Wednesday, January 9, 2013

በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን? (ክፍል አንድ)



የቤተ ክርስቲያን መለያ ባሕርያት 
Read in PDF

በአንቀጸ ሃይማኖታችን ላይ « ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት፤ ከሁሉ በላይ በምትሆን፥ ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።» በማለት እናውጃለን። ይህ በኒቅያና በቍስጥንጥንያ የተወሰነው አንቀጸ ሃይማኖታችን የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ባህርያት ይነግረናል። ምናልባትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ዐቢይ ችግር ለመረዳት የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ባህርይ መረዳት ይኖርብን ይሆናል።

በአንቀጸ ሃይማኖታችን መሠረት፤
ሀ. በአንዲት (አሐቲ) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
ለ. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
ሐ. በሐዋርያዊት (ጉባኤ ዘሐዋርያት) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
መ.  ከሁሉ በላይ በምትሆንና በሁሉ ባለች (እንተ ላዕለ ኵሉ) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። 


ሀ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን። 

አንድ ጸሐፊ «የቤተ ክርስቲያን አንድነት ማኅበረ ምእመናን የሚፈጥሩት ሳይሆን ከጌታ የተቀበሉት ነው።» እንዳሉት፥ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ምንጩ ቤተ ክርስቲያን በአንዱ በክርስቶስ መመሥረቷ ነው። በኤፌሶን 4፥5-6 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን « አንድ ጌታ፥ አንድ ሃይማኖት፥ አንዲት ጥምቀት፥ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉ የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።» ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ጥምቀት አማካይነት የአንዱ ጌታ አካል የሆነች፥ አንዱን አምላክ የምትቀድስና የምትወድስ፥ በአንዱ መንፈስ የምትመራ ናት። 


አካላዊ ቃል በቅድስት ድንግል ማርያም ያደረውና የእኛን ባህርይ ገንዘብ ያደረገው ይህን አንድነት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል እንዲሁም በሰዎች መካከል እንዲሆን ነው። በዮሐ ም. 17 ላይ የተጻፈው የሊቀ ካህንነቱ ጸሎት የሚያመለክተን ይህን ነው፤ እርሱና አብ እንድ እንደሆኑ እኛም አንድ እንሆን ዘንድ።  ስለሆነም የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ ያየልን አንድነት በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ያለችውን አንድነት ነው።  እኛ ከእርሱ ጋር በዚህች ቅድስት አንድነት አንድ እንድንሆን፤ እርስ በእርሳችንም አንድ እንሆን ዘንድ። ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች በሚገባ ያብራራልን ይህን ባለሁለት አቅጣጫ እርቅና ከእርሱም የተገኘውን አንድነት ነው። ኃጢአት ወደ ዓለም በገባ ጊዜ በመጀመሪያ ከእግዚእብሔር ጋር ጠላቶች አደረገን።
እግዚአብሔርን እንድንፈራው ( በአክብሮት አይደለም )እንድንሸሸገው አደረገን። ሁለተኛ እርስ በእርሳችንም እርቃናችንን እንድንተያይ፥ አንዳችን በአንዳችን ላይ ጣታችንን እንድንጠቁም አደረገን። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኃጢአት እነዚህን ሁለት አሳዛኝ ነገሮች ሲያደርግ እናያለን ሰውን ከእግዚአብሔር ያርቃል፤ በወንድሞችና በእኅቶች መካከል ጠላትነትን ይፈጥራል። 

ይህ ሁሉ ግን በክርስቶስ ሰው መሆን ተለወጠ። « እርሱ ሰላማችን ነውና።» በከበረ የደሙ መፍሰስ፥ በመስቀሉ ሥራ፥ ጠላቶቹ የነበርነውን ከአባቱ ጋር አስታረቀን፥ ሕዝብና አሕዛብ ተብለን ተለይተን የነበርነውንና እርስ በእርሳችን በሕግና በትእዛዛት ጠላቶች የነበርነውንም አስታርቆ  አንድ አደረገን። ቀርበው የነበሩትን (አይሁድን) ከሕግ ቀንበር ነጻ አወጣቸው። በጸጋው ፍጹማን አደረጋቸው። ርቀን የነበርነውንም በልጅነት አቀረበን። ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዚህ አንድነት ነው። 

ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴዋ ስትጸልይ የነበረው ይህ አንድነት እውን እንዲሆን ነው። በቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድና በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ትምህርት ( Teaching of the Twelve Apostles, 9)  ቤተ ክርስቲያን የሚከተለውን ጸሎት ትጸልያለች። « ይህች ኅብስት በተራራና በኮረብታ በበረሓና በቈላ  መካከል የተበተነች ስትሆን እንደ ተሰበሰበች፥ ተሰብስባም አንዲት ፍጽምት ኅብስት እንደሆነች፥ እንዲሁም እኛንም በመለኮትህ ከክፉ የኃጢአት አሳብ ሁሉ ለይተህ በፍጹም ሃይማኖትህ ሰብስበን።» ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፤ ቊ. 91።  

