል። « ኑፋቄ» የሚለው ቃል ነፈቀ ተጠራጠረ፥ ከፈለ፥ ገሚስ አምኖ ገሚስ ተወ ማለት ነው። በክርስትናው ለምሳሌ በኦርቶዶክሱ ዓለም ኑፋቄን ለመለየት ቅዱስ መጽሐፍና የአባቶች ጉባኤያት ወሳኝነት አላቸው። « የኑፋቄ ፖለቲካ» ማለት ግን፥ በልዩነታችን ውስጥ ድል አድራጊ ለመሆን፥ አንድን ሰው በኑፋቄ መክሰስን ነው። ይህም ብዙ ጊዜ ለአዲስ አሳብና አመለካከት ካለን ፍርሃት ጋር የተያያዘ ነው። 
ለምሳሌ ከመስከረም አንዱ የኒዮርኩ የሽብር ጥቃት በኋላ፥ « ሽብርተኝነት» የሚለው ቃል የኑፋቄ ፖለቲካም ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖአል።  በብዙ መንግሥታት ዘንድ ሥልጣኔን ይቀናቀናል የሚሉትን በሽብርተኝነት መክሰስ የተለመደ ነገር ሆኖአል። ድጋዜጠኞች፥ ጸሐፊዎች፥ የፖለቲካ ተንታኞች በሽብርተኝነት ሲከሰሱ እናያለን። በእኛው አገር እንኳ በሽብርተኝነት የተከሰሱትን ጋዜጠኞችን እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢ ነው። የሚያስከስሳቸው ነፍጥ አንግበው ወይም ሽብር ፈጥረው ሳይሆን አዲስ አሳብ ይዘው መገኘታቸው ነው። 
  በእምነት አደባባዮቻችንም በየጊዜው አንዱ ወገን ሌላውን ለማጥቃት የኑፋቄ ፖለቲካን እንደ መሣሪያ ሲጠቀምበት ይታያል።  ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያኔ ታሪክ « ካቶሊክ» የሚለው ቃል የኑፋቄ ፖለቲካ መሣሪያ ነበር። ስለ ሳይንስ ሰው ቢጠይቅ፥ ወይም ለመመርመር ልቡናውን ቢከፍት የሚሰጠው መልስ « አንት ኮተሊክ» የሚል ነበር። በሊቅነታቸው ሰፋ ያለ አሳብ በማቅረባቸው  « እርሳቸው ኮተሊክ ናቸው» ተብለው መቆሚያ መቀመጫ አጥተው የተሰደዱ መምህራን ጥቂት አይደሉም። የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና የመምህራቸው የመምህር ክፍሌ ታሪክ ለዚህ ማስረጃ ነው።   
የኑፋቄ አሳብ የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆን ማናቸውም ነገር መክሰሻ ይሆናል። በእምነቱም ሆነ በፖለቲካው አደባባይ በአሁኑ ወቅት የማያስወግዝ ምንም ነገር የለም።  ሁሉም ነገር ዶግማ ሲሆን ሁሉም ነገር የሚያስወግዝ ይሆናል። በእኛ ታሪክ በአጠቃላይ አዲስ አሳብ እጅግ በጥርጥር የሚታይበት ባሕል ውስጥ ስለኖርን ፥ ሊቅ የሚባለው የመምሕሩን ጭነት እንዳለ ሳየለውጥ ይዞ የተገኘ ሰው ነው። አተነፋፈሳቸውን  ሳይቀር። ከዚህ የተነሣ መምሕራን « በኑፋቄ» ጥላሸት እንዳይቀቡ ወይም በውግዘት ነፋስ እንዳይመቱ የተጫኑትን ነው ለትውልድ አስተላልፈው የሚሄዱት፤ ለየት ያለ ምዕላድ ቢኖራቸውም ለታማኝ ተማሪያቸው ካልሆነ በስተቀር በጉባኤ አያስተምሩትም። ለትውልድ ብዙ ማስተላለፍ የሚችሉ ሊቃውንት « ከምወገዝ» በማለት ዝምታን መርጠው መቃብር ወርደዋል። 
አዲስ አሳብን እጅግ የምንፈራ ከመሆናችን የተነሣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳ የኢንኵዝሽን ዘመንን ሕግ ይዘን አፍንጫ ብንፎንን፥ ምላስ ብንቆርጥ፥ መጻሕፍት ብናቃጥል ደስ የሚለን ብዙ ነን። በዚህ በአሜሪካ የቤተ መጻሕፍት ማኅበር ( America Library Association) በየዓመቱ የታገዱ መጻሕፍትን የሚያስብበት ሳምንት አለው። ይህ ሳምንት የሚታሰበው የአስተሳሰብ ነጻነትን ለማዳበር አንባቢው የምርጫ ነጻነት እንዲኖረው ነው። እዚህ ላይ አዲስ አሳብ ሁሉ መልካም ነው ማለት አይደለም። ነገር ግን ያን አሳብ ወደ ሕዝብ ዘንድ ሳይደርስ ማፈኑ ግን አደገኛ ወደሆነ ነገር ያደርሰናል። 

የመሪዎች ኃላፊነት 
ይህ ወደ ሦስተኛው ነገር ያመጣናል።   በአዲሱ አሳብና በነባሩ አሳብ መካከል ያለውን አስታርቆ ለአሁን ዘመን ወይም በፊታችን ላለው ችግር የሚበጀውን ማዘጋጀት አንዱና ዋናው ችግራችን ነው። ምክንያቱም ልዩነታችንን አቻችለንና አቀራርበን ወደ አንድነት የምናመጣበት ችሎታችንን ልናዳብር አለመቻላችን ነው።  ጥቂቱ ልዩነታችን ታላቁን ሥራችንን ሲያበላሸው አይተናል። ልዩነትን ለማጥበብና ወደ አንድነት ለማምጣት በሁለቱም ወገን ባሉት አሳቦች ውስጥ ዋጋ ያለውን ነገር ማየት ያስፈልጋል። ሁለቱም ወገኖች የኔ የሚሉትን ወደ አንድ ጠረጴዛ ላይ እንዲያመጡትና ከግል አንጻር ያቀረቡትን አሳብ ከሕብረት አንጻር እንዲከልሱት  ማድረግ ይኖርብናል። 
ይህ የመሪዎች ተግባር ነው። የእውነተኛ መሪ ችሎታ ሕዝብን በአንድ ታላቅ ተልእኮ ወይም ራዕይ ዙሪያ ማሰባሰብና በእነርሱ ተሳትፎ ውጤታማ ወደ ሆነ ግብ እዲደርሱ ማድረግ ነው። የእውነተኛ መሪ ችሎታ ሕዝብን መንዳት ሳይሆን ሕዝብን ማሳተፍ ነው።  በእኛ ዘንድ ግን መሪ ማለት እርሱ ያመነጨውን እሳብ የሚንከባከብ ነው። የመሪነቱ ኃይልም የሚገለጠው ከእርሱ አሳብ ለየት ያለ አሳብ ይዘው የሚነሡትን በማጥቃት ነው። መሪ የምንላቸው የአሽከር ያለህ የሚሉ እንጂ በራዕያቸው ዙሪያ የሚያሰባስቡ ወይም ራዕያቸውን በማካፈልና የሌሎች አሳብ ታክሎበት እንዲያድግ የሚፈልጉ  አይደሉም። ዛሬ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ በትንሹም በትልቁም እንዳንታረቅ ሆነን የተለያየነው ከዚህ የመሪነት እጦት ነው። የተለያየንበት ነገር ጥቂት ብዙ ነገር ከመሆኑ የተነሣ፥ የተለያየንበትን ነገር ረስተን እንድ ነገር ብቻ ይዘን ተቀምጠናል። ጠላት መሆናችንን። 
በብዙ ነገሮች እየተጯጯህን ነን እንጂ ገና መነጋገር አልጀመርንም።  የራሳችንን አሳብ ምሬታችንንና ብስጭታችንን ስለተወጣን፥ ልባችን ላይ ያለውን ስለተነፈስን፥ ከሌላው ጋር ተነጋግረናል ማለት አይደለም። እውነተኛ ንግግር የራስን አሳብ ለማካፈል በሚደረገው ጥረት ትይዩ ሌላውን ሰው ለመረዳት ለማድመጥ የሚኖረንን ፈቃደኝነት ይጨምራል።  መደማመጥ ማለት ድምጽ መስማት ማለት አይደለም። ማድመጥ ማለት ኢንፎርሜሽን መሰብሰብም አይደለም። ማድመጥ ማለት ራስን መስጠት ማለት ነው። ማድመጥ ማለት ከፊታችን ለተቀመጠው ሰው ዋጋ መስጠት ማለት ነው። ልዩነታችንን ማጥበብ የምንችለው አንዳችንን አንዳችን ማድመጥ ስንችል ነው። 
(ይቀጥላል።) 

Wednesday, November 20, 2013

አልቃሹም፥ አስለቃሹም፥ ማልቀሻውም . . .በአገሬ በኢትዮጵያ አንድ የቆየ ልማድ አለን። አንድ ታላቅ ሰው ይሞትና ለቀብሩ ዘመድ አዝማድ ከሩቅ ቦታ ላይደርስ ይችላል። በዚህ ላይ የቆላው ደጋ መውረድ ስለማይችል። ቀብሩ ከተፈጸመ በኋላ በቀጠሮ ይገናኛል። ለለቅሶ። 
ለለቅሶም ለጩኸትም ዛሬ ሎስ አንጀለስ ላይ ከየቦታው ተገናኝተን ነበር። 
ለዚያች እህቴ፤ ለውርደቷ፥ ለስቃይዋ፥ ለሕመሟ. . . ጮኽን 
ለዚያ ለወንድሜ፤ የአረቢያ ምድረበዳ ደሙን ለጠጣው. . . አለቀስን 
ለእኛም ለሁላችን፤ አገር ሳናጣ፥ በረከት ሳያንሠን እንዲህ ለሆንነው . . . ተላቀስን 
ለቅሶ የሩቅ ዘመድን፥ የናፍቅነውን ያገናኛል . . .  ወንድሞቻችንን እህቶቻችንን ከወደ አሥመራ . . . ተያይዘን እሪ አልን። 
እሥመራ መድኃኔ ዓለም ትዝ አለኝ፤ ወንድሞቼና እህቶቼ 
ሁላችን አለቅስን፥ ሁላችን አስለቀስን፥ ስለሁላችን አለቀስን 

ስለእህት ስለወንድም፤ ስለአገር ስለወገን፤ ስለክብር ስለሕይወት. . . . ስለራስ አነባን። እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጠን። 

Tuesday, November 19, 2013

የምትጮኹት ለማን ነው ለሚሉ ሁሉ . . .

የምንጮኸው የገዛ ወገኖቹን ሰብዓዊ መብት ሳይሰጣቸው ረግጦ ለሚገዛ መንግሥት ባለሥልጣናት አይደለም።
የምንጮኸው ዜጎቹ የሆኑ ሴቶችን መኪና ለመንዳት እንኳ ላልፈቀደላቸውና ይህን አሳብ ያነሡትን የነፃነት ተሟጋቾች እሥር ቤት ለወረወረ መንግሥት አይደለም።
የምንጮኸው ሽብርን በመንግሥት ደረጃ እየፈበረከ በሃይማኖት ስም በየአገሩ ለሚበትን መንግሥት አይደለም።
የምንጮኸው ለታሪክ ምስክር ልንሆን ነው። የትናንት እንግዶቻችን የዛሬ አራጆቻችን እንደሆኑ ለማመልከት ነው።
የምንጮኸው ሰማይ ስሚ ምድር አድምጭ ልንል ነው።
የምንጮኸው ሐዘናችንን ነው። ስለ ወደቀችው፥ ስለተደፈረችው ፥ ስለታረደችው፥ እህታችን ነው።
የምንጮኸው አንድ እንድንሆን፥ በአንድ እንድንቆም፥ በአንድነት እንደ አገር እንድናስብ ነው።
የምንጮኸው በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲታረቀን ነው።

ለታሪክ ምስክር እንሁን፤ 

ከእንግሊዝ አገር የሚሰማው ማስጠንቀቂያና የቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሁኔታ ?

