Tuesday, May 29, 2012

ክፍል ሁለት ሕይወትን የሚለውጥ መልእክት 1:11-2:21



ይህን ከመጀመራችን በፊት ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን ነገር ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቴ ያለው ቦታ ምን ያህል ነው:: የክርስቶስ ወንጌል ሕይወቴን ምን ያህል ለውጦታል? ይህን የእግዚአብሔርን ቃል መማሬ በተግባሬ በኑሮዬ አካሄድ እና እርምጃ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ አምጥቶአል? ክርስትና የለውጥ ሃይማኖት ነው:: በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ በሚገርም ሁኔታ የእርሱን ሕይወት በጥንቃቄ እንድንመለከት ይነግረናል:: ገላትያ 4:12:: 1ቆሮ 4:16:: 11:1:: ፊል 3:17:: 4:8-9:: 

ሀ. ጳውሎስ የጸጋውን ወንጌል በቀጥታ ከጌታ ስለመቀበሉ:: 1:10-12
ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤12 ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።
1. ጳውሎስ ወንጌሉን የሰበከው በሰዋዊ መንገድ አይደለም። 
2. ጳውሎስ ወንጌሉን  ከሰው አልተማረውም ወይም አልተቀበለውም።
<< እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም>>


ለ. የጳውሎስ የቀደመው የይሁዲነት ሕይወት ለጸጋው ወንጌል መነሻ አለመሆኑ 1:13-14
በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥14 ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።

ሐ. ጳውሎስ ወንጌሉን የተቀበለው ከሰው አይደለም:: 1:15-24:: 
በቍጥር 11-12 ላይ የጀመረውን ወንጌሉን በትምህርትና በሰው ትውፊት እንዳልተቀበለው ይልቁኑም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገለጠለትና ይህንንም ወንጌል ለማስተማር ሲነሳ ከማንም ሰው ጋር እንዳልተመካከረ በመግለጥ የእርሱ ወደ ክርስትና መግባት በይሁዳ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት (ማኅበሮች) መካከል እንዴት አድናቆትን እንደፈጠረ ይነግረናል:: 

1. እግዚአብሔር የክርስቶስን የጸጋ ወንጌል ለጳውሎስ የገለጠበት ሁኔታ
 ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥

2. ጳውሎስ ከሐዋርያት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘበት ሁኔታ 
ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። 18 ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤19 ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። 20 ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።21 ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። 22 በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ 23 ነገር ግን ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ 24 ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።

መ. ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተቀባይነት ስለማግኘቱ 2:1-10
በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረውን ወንጌልና የሐዋርያነቱን ተልዕኮ ከተቀበለ በኋላ ለሚቀጥሉት 14 ዓመታት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደነበረ ይገልጥልናል:: በዚህ ክፍል ቅዱስ ጳውሎስ  ከአሥራ አራት አመት በኋላ እንደገና ከሐዋርያት ጋር ሲገናኝ የነበረውን ሁኔታ እናያለን:: በአስራ አራተኛ ዓመት በኋላ የሚለው የትኛውን ነው? ወደክርስትና ከገባ በኋላ ነው ወይስ ከመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ጉብኝት በኋላ ነው ለሚለው በሊቃውንቱ መካከል የተለያየ አስተያየት አለ:: አብዛኛው ሊቃውንት የሚስማሙበት ይህ አስራ አራት ዓመት ጳውሎስ ወደ ክርስትና ከገባ በኋላ ጀምሮ ያለውን ነው::  
የጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ 
መነሻ                ቀን             ማስረጃ                     ትይዩ                     ምክንያት  
ደማስቆ             35                  9:22-30             ገላ1:18-24          ጴጥሮስን ለማነጋገር 
የሶርያ አንጾኪያ   46            11:30;12:25          ገላ 2:1-3,6-10    ለድሆች እርዳታ
                                                                                                     የአሕዛብ ጉዳይ 
የሶርያ አንጾኪያ   49            14:26-15:29                                    የአሕዛብ ወደ ክርስትና       
                                                                                                      መግባት
ቆሮንቶስ            52             18:1,18,22                                         የፋሲካ በአል
                                                                                                      የድሆች እርዳታ 
ግሪክ                57             20:2-3;21:17                                       ለድሆች እርዳታ 
                                       ሮሜ15:25-31

