Saturday, November 16, 2013

ያንተ መሣሪያ አድርገኝ

ዓይኖችህ በምድር ሁሉ የሚመለከቱ፥ የሁሉ አባት ልዑል ሆይ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።
በመንፈስህ ቀድሰኸኝ በቃልህ መርተኸኝ፥ በቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ መከረኸኝ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።
ጌታ ሆይ በመስቀልህ የገለጠከውን ፍቅርህን፥ ትህትናህን፥ ራስህን ባዶ ማድረግንህን፥ ዝምታህን፥ ትዕግሥትህን በሕይወቴ እንድገልጥ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

የሰማዕታትህ የምስክርነታቸው ተጋድሎ፥ የቅዱሳንህ የንጽሕና ሕይወት ኃይል ሆኖልኝ ያንተ መሣሪያ አድርገኝ። የመላእክትህ ምስጋና የሊቃነ መላእክትህ ጥበቃ ለእኔ እንዲሆን ፈቅደኽልን ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

አንተ ልታጽናና የወደድኸውን የማጽናና፥ አንተ ልትምረው የፈቀድከውን እንድምር፥ አንተ ልታነሣው ያያኸውን እንዳነሣ፥ አንተ ይቅር ያልከውን ይቅር እንድል ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

ፍቅርህን፥ ደስታህን፥ ቸርነትህን፥ ርህራሄህን፥ ሰላምህን ለሰው ሁሉ እንድናገር ያንተ መሣሪያ አድርገኝ።

ደካማነቴ ሳይሆን ብርታህ፥ ባዶነቴ ሳይሆን ሙላትህ፥ ችኮላዬ ሳይሆን ትዕግሥትህ ተገልጦ መሣሪያህ አድርገኝ።
ስለ ቅዱስ ስምህ ስትል አሜን።

( ከቀሲስ መልአኩ ባወቀ )


No comments:

Post a Comment