ክርስትና አደጋ ላይ ነው? ከወደ እንግሊዝ የሚሰማው ንግግር ይህን የሚያጸድቅ ይመስላል። የካንትሪበሪ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ሎርድ ኬሪ ክርስትና በተለይ በእንግሊዝ አገር  ከአንድ ትውልድ በኋላ እንደሚጠፋ በቅርቡ በተደረገ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።  
lord carey
ሎርድ ኬሪ ቤተክርስቲያንን ከጥፋት ለመጠበቅ በወጣቱ ትውልድ ላይ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የሎርድ ኬሪ አስተያየት የተሰማው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሲኖዶስ ባደረገው ስብሰባ ላይ በቀረበው ሪፖርት የቤተክርስቲያኒቱ አባላት ቁጥር ክፉኛ ማሽቆልቆሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብሔራዊ ተቋም ሆና ለመቀጠል በሚያጠራጥር ሁኔታ እንዳስቀመጣት መነገሩን ተከትሎ ነው። 
ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው አስደንጋጭ ሁኔታ በመናገር የቀድሞው ሊቀ ጳጳስ ብቻቸውን አይደሉም። የዮርክ ሊቀ ጳጳስ የሆኑ ት ዶክተር ጆን ሴንታሙም አዲስ አባላትን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሳብ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበትና « ከዚህ ውጭ የሆነው ነገር ሁሉ ቤት በእሳት ተያይዞ የቤት ዕቃን እንደማሳመር ይሆናል ብለዋል። 
የዮርኩ ሊቀ ጳጳስ ጨምረውም ቤተ ክርስቲያን ወንጌላዊት ወይም ቅሬታዊት "evangelise or fossilise" እንደምትሆንና ምርጭዋ የእርሷ እንደሆነ ተናግረዋል።  
dr john sentamu
የሎርድ ኬሪ ንግግርን የዮርኩ ሊቀ ጳጳስ አስተጋብተውታል። 
ሎርድ ኬሪ ባደረጉት ንግግር በእንግሊዝ ያሉ ክርስቲያኖች « ድል የተነሱና አንገታቸውን የደፉ» እንደሆኑና ከዚያ መንፈስ ለመውጣት ታላቅ እንቅስቃሴ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል። በተለይም በወጣቶች ላይ ቤተ ክርስቲያን ጊዜዋን ማጥፋት እንዳለባት ተናግረዋል። ስለዚህ ሲናገሩም « በራሳችን ልናፍር ይገባናል። ምክንያቱም በወጣቶቻችን ላይ ያለ የሌለ ኃይላችንን ካላዋልን ከአንድ ትውልድ በኋላ እንጠፋለን፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማንም ሰው ስለማይኖር " 
 +++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ይህ የእንግሊዝ ሊቃነ ጳጳሳት ንግግር በአብዛኛው በእንግሊዝ አገር ያለውን እውነታ የሚያንጸባርቅ ቢሆንም፥  « ለእኔ ብለህ ስማ» የሚያስብል አባባል ነው። በአንድ በኩል ክርስትና በብዙዎች አዳጊ ዓለማት (ቻይና፥ ሕንድ፥ አፍሪካ በአጠቃላይ) በሚገርም ፍጥነት እያደገ ያለ ሃይማኖት ቢሆንም በሌላ በኩል ግን በአደጉት ዓለማት ( በተለይ  በአውሮፓ  ) ክርስትና በከፍተኛ ፍጥነት ተከታዮቹን እያጣ የመጣ ሃይማኖት ሆኖአል። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። በአደጉት አገሮች አብያተ ክርስቲያናት እያቀረቡት ያሉት ወንጌል የሞተ ወንጌል ነው። የሕይወት ለውጥ ማምጣት የማይችል። ስለሆነም ወንጌል « የሚያሰለች ማኅበራዊ ትንታኔ» ለታላቅ መንፈሳዊ ለውጥ የሚያነሣሣ፥ ሕይወትን እስከሞት የሚያሰጥ ለውጣዊ መልእክት አልሆነም። የአውሮፓና የአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት ዘመናዊነት ከእጃቸው ላይ የጣለውን ሕያው የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እንደገና ማንሳት ይኖርባቸዋል። የዚያን ጊዜ አይደለም በሰንበት ቤተ ክርስቲያን መምጣት፥ ሕይወትን ለታላቅ ተልዕኮ መስጠት በሰዎች ውስጥ ይታያል። 
የእኛ አገር ከዚህ ምን እንደምትማር አላውቅም። ለአሁን አደባባዮቻችንን በሰው ተጥለቅልቆአል። አሐዞቻችን ግን አስደንጋጭ ምልክቶች እያሳዩን ናቸው። እንደ ሕዝባችን ቁጥር እድገት የቤተ ክርስቲያናችን አባላት ቁጥር አድጓል ወይ? ቤተ ክርስቲያን በአገር አቀፍ ደረጃ ወጣቱ ትውልድ ላይ ኢንቨስት እያደረገች ነውን? ለሕዝባችንስ የምናስተላልፈው መልእክት የሕይወት ለውጥን የሚጋብዝ ነው? ተወያዩበት 
ምንጭ፦ huffington post

ጸሎተ ስምዖን ዓምዳዊ

ምዕራፍ ፵፭ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ እጁ የሰለለችበትን ሰው እንደፈወስከው፥ ልቡናዬን ፈውሰው፥ ፍቅርህን እንዳስተውል አድርገን። አንተ ሕይወትና ፈውስ ነህና። 
ምዕራፍ ፵፮ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ከባሕር ማዕበልና ጽኑ ከሆነ ሞገድ ያዳንካቸው፤ በአንተ እድን ዘንድ ዘንድ፥ ክፉዎች ከሆኑ መታወክና መደንገጥ አድነኝ። በአንተ ለሚያርፉ ደካሞች ሁሉ ፥ ወደብና መጠጊያ ነህና። 
ምዕራፍ ፵፯ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ሕይወትንና ዕረፍትን አገኝ ዘንድ፥ በፍቅርህ ገመድ ለዘለዓለም እሰረኝ። 
ምዕራፍ ፵፰ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ከነአናዊቷ ሴት ወደ አንተ አንደጮኸች፥ አንተም ልመናዋን እንደሰማህ፥ አሁንም ወደአንተ የምጮኸውን እኔን ኃጢአተኛውን ባርያህን ስማኝ። 
ምዕራፍ ፵፱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ከመንገድህ ሊያስወጣኝና ሊያስተኝ ከሚያውከኝ ከሰይጣን ሁከት አድነኝ። 

ምዕራፍ ፶  ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ በሃይማኖት ዓለት ላይ አጽናኝ፤ እግሬንም በእርሷ ላይ አቅና፤ በእርሱዋ በፍቅርህ እመላለስ ዘንድ ከአንተም ጋር አንድ እሆን ዘንድ። 

Monday, November 18, 2013

ዘመነኛው ቃል « ጥንቆላና ሙስና»

አንዳንድ ጊዜ የዚህ ሰለባ የሚሆኑት ጋዜጠኞች ናቸው ዘመን ያነሳውን ቃል ይዘው አብረው ይነጉዳሉ። ፖለቲከኞች ደግሞ ለታላቁ ተልዕኮአቸው አቅጣጫ መቀየሪያ ያደርጉአቸዋል። « war on terror» የሚለውን ቃል ይዘው ልጓም በሌለው ፈረስ የጋለቡ የአሜሪካ ፖለቲከኞች  የአሜሪካንን የውጭ ፖሊሲ ለሚመጡት አያሌ አመታት እንዴት እንደጎዱት ያስተውሉታል።

የዓለሙስ ይሁን የቤተ ክርስቲያኑ ከየት መጣ። ለቤተ ክርስቲያን አጀንዳ የሚቀርጽላት መልእክት የሚያቀብላት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንጂ የቄሣር ቤተ መንግሥት አልነበረም። አሁን ግን ቃላት ብቻ መልእክቱንም የሚያቀብላት ቄሣር ሆኖአል።

ከሰሞኑ « ሙስና» የቤተ ክርስቲያኒቷ ነገር ያገባኛል ያሉ ድረ ገጾች ሁሉ የሚለፍፉት ነገር ሆኖአል። ቃላት ሲደጋገም ማሰልቸቱ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ማጥቂያ ሲሆን ማሳዘኑ። ከሰሞኑን ሐራ ተዋህዶ የተባለው ድረ ገጽ ያወጣው ግን ይህ የቃላት ጋጋታ ወደ የት እንደሚያደርስ ቆም ብለን እንድናስብ አድርጎናል። ድረ ገጹ በየጽሑፉ ሲያለፋው የነበረውን « ተሐድሶ» የሚለውን ቃል ሰሞኑን ጡረታ ከትቶት አዲስ ቃል ይዞ ተነስቶአል። « ሙስና» የሚል። እርሷ በደንብ ሥራ አልሰራችም መሰለኝ ሌላ ተጨማሪ ቃል አምጥቶአል። « ጥንቆላ የሚል። ያወጣውም አቢይ ርእስ እንዲህ የሚል ነው።   ሀገረ ስብከቱ « የመንበረ ጵጵስና ልዩ ጽ/ቤት» እስከ ማቋቋም በደረሱ ሙሰኞችና ጠንቋዮች እየታመሰ ነው በሚል ርእስ ባወጣው ጽሑፍ ጠንቋዮች የሐገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳሳት እየመሩት እንደሆነ ጽፎአል። ለመሆኑ እንዲህ አይነቱ ጽሑፍ የሚጠቅመው ማንን ይሆን????አስተዳደራዊ በደል ሰርተዋል ያስኬዳል። ነገር ግን የፖለቲካውም የመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ጥርስ የሚያስገቡ ስሞችን መፈለግ ለምን አስፈለገ። ጠንቋዮች የሉም አይደለም። የጥንቆላ ሥራ ትዝ የሚለን እኛ ሰው መደብደብ ሲያምረን መሆን የለበትም።  የራስን ሥልጣን ለማደላደል አገርና ቤተ ክርስቲያን ስንት ጊዜ ትጎዳ፤ ከዚህ የከሳሽ መንፈስስ የሚያወጣን ማን ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜ ቅዳሴ

አንድ ወዳጄ ጠጋ ብሎ አንድ ቅር የሚለውን ነገር  ነገረኝ፤ በጊዜ ቅዳሴ ስለሚነበቡት ምንባባት። ወዳጄ በመጀመሪያ የጠየቀኝ ጥያቄ እነዚህ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡት የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት አስፈላጊ ናቸው ወይ? የሚል ነው። እንዴታ አልኩት። እርሱ ግን አሁንም በመልሴ ሳይረካ « እናንተ ካህናቱ ግን የምታስተላልፉት መልእክት ይህን አይመስልም!» አለኝ። « እንዴት?» አልኩት። እርሱም « መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መጻሕፍት አሥራው መጻሕፍት ብላ ቤተ ክርስቲያን አክብራ ብትጠራውም። እናንተ ግን ገና ምዕራፍና ቁጥሩን አንባቢው ተናግሮ ሳይጨርስና ወደ ምንባቡ ሳይዘልቅ « ቅዱስ» ብላችሁ መርገፉን ማዜም ትጀምራላችሁ። ለመሆኑ መርገፉ ነው የሚበልጠው  ወይስ ንባቡ ነው የሚበልጠው» አለኝ።

የዚህ የወዳጄን ጥያቄ ሰሞኑን አንድ በአገልግሎት የኔው የቅርቤ የሆነ ዲያቆንም ጠይኸንኑ ደግሞ ጠየቀኝ። በእነዚህ በሁለቱ ወዳጆቼ ማሳሰቢያ በኩል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለእኔ ተናግሮኛል ብዬ አስባለሁ። በጊዜ ቅዳሴ የሚነበቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ትኩረት ስለማይሰጣቸው አብዛኛው ሰው ምንም ቦታ አይሰጣቸውም። ቤተ ክርስቲያን ግን በዕለቱ ወይም በሰንበቱ ሊነበቡ የሚገባቸው ያለቻቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በግጽው ወይም በመጽሐፈ ግጻዌ ለይታ አስቀምጣልናለች። እነዚህ ምንባባት ተነበው እስከሚያልቁ በአትኩሮት ልንሰማቸው ልንማርባቸው ይገባል እላለሁ። እናንተስ ምን ትላላችሁ?