ቆም ብለን ካስተዋልነው ይህ የቅዳሴያችን ጸሎት በአንድነት ዙሪያ ለሚፈጠሩ  ለሚችሉ ብዙ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ነው። የመጀመሪያው አንድነታችንን የምናገኘው ከየት ነው የሚል ነው? አንዱ ሕብስት ክርስቶስን የሚያመለክት ነው። ይህ ሥጋዬ ነው እንዳለ። ሞቱንና ትንሣኤውን የምንናገርበት የምናውጅበት ነው። ከላይ ደግመን ደጋግመን እንደጠቀስነው ይህ አንድነት ከክርስቶስ የሚሰጠን እንጂ እኛ የምንፈጥረው አይደለም። ቤተ ክርስቲያን አንዲት የሆነችው ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር አንድ ከመሆኑ የተነሣ ነው።  « በኵሉ፡ ልብ፡ ናስተብቍዖ፡ ለእግዚአብሔር፡  አምላክነ፡ ኅብረተ፡ መንፈስ ቅዱስ፡ ሠናየ፡ ከመ፡ ይጸግወነ። በፍጹም ልብ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንለምነው፥ ያማረ የመንፈስ ቅዱስን አንድነት ይስጠን ዘንድ» በማለት ዲያቆኑ በቅዳሴ ጊዜ የሚያሳስበንም ለዚህ ነው። 


ሁለተኛው አንድ የሚሆኑት እነማን ናቸው? በኅብስቱ ውስጥ የሚገኘው የስንዴ ደቂቅ « በተራራና በኮረብታ በበረሓና በቈላ የተበተነች ስትሆን እንደ ተሰብሰብች» በክርስቶስ አንድነት የሚሰበሰቡት ማኅበረ ምእመናን (ቤተ ክርስቲያን) ከተለያዩ የሕይወት ጉዞዎች የሚሰበሰቡ ናቸው። ዘማሪው « ለኛ ወገኖችህ ኃጢአት ላደከመን፤ የመስቀልህ ጥላ ማረፊያ ይሁነን » ብሎ እንደተቀኘ፥ በክርስቶስ አንድ የሚሆኑት፥ ኃጢአት ያደከማቸውና በመስቀሉ ጥላ ያረፉ ናቸው። ያለፈ ሕይወታቸው፥ ያለፈ ኑሮአቸው ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናቸው ላይ ለውጥ አያመጣም፤ በክርስቶስ የመስቀሉ ጥላ እስካረፉ ድረስ። 

አንድ የሚሆኑት በመላው ዓለም ተበትነው ያሉ ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ናቸው። የሁሉ ጌታ አንዱ ክርስቶስ ስለሆነ በአፍሪካ በእስያ፥ በአሜሪካ ቢሆኑ፤ ወይም የጥንቱን ይዘን በኢየሩሳሌም፥ በአንጾኪያ በሮምና በእስንድርያ ቢሆኑ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ። ቤተ ክርስቲያን በገጠር ብትሆን በከተማ፥ በወርቅ በብር ያማረች ትሁን በእንጨት የተሠራች ፥ ራሷና መሪዋ አንዱ ክርስቶስ ነው። የሚመራት እውነቱን የሚገልጥላት አንዱ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው። የምታመልከው በአንድነቱ በሦስትነቱ የሚመሰገነውን አንዱን እግዚአብሔርን ነው። ይህ የአንድነቷ መሠረት ነው። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኬልቄዶንን ጉባኤ አትቀበለውም። የኬልቄዶን ጉባኤን ጉድለቶች እዚህ ለመተቸት ቦታው ባይሆንም ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ላይ ካመጣቸው ዐቢይ ጉዳቶች አንዱ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አደጋ ላይ መጣሉ ነው። ከዲዮስቆሮስ አለዳኝነት መወገዝ ባሻገር፥ በኬልቄዶን ጉባኤ ላይ የሮም መልእክተኞች ያሳዩት ተግባር የቤተ ክርስቲያን አካል እንደሆኑ ሳይሆን እነርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆኑ ነበር። እስክንድርያና እርስዋን የተከተሉ በዚህ ቢያዝኑ አያስደንቅም ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዓለም ቤተ ክርስቲያን መከፋፈሉዋ ቀጥሎ ዛሬ ያለንበት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ደርሰናል። 