1.ጳውሎስ ከበርናባስና ከቲቶ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ:: 
1ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤2 እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ 
በርናባስ በአገልግሎቱ << የመጽናናት ልጅ>> ተብሎ በሐዋርያት የተጠራ (ሐዋ ሥራ 4:36) የማርቆስ አጎት (ቆላ 4:10) ነው:: ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዙ እና ሰዎችን በማበረታታትና በማጽናት ለአገልግሎት ማብቃቱ እና በመንፈስ ቅዱስ መመራቱ  በሁሉም ዘንድ የታወቀለት ሐዋርያ ነው:: ሐዋ 4:36-37:: 9:26-30:: 11:22-26:: በሐዋርያነት ከጳውሎስ ጋር በአንድነት ያገለገለ ነው:: 14:14::15:12,25::  በዚሁ በገላትያ መልእክት በምናገኘው በጴጥሮስ ድርጊትና እና በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት በማርቆስ ምክንያት ጳውሎስ እና በርናባስ ተጋጭተዋል:: (ገላ 2:11-21:: ሐዋ ሥራ 15:39-40::) ሆኖም ይህ ግጭት በስተመጨረሻ በእርቅ ተቋጭቶአል:: 1ቆሮ 9:6:: ሁለተኛ ከበርናባስ ጋር ይዞ የወጣው ቲቶን ነው:: ቲቶ ጳውሎስ ወደ ክርስትና ካመጣቸው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አንዱ እና በመንፈሳዊ ሕይወቱና በክርስትና እውቀቱ ለታላቅ የመሪነት አገልግሎት የበቃ ነው::  ቲቶ 1:4:: 
2. ጳውሎስ የሚሰብከውን ወንጌል ገለጠላቸው:: 
ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው።

3. የኢየሩሳሌም መሪዎች ቲቶ ይገረዝ ዘንድ አላስገደዱትም:: 
3ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤ 

4. ሐሰተኞች ወንድሞች ወደ ኦሪት ባርነት ሊያስገቡዋቸው ሞከሩ:: 
ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።5 የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።

5. ሐዋርያት ጳውሎስ ለሚሰብከው ወንጌል አንድነታቸውን ገለጡ:: 
6አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥7ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤8 ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። 9ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤10 ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።

ሠ. ጳውሎስ ኬፋን (ጴጥሮስን) ስለመገሰጹ 2:11-14
ይህ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መገኘቱ ቅዱሱ መጽሐፋችን ምን ያህል የእውነት መጽሐፍ እንደሆነ የሚያሳየን ነው:: የሙሴ አለመታዘዝ የዳዊት በኃጢአት መውደቅ የጴጥሮስ ክህደት እንደተመዘገበበት ሁሉ በዚህም ቦታ በሁለት ወይም በርናባስን ከጨመርን በሦስት ታላላቅ መምህራን መካከል የተፈጠረውን ግጭት እና ይህም ለምን እንደሆነ እናያለን:: 

11 ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።12 አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። 13 የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። 14 ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት። 

ረ.  በሥራ ሳይሆን በእምነት ስለሚሆን ጽድቅ 2:15-21
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ራሱ ሕይወት በመመለስ በአይሁዳዊነቱ የጽድቁ መሠረት የሆነው አይሁድነቱ ሳይሆን በክርስቶስ ማመኑ እንደሆነና ይህም ለምን እንደሆነ ያብራራልና:: 
1. የጽድቃችን መሠረት በክርስቶስ ማመናችን ነው:: 
15 እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ 16 ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። 
2. በክርስቶስ በማመን መጽደቅ ማለት ምን ማለት ነው? 
17 ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። 18 ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና።19 እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። 20 ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። 21 የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።
1. በክርስቶስ በማመን ጸድቀናል በክርስቶስ መንፈስ እንመራለን ማለት ነው:: 

2. በክርስቶስ በማመን ጽደቀናል ማለት ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለናል ማለት ነው:: 

3. በክርስቶስ በማመን ጽድቀናል ማለት ክርስቶስ በእኛ ይኖራል ማለት ነው:: 

Tuesday, May 22, 2012


ወንጌልና ተጽዕኖ  1:1-10

1-2 በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤3 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።4 ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።5 ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። 6 በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤7 እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ።8 ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።10 ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
ሀ. የመልእክቱ ምክንያት 

ለ. የጳውሎስ የሥልጣኑ ምንጭ 
<< በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ>>

ሐ.የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የተቀበሉት ጸጋ 

  1. ወንጌል ጌታ ኢየሱስ ከርስቶስ ነው::    << በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ...>>
  2.  ወንጌሉ ጸጋና ሰላም  ነው::   << 3 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።>> 
  3. ወንጌል ከክፉው ዓለም ሊያድነን ራሱን አሳልፎ ስለሰጠው ስለ ክርስቶስ ነው። << ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። >> 
  4.  ወንጌሉ ወደ ክርስቶስ ጸጋ የሚጠራን ነው። <<  በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ....