ከሾፐን ትካዜ . . . ( Waltz in A minor)

ምሕረት መላኩ በኮልበርን የሙዚቃ ትምህርት ቤት በተዘጋጀው Piano workshop  ላይ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና ወላጆች ፊት የሾፐንን ኤ ማይነር ዋልትዝ ሲጫወት፤ የእርሱንና የሌሎችን ወጣቶች የፒያኖ ምጥ ስመለከት አእምሮዬ የወሰደኝ ወደ ክቡር ከበደ ሚካኤል ግጥም ነበር። . . . ብራቮ ምሕረት። ይበል ብለናል። 

 ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ራስ 
ከቤቶቨን ናላ ከሞዛርት መንፈስ 
ከሾፐን ትካዜ ከያሬድ ልቡና 
መዓዛ የሞላብሽ የብስጭት ቃና 
ረቂቋ ድምፅ ሆይ ውቢቷ ሙዚቃ 
ውብ እንደ ፀሐይ ንጽሕት እንደ ጨረቃ 


« ሙዚቃ» በክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል


ራሳችሁን መርምሩ

ከአንድ ወር በፊት በዚህ በሎስ አንጀለስ የሚገኝ የእኅትማማቾች ማኅበር አስራ ሰባተኛ ዓመት በዓሉን ልዩ በሆነ መንገድ አክብሮ ነበር። በፕሮግራማቸው ላይ ባልገኝም የቪዲዮ መልእክት እንዳስተላልፍ ጠይቀውኝ ስለነበር ይህን የቪዲዮ መልእክት ልኬላቸው ነበር። እነርሱ በብዙ እንደተጠቀሙበት ስለነገሩኝ መልእክቱ ለሁሉም ስለሆነ ተጠቀሙበት። ርእሱ ራሳችሁን መርምሩ የሚል ነው።Sunday, November 17, 2013

ከቅዳሴ መልስ፤ « ስደት እስከ መቼ? »

በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ቸርነት ቃለ እግዚአብሔርን ያስተማሩን ኦርቶዶክሳዊው ሰባኬ ወንጌል አባ ወንጌል አያልነህ ነበሩ። ሐዲስ ሐዋርያ አባ ወልደ ትንሣኤ « ስደት እስከ መቼ?» በሚል ርእስ ባስተማሩት ትምህርት ዮሴፍ በመልአከ እግዚአብሔር በተነገረው መሠረት ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዞ ወደ ናዝሬት መመለሱን፤ ይህም የሆነው የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልገው ሄሮድስ በመሞቱ እንደሆነ ገልጠዋል።

በመሆኑም ስደት የሚያበቃው ለስደት ምክንያት የሆነው ነገር ሲወገድ እንደሆነ በማብራራት፥ ዛሬ ለእኅቶቻችንና ለወንድሞቻችን ሰቆቃ ምክንያት የሆነው ስደት ምክንያቶች ብዙዎች እንደሆኑና እነርሱን ለማስወገድ በአንድነት ማሰብ እንዳለብን አስተምረውናል።

ለእመቤታችንና ለልጅዋ ስደት ምክንያት የሆነው ሄሮድስ ነበር። ሄሮድስ በፍቅረ ሲመት ዓይኑ ታውሮ፥ ገና አድጎ መንግሥቴን ይቀናቀናል ብሎ ስለጠረጠረ ጌታን ለመግደል ፈለገ። የቤተ ልሔም ሕፃናትንም አስገደለ። ፍቅረ ሲመት (የሹመት ፍቅር) አደገኛ ነገር ነው። ያሳውራል ያሳብዳል፤ ደም እስከማፍሰስ ያደርሳል። በዚህ የወደቁት የፖለቲካ ሰዎች ብቻ አይደሉም። ዛሬ ዛሬ እንደምናየው ጳጳሳቱና ካህናቱ ሁሉ ሳይቀሩ በዚህ ወድቀዋል ብለዋል።

ሐዲስ ሐዋርያ በዚህ ሳያቆሙ ሄሮድሳዊ ሕይወት ስንይዝ ከውስጣችን የሚሰደዱ ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩና ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነው የሥጋ ወደሙ ሕይወት ከብዙዎቻችን ሕይወት እንደተሰደደ በማስታወስ ዛሬ ክርስቶስ በልባችን እንዲነግሥና እኛም የሥጋ ወደሙ ሕይወት እንዲኖረን አሳስበውናል። 

Saturday, November 16, 2013

እግዚአብሔር ረሳኝ አትበሉ።

የፈጠረህ የፈጠረሽ፥ ከማኅፀን የተሸከመህ የተሸከመሽ እርሱ ነውና እግዚአብሔር ረሳኝ አትበሉ። ያልተፈጠረውን ቀናችሁን ያልኖራችሁበትን ወራት ያየ ነውና እርሱ ረስቶኛል አትበሉ። በእናታችን ማኅፀን ውስጥ የመገበን እርሱ ነውና ረስቶኛል አትበሉ።

ወደ ብርሃን ያመጣን፥ እስትንፋስን የሰጠን አልረሳንም።
በእናታችን ጫንቃ ላይ ምቾት የሆነን አልረሳንም።
ያቆመን አንደበት የሆነን አልረሳንም።
ያሳደገን በበረከት የመረቀን አልረሳንም።
ለምኞታችን ለክፋታችን ያልሰጠን አልረሳንም።
አልረሳንም።

ፈጥሮ
መግቦ
አቁሞ
አሳድጎ
መክሮ
ሰው አድርጎ
ለዚህች ቀን አድርሶናልና ረስቶናል አትበሉ።

ቀኑ ቢጨልምም አይረሳንም።
በሐዘናችን ቀን እንኳ አይረሳንም።
አቅጣጫ የጠፋን ሲመስለን አይረሳንም
ለጥያቄዎቻችን መልስ ባይኖረን አይረሳንም።
« እናት የወለደችውን ልጅ ልትረሳ ትችል ይሆናል እኔ ግን አልረሳችሁም» ብሎአልናል።
« አልረሳህም ከቶም አልጥልህም» ብሎአልና።ያንተ መሣሪያ አድርገኝ

ዓይኖችህ በምድር ሁሉ የሚመለከቱ፥ የሁሉ አባት ልዑል ሆይ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።
በመንፈስህ ቀድሰኸኝ በቃልህ መርተኸኝ፥ በቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ መከረኸኝ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።
ጌታ ሆይ በመስቀልህ የገለጠከውን ፍቅርህን፥ ትህትናህን፥ ራስህን ባዶ ማድረግንህን፥ ዝምታህን፥ ትዕግሥትህን በሕይወቴ እንድገልጥ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

የሰማዕታትህ የምስክርነታቸው ተጋድሎ፥ የቅዱሳንህ የንጽሕና ሕይወት ኃይል ሆኖልኝ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ። የመላእክትህ ምስጋና የሊቃነ መላእክትህ ጥበቃ ለእኔ እንዲሆን ፈቅደኽልን ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

አንተ ልታጽናና የወደድኸውን የማጽናና፥ አንተ ልትምረው የፈቀድከውን እንድምር፥ አንተ ልታነሣው ያያኸውን እንዳነሣ፥ አንተ ይቅር ያልከውን ይቅር እንድል ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

ፍቅርህን፥ ደስታህን፥ ቸርነትህን፥ ርህራሄህን፥ ሰላምህን ለሰው ሁሉ እንድናገር ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

ደካማነቴ ሳይሆን ብርታህ፥ ባዶነቴ ሳይሆን ሙላትህ፥ ችኮላዬ ሳይሆን ትዕግሥትህ ተገልጦ መሣሪያህ አድርገኝ።
ስለ ቅዱስ ስምህ ስትል አሜን።

( ከቀሲስ መልአኩ ባወቀ )


በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም

በሩቅም በቅርብም ያለን በዕለተ ሰንበት በእግዚአብሔር ፊት እንቆማለን። በዚህ ወቅት የሚከተሉትን ነገሮች እናስብ። 

 
በዳዊት መዝሙር 136 እንደምናገኘው በባቢሎን ምርኮ የነበሩት ኢየሩሳሌምን ባሰቡ ወቅት በእንባ ፊታቸው ተሸፍኖ ሀገራቸውን ላይረሱ « ኢየሩሳሌ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ»  ቃል ገብተዋል። 

ለእኛም ይህ ዕለት በችግር ያሉትን እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን ላለመርሳት ቃል የምንገባበት ጊዜ ይሁንልን። 
 ይህ ዕለት በችግር ያሉትን እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን በጸሎት ለማሰብ ቃል የምንገባበት ጊዜ ይሁንልን። 
ይህ ዕለት የእህቶቻችንንና የወንድሞቻችንን ሥቃይ ተመልክተን በፍቅር በአንድነት በይቅርታ የምንቆምበት ጊዜ ይሁንልን። 

Friday, November 15, 2013

መከራችንን ያረዘሙ ነገሮች

(ክፍል አንድ) 


ከሰሞኑ ከየአቅጣጫው የሚሰማው የወገኖቻችን እንግልት ያስታወሰኝ የራሔልን ታሪክ ነው። መተርጉማን አባቶቻችን በትውፊት እንደሚነግሩን ከሆነ ራሔል በግብፅ በስደት ዓለም የነበረች እስራኤላዊት ነበረች። ነፍሰጡር ሆና ሳለ ለፒራሚድ መሥሪያ የሚሆን ጡብ እንድትሠራ የታዘዘች ሴት ነበረች። ለጡብ የሚሆነውን ጭቃ እየረገጠች ሳለች ምጥ መጣባት፤ አሠሪዎቿ አታቁሚ አሉአት። ደም ሲፈሳት አታቁሚ እንዲያውም ደሙ ጡቡን ያበረታዋል አሏት። መንታ ልጆች ከማኅፀኗ ወትተው ከጭቃው ወደቁ፤ አታቁሚ አብረሽ ከጭቃው ጋር አብረሽ ርገጫቸው አሉአት። የዚያን ጊዜ ወደሰማይ ቀና ብላ « ኢሃሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እሥራኤል፤ በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምን?» ብላ እንባዋን ወደሰማይ ረጨች። የእግዚአብሔርን ሕልውና የመጠራጠር ጥያቄ ሳይሆን « ይህን ግፍ አትመለከትምን? አታይምን? ለማለት ነው።  
እግዚአብሔር አየ ተመለከተ፤ እሥራኤላውያንንም ከባርነት ነጻ አወጣቸው። ልበ አምላክ ዳዊት እንደተናገረው፥ እስራኤላውያንን « በብርና በወርቅ አወጣቸው።» መዝ 104፥ 37። ነገር ግን ምንም እንኳ ከባርነት ነጻ ቢወጡም፥ የልባቸው ደንዳናነትና እግዚአብሔርን ለመስማት እምቢ ማለታቸው የመከራቸውን ቀን አረዘመው። በአርባ ቀን የሚገቡባትን ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ለመውረስ አርባ ዓመት ፈጀባቸው። የሚበዙቱ ባለማመናቸው ጠንቅ በምድረ በዳ ወድቀው ቀሩ። 
 በሕዝቤ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል፥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለስደት መዳረጋቸውና እርሱን ተከትሎ እየደረሰባቸው ያለው ሰቆቃ፥ እንዲሁም አገራችን ያለችበት ፈርጀ ብዙ የሆኑ መስቀለኛ መንገዶችን ሳስብ የጠየቅሁት ይህንን ነበር፦ ፥ መከራችን ለምን ረዘመ? መከራችንን ያረዘምነው እኛ እንሆንን? ከሆነስ ለመሆኑ መከራችንንስ የምናረዝመው እስከመቼ ነው? እስከመቼስ ነው በዚህ ዓይነት ሁኔታ የምንኖረው? 
ከዚህ በታችን የምንመለከታቸው ነጥቦች እንደእኔ እምነት መከራችንን እንዲረዝም አድርገዋል የምላቸው ነጥቦች ናቸው። የአንድ ሕዝብን ለዚያውም ረጅም ታሪክና ውስብስብ ችግሮች ያሉበትን ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮች በዚህ አጭር ጽሑፍ በዝርዝር ለመግለጥ ከባድ ነው። ሆኖም ግን እነዚህ ነጥቦች ነጥቦች ዋና ዋና የሆኑትን ችግሮቻችንን ይዳስሳሉ ለበለጠ ውይይትም ያነሣሡናል ብዬ አምናለሁ። 