ሰለአንድነት ስንናገር ግን አንድ ልንረሳው የማይገባን ነገር ቢኖር ቀደም ሲል እንደተናገርነው፥ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ያየው አንድነት በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ማለትም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ያለውን አንድነት ነው። በዚህም ምክንያት በምሥራቃውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘንድ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የሥላሴ አምሳል (Icon) ተብላ ትጠራለች። ይህ ከሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው አንድነት በመጀመሪያ ሕብራዊ ነው።« አብ አኮ ወልድ. . . አብ ወልድን አይደለም በማለት የሦስቱን አካላት ስምና ግብር  ተናግራ ስትጨርስ አብ ውእቱ እግዚአብሔር ፥ ወልድ ውእቱ እግዚአብሔር ፥ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ እግዚአብሔር . . . አብ እግዚአብሔር ነው። ወልድ እግዚአብሔር ነው። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። ብላ መለኮታዊ አንድነታቸውን ትናገራለች። ቤተ ክርስቲያንም እንዲህ ናት። አንድ የሚያደርጋት ነገር አለ። ከክርስቶስ የተቀበለችውና በሐዋርያትና በነቢያት የተመሠረተችበትና የተሰበከችው እውነት፤ ይህ እውነት መልካሙ የምሥራች ነው። እግዚአብሔር ሰውን ለማዳንና የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ በሥጋ ተገለጠ የሚለው።  

ሆኖም ግን የምትለያይበት ደግሞ ሊኖር ይችላል። ገና ከጥንቱ በኢየሩሳሌም ያለችው ቤተ ክርስቲያን እና በአንጾኪያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን፥ በመገረዝና ባለመገረዝ፥ በሚበሉትና በማይበሉት፥ የተለያየ አካሄድ ነበራቸው። የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ሲኖዶስ ሲደረግ እንዳየነው ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስና የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበረው ያዕቆብ ሚዛናዊ አድርገው « እኛና መንፈስ ቅዱስ ወስነናል» ያሉት ይህን ነበር። አይሁድና አሕዛብ አንድ መሆናቸው፥ ዘላለማዊ እውነት ነበር። ይህ በአንጾኪያም በኢየሩሳሌም ሊያከብሩት የሚገባ የወንጌል እውነት ነበር። ይህን እውነት መሻር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አደጋ ላይ ስለሚጥል ነው የኢየሩሳሌሙ ሲኖዶስ (ስብሰባ) የተካሄደው። አይሁድና አህዛብ አንድ መሆናቸውን ጉባኤው እንዳስረገጠ ሁሉ የአይሁድን አነዋወርና የአሕዛብን አነዋወር ልዩነት እውቅና ሰጥቶአል።  

ይህ እንግዲህ የወንጌልን እውነትና ታሪክን ስንዳስስ የምናገኘው እውነት ይህ ነው። በዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ናት? ይህ የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ መገለጫ የሆነው « በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን»  የሚለው ይገለጣታል ወይ? መልሱ በጣም ውስብስብ ነው። ምክንያታችን እናቅርብ፤ 

ዘር፥ ባህል፥ ሥልጣን 
የቤተ ክርስቲያን አንድነት በአንዱ በክርስቶስ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው ብለናል። ይህንም ያልንበት ምክንያት የምንቆርሰው አንዱን ኅብስት ነው። የምንጠጣውም አንዱን ጽዋ ነው። የምንሰብከውም አንዱን ክርስቶስን ነው። በአሁኑ ወቅት ግን  የተሰባሰብንባቸው እውነቶች ከክርስቶስ የራቁ ናቸው። ጥቂቶቹን ብንዘረዝር፥ ዘር፥ ባህል፥ ሥልጣን፥ የክርስቶስን እውነት ሸፍነውና ጣዖት ሆነው ለአንድነታችን አደጋ ሆነዋል። የትግራዩን ተወላጅ በጥርጣሬ ማየት፥ የጎንደሩን ወንድም ማሽሟጠጥ፥ የሸዋውን ሰው መጎነጥ ለአውደ ምሕረታችን እንግዳ አይደለም። የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ይህን የዘረኝነት በሽታ ለምእመናን በማስተላለፋችን መቼ በእግዚአብሔር ፊት በይፋ ንስሐ እንደምንገባ አላውቅም። ይህ አሁን የመጣ ክስተት አይደለም። ልደታ የጎንደር፥ በዓታ የሸዋ፥ ጎፋ የጎጃም፥ እያልን አብያተ ክርስቲያናቱን በጎሣ ከፋፍልነ ማስቀመጥ የጀመርነው ገና ቀደም ብለን ነው። ለምእመኑ ያጋባንበት ስንል አለምክንያት አይደለም። ያ ሕዝብ ይህን የቤተ መንግሥት ሽኩቻ የወለደውን ዘረኝነት አያውቀውም። ጎጃሜዋ ሴት ወይዘሮ ቅኔ ሊማር ለመጣው ተማሪ እንጀራዋን ከሌማትዋ አንስታ ስትሰጠው « ተሜ» ብላ ነው እንጂ ጎሳውን ጠይቃ አይደለም። ጎንደር ለአቋቋም የሄደውም በወግ በማእረግ የሚማረው በቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ ነው። ወሎ ዋድላና ደላንታ የሚሄደውም እንዲሁ። የቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ የአንድነቱ መሠረት ነው። አሁን ግን ከቤተ ክርስቲያናችን ስም አጠገብ የጎሳችንን ቅጽል እስከማስቀመጥ እና እስከ መከፋፈል ደርሰናል። የእነ እከሌ ቤተ ክርስቲያን እስከ ማለት።

