Read in PDF
የትምህርት ቤቱ አመሠራረት
የትምህርት ቤቱ አመሠራረት
የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ስንል፥ በዘመናዊ አስተሳሰብ የትምህርት ቤት ሕንፃ አናስብም፤ ሌላው ቀርቶ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እንኳ አናስብም። ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በአስተማሪው ቤት ነው። (ይህ አሁን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጠው ማለት ነው።)
ይህ የክርስቲያን ትምህርት ቤት በመጀመሪያ የተጀመረው እንደ ንዑሰ ክርስቲያን (ካታኪዝም) ትምህርት ቤት ነው። ማለትም የክርስትናን እምነት ተምረውና መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ለጥምቀት የሚዘጋጁ ከአረማዊነት ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች የሚማሩበት ነው። የትምህርት ቤቱ ዲን ንዑሰ ክርስቲያንን ለጥምቀት የሚያዘጋጁ ነበሩ። የትምህርት ቤቱ ዲን የነበረው አርጌንስ በመጻሕፍቱ ውስጥ ስለእነዚህ ንዑሰ ክርስቲያንን አስተማሪዎች (ካታኪስት) ዘግቦአል። አስተማሪው የክርስትናን አስተምህሮና ክርስቲያናዊ ሕይወት ያስተምር ነበር። « ጥምቀትን ለመቀበል ከፈለጋችሁ» ይላል አርጌንስ፥ « በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ቃል መማር አለባችሁ፤ ከቀደመው ከክፋት፥ የአሕዛባዊ ሕይወትና አነዋወር ሥር መለየት አለባችሁ፥ የዋህነትንና ትህትናን መለማመድ አለበኣችሁ። የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ለመቀበል የተገባችሁ የምትሆኑት ከዚህ በኋላ ነው፤»