1. ያለፈ ታሪካችን እስረኞች መሆናችን  
የሃይማኖት ሰው እንደመሆኔ ታሪክ በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ታላቅ ሥፍራ አስተውላለሁ። ነገር ግን ታሪክ የምንማርበት እንጂ በትምክህትም ሆነ በጥላቻ የምንታሰርበት አይደለም። ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት ወደኋላ ዘወር ብለን ብንመለከት፥ ማኅበራዊ ውይይታችን በአብዛኛው የሚያጠነጥነው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ሳይሆን ባለፈው ነገራችን ላይ ነው። ከሁሉም የሚያሳዝነው ይህ ዓይነቱ ዕይታ በጣም ተጽእኖ ከማድረጉ የተነሣ  ስለ ዛሬዋ ኢትዮጵያ « ትንታኔ» የሚሰጠው በዚሁ የትናንት ማንነት ላይ ነው። 
ይህ የያለፈ ታሪካችን እስረኞች የመሆናችን ነገር የተመሠረተው በሁለት ተቃራኒና ጽንፈኛ እይታዎች ላይ ነው። እነዚህ ጽንፈኛ እይታዎች በተቃራኒ ይቁሙ እንጂ አደገኝነታቸው በብዙ መንገድ ያመሳስላቸዋል።   
 እንደኛው ከዛሬ ኃላፊነትና የትውልድ ጥያቄ ለማምለጥ በትላንት ታሪካችን ውስጥ የመሸሸግ አካሄድ  ነው። በእንደዚህ አካሄድ የሚሄድ ሰው የኔ ብሎ የሚጠቅሰው ትላንት ከትናንት ወዲያ አባቶቹ የሠሩትን ነገር ነው። የዛሬውን ሲጠየቅ፥ ወይም ጊዜና ትውልድ ሲጠይቀው ታሪኩን ማምለጫ ያደርገዋል፤ ከትናንቱ ተምሮ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ደግሞ ቆሞ መመለስ አቅም ስለሚያንሰው [ስላልጣረ]፥ የአቋራጭ መንገድ ያደረገው ወጉን ነው። የትናንቱን የአባቶቹን ታሪክ መተረኩን ነው። አባቶቻችን በታሪካቸውና በጊዜያቸው መልካም አድርገዋል። የተሳሳቱበትም ጊዜ አለ። በዚህ ተመስግነውበታል ተወቅሰውበታል። አንተ ደግሞ በአንተነትህ በጊዜህና በታሪክህ ተመስገንበት ተወቀስበት ስትሉት ቶሎ ብሎ የቀድሞውን ጥግ ያደርጋል። እንዳይወቀስ። ምክንያቱም በዚህ በእርሱ አስተያየት የትናንቶቹ አይተቹም አይወቀሱም፤ የትናንቱን ታሪክ የሚያየው ለትምክህት ሌላውን ለመናቅና አሳንሶ ለማየት እንጂ ለትምህርት ስላይደለ፥ ስህተቱንና ትክክለኛውን ታሪክ ለይቶ አያውቀውም። ታሪኩን ዶግማ አድርጎ ስለያዘው እንዳለ መቀበልን ታላቅ ተግባር አድርጎ መያዝ ብቻ ሳይሆን በትናንት ላይ ጥያቄ የሚያነሣውን በኑፋቄ ይከሰዋል። የአባቶቹን ታሪክና ወግ እንደረሳ አድርጎ። 
ይህ በእኛ ውስጥ ብዙ ይታያል። ታሪክ የመውደዳችን ያህል ታሪካችን የኋልዮሽ የወሰደን ይመስለኛል። አፍሪካ አሜሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በንቀት ለማየት የኢትዮጵያን ታሪክ የሚጠቅሱ አጋጥመውኛል። በመካከላችን እንኳ እርስ በእርስ ለመከባበርና ለመቀባበል ታሪክ ገደብ የሆነብን ሞልተናል። ስለዚህ ጉዳይ በሰፊው ስለምናትት ለጊዜው እናቁም። 
ከዚህ ጽንፍ ወደተቃራኒው ጽንፍ ስንሄድ ደግሞ የምናገኘውፍ ሁለተኛው ጽንፋዊ እይታ ያለፈ ታሪካችን እስረኛ ከመሆኑ የተነሣ የዛሬ ሁለት መቶ ዓመት ተሠራ በሚለው ግፍ ደረት የሚያስደቃውና ሙሾ የሚያስወርደው ክፍል ነው።  አሁንም  ይህ ክፍል የዛሬውን ማንነቱን በትናንንቱ ታሪክ ውስጥ ያስቀመጠ ብቻ ሳይሆን ከትናንት አገኘሁት ባለው ታሪክ፥ የምሬትና የጥላቻ ታሪክ  ዛሬን መቅረጽ የሚፈልግ ወገን ነው። ስለዛሬ ተናገር ሲባል የሚጀምረው « አፄው. . . አማራ. . . ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን»  አደረሱት የሚላቸው በደሎች በመዘርዘር ነው። ገና ከጅምሩ የትናንቱን ታሪክ እጅግ በከረረ ጥላቻ ስለሚያየው በትናንቱ ውስጥ የነበሩትን መልካም ነገሮች ለማየት ፈቃደኛ አይደለም። ከዚህ በላይም በትናንቱ ታሪክ ውስጥ ዓይነተኛ ሚና የነበራቸው አካላት ወራሾች ናቸው የሚላቸውን ሕዝቦች እና ተቋሞች ዋነኛ ጠላቶቹ ናቸው።እነዚህ ተቋሞችና ሕዝቦች ዛሬ ያላቸውን ሁኔታ ከግምት ማስገባት ለእርሱ ማመቻመች መስሎ ስለሚታየው ቆም ብሎ ለማየት ጊዜ የለውም። በታሪክ እንደምናየው ይህ ዓይነቱ አደገኛ የሆነ የታሪክ አተረጓጎም ሁል ጊዜ የሚያደርሰው ወደ አስፈሪ ድምዳሜ ነው። የሕልውናዬ መሠረት የእነርሱ መጥፋት ነው ወደሚል። ናዚ ጀርመን በጀርመን አይሁዶች ላይ፥ ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ ያደረሱት እልቂት የመነጨው ከዚህ ነው። 
የእነዚህ ሁለት ጽንፋዊ ዕይታዎች ተመሳሳይነት ምንድነው? አንደኛ ታሪክን ግልብ በሆነ እይታ ለመተርጎም መሞከራቸው ነው። ሁለቱም ክፍሎች ታሪካዊ አተረጓጎም ላይ ላዩን ስለሆነ ከታሪክ የሚማሩበትን በታሪካቸውም ራሳቸውን የሚወቅሱበትን ነገር አይጨብጡበትም። ይህ ወደ ሁለተኛው ተመሳሳይነታቸው ይመራናል። ሁለቱም ጽንፋዊ ዕይታዎች ታሪክን መሸሸጊያ ያደረጉት ከዛሬ ለመሸሽ ነው። አንደኛው ዛሬን ለመሸሽ ታሪክን ትምክህት ሲያደርግ ሌላው ደግሞ ዛሬን ለመሸሽ ታሪክን መክሰሻ ያደርጋል። 
++++++++++++++

ባለፈው ዘመን ጥፋት አልነበረም አንልም። የኢትዮጵያ ታሪክን በማስተዋል ያነበበ ሰው እንደሚገነዘበው፥ ባለፉት የአገራችን ታሪኮች ብዙ አሳዛኝ ነገሮች ተከናውነዋል። በባርያ ንግድ የገዛ ወገናችንን ሸጠናል። ፋሺስት ጣልያን በመንግሥታቱ ድርጅት አገራችን ቅኝ ለማድረግ የሞገተው ይህን ድካማችንን ጥግ አድርጎ ነው። ይህን የከፋ ሁኔታ ለማስወገድ፥ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ አጼ ኃይለ ሥላሴ ድረስ የኢትዮጵያ መሪዎች የባሪያ ንግድን ለማስወገድ ያደረጉትን ጥረት ማስታወሱ ይበቃል። 
ባለፈው ዘመን ሙያ እንደወንጀል ተቆጥሮ ባለሙያነት ጋብቻን የሚከለክል ነበር። ጸሐፊው ደብተራ ወይም ጠንቋይ ተብሎ ስለሚንቋሸሽ የአገር ታሪክን ጽፎ ለትውልድ የሚያስተላልፍ ሰው ማግኘት እንደ  ብርቅ ነበር። ብረቱን የሚያነጥረውን ቆዳውን የሚዳምጠውን ፋቂና ቀጥቃጭ ብለነው ልጆቹን የፋቂና የቀጥቃጭ ልጅ ብለነው ፈጠራንና ግኝትን አፍነነዋል። 
በሕዝቦች መካከልም ባለፈው ታሪካችን ግጭት ነበር። ግጭቶች በተለያዩ መንገዶች ይፈጠራሉ። የፖለቲካ ግጭቶች አሉ። መንግሥት ለአገዛዜ ይጠቅመኛል ብሎ ያሰበውን ለማድረግ ሲሞክር ተቃውሞ ይነሣል፤ ጦርነት ይከፈታል ። አንዳንድ ጊዜም ግጭቱ ሃይማኖታዊ ወይም ጎሳዊ መልክ ይኖረዋል። አንዳንድ ጊዜ ግጭቱ የኢኮኖሚ ይሆናል። የሕዝብ ከቦታ ቦታ ዝውውርንና መስፋፋትን ተከትሎ ግጭት ይፈጠራል። ባለፉት የአገራችን ታሪኮች ይህ አይነቱ ግጭት ነበረ። ዛሬም  በአርብቶ አደርነት  (ዘላንነት) በሚተዳደረው ሕዝባችን መካከል በግጦሽ መሬት ምክንያት የሚፈጠረውን ግጭትና የሰውና የንብረት ውድመት ስንመለከት ያለፈውን የሕዝቦች ግጭት በጥንቃቄ እንድናጠና ያደርገናል። 
ስለ ታሪክ አተረጓጎም የታሪክ ባለሙያዎች የሚሉትን እዚህ ማተት ባያስፈልግም ነገር ግን ከላይ ባየናቸው በሁለቱም እይታዎች ውስጥ ያለው ታላቁ ድካም ታሪክን በዛሬው ማነታችን አውድ ( context )  ለመተርጎም አለመሞከራቸው ነው። ይህ ዓይነቱ የተጣመመ የታሪክ አመለካከት ዛሬ የሚታየው አልተማረም በምንለው ሕዝባችን መካከል ሳይሆን፥ በዕውቀት ማማችን ላይ ተቀምጠን ሕዝባችንን እንመራዋለን በምንለው ነው።  ሕዝባችንማ ያለፈውን ድካምም ሆነ ብርታት አብሮ አልፎ ዛሬ ያለችውን አገር አስረክቦናል። ያስረከበን መንግሥት ሳይሆን ሕዝብ ነው። 
ታሪክን ከመንግሥት አንጻር ሳይሆን ከሕዝብ አንጻር ማጥናት ከብዙ ስሕተት ያድናል። አጼ ምኒልክን ረግሞ ግራኝ መሐመድን ነጻ አውጪ ማድረግ የሚመጣውም ከዚህ ታሪክን ከመንግሥት አንጻር ከመመልከት የተሳሳተ አካሄድ ነው። ታሪካችንን ከመንግሥት አንጻር ካየነው አንዳችን ተቃዋሚ አንዳችን ደጋፊ ስለምንሆን አንዱን አጽድቀን አንዱን መኮነናችን የማይቀር ነው። የአንድ ጸሐፊ አገላለጥን ልጠቀምና፥ « እግሩ የት አንደሚያልቅና አፈሩ የት እንደሚጀምር» የማይታወቀውን አፈር ለብሶ አፈር የመሰለውን ደሃ ገበሬ ፥ « የገዢው መደብ፥ ነህ » እያልን በወጣን በገባን መጠን የምንረግመው ከዚህ ቀላል ከሚመስል ነገር ግን እጅግ አደገኛ ከሆነ የታሪክ « ትንታኔ» ስለምንጀምር ነው። ታሪካችንን ከሕዝብ ዛሬ ላይ ቆመን ስንጀምር ግን አንድ መሠረታዊ ነገርን እንገነዘባለን። ይህ ሕዝብ ችግርም ደስታም አንድ አድርጎት ዛሬን በተስፋ ያለ ሕዝብ ነው። በእኛ ትንታኔ ያን ተስፋውን አንውሰድበት። ተስፋ የሌለው ሕዝብ ከማየት በላይ የሚያስፈራ ነገር የለምና። 