መ. የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የገቡበት ወጥመድ አስፈሪነት 
  1. በክርስቶስ ጸጋ ከጠራቸው ወንጌል ወደ ልዩ ወንጌል ፈጥነው አልፈዋል። << 6 በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤>> 
  2. ይህ ልዩ ወንጌል ወንጌል ያይደለ የተጣመመና ከክርስቶስ ጸጋ የሚያናውጥ ነው።  <<7 እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ።>>
  3. ይህ ልዩ ወንጌል ወደ እርግማን የሚወስድ ነው። << ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። >>
ሠ. የጳውሎስ ቁርጠኝነት 
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
      



የቅዱስ ጳውሎስ አጭር ታሪክ 

ስለ ጳውሎስ ማንነት በጥልቀት የምናገኘው ሉቃስ ከጻፈልን ከሐዋርያት ሥራ እና ከራሱ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ነው።
1. በጠርሴስ ተወለደ 
ቅዱስ ጳውሎስ በአሁኑ ዘመን በደቡብ ምሥራቅ ቱርክ በምትገኘውና በዚያን ዘመን የትምህርት ማዕከላት ከሆኑት ከአቴንስ እና ከእስክንድርያ ጋር በእኩልነት ከምትጠራው ታዋቂ ከተማ በጠርሴስ ተወለደ። ወላጆቹ ከብንያም ነገድ ወገን የፈሪሳውያን ወገን ሲሆኑ ልጃቸውንም ከብንያም ወገን ታዋቂ በሆነው በንጉሥ ሳኦል ሰይመውታል። ምንም እንኳ የጳውሎስ ወላጆች አጥባቂ ፈሪሳውያን ቢሆኑም በዜግነት ሮማውያን እንደሆኑ በሐዋ ሥራ 21: 39 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ጠቅሶአል። ሐዋ ሥራ 16:37፤ 22:25፤ 25:11። 
2. በገማልያል እግር ሥር ተማረ:: 
የተወለደባት የጠርሴስ ከተማ በግሪክ ፍልስፍና በተለይም በስቶይክ ፍልስፍና ትምህርት ማዕከልነትዋ የታወቀች ቢሆንም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ እንደነገረን የተማረው በገማልያል እግር ሥር ነው። ሐዋ ሥራ 22:3። ገማልያል ታዋቂ የሆነው የሂለል የረበናት ትምህርት ቤት መሪ የነበረ ሲሆን በጥበቡና በአስተዋይነቱ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በረበናት ትምህርቱ ከብዙዎች ጓደኞቹ የበለጠ ዕውቀት እንደነበረው በዚሁ በምናጠናው መልእክቱ ውስጥ ገልጦልናል። ገላ 1:14። 
3. ክርስቲያኖችን አሳዳጅ ነበረ ::
ምንም እንኳ በገማልያል እግር ሥር ሆኖ ቢማርም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሕጉና ስለሃይማኖቱ እጅግ ቀናኢና ከገማልያል ይልቅ የክርስትና መልእክትን ተጽዕኖ የተረዳ ይመስላል። ሐዋ ሥራ 5:34-39። በመሆኑም ገና የተመሠረተችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ ያሳድዳት ነበር። ገላ 1:13። በሐዋ ሥራ ላይ የምናየው ደብዳቤም ይህ ክርስቲያኖችን ማሳደዱ በኢየሩሳሌም ባሉት የአይሁድ መሪዎች ይሁኝታን ያገኘ ነበር። ሐዋ ሥራ 8:3። 
4. ለሐዋርያነት መጠራቱ:: 
ከሊቀ ካህናቱ ተልእኮ ተቀብሎ በኢየሱስ የሚያምኑትን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ በጉዞ ላይ ሳለ ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ለጳውሎስ እንደተገለጠለት በሐዋ ሥራ 9 ላይ እናገኛለን። ጌታ ኢየሱስ በደማስቆ ላይ የጳውሎስን ሕይወት መቀየር ብቻ ሳይሆን ለታላቅ የወንጌል አገልግሎትም ነበር የጠራው። እስከዚያች ሰዓት ድረስ እንደመልካም የኦሪት ተማሪ ጳውሎስ የሚያምነው በእንጨት የሚሰቀል ሰው የተረገመ እንደሆነና በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሞተ ሰው መሲህ (ክርስቶስ) መሆን እንደማይችል ነበር። ነገር ግን የተሰቀለውን ኢየሱስ ፊት ለፊት ተገናኘው። የኢየሱስ ተከታዮች የሚሉትም እውነት እንደሆነ ተመለከተ። ጳውሎስን ከሁሉ በላይ ያስደነገጠው ነገር ቢኖር እየተከተለው ያለው መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ያ ሕይወቱን የሰጠለት የኦሪቱ ሕግ አለማሳየቱ ነበር። ከዚያ ይልቅ ወሰን የሌለው የክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ በምህርቱ እንደጠራው አስተዋለ። በመሆኑም ለእርሱ ከዚያች ቀን ጀምሮ << ሕይወት ክርስቶስ >> እንደሆነ አወጀ። ፊል1:21። ሕይወቱን ሁሉ ለክርስቶስ ለመስጠት ወሰነ።