ባህላችን እውነት ሆኖብናል። ወንጌል በባህል ሊተረጎም እንደሚገባ ግልጥ ነው። ሆኖም ግን ወንጌል ባህል ተሻጋሪ ነው። ባህልና ወግ ወንጌል ሆኖ ወልደ እግዚአብሔርን አሰቅሎአል። በጌታ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል አንዱ፥ በሰንበት በሽተኞችን ፈውሰሃል የሚል ነው። ደቀመዛሙርቱም ከተነቀፉበት ነገር መካከል አንዱ እጃቸውን ሳይታጠቡ በልተዋል የሚል ነው። 

መሠረታዊ የሆነው እና ልንሰበሰብበት የሚገባን የወንጌል እውነት የሚነግረንን ፍቅርን፥ ሰላምን፥ ትህትናን፥ ራስን አሳልፎ መስጠትን መለማመድ ሲገባን፥ በቀኖናችን፥ በባህላችን፥ በወጋችን አንዳችን አንዳችንን በማውገዝ ላይ ነን። በዚህም አንድነታችን አደጋ ላይ ነው። የወንጌልን እውነት ለመከተል ውስጣዊ ለውጥ ያስፈልጋል። በመሆኑም ያ ውስጣዊ ለውጥ ሲያስቸግር ውጫዊ ላይ ማተኮር ይመጣል። ዛሬ በየአደባባዩ ያለውን መቆራቆስ እንመልከት፤ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያናቸው እንደተደፈረች እንደ ጠፋች እየቆጠሩ ያሉበት ነገር ከዛሬ  ሃያ ዓመት በኋላ የምንስቅበት ነገር። ይህም በልጅነት ሕይወቴ ያየሁትን ያሳስበኛል። የዛሬ 20ዎቹና 30ዎቹ ዓመታት ገደማ የሴቶች በቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ መዘመር ቤተ ክርስቲያንን እንደማርከስ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በመቋሚያ የተደበደቡ እህቶቻችን ብዙዎች ናቸው። ዛሬ ግን የቤተ ክርስቲያን ውበት ናቸው። የዛሬ ሃያዎቹ ዓመታት ገደማ ስብከተ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትርፍ ነገር ነበር። የዛሬ ሃምሳ አመት ገደማ የቤተ ክርስቲያናችን ሰባክያን የነበሩት ባህታውያን ብቻ ነበሩ። የዛሬ መቶ አመት ገደማ ብላታ መርስኤ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ በትውስታቸው ላይ እንዳመለከቱን፥ ሰባክያን ተብለው የሚታወቅቱ የአንድምታ መምህራን ነበሩ። በቀጥታ የእለቱን ምንባብ በንባብ ማውረድ፤ ዛሬ ደግሞ ዘመናዊውን የስብከት ዘዴ (ሆምሌቲክስ) ሥርዓት ያወቁ፥ በነገረ መለኮት ተቋማት የተመረቁ፥ በየአደባባዩ ሕዝቡን ወደቤተ ክርስቲያን እየማረኩት ነው። ባህል ይቀየራል። ባህል ማለት ሌማት ማለት ነው። ባህል ማለት ጻህል( ሳሕን) ማለት ነው። ምግቡ የሚቀመጥበት። ሌማቱን የሚሠራው ዘመኑ ነው። ቅዳሴው የሚተላለፍበት ፕሮጀክተር ሲተክል ፊልም ቤት አደረጉት የሚል ትውልድ፥ በአርጋኖን (በፒያኖ) ሲዘመር ደነሱበት የሚል ትውልድ፥ አድማሳቸው ሰፊ የነበረውን የቀደሙትን አባቶች ታሪክ በሚገባ ያላስተዋለ ትውልድ ብቻ ሳይሆን፥ ወንጌልንም በሚገባ ያልተገነዘበ ትውልድ ነው። 

ቤተ ክርስቲያን አንድነትዋ አደጋ ላይ የወደቀበት ሌላው መንገድ ሥልጣን ነው። የዘመነ መሳፍንቱን፥ ስንቶች ሊቃውንት በመድኃኒት፥ በመተትና በጥንቆላ የረገፉበትን ታሪካችንን ገታ እናድርገውና፥ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች የመመራት እድል ካገኘችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን አጭሩን ታሪክ ብንመለከት፥ ሁለተኛውን ፓትርያርካችንን ገድለን አንዱን አሳደን ነው ያለነው። ይህ የእኛ ታሪክ ነው። አቡነ ጴጥሮስን ፋሺሽት ጣልያን አስገደላቸው ብንልም ተፈራርመው ለጣልያን አሳልፈው የሰጡአቸው የአኛው ሰዎች ናቸው። ሰማዕቱን አቡነ ቴዎፍሎስንም እንዲሁ። 