(ይቀጥላል) 

Thursday, November 14, 2013

የስምዖን ዓምዳዊ ጸሎት (ካለፈው የቀጠለ

ምዕራፍ፵፪። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ያች ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት የልብስህን ዘርፍ በዳሠሠች ጊዜ በጊዜዋ እንደተፈወሰች፥ እንደዚሁ የተናቁና ከንቱ የሆኑ የሚያደክሙ አሳቦች ከነፍሴ ይፈሳሉና፥ አንተ በምሕረትህ ነፍሴን ፈውሳት ፤ አምላካዊ የሆኑ አሳቦችና የተሠወሩ ምሥጢራት ያድሩባት ዘንድ የሕይወትን ምንጭ አንተ በውስጡዋ አስቀምጥ። 

ምዕራፍ፵፫። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ከኃጢአት መልእክተኛ ከሆዱ ምንጭ አድነኝ። የማትመረመረውንና ከመታወቅ ያለፈችውን የምሥጢራትህን ወንዝ በውስጤ አፍልቅ። በአንተ ሕያው ልሁን፤ በአንተ ልቀደስ፤ አንተ የቅዱሳን ቅዱስ ነህና። 


ምዕራፍ፵፪። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥መፃጕዕን ለመፈወስ ወደበጎች መተላለፊያ የመጣህ፥ ቅዱስ ስለሆነው ስምህ ከኃጢአት፥ ከበደልና ከሐኬት አንካሳነት ፈውሰኝ፤ ከሕመም አልጋም አድነኝ። ከአንተ ዘንድ የሚሆነውን ኃይልህን ስጠኝ በምሕረትህም ፈውሰኝ። ( ይቀጥላል)  

ይህ ማንነውይህ ማንነው? 
ሥጋን ከብለየቱ ያደሰው 
ከመለወጥ አድኖ የተዋሐደው 
ይህ ማንነው?  

ሰማያዊ ሳለ ምድራዊ 
ሥጋን የተዋሐደው  
ይህ ማነው? 

ያለመለወጥ የተወለደ 
ሕማም ሞትን ገንዘብ ያደረገ 
ይህ ማነው? 

ከኃጢአት የተለየ 
ይህ ማነው? 

አሕዛብን ከአጋንንት የለያቸው  
በፍቅሩ የሚማርካቸው 
ይህ ማነው?
  
ለሞት የተሰጠ 
ሞትን ያሸነፈ 
ይህ ማንነው? 

ሲኦል ያልያዘው 
መቃብር ያላስቀረው 
ይህ ማነው?


ያለኃጢአት የሞተው 
በብርሃኑ ድምቀት ዲያብሎስን ያሳወረው  
በሥልጣኑ ያሰረው
ከሥልጣኑ የሻረው 
ይህ ማንነው? 

ኃጢአት ያልተቆራኘው 
ወገኖቹን ያልተወ 
ሕፀፅ የሌለበት 
ብርሃን የሚከበው 
ይህ ማነው? 

ኢየሱስ ክርስቶስ ነው 
የተሰቀለው 
የግራው በቀኝ ያለፈበት

ኢየሱስ ነው  
በሲኦል የነበሩ 
ትሑታንን   
ወደሰማይ ያወጣቸው 
ኋለኞችን ፊት ያረጋቸው 
ኢየሱስ ነው። 


ከእልመስጦአግያ የተወሰደ 

በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ


እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፤ ፊልጵስዩስ 2፥6 

« በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ» የሚለውን የግእዙ ዘር « ዘውእቱ አርአያሁ ለእግዚአብሔር» እርሱ የእግዚአብሔር አርአያ መልክ ነው ይላል። አማርኛችን « መልክ» ግእዙ « አርአያ» ግሪኩ « ሞርፌ» የሚለውን ቃል በዚህ ንባብ ውስጥ ቁልፍ ቃል ነው። መልክ ወይም አርአያ ተብሎ የተተረጎመው ቃል  አንዳንዶች ለመተርጎም እንዳሰቡት ውጫዊ ቅርጽን ሳይሆን ውስጣዊ ባህርይን ወይም እውነተኛ ማንነትን የሚያመለክት ነው። ሐዋርያው ይህን ቃል የተጠቀመው የክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት ግልጥ አድርጎ ለማሳየት የሚጠቅም ቃል ስለሆነ ነው። ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለዚህ ሲናገር «  ልክ በእግዚአብሔር ምሳሌ እንደተፈጠረው ሰው « እንደ እግዚአብሔር የመሰለ ባሕርይ ይዞ» አላለም። ነገር ግን ጳውሎስ « በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ አለ»  ይህም [የሚያመለክተው] አብ በወልድ ውስጥ ህልው መሆኑን ነው።» ይኸው ጎርጎርዮስ ስለእግዚአብሔር መልክ ሲናገር   « የእግዚአብሔር መልክ (አርአያ) ፍጹም ከባሕርዩ ( essence ) ጋር አንድ ነው። ነገር ግን በባርያ መልክ ይሆን ዘንድ በመጣ ጊዜ፥ [ሰው በሆነ ጊዜ] አንዱን ባሕርይ ብቻ አልወሰደም። ከእግዚአብሔርነቱ ባሕርይም አልተለየም።  ም 
ቅዱስ ጎርጎርዮስ በሚገባ እንዳሳየን ጳውሎስ በዚህ « በእግዚአብሔር መልክ»  በሚለው ቃል ክርስቶስ ቅድመ ሥጋዌ በአምላክነቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሲመለክ መኖሩን ካመለከተን በኋላ በሥጋዌው ወራት ግን ይህን አምላክነቱን በንጥቂያ አልወሰደም።  መከራ ለመቀበል የመጣ ስለሆነ በአምላክነቱ መከራ የሚያሳዩትን ለማጥፋት አልሞከረም።  የአምላክነቱን ባሕርይ ለማዳን ሥራው አቋራጭ መንገድ አድርጎ በንጥቂያ ወይም በሥርቆት ( መቀማት የሚለው የግሪኩ ቃል የሚያመለክተው ይህን ነው) አልሄደበትም።  
እዚህ ላይ ይህ ንባብ የሚያሳስበን የቀደመው አዳምን ነው።  እግዚአብሔር በመልኩ በአምሳሉ የፈጠረው ቢሆንም ትእዛዙን እንዲፈጽም ነግሮት ነበር ሆኖም ግን የእባቡን ቃል በመስማት ለእግዚአብሔር አልታዘዝም አለ። የእባቡ የማታለያ ቃል « እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ የሚል ነበር። ዘፍጥረት ም. 2 እና 3ን ተመልከቱ።
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
ባሪያ የሚለው ቃል በመጀመሪያ ለተጻፈላቸው ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ከዚህ በፊት እንዳመለከትነው ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ነው። ባሪያ ማለት ምንም ነፃነት የሌለው በጌቶቹ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚደገፍ ማለት ነው። « ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በክብር በባሕርይ የሚተካከለው በከፍታ ያለው አምላክ የሮም ዜጎች እጅግ የሚጸየፉትን እጅግ ዝቅ ያለውን ሕይወት ባርነትን መረጠ። ባሪያ ሆነ። የኛ አባቶች በትርጓሜያቸው እንዳመለከቱን እርሱ እግዚአብሔርነት ሳይኖረው እግዚአብሔርነትን የፈለገ አይደለም፥ ነገር ግን ለባሕርዩ የማይስማማና የሌለውን የባርያን መልክ ወሰደ። 

አምላክ ሰው ሰው የሆነበት ምሥጢር ከመዳን ነገር ጋር የሚያያዘው ለዚህ ነው። ሰው ሆነ ስንልም ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ ነው። ሐረገ ትውልድ ተቆጥሮለት ነው። ከመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ዘመን ጀምሮ የተነሡ የስህተት ትምህርቶች በዋናነት የሚክዱት በመጀመሪያ አምላክነቱን ሲሆን በሁለተኛ ሰውነቱን ነው። ይህ ንባብ ግን ቀደም ሲል ዮሐንስ አፈወርቅ እንደጠቀሰው የክርስቶስን አምላክነትና ሰውነት የሚክዱትን መናፍቃን አፍ የሚያዘጋ ነው። ለምሳሌ በእግዚአብሔር መልክ ሳለ የሚለውን « መልክ» የሚለውን ቃል በሌላ ለመተርጎም የሚፈልጉ አርዮሳውያን አሉ። ስለሆነ የምንጠይቃቸው ጥያቄ ይህ ነው። በእግዚአብሔር መልክ ሳለ የሚለው ቃል እግዚአብሔርነቱን የማይገልጥ ከሆነ በባሪያ መልክ  የሚለውስ ቃል ምንነቱን ይገልጣል?  በእግዚአብሔር መልክ ሳለ ሲል በእግዚአብሔርነቱ ወይም በመለኮትነቱ ሳለ ማለቱ ነው። ልክ እንደዚሁ የባሪያን መልክ ያዘ የሚለው ቃልም ፍጹም ሰውነቱን የሚያመለክት ነው። ይህም « ቃል ሰው ሆነ» ከሚለው የወንጌል ቃል ጋር ይስማማል። 

