Thursday, January 2, 2020

በጨለማው ዓለም የተገለጠው ብርሃን

የጌታን ልደት ከማክበራችን በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላቅ ሥፍራ አላቸው። ከዘጠኙ ንዑሳን የጌታ በዓላት መካከል የሚቆጠሩም ናቸው። የመጀመሪያው ሳምንት ስብከት፥ ሁለተኛው ብርሃን፥ ሦስተኛው ደግሞ ኖላዊ ይባላል። በጨለማው ዓለም ብርሃን ሊሆን ወደ ዓለም የመጣውን፥ የእውነተኛውን ብርሃን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ለመቀበል ልባችንን የምናዘጋጅበት፥ እንዲሁም ነቢያት « ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክልን» እያሉ መጸለያቸውን የምናስብበት ሁለተኛው ሳምንት ብርሃን ይባላል።
፩. ብርሃን የሕይወት ምንጭ ነው። በዚህ ባለንበት ዓለም ላይ ብርሃን ከሌለ ሕይወት የለም። ሁላችንም እንሞታለን። ለምሳሌ ለፕላኔታችን የብርሃን ምንጭ የሆነችውን ጸሐይን ብንወስድ እንኳ፥ እርሷ ባትኖር ኖሮ፥ ሁላችንም በረዶ ሆነን ነበር የምናልቀው። እጽዋት ሕያዋን የሚሆኑት በብርሃን እንደሆነም ሳይንስ ይነግረናል። በመንፈሳዊ ሕይወትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን ምንጭ ነው። እርሱ ለእኛ ሕይወቱን ሰጥቶ፥ በሞቱ ሕይወትን አግኝተናል።
፪. ብርሃን የእውነት ምንጭ ነው። ጨለማ የድብቅ ሕይወት ነው። በጨለማ ውስጥ ሁሉ ነገር ሥውር ነው፤ድብቅ ነው። በብርሃን ውስጥ ግን የተሠወረው ሁሉ ይገለጣል። ሁሉም ወደ ግልጥ ይመጣል። እውነተኛው ብርሃን ከመምጣቱ በፊት የጨለማው አበጋዝ ሰልጥኖብን ነበር። የሞት ፍርሃት ነግሦብን ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ በጨለማ እና በሞት ጥላ ለነበሩ ሕዝቦች ብርሃን ወጣላቸው ያለው ለዚህ ነው። እርሱ ብርሃን የሆነ አምላክ ስለመጣልን ዛሬ በብርሃን በእውነት እንመላለሳለን። እውነትም አርነት ያወጣናል።
፫. ብርሃን የደስታ ምንጭ ነው። በምድራችን በዓመት ውስጥ ውሱን ለሆኑ ጊዜያት ብቻ ብርሃን የሚያገኙ አካባቢዎች አሉ። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በጭንቀት እጅግ ይጠቃሉ። ሳይንቲስቶች ይህን ጭንቀታቸውን ለማቃለል፥ አርቲፊሻል ብርሃን ( ጸይን የሚመስል ለማስቀመጥ ሞክረዋል። ከጭንቀት ነጻ ለመውጣት የጸሐይ ብርሃን ያስፈልጋቸዋል። ነፍሳችን የልብ ደስታ እንድታገኝ፥ የጽድቅ ጸሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ በነፍሳችን ላይ ሊያበራ ይገባል።
እርሱ ራሱ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ብሎአልናል።