5. የአሕዛብ ሐዋርያ መሆን 
ቅዱስ ጳውሎስ ለሐዋርያነት ከጌታ ኢየሱስ የቀረበለትን ጥሪ ምላሽ የሰጠው ወዲያው ነበር። መጀመሪያ ወደ አረቢያ (ገላ 1:17) በመቀጠልም ወደ ደማስቆ  ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ በመሄድ በዚያም ጴጥሮስን እና የጌታ ወንድም ያዕቆብን አግኝቶአል። (1ቆሮ 15:5) ወደ ተወለደበት ወደ ተርሴስ በመሄድም ሊያጠፋው የሞከረውን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ሰብኮአል። (ገላ 1:21-24)  ቀድሞ ወደ ሐዋርያት ያመጣው በርናባስ እንደገና ወደ አንጾኪያ ሄደው በዚያ እንዲያገለግሉ ጋበዘው።ሐዋ 11:19-26። የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች በብዛት ያሉባት ነበረች። 
6. የኢየሩሳሌም ጉባኤ 
የአንጾክያ ምዕመናን በሃይማኖት የበረቱና ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተብለው የተጠሩ ነበሩ። አገልግሎታቸውም በአሕዛብ መካከል ወንጌልን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን መርዳት ነበር። ይህን እርዳታ ለማድረስ ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጡበት ወቅት በኢየሩሳሌም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ይመሩ የነበሩት ጴጥሮስ ዮሐንስና የጌታ ወንድም ያዕቆብ በአንጾኪያ ያለውን አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ለበርናባስና ለጳውሎስ ድጋፋቸውን ገለጡ። (ቀኝ እጃቸውን ሰጡ።) ሐዋ 11:27-30። ገላ 2:1-10። ሆኖም በኢየሩሳሌም በአይሁድ መካከል ያለችው ቤተ ክርስቲያን እና በአንጾኪያ በአሕዛብ መካከል ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሊከተሉት ስለሚገባቸው መንገድ የተለያየ አቀራረብ ነበራቸው። በመሆኑም ከኢየሩሳሌም ወደአንጾኪያ የሚሄዱ አንዳንዶች ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የገቡትን የኦሪትን ሥርዓት መቀበል እንዳለባቸው ማስገደድ ስለጀመሩ በኢየሩሳሌም እንደገና ወንጌልን በአሕዛብ መካከል እንዴት መስበክ እንደሚገባ የሚወስን የሐዋርያት ጉባኤ ወይም የሐዋርያት የመጀመሪያው ሲኖዶስ ተካሄደ። ሐዋ 15:1-29። ቅዱስ ጳውሎስ ከጉባኤው በኋላ አገልግሎቱን በማስፋት በብዙ ቦታዎች ላይ አብያተ ክርስቲያናትን የመሠረተ ሲሆን ከኢየሩሳሌሙ ጉባኤ በኋላ ለሁለት ጊዜ ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶአል:: በመጨረሻም የተያዘውና በእሥር ወደሮም የተወሰደው ከኢየሩሳሌም ነው።
ጳውሎስ በዘመናት ውስጥ 
33    ለሐዋርያነት ተጠራ:: ወደ ዓረብ ምድር ሄደ 
35    ወደኢየሩሳሌም ለአጭር ጉብኝት ሄደ 
35-45 ኪልቅያ ሶርያ አንጾኪያ 
46    ከአዕማድ" መሪዎች ጋር  በኢየሩሳሌም መገናኘቱ (ገላ 2:1-10) 
       ከአንጾኪያ ይዞት የሄደውን እርዳታ ለኢየሩሳሌም ቅዱሳን ማድረሱ (ሐዋ ሥራ 11:27-30) 
47-48 ጳውሎስ እና በርናባስ የመጀመሪያውን ሕዋርያዊ ጉዞ ማድረጋቸው (ሐዋ 13:4-14:28)
48/49 የሐዋርያት ጉባኤና ውሳኔ 
49-51/52  ጳውሎስና ሲላስ በመቄዶንያና በአካይያ:: የፊልጵስዩስ በተሰሎንቄ በቤሪያ እና በቆሮንቶስ 
                አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ:: (ሐዋ ሥራ 16:9-18:18) 
51/52 ጳውሎስ በኢየሩሳሌም አስቸኳይ ጉብኝት አደረገ 
52-55 ጳውሎስ በኤፌሶን (ሐዋ ሥራ 19:1-20:1) 
55-57 ጳውሎስ በመቄዶንያ በእልዋሪቆን እና በቆሮንቶስ 
57      ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ኢየሩሳሌምን መጎብኘቱ::መያዙ እና መታሠሩ:: 
57-59  በቂሳርያ መታሠሩ (23:35-26:32) 
59-60 ወደኢጣሊያ ጉዞ 
60-62 በቁም እስር በሮም መቀመጡ 
62      ጳውሎስ በቄሳር ፊት 
64      የሮም መቃጠል 
65      የጳውሎስ ሰማዕትነት 