ብታረዝ አልብሳችሁኛል በተግባር ሲገለጥ


ጎዳና ተዳዳሪ የሆነው  ሰው በወገኖቹ ፍቅርና  እርዳታ በዓይናችን ፊት ሲቀየር 

እግዚአብሔር የሚከብርበት ክርስቲያናዊ ጋብቻ ባሕርያት
እግዚአብሔር የሚከብርበት ክርስቲያናዊ ጋብቻ የሚከተሉት አምስት ባሕርያት ይኖሩታል። 
  1. የእግዚአብሔር ቃል የኑሮአቸው መመሪያ ነው። « ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው»  በማለት መዝሙረኛው እንደተናገረው፥ ክርስቲያዊ ቤተሰብም በቃሉ በመመራት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያከናውናል። መዝ 119፥105። 
  2. ጸሎት የሕይወታቸው መሠረት ነው።  «እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል።ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።» በማለት ጌታ እንዳስተማረን ክርስቲያናዊ ቤተሰብ  የማይቻለውን ለእግዚአብሔር እያቅረበ የእግዚአብሔርን ጸጋ ይቀበላል። ማር 11፥23_24። 
  3. ፍቅር የቤታቸው ቋንቋ ነው። «  በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።» በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው፥ የክርስቲያናዊ ሕይወታችን ዋና አምድ ፍቅር ነው። በባልና በሚስት መካከል ሊኖረው የሚገባውም ፍቅር በሁኔታዎችና በጥቅም ላይ የተመሠረተ ፍቅር ሳይሆን መሥዋዕታዊ ፍቅር ነው። 1 ቆሮ 13፥1። 
  4. መደማመመጥ የዕለት ምግባቸው ነው። «የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ ሰማም» በማለት ነቢዩ እንደተናገረው፥ ( ሚልክያስ 3፥ 16 በመደማመጥ ውስጥ ፍቅር ይዳብራል። የተሰበረ ይጠገናል፤ የታመመ ይፈወሳል። እግዚአብሔር ጸሎትን ይሰማል። «ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።» 1 ጴጥሮስ 3፥ 7። 
  5. ደስታ ውበታቸው ነው። የእግዚአብሔር ቃል «ምንጭህ ቡሩክ ይሁን ከጕብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ።እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ፥ ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ፥ በፍቅርዋም ሁልጊዜ ጥገብ።» ምሳሌ 5፥ 18_19። ይላል።  እግዚአብሔር የከበረበት ቤተሰብ ደስተኛ፥ ፈገግተኛና ለዛ ያለው ቤተሰብ ነው። 


Wednesday, November 13, 2013

የሥራ ቦታችሁ ለጤናችሁ ጠንቅ የሚሆንበት አምስት መንገዶች (አምስተኛ ክፍል)

የፉክክር ስሜት
  
Slide Image
በቢሮ አካባቢ የሚሆን ውስጣዊ ፉክክር ለድርጅቶች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ሰዎች በርትተው እንዲሠሩና ሰፋ አድርገው እንዲያስቡም ያአርጋቸዋል። ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ ውድድር ወይም ፉክክር  ጤናማ ወደ አልሆነ አቅጣጫ ሊወሰድም ይችላል። ሰዎች እርስ በእርሳቸው ሊቃረኑ፥ ስለ ሥራቸው ዋስትና ሊፈሩ ና መላ ሕይወታችው ላይ ተጽእኖ እስከሚያመጣ ሊዘልቅ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሰዎች ከሌላው ሁሉ በልጠው ለመታየት እንዲያስቡ ሊመራቸው ወይም አንዱ ሌላውን ወደ ታች እንዲስብ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይህም አንዱ አንዱን ከበስተኋላ መውጋት ቡድናዊ መሆንና ሌላውን ማጥቃት ሊያመጣ ይችላል።   
  
ታዲያ ምን እናድርግ? በአመራር ላይ ያላችሁ ሁኑ ወይም የበታች ሠራተና ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትን አበረታቱ፤ ከሥራ ጓደኛችሁ ጋር ጤናማ የሆነ ውይይት ለማድረግ ራሳችሁን ክፍት አድርጉ፤ ይህም ለሰውነታችሁ ሆነ ለአእምሮአችሁ ጤናማ የሆነ እርምጃ ነው። ይህን በማድረጋችሁ ውጤታማ ትሆናላችሁ አዎንታዊና ጤናማ በሆነ መንገድም ዕድገት ከፍ ወዳለ ደረጃ ልትደርሱ ትችላላችሁ።

ምንጭ beliefnet 

ኃያላን እንዴት ወደቁ

ባለፈው ወር የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ኮንግረስ) እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቶ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ውኃ እንዲበላው ሲያደርግ፥ ዓለም ሁሉ አሜሪካውያን ምን ነካቸው እንዲል አድርጎ ነበር። ከዚህ የሚቀጥለው ምስል ግን ችግሩ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
ይህ ምስል እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1989 የነበረው ኮንግረስ ሁለቱ ፓርቲዎች እንዴት አብረው ይሠሩ እንደነበረ የሚያሳይ ነው። ሪፐብሊካንና ዲሞክራት ለአገራቸው በአንድ አሳብ በመስማማት ይሠሩ ነበር። 

ይህ ደግሞ አሁን በሥራ ላይ ያለው ኮንግረስ የሚሠራበት መንገድ ነው። አገር ሲወድቅ እንዲህ ነው ይሉሃል ። ይህን ግራፍ ሳይ ወደ አእምሮዬ የመጣው ሕያው የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ነው። « እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም።» ማቴዎስ 12፥25    ቶማስ ፍሪድማን እንዳለው እሜሪካ ባንቀላፋችበት በእነዚህ ዓመታት ቻይና ዓለምን እያስገበረች ነው። የኛዋንም ኢትዮጵያን ሳይቀር። ሙሉ ትንተናውን ለማየት እዚህ ላይ ይጫኑ


የሥራ ቦታችሁ ለጤናችሁ ጠንቅ የሚሆንበት አምስት መንገዶች (አራተኛው ክፍል)

ውኃ አለመጠጣት 
Slide Image
በቂ ውኃ አለመጠጣት የተለያዩ የጤና ቀውሶችን ያስከትላል፤ ከእነዚህ መካከል፦ ራስ ምታት፥ የስሜት መጨቆን ድርቀት ይገኛሉ። በማናቸውም ሁኔታ መልካም ያይደሉ በተለይም ደግሞ ንቁና ምርታማ መሆን በምትፈልጉበት በሥራ ገበታችሁ  መፍዘዝ፥ ድካም እና ከመጠን ያለፈ ትኩሳት ሊያጋጥማችሁ ይችላል።   

ታዲያ ምን እናድርግ? ምንም ባይጠማችሁ እንኳ ውኃ ዝም ብላችሁ ጠጡ። ስምንት ብርጭቆ ፈሳሽ በቀን ለመጠጣት ዓላማችሁ አድርጉ፤ ቢሮአችሁ ወይም ውጭው የሞቀ ከሆነ ከዚህ የበለጠ ብትጠጡ የተሻለ ነው። የውኃ መጠጫ በቢሮ ጠረጴዛችሁ አቅራቢያ መሆኑ ቀኑን ሁሉ በየጊዜው ለመጠጣት ይረዳችኋል፤ ከዚህ በተሻለ ደግሞ በቢሮአችሁ አካባቢ ወዳለው የውሃ መጠጫ እየሄዱ ቀድቶ መጠጣትን ልማድ አድርጉ። ይህም ሰውነታችሁን ለማንቀሳቀስና ለማርካት ይረዳል።   የውሃ ኮዳ ወይም እንደገና ልትጠቀሙበት የምትችሉበትን የውኃ መጠጫ ለመጠቀም ሞክሩ። በዚህም በእንድ ጉዞአችሁ ብዙ ውኃ ልትቀዱበት ትችላላችሁ አካባቢያችሁንም ከብክለት ትጠብቃላችሁ። 

የሥራ ቦታችሁ ለጤናችሁ ጠንቅ የሚሆንበት አምስት መንገዶች ( ሦስተኛው ክፍል)

ያልተመጣጠነ አመጋገብ  
 
Slide Image
የምግብን ነገር ወደኋላ ማድረግ ቀላል ነገር ነው። ቍርስን መተው ፥ ጤናማ ያይደለ ነገር መቀማመስ፥ በጥድፊያ፥ በመንገድ ላይ ሆኖ ወይም በቢሮ መብላት የተለመደ ነው። ፈታኙ የቢሮ የልደት ኬክ ሳይጠቀስ ነው።  

 ታዲያ ምን እናድርግ? በመጀመሪያ ሰውነታችሁ ኃይል እንዲያገኝና ለውሎአችሁ ጉልበት እንዲሰጣችሁ በቂ ቁርስ ማግኘታችሁን እንዳትዘነጉ። በዕለቱ ስለምትመገቡት ምግብ አስቀድማችሁ ዕቅድ አውጡ። ዕቅድ ማውጣት ከመቅሰስ መቸርቸሪያ ማሽኖች ( Vending machines) እና የይድረስ ይድረስ ምግቦች  ( fast food.) ራቅ እንድሉ ያደርጉአችኋል። ለመቅሰስ ሊሆኑ የሚችሉ ምግባ ምግቦች በ ለምሳሌ አትክልት፥ ቅጠላቅጠሎች ጥራጥሬዎች (በተለይ የለውዝ ዝርያዎች) በአጠገባችሁ ይሁኑ፤ ሆኖም ምግባችሁን ከጠረጴዛችሁ አጠገብ አርባ አርቁት። በተቻለ መጠን የምትበሉትን እያስተዋላችሁ እንጂ በችኮላ ወደ አፍ በመውሰድ አትብሉት። 

የሥራ ቦታችሁ ለጤናችሁ ጠንቅ የሚሆንበት አምስት መንገዶች (ሁለተኛው)

ረጅም ሰዓት ያለዕረፍት መሥራት
   
Slide Image
ያለማቋረጥ ተጨማሪ ሰዓት መሥራት ጠቀም ያለ ገንዘብ ቢያስገኝም ነገር ግን ተገቢ የሆነ እረፍት እና የተስተካከለ አመጋገብ እንዳይኖራችሁ ያደርጋል። የዕንቅልፍ ዕጦት በአካላዊና የአእምሮ ጤና መቃወስ ላይ ዓይነተኛ የሆነ ተጽዕኖ አለው። የዕንቅልፍ ዕጦት የማስታወስ ችሎታን ይቀንሳል፤ የመንፈስ መናወጥን ( Depression) አሉታዊ የሆነ ማኅበራዊ ግንኙነትን ይጨምራል። 


ስለዚህ ምን እናድርግ? በተቻለ መጠን የማይቋረጥ የሰባት ሰዓት ዕንቅልፍ በቀን ለማግኘት ዓላማ አድርጉ። ሁለንተናዊ ጤናችሁን ተከታተሉ፤ ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር የበለጠ ጊዜ ይኑራችሁ። ይህን ካደረጋችሁ ውጥረታችሁ ቀንሶ በሥራ ገበታም ሆነ በሕይወታችሁ የሚያጋጥማችሁን ተግዳድሮት ለመጋፈጥ ትችላላችሁ።   
(ይቀጥላል ) 
ምንጭ ፦ beliefnet 

የሥራ ቦታችሁ ለጤናችሁ ጠንቅ የሚሆንበት አምስት መንገዶች

መቀመጥ                                                                                                              
of 7

Slide Imageለረጅም ጊዜ መቀመጥ አሉታዊ የሆነ 
ተጽእኖ በጤናችን ላይ ያመጣል።  ለክብደት መጨመር፥ ለልብ ድካም በሽታ እና ሌላው ቀርቶ ለካንሰር መጋለጥን ያፋጥናል። ወደ ጀርባ፥ አንገትና ትከሻ ሕመም የሚመራ አጓጉል የሆነ የሰውነት አቋም እንዲኖርና ወደታችኛው የሰውነት ክፍል የደም መዘዋወር በሚገባ እንዳይኖር ያደርጋል። 
ታዲያ ምን እናድርግ? መቀመጥን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አንችልም። ነገር በተቻለ መጠን አመቺ ጊዜ ባገኘን ቁጥር ለመቆም እንሞክር፤ ከተቻለም 
 በየመሃሉ ለመቆም ዕረፍት እንውሰድ። ከሥራ ባልደረባችሁ ጋር ስትወያዩ ወይም የቴሌፎን መልእክት ስትቀበሉ ራስን ለማፍታታት መንጠራራትንና በዚያው ባላችሁበት ቦታ መንቀሳቀስን ልምድ አድርጉ። በቀን ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት በቢሮአችሁ ውስጥ የምታደርጉት  የአምስት ደቂቃ ያህል የሰውነት ማፍታታት እና እንቅስቃሴ የሰውነት የደም መዘዋወርን የሚያሻሽልና ኃይልን የሚሰጣችሁ ነው።  
(ይቀጥላል)

