ዶክተር ሊሊያን አልፊ (ትርጉም ቀሲስ መልአኩ ባወቀ)
የሚከተለው መጣጥፍ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን የሆኑ ዶክተር ሊሊያን አልፊ « የሰማይ መጽናናት» በሚለው መጽሐፋቸው ካስቀመጡት ጽሑፍ የተቀነጨበ ነው።
ፈተና ኢዮብን ባጥለቀለቀው ጊዜ የኢዮብ ጓደኞች ጎብኝተውት ነበር። በደረሰበት ነገር በጣም ደንግጠው ስለነበር ሳምንት ሙሉ በዝምታ ተቀምጠው ነበር። እንደእውነቱ ከሆነ ዝምታቸው ከቃላቸው ይልቅ እጅግ የሚያጽናና ነበር። ለንግግር አንደበታቸውን በከፈቱ ወቅት፥ ይህ መከራ ለምን እንዳገኘው ለመናገር መሽቀዳደም ጀመሩ።
ቴማናዊው ኤልፋዝ « ኢዮብ ችግር ውስጥ የገባው በኃጢአቱ ምክንያት እንደሆነ» እርግጠኛ ነበር። ሹሐዊው በልዳዶስ ደግሞ ኢዮብ « ኃጢአት መሥራቱ ብቻ ሳይሆን፥ ኃጢአቱን አለማወቁና አለመናዘዙ» ችግር ውስጥ እንደጣለው በእርግጠኝነት መናገር ጀመረ። ነዕማታዊው ሶፋር ደግሞ « የኢዮብ ኃጢአት ከዚህ የከፋ መከራና ሐዘን ሊያመጣበት ይገባ ነበር» አለ። ቃላቸው በኢዮብ ላይ ሌላ ተጨማሪ ሐዘንን ነበር ያመጣበት፤ በመጨረሻ ኢዮብ ይህን ተናገረ
ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ
እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ።
በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን?
ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው?
እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር
ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥
እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥
ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር።
በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር
የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር። ኢዮብ 16፥1-5
የትዕግሥት አባት የሆነው ኢዮብ እነዚህን በምሬት የተሞሉ ቃላት ሲናገር፥ እኛም ልናስተውልና እንደእነርሱ እኛም አድካሚ አጽናኞች እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል። በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ያለፈ ሰው ሁሉ እንደሚያስታውሰው አንዳንድ ሰዎች መጥተው ባይጎበኙን ሳንመኝ አንቀርም።
የሕክምና ተማሪዎች የሚማሩት የመጀመሪያው ጠቃሚ ትምህርት « በሽተኛውን መርዳት ባትችሉ. . . . ሌላው ቢቀር እንዳትጎዱት» የሚል ነው።
አንድ በሽተኛን፥ ባል ወይም ሚስትን በሞት የተቀሙ፥ ወይም ልጇ የሞተባትን እናት ከማጽናናታችን በፊት እንዴት ማጽናናት እንዳለብን ልንማር ይገባል። በመጀመሪያ በመከራ ያለ ሰውን ለማጽናናት ሰማያዊ ጥበብ እንደሚያስፈልገን ልንገነዘብ እና ለበለጠ ሐዘን ምክንያት እንዳንሆን የስጦታ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔርን ልንለምን ይገባል። በሁለተኛ ደረጃ ሌሎችን ለማጽናናት የሚፈልግ ሰው ርኅሩህ፥ ዝተኛና ጉዳታቸው የሚገባው መሆን አለበት። ያረጁ የነተቡ ቃላትን መደጋገም ወይም ጉዳታቸውን ሕመማቸውን የሚያናንቁ የታወቁ ቃላትን መጠቀም በፈተና ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን ልያስቆጣ ይችላል።
በመከራ ውስጥ ያለ ወንድም ወይም እህት በመከራ ውስጥ ከቶውንም ባላለፉና በተንደላቀቀ የኑሮ ማማ ላይ ተሰቅለው በሚኖሩ ሰዎች ሲገጹና ሲወቀሱ የበለጠ ሊጎዱ ይችላሉ። ምክንያቱም መከራቸውን መረዳት ስለማይችሉ።
በመሆኑም « ክብር ያለው ዝምታ» ከከንቱ ቃላት ይልቅ ይመረጣሉ። ፍቅርን የተመላ እይታ፥ ወይም የእጅ ሰላምታ ብዙ ነገር ይናገራል። በዚህም ምክንያት ጠቢቡ « ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገር ጊዜ አለው።» ብሎአል። መክብብ 3፥1-7
ኢዮብ ጓደኞቹን እንደመከራቸው፥ በመከራ ያሉትን ሰዎች ሁኔታ ልናስብና ራሳችንን በእነርሱ ቦታ ለማስቀመጥ መሞከር አለብን። አንዳንድ ጊዜ « ችግርህ ይገባኛል» ወይም « ሐዘንህ ይገባኛል» የሚለው ቃል አደገኛ ቃል ስለሆነ ልንጠነቀቅ በተቻለ መጠን እንዲህ ያሉትን አነጋገሮች ከመጠቀም ልንከለከል ይገባል። « ልጅ ሞቶብህ ያውቃል?» ወይም ካንሰር ሕይወትሽን ሊወስድ ሞት አፋፍ ደርሰሻል?» ብለው ሊጠይቁን ይችላሉ። ዶክተር ሊሊያን እዚህ ላይ ይህን ያለችው የተስተካከለ ዕይታ እንዲኖረን እንጂ እነርሱ ያለፉበትን ልምምድ እናልፍበታለን ብላ አይደለም።
አንድን ወንድም ወይም እህትን ለመጎብኘት ከመሄዳችን በፊት የሚከተሉትን ነገሮች ማሰላሰል አለብን። ለመጎብኘት ትክክለኛ ጊዜና ቦታ ነው? ከእኔ ቃላት ዕረፍት ያስፈልጋቸው ይሆን? የምጎበኛቸውስ መጎብኘት ስላለብኝ በግዴታ ነው ወይስ ከእውነተኛ ፍቅርና ያን ፍቅሬን ለወንድሜ ለእኅቴ ማካፈል አለብኝ ከሚል ነው? ልምዴን ለማካፈል እነርሱ ባለፉበት ተመሳሳይ መንገድ አልፌአለሁ? ወይስ እግዚአብሔር ታድጎኛል? በከበረ ዝምታ ፍቅሬን፥ ሐዘኔን ለመግለጥ የትኛው ሁኔታ ይመረጣል?
በዚህ ሁሉ ግን ለማጽናናት ያሰብናቸውን ሰዎች በጸሎታችን ወደ እግዚአብሔር ልናቀርባቸው ያለማቋረጥ ልንጸልይላቸው ይገባል። ዓይናቸውን ልባቸውን ወደ ተሰቀለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያደርጉ፥ ከእርሱም መጽናናትን እንዲጠይቁ ልንመራቸው ይገባል። አንድ ልጇ በመስቀል ላይ በተንጠለጠለ ጊዜ « ሰይፍ በነፍሷ ያለፈባትን» የቅድስት ድንግል ማርያምን ምልጃ ልንጠይቅ ይገባል። የመከራን ምሬት ስለምታውቀው የተናወጠችን ነፍስ ልታጽናና ትችላለች።
« በአንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ
ወይም በሚያበረታታታ በአንድ ቃል
የሌሎችን ሸክም በመሸከም እንደቀሬናዊው ስምዖን ለመሆን ሞክር፤
ይህን ባትችል ሌላው ቢቀር ስቃያቸውንና ሐዘናቸውን አታብዛባቸው።»
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሸኑዳ
No comments:
Post a Comment