ሥልጣነ ክህነት ምድራዊ ማዕረግ ሳይሆን ወገናችንን የምናገለግልበት ጸጋ ነው። ይህን እውነት ስንረሳ ግን በፖለቲካ አደባባይ ያልታየ አደገኛ የሙስና አካሄድ ውስጥ እንገባለን። ምንኩስናውን በብቸኝነት ሕይወት ጌታን ለማገልገል ሳይሆን ለሥልጣን መንጠላጠያ ስናደርገው፥ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የታየው ግብረ ሰዶሙና ሌላው ሌላው በእኛ ለምን አይታይም? ከማን በምን በልጠን ነው? ስለዚህ እነሆ ዛሬ ዳር ዳሩን እየሰማን ነው። አያስገርመንም። 

የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ለመጠበቅ ምን እናድርግ?  (ይቀጥላል።) 




17 comments:

  1. እግዚአብሔር ይስጥልን ቀሲስ፦ በጣም ደስ የሚል እይታ ነው። እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልዎት እያልሁ የሚከተለውን አስተያየት ብሰነዝርስ፦ መቼም ኦርቶዶክሳውያንን ከሚያጠቃን ነገር አንዱ ጠባብነት ነው። አንዲት ሃይማኖት ማለት ኦርቶዶክስ ናት እየተባልን አድገን አዕምሮአችን አለማቀፋዊ የሆነ እይታን ማየት ተስኖታል። በክርስቶስ የሚያምን የሌላ ዲኖሚኔሽን አማኝ የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ አይመስለንም። አንዲት ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክስ ወይም ጴንጤ ሳይሆን በክርስቶስ ያሉ ሁሉም ናቸው። ይህንን በድፍረት መቼ ይሆን መናገር የምንጀምረው። በሚቀጥለው ጽሁፈዎት ላይ ይህንን ሰፋ አድርገው የበለጠ ዓለማቀፋዊ ቢያደርጉትስ?

    ReplyDelete
    Replies
    1. የተወደዱ አስተያየት ሰጪዬ ይህ ችግር መጀመሪያ የመነጨው ከምዕራባውያን ወንድሞቻችን እንደሆነ ከታሪክ ማስተዋል እንችላለን። ሚስዮናውያን ወደሀገራችን ሲመጡ ምድሪቱ ወንጌልን እንዳልሰማች ቆጠረው እንደሆነ ማስተዋል አለብን። በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት የጻፉትን መጣጥፎች The Missionary Factor in Ethiopia (Studien Zur Interkulturellen Geschichte Des Christentums) ማየት ይችላሉ። እውነተኛ የሆነ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በኢኩሜኒዝም መንፈስ ለመወያየት ብዙ በሮች ይኖራሉ ብዬ አምናለሁ። ይህም ከሁሉም ወገን ሲሆን ነው። ስለዚህ ጉዳይ በሦስተኛው የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ ላይ እንመለሳለን። ይቆየን።

      Delete
    2. Endew Pentew kereto, yetekerew Orthodox ande behone. I don't care about Pente because that is not my faith. Let them care about themselves. The idea of ecumenicalism is not practical given the animosity that Penetes have against the Orthodox church.

      Also, despite their delcared mission, the Western Pentes and the Catholics for that matter came to Ethiopia for other reasons other than the Gospel: 1) to spy Ethiopia for their governments, 2) to divide and weaken the Orthodox church and hence its government etc... Most of the Ethiopian emperors had wondered and asked why/how the missionaries skipped Libia, Egypt and Sudan and focused on Ethiopia if their mission were spreading the Gosple. The answer is obvoius. So, please let us focus on the Orthodox church; the Penete and Catholic chruches have their own leaders who care about their unity etc...

      Delete
    3. እርግጥ ነው፥ በዋናነት ልንነጋገር የሚገባን የእኛን አንድነት ነው። ሆኖም ግን የእኛዋም ቤተ ክርስቲያን ብትሆን የዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን አካል ስለሆነች፥ በዓለም ደረጃ ስላለው ክርስትና መነጋገራችን አይቀርም። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት World Church Council መሥራች አባል የሆነውም ለዚህ ነው። ዘመናዊው ኢኩሚኒዝም ሊመዘን የሚገባውም በምናየው የዲኖሚኔሽን ጥላቻና የበጎች ነጠቃ ሳይሆን በሊቀ ካህናቱ ጸሎት ነው። አንድ አድርገን በሚለው።

      Delete
    4. እግዚአብሔር ይስጥልን ቀሲስ። ይች ብሎግ በጣም ሳትስማማኝ አትቀርም። እስዎ በቀጥታ ለአስተያየቶች መልስ መስጠትዎ ደስ ይላል። ከላይ ለኔ በሰጡት አስተያየት እስማማለሁ። በርግጥም ይሄ ጠባብነት ምዕራባውያንንም እንዳጠቃ እርግጥ ነው። አጅሬ ሰይጣን ምን ይስራ፦ የመለያየትንና ከኔ ማን ይበልጣል የሚለውን ክፉ መንፈስ በሁሉም ውስጥ ለማስቀመት ይሞክራል።