Tuesday, April 10, 2018

ጸሎት

የአባቶቼ አምላክ፥ አምላከ ቅዱሳን አምላከ አበው ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ከፍ ካሉት ሁሉ በላይ ከፍ ያልህ ነህ፤ ሥራህ ከአእምሮ በላይ ነው። ኃይል ከመነገር በላይ ነው። ኃጢአተኛ እና በደለኛ የሆንኩትን እኔን ልጅህን ልከህ ያዳንከኝ፥ ፍቅርህ እጅግ ድንቅ ነው። የእግዚአብሔር ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ጠላት መሆኔን በልጅነት የቀየርከው፥በራቅኹህ መጠን በፍቅርህ የሳብከኝ፥ ውለታህ ዕለት ዕለት ይታወሰኝ፤ዓለም በአዚሟ እንዳታሳውረኝ፥ መስቀልህ በፊቴ ይሳልብኝ። የሰጠኸኝን፥ በሞትህ ያገኘሁትን መዳኔን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እፈጽመው ዘንድ ኃይልን ስጠኝ። አንተ የቅድስና መንፈስ፥ የኃይል መንፈስ ፥ ራስን የመግዛት መንፈስ፥ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፥ ሁለንተናዬን ቀድሰው፤ ሰውነቴ፥ ሥጋ ነፍስ መንፈሴ ያንተ መቅደስ ይሁን። ኃጢአት አያድክመኝ። ዓለም አያዝለኝ። በቃልህ ነፍሴ ሐሴት ታድርግ፤ ካንተ ጋር የሚኖረኝ ጊዜ የደስታዬ ምንጭ ይሁን። አሜን።

Monday, February 6, 2017

የ2ኛ ጴጥሮስ መልእክት አጭር መግቢያ

የመለኮቱ ክብር ተካፋዮች፤ የ፪ኛ ጴጥሮስ ጥናት 


ሀ. የመልእክቱ ጸሐፊና ተቀባዮች 
የመልእክቱ ጸሐፊ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሆነ ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን መስክራለች። መልእክቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፥ ከሐዋርያት ቀጥሎ በተነሡት በሐዋርያውያን አበው ( apostolic fathers) የተጠቀሰ ሲሆን፥ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት አርጌንስና ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያም በጽሑፋቸው ላይ ጠቅሰውታል። ቅዱስ ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው በሰማዕትነት ሊሰዋ በተዘጋጀበት ወቅት ነው። የጻፈላቸውም፥ የመጀመሪያውን መልእክት ለጻፈላቸው በታናሽ እስያ ( Asia Minor) ለሚገኙ ክርስቲያኖች ነው። ልክ እንደመጀመሪያው መልእክት፥ ይህን መልእክት ሐዋርያ የጻፋላቸው በሮም ሳለ ነው። በ1፥14 ላይ የተሰጠውን ምንባብ ስንመለከት ሐዋርያው  ከ60-65 ዓ.ም መልእክቱን ጽፎአል ልንል እንችላለን።  

ለ. የመልእክቱ ዓላማ 
ሐዋርያው መልእክቱን የጻፈው ስለ ሦስት ዋና ምክንያት ነው። 
የተማሩትን እና የተሰበከላቸውን የወንጌል እውነት አጥብቀው እንዲይዙና በእርሱም ላይ እንዲቆሙ፤ 
 ወደ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንደሚገቡና እውነተኛን ወንጌል ለመበረዝ እንደሚሞክሩ ለማስጠንቀቅ ። 
እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሰማይና ምድር ከጥንት ጀምሮ ነበሩ ወደፊትም ይኖራሉ፥ ክርስቶስም ዘግይቷል አይመጣም በማለት በራሳቸው ምኞት ለመጓዝ የሐሰት ትምህርታቸውን ያስተምሩ ስለነበር፥ ክርስቶስ ዳግም በግርማ እንደሚመጣ፥ በዓለምም ላይ እንደሚፈርድ፥ የእርሱ የሆኑ ደግሞ በትጋት ነቅተው በተስፋ እንዲጠብቁ ይነግራቸዋል። 