ምንጭ ከ beliefnetኢትዮጵያዊነት በአደባባይ ሲወድቅ


የፋሽሽት ጣልያንን ወረራ ጊዜና እርሱን ተከትሎ የነበረውን ሰቆቃ ያስተዋሉ ሰዎች፥ ሁሉ አልፎ ነጻነት ካገኙ በኋላ፥ አንዳንድ ጊዜ ነጻነታቸው ሲገፈፍ እና መብታቸው ሲታፈን “ በሕግ አምላክ ወድቆ በተነሣው ባንዲራ!” ይሉ ነበር። ዛሬ በአረብ አገር ላይ ወድቆ እያየነው ያለነው  ባንዲራው ወይም ሕጉ ሳይሆን ኢትዮጵያውነት ራሱ ነው። 
ዛሬ በአረብ አገሮች እንደ አበዱ ውሾች እየታደኑ የሚደበደቡት የሚታሠሩት ኢትዮጵያውያን የሚጮኽላቸው ለዜጎቹ የሚቆምላቸው አካል እንደማይኖር ስለታወቀ ነው። በእኛ ኢትዮጵያውያን ነን ስንል በኖርነው ዘንድ እንኳ ኢትዮጵያውነታችን ነውረኛ አሳብ ስለሆነብን፥ ከኢትዮጵያውነታችን ይልቅ ጎጣችንን መንደራችንን ጎሳችንን ዘራችንን መቍጠር ስለጀመርን ኢትዮጵያዊን ከሰው የሚቆጥረው የለም። 

ኢትዮጵያዊነት በአደባባይ የወደቀው በአረብ አደባባይ አይደለም፤ በአረብ አደባባይስ ኢትዮጵያዊነትን ለመግደል፥ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ለዘመናት ተጎንጉኖ፥ ተቋጥሮ ተፈቶ አልተሳካም ነበር። የአልጄሪያው ደባ፥ የሊቢያው ስጦታ፥ የሳውዲው ስለት፥ የደማስቆው ፖለቲካ ምንም አላመጣም ነበር። 
ኢትዮጵያውያዊነት የወደቀው በራሷ በኢትዮጵያ አደባባዮች ላይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ክብር ሳይሆን መርገም እንደሆነ የተነገረው በራሷ አደባባይ ነው። ወጣቱ በገዛ አገሩ ተስፋውን ሲያጣ አብሮ የመኖር ተስፋን ሲያጣ፥ የማደግ ተስፋን ሲያጣ፥ በገዛ አገሩ የዝግታ ሞት ከሚሞት፥ በሶማሊያ በረሃዎች በረሃብ ተቃጥሎ መውደቅ ይሻለኛል አለ። ጠኔ በገደለው አንጀቱ በገዛ አገሩ የሞት ሞትን ከምሞት በሲናይ በረሃዎች በበድዊኖች ተገድሎ ሬሳው ለሽያጭ እንዲቀርብ አደረገው። ወደየመን ለመሻገር ሲሉ ቀይ ባሕር የበላቸው ወደ ማልታ፥ ወደስፔይን፥ ወደጣልያን ለመሻገር የሜዲተራኒያን ባሕር የበላቸው ስንቶች ናቸው።  
ዛሬ ጥቂት የዩቱዩብ ቪዲዮዎች ስሜታችንን መቀስቀሳቸው መልካም ነው። ግን ይህ የተቀሰቀሰው ስሜታችን ሊጠይቀው የሚገባው ነገር ይህ ነው። በገዛ ደጃፋችን የወደቀው ኢትዮጵያዊነታችን የሚነሣው መቼ ነው?  ኢትዮጵያዊው በብሔሩ፥ በጎሳው ወይም በመንደሩ ሳይሆን በሰውነቱ ክብር የምንሰጠው መቼ ነው? ይህ በሽታ ሁላችንም ላይ ከላይ እስከታች የተጋባብን ነን። 

ለገዛ ወገናችን፥ ለዚያ  ለአንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ ክብር መስጠት እስካልቻልን ድረስ ለብዙዎቹ ክብር መስጠት አንችልም። እኛው ለራሳችን ክብር ካልሰጠን ማንም ክብር ሊሰጠን አይችልም። ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ . . . እንዲሉ አባቶች። 

የግብጽ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የአገሪቱ ፕሬዝደንት ልዩ ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልጠው ሕግ ውድቅ ሆነ

  • ይህ ድርጊት ለዘመናት ሲሠራበት የነበረ ሲሆን አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻቸውን ቀለም ለመቀባት ተከልክለው ከዓመታት በላይ አሳልፈው ነበር 

የሙስሊም ወንድማማቾች (muslim brotherhood) መንግሥትን መወገድ ተከትሎ በግብጽ የኦርቶዶክስ ምእመናን ላይ የሚደርሰው ግፍና አፈና እንደቀጠለ ቢሆንም ባለፉት መቶ ዓመታት በግብጽ ክርስቲያኖች ጫንቃ ላይ ተጭኖ የነበረው አንድ ሕግ በመሻሩ በመከራቸው ውስጥ ታላቅ የምሥራች አግኝተዋል። 

ከሃይማኖታዊ መልኩ ይልቅ የፖለቲካ እስልምናን  በሚያራምደው የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ጸቅቆ የነበረውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥትን አሻሽሎ ሁሉን የአገሪቱን ዜጎች በእኩል ዓይን የሚመለከት ሕገ መንግሥት ለማድረግ  የተሰበሰበው የምሑራን ክፍል ከዚህ በፊት ባሉት መንግሥታትም ለምሳሌ በሆስኒ ሙባረክ ጊዜም ለብዙ ዓመታት ሲሰራበት የነበረውንና ክርስቲያኖችን ለማፈን ዓይነተኛ መሣሪያ የነበረውን ቤተ ክርስቲያንን ለመሥራት የአገሪቱ ፕሬዝደንት ልዩ ፈቃድ ያስፈልጋል የሚለውን ሕግ ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሠርዘውታል። በዚህ ሕግ መሠረት እድሳት ለማድረግ ከ50 ዓመት በላይ ፈቃድ ሲጠብቁ የኖሩ አብያተ ክርስቲያናት እንደነበሩ ተጠቅሶአል። አሁን ግን ቤተ ክርስቲያኗ የማንንም ፈቃድ ሳትጠይቅ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ትችላለች። በነገራችን ላይ በዚህ በሰሞኑ የእስላማውያን ቅስቀሳ ከ80 በላይ አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉ ሲሆን እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ግምት ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ ንብረት ወድሞአል። 

በጥልቀት ለማንበብ pravoslavie.ru ይጎብኙምን ያህል ዕዳ አለባችሁ?

የአሜሪካንን የመካከለኛ መደብ ማኅበረሰብን እግር ከወርች ቀይዶ የያዘው የዕዳ ጉዳይ ነው። ሕይወት ማለት ለብዙ አሜሪካውያን የባንክ ወለድ መገፍገፍ ሆኖአል። የክሬዲት ካርድ ያላማረረው ማን ነው? ከመካከለኛ መደብ እጅግ በባሰ ሁኔታ ደግሞ መጤውንና ( immigrants) ደኃው ኅብረተሰብ በሆነ ባልሆነው እያባበሉት ከማይወጣበት የዕዳ ሐዘቅት ውስጥ እያስገቡት ነው።

Occupy Wall Street
" የኛ ዋና ዓላማ ይህን የሁለተኛ ዕዳ ገበያ (Second Debt Market) መረጃን ማሰራጨት ነው።   Photograph: Spencer Platt/Getty Images
ሆኖም ግን የ2011 ዓም በባንኮች ላይ የተካሄደውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ የመራው አካል ( Occupy Wall Street) ይህን የባንኮች በስስት ላይ የተመሠረተ አይጠግቤነትና ኅብረተሰቡን በወለድ አግድ በዕዳ መያዙ አምርሮ መቃወሙ ይታወቃል። በመሆኑም ይህ እንቅስቃሴ የወለደውና  የግለሰቦችን ዕዳ በማስወገድ ላይ በዋናነት ያተኮረው Rolling Jubilee ተባለው ቡድን የግለሰቦችን ዕዳ ከባንኮች እጅግ በቅናሽ ዋጋ በመግዛት ከ15 ሚሊዮን በላይ የግለሰቦችን ዕዳ ለማስወገድ ችሎአል። 
ዕዳውን ከባንኮች እጅግ በቅናሽ ዋጋ ስለሚገዛው ቡድኑ የ14,734,569.87 ዶላር የግለሰቦችን ዕዳ 400,000 ዶላር በማውጣት  ማቃለል ችሎአል። እንደ አንድሪው ሮስ የቡድኑ አባልና በኒዮርክ ዩንቨርስቲ የማኅበራዊና ባህላዊ ትንታኔ ፕሮፌሰር ገለጻ ከሆነ  ዕዳው እንደዚህ ሊቀል የቻለው የሁለተኛ ዕዳ ገበያ ካለው ባህርይ የተነሣ ነው። ባለዕዳዎች ብዙ ጊዜ ስለማይከፍሉ፥ ባንኮች ዕዳውን ለሌላ ሦስተኛ ወገን የሚሸጡት እጅግ ርካሽ በሆነ ሁኔታ በአብዛኛው ለአንድ ዶላር  ዕዳ እምስት ሳንቲም ያህል በመጠየቅ ነው። በመሆኑም የዕዳ አስወጋጁ አካል ዕዳውን በርካሽ ከባንኮች በመግዛት ግለሰቦችን የዕዳ ኪሳራ ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል። ዕዳ አስወጋጁ አካል በዋናነት ያተኮረው የሕክምና ዕዳ ላይ ነው። 
ሮስ እንደሚለው ከሆነ ዕዳቸው በዕዳ ሰብሳቢዎች (debt collectors) ምን ያህል በርካሽ እንደተገዛ የሚያውቁ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ሲሆን ይህን ማወቅ ደግሞ ስለ ዕዳ ሥነ ልቡናዊ ለውጥ ይሰጣል ። በመሆኑም ዕዳ ሰብሳቢዎች ሲደውሉና ዕዳችሁን በሙሉ እንድትከፍሉ ሲጠይቁ፥ ዕዳ ሰብሳቢዎች ዕዳችሁን እጅግ በጣም በጣም ርካሽ በሆነ መንገድ ገዝተውት እንደሆነ ታውቃላችሁ ማለት ነው። ይህም ከዳ ሰብሳቢዎች ለምታደርጉት ንግግር የሞራል ብርታት ይሰጣችኋል 
በመልካም ነገር ሕዝቡን የሚያስተምርና ነጻ የሚያወጣ አዎንታዊ ተቃውሞ ማለት ይህ ነው። 
  ምንጭ፦ ዘጋርዲያን 

Tuesday, November 12, 2013

አዘክሪ ኵሎ


ታላቁ ባለቅኔና ደራሲ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፥ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ልጇ ወዳጇን ይዛ በስደት ወደ ምድረ ግብጽ መሄዷን አነጻጽሮ በፋሽሽት ጣልያን ለስደትና ለስቃይ የተዳረጉትን እያሰበ የተቀኘው ቅኔ ሰሞኑን በስደት ዓለም ሳሉ ሕይወታቸው በስቃይ ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን የበለጠ የምናስብበት ይሆናል። ዘመኑም የጌታችንን ከእናቱ ጋር ስደት የምናስብበት ስለሆነ፤ አሁንም ወገኖቻችንን ወደ አገራቸው በሰላም ያግባልን። 