      Delete
    5. በረከት፥ ስለተሳትፎዎ በጣም አመሰግናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ብሎጊቱን በማስተዋወቅ ደረጃ ያግዙን። ለሌሎች የድረገጽ ወዳጆችዎ በኢሜይል በፌስ ቡክ በትዊተር ያስተዋውቁአት። ይስደዱዋት።

      Delete
  2. ቀስቶ ወተረ እግዚአብሔር የመስገን አርሱ ሥራውን ሲጀመር አንዲህ ነው ከባጣገባቸው እያለ ሳናየው የኖርረነውን እንድናየው ያደርጋል ቀሲስ ማተዎስን ይመስል የሰውን ስምት የመነካት ተሰጦዎ በስከተዎ ብቻ ሳይሆን ወደ ጽሁፈዎም እየተጣበቀበዎ ነው ይበርቱ ማጠሩም ጥሩ ነው ግን እንዳይቋረጥ አደራ ይቀጥለ አንድገና እግዚአብሔር የቤተ ክረስቲያን ልሳን ስለ አደረገዎ ምሳጋናው ለርሱ ይሆን

    ReplyDelete
    Replies
    1. ቀስቶ ወተረ ስምዎ ያስፈራል። አሜን ከማለትስ ውጪ ምን ይባላል? እንግዲህ ከምርቃትዎ ጋር እጅዎ ከምን እያልን ስለሆነ፥ በተጻፉት ነገሮች ላይ አስተያየቶዎን በሰፊው ሰንዘር ያድርጉ።

      Delete
  3. በመጀመሪያ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የቤተክርስቲያን አንድነት በሚል ርዕስ ራሳችንን እንድንመረምር ስለፈቀደ ክብር እና ምስጋና ለእርሱ ይሁን። ቃለ ህይወት ያሰማልን ቀሲስ። በእውነት ይህ ጥያቄ ብዙ ሊያነጋግረን የሚችል ነው። ምክኒያቱም የራሳችንን ህይወት ቁጭ ብለን መመርመር እንደሚገባ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነቷ እና አንድነቷ ምን ደረጃ ላይ ነው የሚለውንም እንደዚሁ በየጊዜው መመርመር ይገባል ብዬ አምናለሁ። እንደ እኔ አስተያየት በመጀመሪያ ጌታ መንፈስ ቅዱስ አይናችንን ከዘር: በከባህል እና ከስልጣን አንስተን በአንዱ በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ላይ እንድናደርግ አይናችንን ያብራ እላለሁ። ሌላው በዚሁ ፁሁፍ ላይ እንደሚለው የውስጥ መለወጥ ያስፈልጋልና ይህ ለውጥ ደግሞ የሚመጣው በእግዚአብሔር ቃል ነውና ከምንም በላይ ጊዜያችንን ቃሉን በማንበብ ልናጠፋ ይገባል። በመጨረሻ ቤተክርስቲያን; ካህናት አባቶችን እና ምዕመናንን ሰብስባ በዚህ ጉዳይ ላይ በመወያየት ያልገባው ጥያቄ በመጠየቅ እና በመረዳት: የሰማው ላልሰማው እያካፈለ: በአንድ መንገድ አና ዕምነት ለመጓዝ ከፍተኛ ጥረት ሊያደርግ ይገባል ብዬ አምናለሁ። እግዚአብሔር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የተመሰገነ ይሁን። አሜን!

    ReplyDelete
    Replies
    1. የተወደዱ አስተያየት ሰጪ በሚገባ እንዳቀመጡት፥ የዚህ የጡመራ መድረክ ዋና ዓላማም በሰከነ መንፈስ ስለራሳችን በግልጽነት እንድንወያይ ነው። ወደዚህ የመነጋገር መንፈስ የሚያመጣንን አሳብ ሁላችንም ከየአቅጣጫው እንወርውር። ለዚህም አምላከ ቅዱሳን ይርዳን።

      Delete
  4. The analysis is fair and encouraging. Growing up, I also had lots of opportunities to see fist hand how the church is divided along tribal lines even before Weyane made it a policy. All your observations are correct in my opinion. Keep it up.... it is a very positive analysis that can help clean up some of the bad things around the church. Joro yalehe sima.

