Tuesday, November 12, 2013

የአባትንና የእናትን ምክር መስማት


ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ 
የእናትህንም ሕግ አትተው
ለራስህ የሞገስ ዘውድ 
ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና።      
መጽሐፈ ምሳሌ 1፥8


ከ1960ቹ ጀምሮ እንደባህል የተያዘው ወላጆች ኋላ ቀር እንደሆኑና ምንም ሊያስተውሉ እንደማይችሉ፤ ወጣቱንም ሊረዱት እንደማይችሉ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አባቶችን እናቶቻችንን መናቅና እንዳላዋቂ ማየት ሊቅነት ሆኖአል። በመሆኑም በዕድሜ የበለጸጉት አባቶቻችንና እናቶቻችን ከዕድሜያቸው የተማሩትን ከቀደመው ሕይወት የያዙትን  ጥበብና የኑሮ ብልሃት እንደያዙ ተለይተውናል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተነሣው ትውልድ አቅጣጫ ጠቋሚ ያጣ ትውልድ ነው። ይህ በአጠቃላይ በመላው ዓለም የታየ ክስተት ነው። 

እኛን በመሰሉ አዲስ መጤ ማሕበረሰቦች ( Imgrant communities) ደግሞ ችግሩ ሰፊ ነው። ልጆቻችን ከእኛ ቀድመው ቴክኖሎጂውን ቋንቋውን ይይዙታል። በዚህን ወቅት በቤተሰብ ውስጥ ሳናውቀው ሚና እንቀይራለን። ልጆች ራሳቸውን እንደ አዋቂ መቁጠር ይጀምራሉ። ወላጆቻቸውን መስማት ያቆማሉ። በወላጆቻቸው የቋንቋ ችሎታ መሳቅ ሲጀምሩ ሁሉ ነገር እዚያ ላይ ያቆማል። ወላጆችም አውቀውት ይሁን ሳያውቁት ልጆቻቸውን እግዚአብሔር ያስተማራቸውን የኑሮ ብልሃት ማሳየት ያቆማሉ። ለምን ተብለው ሲጠየቁ « እኔን የሚያስተምሩኝ እነሱ ናቸው» ይላሉ። የአውራ ጎዳናውን መውጫ መግቢያ ሊያሳዩን ይችላሉ። ቋንቋውን እንደ አገሬው ተወላጅ (እነርሱም እዚህ ተወልደው ሊሆን ይችላሉ) ሊያንበለብሉት ይችላሉ። ነገር ግን የሕይወትን ጥበብ ከየት ይማራሉ። 
ሕይወት ከቋንቋ በላይ ነው። ሕይወት ከtexting, surfing, driving በላይ ነው። ሕይወት ጥበብ ይጠይቃል። የዚያ ጥበብ መጀመሪያ ደግሞ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።  ልጆች እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ችሎታ አለ። አንዳንዱን በዚያ በብሩህ አእምሮአቸው ከአካባቢያቸው ቀስመውት ያገኙታል። ነገር ግን ከሌላ ከማንም  የማያገኙት ከእኛ የሚማሩት ብዙ ነገር አለ። በሕይወታቸው እጅግ ወሳኝ የሆነ ነገር። 
እግዚአብሔርን መፍራት ከእኛ ይማራሉ። 
ኑሮን በጸጋና በምስጋና መቀበልን ከእኛ ይማራሉ። 
በትንሹ ማመስገንን ከእኛ ይማራሉ። 
ለሌላው መኖርን ከእኛ ይማራሉ። 
በጥንቃቄ መመላለስን ከእኛ ይማራሉ።
የመጀመሪያው የልብ ስብራት ሲያጋጥማቸው፥ የመጀመሪያውን ቼክ ሲቀበሉ፥ የመጀመሪያ ጓደኛ ሲይዙ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ውጪ ሲያመሹ፥ የሚጠቅማቸው ከወላጆቻቸው የተማሩት መሠረታዊ የሆነው የኑሮ ጥበብ ነው። 
አባትና እናት ካለፈው ስኬታቸውም ሆነ ስህተታቸው ተምረው አደጋን ወይም ጥፋትን ከሩቅ ያስተውላሉ። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ወላጆችን  እንደ smoke detector ወይም ወይም እንደ ውሻ አፍንጫዎች እመስላቸዋለሁ። የጢስ አመልካቹ መሣሪያ በተለይ እንደኔ ላላችሁት ቡና ለምትወዱ እሪታው መንደር ላትወዱት ትችላላችሁ። ሆኖም ቤትን ከመቃጠል ያድናል። እሳት ያሸታል፤ ከእሳት ያድናል።።  በዚያ በክረምቱ በአዲስ አበባ ብዙዎች  በከሰል ጢስ (ካርቦን ሞኖኦክሳይድ)  ታፍነው ያለቁት ጢስ አመልክቴ (smoke detector)  በቤታቸው ስለሌለ ነው። የውሻ አፍንጫ የተቀበረ ፈንጂ  በማነፍነፍ ሰዎችን ከዕልቂት የሚያድን ሆኖአል።  ወላጆች እንደዚህ ናቸው። ዕድሜ፥ ኑሮ፥ የራስ ስህተትና ስኬት ያስተማራቸውን ይዘው ይመክራሉ። ለልጆችና ለወጣቶች የምላቸው ይህን ነው። ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ የእናትህንም ህግ አትተው። 

No comments:

Post a Comment