ድንግል ሀገሬ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ
ሕፃናቱም ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ
ልጅሽ ተሰደደ አንቺን ተከትሎ፣
የሕፃናቱን ደም አዘክሪ ኩሎ፡፡
አስጨነቀኝ ስደትሺ፣
እመቤቴ ተመለሺ፣ ተመለሺ…

ተአምራት በሥራ ገበታ፤ የኤቢሲ ጋዜጠኛ ማሞግራምና ውጤቱ

በጥቂቱም በብዙም ማዳን የሚቻለው እግዚአብሔር አድኅኖቱን የሚያሳይበት መንገድ ብዙ ነው። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ተአምራቱን የሚያሳየው በዕለት ተግባራችን በምናሳየው ታማኝነት ነው። በዚህ በአሜሪካ የአሜሪካ ዜና ማሰራጫ ድርጅት ( abc) ጋዜጠኛ የሆነችው አሚ ሮባክ አለቃዋ አንድ ነገር እንድታደርግ ይጠይቃታል። የካንሰር ቀንን ምክንያት በማድረግ በሚሊዮን ተመልካቾች ፊት አሚ የጡት ካንሰር ምርመራ ( ማሞግራም) እንድታደርግ ይጠይቃታል። እርሷም እሺ ትላለች፤ ምርመራውን ለGood moring America ካቀረበች በኋላ ዶክተሮች ዱብ እዳ ይነግሩአታል። የጡት ካንሰር በሽተኛ መሆኗን። ሆኖም ግን አስደሳች ነገር ይነግሯታል። ያ በሥራዋ ምክንያት ለቴሌቪዥን ማስታወቂያ ያደረገችው ምርመራ ሕይወቷን አድኖአታል። ምክንያቱም ገና በመጀመሪያ ደረጃው ነበር ካንሰሩን ያገኙት።   አሚ በጻፈችው መጣጥፍ ላይ እንደገለጠችው ይህ በእርሷ ሕይወት ያጋጠማት ድርጊት ለብዙ እህቶች ትምህርት ሆኖ በጊዜ የጡት ምርመራ እንዲያደርጉ እንደሚያነሣሣ ተስፋዋ ነው። እኔ ይህን ተአምር ብዬዋለሁ በእለት ተእለት ሕይወታችን በሚኖረን ታማኝነት የምናገኘው በረከት።

ምንጭ ABC News


የአባትንና የእናትን ምክር መስማት


ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ 
የእናትህንም ሕግ አትተው
ለራስህ የሞገስ ዘውድ 
ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና።      
መጽሐፈ ምሳሌ 1፥8


ከ1960ቹ ጀምሮ እንደባህል የተያዘው ወላጆች ኋላ ቀር እንደሆኑና ምንም ሊያስተውሉ እንደማይችሉ፤ ወጣቱንም ሊረዱት እንደማይችሉ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አባቶችን እናቶቻችንን መናቅና እንዳላዋቂ ማየት ሊቅነት ሆኖአል። በመሆኑም በዕድሜ የበለጸጉት አባቶቻችንና እናቶቻችን ከዕድሜያቸው የተማሩትን ከቀደመው ሕይወት የያዙትን  ጥበብና የኑሮ ብልሃት እንደያዙ ተለይተውናል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተነሣው ትውልድ አቅጣጫ ጠቋሚ ያጣ ትውልድ ነው። ይህ በአጠቃላይ በመላው ዓለም የታየ ክስተት ነው። 

እኛን በመሰሉ አዲስ መጤ ማሕበረሰቦች ( Imgrant communities) ደግሞ ችግሩ ሰፊ ነው። ልጆቻችን ከእኛ ቀድመው ቴክኖሎጂውን ቋንቋውን ይይዙታል። በዚህን ወቅት በቤተሰብ ውስጥ ሳናውቀው ሚና እንቀይራለን። ልጆች ራሳቸውን እንደ አዋቂ መቁጠር ይጀምራሉ። ወላጆቻቸውን መስማት ያቆማሉ። በወላጆቻቸው የቋንቋ ችሎታ መሳቅ ሲጀምሩ ሁሉ ነገር እዚያ ላይ ያቆማል። ወላጆችም አውቀውት ይሁን ሳያውቁት ልጆቻቸውን እግዚአብሔር ያስተማራቸውን የኑሮ ብልሃት ማሳየት ያቆማሉ። ለምን ተብለው ሲጠየቁ « እኔን የሚያስተምሩኝ እነሱ ናቸው» ይላሉ። የአውራ ጎዳናውን መውጫ መግቢያ ሊያሳዩን ይችላሉ። ቋንቋውን እንደ አገሬው ተወላጅ (እነርሱም እዚህ ተወልደው ሊሆን ይችላሉ) ሊያንበለብሉት ይችላሉ። ነገር ግን የሕይወትን ጥበብ ከየት ይማራሉ። 
ሕይወት ከቋንቋ በላይ ነው። ሕይወት ከtexting, surfing, driving በላይ ነው። ሕይወት ጥበብ ይጠይቃል። የዚያ ጥበብ መጀመሪያ ደግሞ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።  ልጆች እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ችሎታ አለ። አንዳንዱን በዚያ በብሩህ አእምሮአቸው ከአካባቢያቸው ቀስመውት ያገኙታል። ነገር ግን ከሌላ ከማንም  የማያገኙት ከእኛ የሚማሩት ብዙ ነገር አለ። በሕይወታቸው እጅግ ወሳኝ የሆነ ነገር። 
እግዚአብሔርን መፍራት ከእኛ ይማራሉ። 
ኑሮን በጸጋና በምስጋና መቀበልን ከእኛ ይማራሉ። 
በትንሹ ማመስገንን ከእኛ ይማራሉ። 
ለሌላው መኖርን ከእኛ ይማራሉ። 
በጥንቃቄ መመላለስን ከእኛ ይማራሉ።
የመጀመሪያው የልብ ስብራት ሲያጋጥማቸው፥ የመጀመሪያውን ቼክ ሲቀበሉ፥ የመጀመሪያ ጓደኛ ሲይዙ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ውጪ ሲያመሹ፥ የሚጠቅማቸው ከወላጆቻቸው የተማሩት መሠረታዊ የሆነው የኑሮ ጥበብ ነው። 
አባትና እናት ካለፈው ስኬታቸውም ሆነ ስህተታቸው ተምረው አደጋን ወይም ጥፋትን ከሩቅ ያስተውላሉ። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ወላጆችን  እንደ smoke detector ወይም ወይም እንደ ውሻ አፍንጫዎች እመስላቸዋለሁ። የጢስ አመልካቹ መሣሪያ በተለይ እንደኔ ላላችሁት ቡና ለምትወዱ እሪታው መንደር ላትወዱት ትችላላችሁ። ሆኖም ቤትን ከመቃጠል ያድናል። እሳት ያሸታል፤ ከእሳት ያድናል።።  በዚያ በክረምቱ በአዲስ አበባ ብዙዎች  በከሰል ጢስ (ካርቦን ሞኖኦክሳይድ)  ታፍነው ያለቁት ጢስ አመልክቴ (smoke detector)  በቤታቸው ስለሌለ ነው። የውሻ አፍንጫ የተቀበረ ፈንጂ  በማነፍነፍ ሰዎችን ከዕልቂት የሚያድን ሆኖአል።  ወላጆች እንደዚህ ናቸው። ዕድሜ፥ ኑሮ፥ የራስ ስህተትና ስኬት ያስተማራቸውን ይዘው ይመክራሉ። ለልጆችና ለወጣቶች የምላቸው ይህን ነው። ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ የእናትህንም ህግ አትተው። 

Monday, November 11, 2013

የተሰባበሩ መስተዋቶች ምሽት (Kristallnacht)

 በመላው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሳውድ አረቢያ ለሚሰቃዩት እኅቶቹና ወንድሞቹ ድምጹን ሲያሰማ፥ በአውሮፓ አንድ ታሪካዊ ዝክር እየታሰበ ነው። በአውሮፓ አቆጣጠር ኖቬምበር 10 ቀን የተሰባበሩ መስተዋቶች ምሽት ወይም በጀርመንኛው Kristallnacht ይባላል። ይህ በናዚ ፓራሚሊተሪዎችና የናዚ ደጋፊዎች የተቀነባበረ ዘመቻ በጀርመንና በኦስትሪያ በሚገኙት አይሁድ ላይ ጥቃትና ድብደባ የተካሄደበት ምሽት 75ኛ ዓመት መታሰቢያ ነው። 
በዚያች አስጨናቂ ምሽት ከ90 በላይ አይሁዶች የተገደሉ ሲሆን ከ30,000 በላይ የሚሆኑ ወደ ማሰቃያ ካምፖች ተወስደዋል። ይህን አሳዛኝ የሆነውን ታሪካዊ ምሽት ለማክበር ክርስቲያኖችና አይሁድ በጋራ ጸሎት አድርገዋል። በኢንግሊዝ አገር በዌስት ሚኒስተር አቤይ ለተሰበሰቡ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ንግግር ያደረጉት ራባይ እንደተናገሩት ይህ ቀን መታሰብ ያለበት በተስፋ መልእክት ነው ብለዋል። 
A boy cleans the street after Kristallnacht in November, 1938.
 አይሁዳውያኑ ሱቆች ተሰባብረው 
A boy cleans the street after Kristallnacht in November, 1938.Photo courtesy Wikimedia Commons/Public Domain

እኚ ራባይ ሲናገሩ « ያን ሽብር፥ ግድያና፥ ውድመት፥ የወላጅ የቤተሰብ የጓደኛ እጦት ስናስብ፥ ዛሬ ክርስቲያኖችና አይሁድ በጋራ ሆነን ተራ የሆኑ ሰዎች አስደናቂ ነገር ማድረግ እንደሚችሉ በማሰብ እናክብር፤. . .  እኛ  ዛሬ በሕይወት ያለነው በመላው ዓለም ላይ ስለሕይወታቸው ፈርተው ያሉትን ልንረዳ ጠመዝማዛውን የቢሮክራሲ ሰንሰለት አልፈን አንድ ነፍስ እንኳ ብንረዳ ብለዋል። በትውፊታችን እንደተጻፈው አንድ ነፍስ ያዳነ አለምን ሁሉ እንዳዳነ ነው» ብለዋል። 
እውነት ነው፤ ራባዩ ያነሱት የአይሁድ ትውፊት ላይ የአንድ ሰውን ሕይወት የገደለ የሰው ዘርን በሙሉ እንደገደለ እንደሚቆጠርም ይነገራል። 
ዛሬ ይህን ታሪካዊ ምሽት ስናስብና 6 ሚሊየን የሚሆኑ አይሁድ ላይ የደረሰውን ሰቆቃ ስናስብ ዛሬም ለአንድ ሰው ሰብአዊ ሕይወት፥ መብትና ነጻነት የመቆም ታላቅ ኃላፊነት አንዳለብን ማስታወስ ይገባናል። 
ይህ አሳዛኝ ድርጊት በአገሩ ላይ ሲደረግ በዝምታ በመመልከቱ ጸጸት ውስጥ የገባው የጀርመን ሉተራን ቄስ ያለውን እዚህ ላይ ማስተዋል አለብን። « መጀመሪያ ወደ ኮሚንስቶች መጡ፥ እኔ ኮሚንስት ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። ቀጥሎ ወደ ሠራተኛ ማኅበራት መጡ የሠራተኛ ማኅበራት አባል ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። ወደ አይሁድ መጡ አይሁድ ስላልሆንኩ ምንም አልተናገርኩም። በመጨረሻ ወደ እኔ መጡ። ስለ እኔ የሚናገርልኝ አንድም የተረፈ አልነበረም። 
 ምንጭ፦Religion News Service