    ReplyDelete
  5. ቀሲስ እግዚአብሄር ይባርክዎት ትምህርቱ እራሳችንን እንድንመረምር የሚያደርግና ወደ አንድነት የሚጠራ ነዉ፡፡ ግዜዎትን ካልተሻማሁ አንዲት ጥያቄ ብጠይቅዎት ደስ ይለኛል፣ ይህዉም እንደሚከተለዉ ነዉ በመልእክትዎ ዉስጥ ‹‹በአርጋኖን (በፒያኖ) ሲዘመር ደነሱበት የሚል ትውልድ›› የሚል አነበብኩ ቤተ ክርስቲያናችን በፒያኖ መዘመር ትችላለች ማለት ነዉ? እንዲህ ማድረግ የሚገባስ ከሆነ እስካሁን በፒያኖ መገልገልን የምትቃወመዉ ለምንድን ነዉ?

    ReplyDelete
    Replies
    1. የተከበሩ አስተያየት ሰጪዬ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ የጠየቁኝን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት እስኪ የተጠቀሰውን ጥቅስ በንባቡ አውድ እንየው። እንዲህ ይላል፥ « ባህል ማለት ሌማት ማለት ነው። ባህል ማለት ጻህል( ሳሕን) ማለት ነው። ምግቡ የሚቀመጥበት። ሌማቱን የሚሠራው ዘመኑ ነው። ቅዳሴው የሚተላለፍበት ፕሮጀክተር ሲተክል ፊልም ቤት አደረጉት የሚል ትውልድ፥ በአርጋኖን (በፒያኖ) ሲዘመር ደነሱበት የሚል ትውልድ፥ አድማሳቸው ሰፊ የነበረውን የቀደሙትን አባቶች ታሪክ በሚገባ ያላስተዋለ ትውልድ ብቻ ሳይሆን፥ ወንጌልንም በሚገባ ያልተገነዘበ ትውልድ ነው።» ስለሆነም ፒያኖም ሆነ ፕሮጀክተር የሚተላለፈውን ቃለ እግዚአብሔር ከሰው ልብ ለማድረስ መሣሪያ ናቸው እንጂ በራሳቸው መልእክት አይደሉም፤ እነርሱን የምናይበት አተያይ ግን ባህል ነው።

      ይህን ካልኩ ግን ጥያቄዎ ወደተመሠረተበት ዋና ሐሳብ ልመለስ። ይኸውም አንድ ቤተ ክርስቲያን በፒያኖ መዘመር ትችላለች ወይ? ሁለት፥ በፒያኖ መዘመር የሚገባ ከሆነ ቤተ በፒያኖ መገልገልን ቤተ ክርስቲያን የምትቃወመው ለምንድነው? ከሁለተኛው ነጥብ ልነሣና፥ ቤተ ክርስቲያን በፒያኖ መዘመርን ተቃውማ አታውቅም። በዘመናዊቱ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሰፊ ቦታ ያላቸውን ሦስት አባቶችን ልጥቀስ። አንደኛው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው። በጊዜው ይታይ የነበረውን የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ለመግታትና ቤተ ክርስቲያኒቱ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንድትሰጥ ንጉሠ ነገሥቱና ፓትርያርኩ የበላይ ጠባቂዎች የነበሩበት ሃይማኖተ አበው የኢትዮጵያ የተማሪዎች ማኅበር ብዙዎች ሊቃውንትን እና ሊቃነ ጳጳሳትን በአባልነት ያቀፈና ያፈራ ሲሆን በፒያኖ ይጠቀም ነበር።

      የዛሬው አቡነ መልከ ጼዴቅ የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት ሃብተ ማርያም ወርቅነህ በሚመሩት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ወጣት ሴቶችና ወንዶች በፒያኖ ከመዘመራቸው በላይ እስከ አቡነ ጳውሎስ ፕትርክና ድረስ (እርሳቸውም ለጥቂት ዓመታት ተጠቅመውበታል) እስመ ኃያል አንተ የሚለው በጊዜ ቍርባን የሚዘመረው የቤተ ክርስቲያናችን ዜማ በቅዳሴ ጊዜ በፒያኖ ይታጀብ ነበር። ይህ በአምስቱም ፓትርያርኮች ዘመን የተከናወነ ነው።

      አሁን የማገለግልበት የድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ የሚገኘው የሰንበት ትምህርት ቤት ስሙ ሃይማኖተ አበው ነው። ከሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶች ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር፥ ፒያኖ ወንጀል ሆኖ በሚታይበት ዘመን መዝሙሩን የሚያጅበው በፒያኖ ነው። ይህን ሰንበት ትምህርት ቤት ሃይማኖተ አበው ብለው የሰየሙትና በፒያኖ እንዲዘመር ያደፋፈሩት፥ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩና፥ የሃይማኖተ አበው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር አባል የነበሩት አቡነ ጳውሎስ ናቸው።

      የታሪክንና የሌሎችን ዝርዝር ማስረጃዎች http://www.ethiopianorthodox.org/amharic/miscellenous/betekirstianbefetena03.html ይመልከቱ።

      በነገራችን ላይ ዛሬ ልጨኛ ( classic) ተብለው የሚታወቁት የቤተ ክርስቲያናችን መዝሙሮች እንደቸርነትህ፥ የአብርሃም አምላክ እና ሌሎችም ለፒያኖ ተብለው በኖታ ተቀምረው የተዘጋጁ መሆኑን ያውቃሉ? ይበቃናል።

