Tuesday, January 8, 2013

የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ችግርና መፍትሔው

 በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ 


መግቢያ 

በፕሮፌሰር ብራድሊ ናሺፍ  የተጻፈውን ስለጳጳሳት ሐዋርያዊ ተልእኮ የሚያትተውን ጽሑፍ በጡመራ መድረካችን ላይ ካስቀመጥንበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አስተያየቶች ደርሰውናል። በዋናነት የሚጠቀሰው ግን ምንም እንኳ ፕሮፌሰር ናሺፍ ያነሡዋቸው ነጥቦች በወል ሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት የሚዳስሱ ቢሆኑም፥ የእኛን ቤተ ክርስቲያን ዐበይት ችግሮች በጥልቀት የሚዳስሱ ጽሑፎች ስለማስፈለጋቸው ነው ምንምን እንኳ ይህ የሁላችንንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም እኛ ቃል እንደገባነው በፕሮፌሰሩ መነሻ ነጥቦች ላይ በመመርኮዝ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ላይ የሚያጠነጥነውን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል አቅርበናል።
ወደጽሑፋችን ዋና ሐሳብ ከመግባታችን በፊት ግን የሚከተሉትን ነጥቦች ለማስጨበጥ እንሞክራለን። አንደኛ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ላለችበት ሁኔታ ተጠያቂ የምናደርገው አንድን ቡድን ወይም አካል ሳይሆን ሁላችንንም ነው። ይህን የምናደርገው ለይምሰል ወይም የዘመናዊ ሐሳብ ፍሰት አካሄድ ስለሆነ ሳይሆን፥ እነ ዳንኤል እነ ኤርምያስ ስለሕዝባቸው ስለአገራቸው ያላቸውን ጭንቀት በገለጡበት ወቅት የተከተሉትን መንፈስ ተከትለን ነው።

ሁለተኛ ይህን ለቤተ ክርስቲያናችን ይጠቅመናል የምንለውን ሐሳብ የምናቀርበው ለቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ ልጆች ነው። እውነተኛ ልጆቹዋ እነማን እንደሆኑ የሚያውቀው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ውጫዊ ምልክቶች ግን አሉዋቸው። ከእነዚህም ምልክቶች ዋነኛው ፍቅር ነው። አገልግሎት የሚመነጨው ከዚህ ፍቅር ነው። እምነታቸው እንኳ ለገላትያ ሰዎች ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው « በፍቅር የሚሠራ እምነት» ከዚህ የተነሣ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ስለሚጠፉት ሰዎች ይገዳቸዋል። በእንባና በጸሎት ያስተምራሉ ይመክራሉ የመድኃኔ ዓለምን ሞቱንና ትንሣኤውን ይመሠክራሉ።

በአሁኑ ወቅት ግን የቤተ ክርስቲያኒቱን አደባባይ ያጣበበው ድምጽ የኑፋቄ ፖለቲካ ነው፤ የምንቃወመውንና የምንጠላውን ወገን  በኑፋቄ ጠልፎ መጣል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ከዛሬ መቶ አመት በፊት ጐሐ ጽባሕን ሲጽፉ ለአገርና ለወገን ጠንቅ የሆኑ ብለው ካነሡዋቸው ነገሮች አንዱ ቤተ መንግሥቱን ጥግ አድርጎ የንጹሐንን ደም ማፍሰስ ነው። የነአባ ዘሚካኤል የነደቂቀ እስጢፋኖስ ደም የፈሰሰው በዚህ መንገድ ነው። እነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍል ተገፍተው የወጡት በዚህ መንገድ ነው። ዛሬም ያን የኑፋቄ ፖለቲካ ያነገቡ ሰዎች የጥንቶቹን  ስመ ጥር ሊቃውንት እነ አቃቤ ሰዓት ከብቴን ይወገዙልን እያሉ እንደሆነ እየሰማን ነው። ስማቸውን ያወቁትም በየሰንበት ትምህርት ቤቱ በሚማሩት « ለመናፍቃን ምላሽ» በሚባል የኑፋቄ ፖለቲካ ነው። በመሆኑም አሁንም በዚህ ጽሑፋችን የምናቀርበው አሳብ ለእነዚህ ሰዎች ኑፋቄ ኑፋቄ ሊሸታቸው ይችላል። ሆኖም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች እንደመሆናችን ለቤተ ክርስቲያናችን ይበጃል ያስፈልጋል የምንለውን በባለቤትነት ማቅረብ ይኖርብናል።