 ሐ. በ2ኛ ጴጥሮስ ውስጥ የምናገኛችው ዋና ዋና አሳቦች  
የክርስቶስ ዳግም መምጣት፤ 2ኛ ጴጥሮስ በሰፊው ከሚዳስሳቸው ነጥቦች አንዱ የክርስቶስ በክብር ዳግም መምጣት ነው። ክርስቶስ በክብር የሚመጣው ለፍርድ እና አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለማምጣት ነው። 
የቅድስና ሕይወት፤ ክርስቶስ በሰዎች ሁሉ ላይ ለመፍረድ በክብር ይመጣል። ይህ የክርስቶስ መምጣት በድንገት ስለሆነ፥ እኛ በቅድስና በመኖር « የጌታን መምጣት እንድናስቸኩል» ይመክራል። 
የእግዚአብሔር ቃል ታማኝነት፤ ቅዱስ ጴጥሮስ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት እንዲሁም የሐዋርያትን ትምህርት ( በተለይም የቅዱስ ጳውሎስን) በመጥቀስ፥ በመንፈስ ቅዱስ የተጻፉና የተነገሩ ስለሆኑ በጥንቃቄ ልንይዛቸው የሚገቡ እንደሆኑ ይናገራል። በመሆኑም 2ኛ ጴጥሮስ ስለመጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ እግዚአብሔርነት ( inspiration) እጅግ ዋና የሆነውን ዶክትሪን የያዘ መጽሐፍ ነው።  
የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ መሆን ፤ 2ኛ ጴጥሮስ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖ እኛን ወደ ምን ዓይነት አስደናቂ መንፈሳዊ ሕይወት እንዳስገባን ይናገራል። እግዚአብሔር የጠራን « የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች እንድንሆን ነው። ( 1፥4) ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር፥ በምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ውስጥ ሰፊ አንድምታ ያለው ነው። በምዕራቡ ዓለም ነገረ መለኮት የክርስቶስ ሰው የመሆን ምክንያት ሁል ጊዜ የሚገለጠው፥ የሰውን ጥፋት ( guilt) ከማስወገድ አንጻር ነው። በምሥራቁ ወይም በኦርቶዶክሱ ዓለም ግን የክርስቶስን ሰው የመሆን ነገር የምንገልጠው፥ እግዚአብሔር ክብሩን ( መለኮታዊ ባሕርዩን) በጸጋው ሊያካፍለንና፥ ወደሚደነቀው ወደ ልጁ መንግሥት ሊያገባን እንደመጣ ነው።  ይህ የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች የመሆናችን መንገድና ሂደት ቴዎሲስ ( ሱታፌ መለኮት) ይባላል።  

መ. 2ኛ. ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን 

ይህ መልእክት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ ክፍል ( liturgy of the word)  ከሚነበቡት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ ነው። ንፍቁ ዲያቆን ( ሁለተኛው ዲያቆን) ከአጠቃላይ መልእክታት ( general epistiles) ተብለው ከሚታወቁት ከጴጥሮስ እስከ ይሁዳ ካሉት መልእክታት እና ከዮሐንስ ራዕይ ያነባል።  በቤተ ክርስቲያናችን ግጻዌ ( lectionary)  መሠረት ይህ መልእክት ከሚነበብባቸው ቀናት መካከል ለምሳሌ የአንዱን ወር ብንመለከት 
መስከረም 6 ( በነቢዩ በኢሳይያስ ቀን) ፥ ( 1፥19 እስከ ፍም 
መስከረም 15 ( የቅዱስ እስጢፋኖስ ፍልሰተ ሥጋ)  ( 2፥15 እስከ ፍም) 
መስከረም 18 ( ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር፤ ቶማስ ዘህንደኬ) ( 3፥14 እስከ ፍም 
መስከረም 25 ( ዮናስ ነቢይ፤ ጴጥሮስ ወጳውሎስ) (3፥1_8)  ናቸው። ( መጽሐፈ ግጻዌን ተመልከቱ) 
እንዲሁም በሰዓታት ዘሌሊት ከሚነበቡት ምንባባት መካከል፥ 2ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ ሦስት አንዱ ነው። 

ሠ. የመልእክቱ አከፋፈል። 
በመልእክቱ ዓላማ ላይ እንዳስቀመጥነው አከፋፈሉም ያንን ተከትሎ ነው። 

ሀ. ማንነታችሁን እወቁ፤« የመለኮት ክብር ተካፋዮች. . . እንድትሆኑ. . . ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን»፤  (1፥1-21)  
ለ. ያመናችሁትን እወቁ፤ « ሐሰተኞች አስተማሪዎች. . . ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ»    (2፥1-22) 

ሐ. ተስፋችሁን እወቁ፤«የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል»  ( 3፥1-21)