Tuesday, May 15, 2012


በክርስቶስ የጸጋ ወንጌል የተገኘ ነፃነት 
የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች 
1. ወንጌልና ተጽዕኖ  1:1-10
2. ሕይወትን የሚለውጥ መልእክት  1:11-2:21
3. የተቀበልነው ስጦታ 3:1-29
4. ልጆች ነን   4:1- 31 
5. ነጻነትና መንፈሳዊ ሕይወት 5:1-1-26
6.በወንጌል የምንኖረው የነጻነት ሕይወት 6:1-18::
የገላትያ መልእክት ዝርዝር አርእስት 
ሀ. መግቢያ 
1. ሰላምታ 1:1-5
2. ስለገላትያ ሰዎች የቅዱስ ጳውሎስ ሐዘን  1:6-9
ለ. የጳውሎስ የሕይወቱ ምስክርነት 1:10-2:21
1. ጳውሎስ የጸጋውን ወንጌል በቀጥታ ከጌታ ስለመቀበሉ:: 1:10-12
2. የጳውሎስ የቀደመው የይሁዲነት ሕይወት ለጸጋው ወንጌል መነሻ አለመሆኑ 1:13-14
3. ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተቀባይነት ስለማግኘቱ 2:1-10
4. ጳውሎስ ኬፋን (ጴጥሮስን) ስለመገሰጹ 2:11-14
5. በሥራ ሳይሆን በእምነት ስለሚሆን ጽድቅ 2:15-21
ሐ. የጸጋው ወንጌል ምንነት ትርጉም 3:1-5:12
1. የእምነት በቂነት 3:1-5 
2. የአብርሃም ምሳሌነት 3:6-9
3. ከሕግ እርግማን ነጻ መውጣት 3:10-14
4. ዘርና መካከለኛ የሆነው ክርስቶስ 3:15-22
5. የእምነት መምጣት 3:23-29
6. ወልድና መንፈስ ቅዱስ 4:1-7
7. እውነተኛ አምላክና ሐሰተኛ አማልክት 4:8-11
8. የጳውሎስ ልመና 4:12-20
9. ይስሐቅና እስማኤል የአብርሃም ሁለት ልጆች 4:21-31
10. በክርስቶስ የሚገኝ ነጻነት 5:1-6
11. ስለማመቻመች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 5:7-12
መ. በመንፈስ መመላለስ 5:13-6:10
1. ሕግና መንፈስ 5:13-21
2. የመንፈስ ፍሬ 5:22-26
3. አንዱ የሌላውን ሸክም ስለመሸከም 6:1-5
4. በቤተ ክርስቲያን ሊኖር ስለሚገባ መረዳዳት 6:6-10
5. በክርስቶስ መስቀል ስለመመካት 6:11-18