ሦስተኛ ይህን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ይበጃል የምንለውን አሳብ የምናቀርበው  ቅዱሳት መጻሕፍትን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትውፊትና ታሪክ አጣቅሰን ነው በዘመናዊነት አስተሳሰብ ተገርኝተን አይደለም። የአውሮፖውያን የአብርሆት ፍልስፍናና አመክንዮ፥ ወይም አምልኮትን ከቃለ እግዚአብሔር የለየው የ16ኛው ክፍለ ዘመን የሃይማኖት እንቅስቃሴ፥ ወደ ደረቅ ምርመራ ሰውን ሁሉ ስለመራ ዛሬ አውሮፓ የክርስትና ምድረ በዳ ሆና የሐዋርያ ያለህ እያለች ነው። በመሆኑም አውሮፓን ያደረቀና እምነት አልባ ያደረገ አካሄድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልምላሜን ሊያመጣ አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ ትውፊታችንን ታሪካችንን ስንል ደግሞ በጭፍን ያለፈውን ጉድለታችንን ሳንመዝን አናግበሰብስም። ፕሮፌሰር ብራድሊ ናሽፍ እንዳሉት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ማለት ትውፊትን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ከመበስበስና ከድንቁርና መጠበቅ ማለት ነው።


                                              ክፍል አንድ 
የቤተ ክርስቲያን መለያ ባሕርያት 

በአንቀጸ ሃይማኖታችን ላይ « ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት፤ ከሁሉ በላይ በምትሆን፥ ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።» በማለት እናውጃለን። ይህ በኒቅያና በቍስጥንጥንያ የተወሰነው አንቀጸ ሃይማኖታችን የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ባህርያት ይነግረናል። ምናልባትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ዐቢይ ችግር ለመረዳት የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ባህርይ መረዳት ይኖርብን ይሆናል።

በአንቀጸ ሃይማኖታችን መሠረት፤
ሀ. በአንዲት (አሐቲ) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
ለ. በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
ሐ. በሐዋርያዊት (ጉባኤ ዘሐዋርያት) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
መ.  ከሁሉ በላይ በምትሆንና በሁሉ ባለች (እንተ ላዕለ ኵሉ) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።

(ይቀጥላል። ) 

4 comments:

 1. It is a good beginning, but it is too short. Part One should have at least been completed to satisfy readers. I am so curious what the details are...

  ReplyDelete
 2. We will be waiting to see the details eagerly. I believe Qesis Melaku is capable to teach us in detail.I am sure he will not teach us anything that is not the teaching of our Orthodox Tewahido church .

  ReplyDelete
 3. Our Brother Ato Kebede thank you for the feedback. This is a forum for the children of this mother church. So, please join the discussion and you can agree or disagree with me. Here I am trying to explain our current problem based on the four nature of the church: Unity, Holiness, apostolic teaching and Universality. As our Orthodox Fathers gave us, these four characteristics are very foundational to identify the solution. If you like the blog please introduce to your friends. Once again thank you.

  ReplyDelete
 4. Dear Kesis Melaku,
  I read a couple of your writings on your blog. I found you writings very impressive and
  powerful. I wish some of your work gets published on a medium that has a wider readership. At the micro level the immediate problem at my church is the imbalance between the capacity of our head priest (bishop) and what the position requires to be a leader and a good shepherd. I wish your writings get published on a medium with more readers.
  Fikru

  ReplyDelete