      Delete
  6. tsegawotin yabzalot kesis awo bergit yebetekirstianachin chigr meweyayet melkam new neger gin wanaw kulf minchu maweki melikam new yehem be betekihent akababi ena yesinodosu siltan manes new yehem yemaygebachew hailoch gebitew silebetebetu new enji be astemirotua lay chigr yelewm mikiniatun eyandandu neger metsihaf kidusawein enji mahilawe hono ayemeslegni eski erso bahilawei yemilutin negerochi gili behone huneta giletsut yehen kebahil akuaya enji metsihaf kidusawei aydel yehen hig yewtaw ye ethiopia behal new yemibalutin eski giletsulin lelaw kononawens lishashal biasfelig siltanu yeman new ?miemanu weyes begroup yetederaje hail new liashashilew yekeyerlin yemilew ? Kesis andanid neger yemiawetut neger sewn wede tirtare yemewsid miemnaninim wedetesasate menged yemiamerachew new lemsale set lije silalet siltan bebetkirstian la ,sile mezimur mesaria argano (piano),yemibelu yemayebelu migbochin betemelet, sile endezih ayenet neger enweyay malet kiftet mefter new erso sinodos benezih neger lay yastelalefewn neger yawekalu biye egemitalew silezih yehenin lesinodosu entewew wanaw wengel eytekesin emenafkan weyem kenetaki tekula begochin madan yeshashal letekulaw bere kemekifet ahun yehe ayedelem yebetekirstian chig biye asbalew

    ReplyDelete
    Replies
    1. ወዳጄ ኤልያ ስ፥ግልጥ ስለሆነው ጥያቄዎችዎ በጣም አመሰግናለሁ። ነገር ግን ብዙ ሐሳቦችን ስላስቀመጡ ሁሉን ለመዳሰስ ቦታ አይበቃንም። ሆኖም ግን ካነሡዋቸው አሳቦች መካከል፥

      1. ቤተ ክርስቲያናችን በአስተምህሮዋ በኩል ችግር የለባትም የሚለው፥ እኔም የምስማማበት ይህ እውነተኛና ትክክለኛ አባባል ነው።
      2. ባህላዊ ነው ስለሚሉት እስኪ ጥቀሱልን ስላሉት ፥ እርስዎ በዝርዝር የጠቀሱዋቸው ነገሮች በሙሉ ማለትም የሴቶች አገልግሎት፥ የሚበሉ የማይበሉ፥ አርጋኖን(ፒያኖ) የመሳሰሉት ነገሮች ላይ ያለን አስተያየት በአብዛኛው የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰባችን ሳይሆን በባህላችን ነው። አባቶቻችን ከአምስት መቶ አመት በፊት የወሰኑትን የገላውዴዎስ ውሳኔን ይመልከቱ።
      3. እንደእነዚህ ዓይነቶቹን ነገሮች አንስቶ መወያየት ምእመናንን ለጥርጣሬ መስጠት ነው የሚለው አደገኛ አመለካከት ይመስለኛል። በተለይም በዚህ የመረጃ ዘመን መወያየትን ከሸሸን ምእመናችንን እሳልፈን የምንሰጠው በዕውቀት ላይ ላልተመሠረተ አይታ ነው። ባህል ሰፊ ነገር ነው። በግልጥ እለመወያየት፥ በእግቦ በሽሙጥ መናገር፥ ሐሜቱ፥ ጠልፎ መጣሉ ባህል ሲሆን ትውልድ ይገድላል። ስለሆነም አሁን እያደረግን ባለው ሁኔታ በግልጥ ሁሉን በመነጋገር መፍትሔ መስጠትይቻላል። ለተኩላ አሳልፍ የሚሰጠው፥ ተኩላውን አለማወቅ እንጂ አጥርቶ ማየት አይመስለኝም። ውይይትና መነጋገር አጥርቶ ማየትን ያመጣል።

      Delete
  7. ቀሲስ ለጥያቄየ መልስ ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ፡፡ የጠቆሙኝንም መረጃዎች ተመልክቻለሁ እንዲሁም ደግሞ የሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ የመጀመሪያ ካሴትም በፒያኖ የተቀመረ እንደነበረ ወንድሜ ነገረኝ በተጨማሪም በፒያኖ መጠቀም ማለት ልክ አሁን መናፍቃን እንደሚጠቀሙት ለእግዚአብሄር የተሰዋ እስከማይመስልና የአለም የአለም እንዲሸት ማድረግ አለመሆኑንም ነገረኝ ስለዚህም እርስዎንም ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጠኝን ወንድምም አመሰግናለሁ እግዚአብሄር ይባርካችሁ ጸጋዉ ይብዛላችሁ እላለሁ፡፡

    ReplyDelete