Friday, January 11, 2013

የስምዖን ዓምዳዊ ጸሎት (ክፍል ሰባት)

Read in PDF

ምዕራፍ ፲፱፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ፴ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ ትጠመቅና ጥምቀትንም ትባርካት ዘንድ መጣህ፤ ዮሐንስ በወንዙ ዳር ቆሞ ሙሽራዪቱን ለማየት ከአዳራሹ የሚወጣውን የንጉሡን ልጅ መምጣት ይጠባበቅ ነበር። እንዲያጠምቅ የላከው እርሱ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድና በራሱ ላይ ሲቀመጥ  ያየኸው (የእግዚአብሔር) ልጅ በእውነት እርሱ ነው አለው። አሕዛብ ሁሉ ተስፋ የሚያደርጉት፥ ይህም የቀደመው መንፈሳዊ ልደት ነው። በመገዘር የአብርሃምን ምሥጢር ፈጸመ። ዳግመኛም የሙሴ ምሥጢር ወደ ቤተ መቅደስ በመግባቱ ተፈጸመ። (የቃልን) ምሥጢር ወደዮሐንስ አደረሰው፤ እርሱም የነቢያት ፍጻሜ፥ በመዐልትና በሌሊት መካከል የቆመ፥ አንደኛው እጁ በነቢያት ዕጣ ሌላ እጁ ከሐዋርያት ጋር የሆነ ነው። እርሱ የነቢያት ፍጻሜ፥ የወንጌላውያን ቀደምት ነው። ስለሙሽራው ሲናገር ከእኔ በፊት የነበረ ከእኔ በኋላ ይመጣል ብሎአልናል። የወልድን የፊቱን መልክ ሲመለከት በጣቱ አመለከተ፤ የዓለምን ኃጢአት የሚሸከምና የሚያስወግድ የእግዚአብሔር ልጅ አለ። 


ዮሐንስ በሙሽሪት ጆሮ የቃልን ምሥጢር የሚያውጅ ነው። ወልድ ወደ ኅሊና የሚገባ የቃል ምሥጢር ነው። ወደ ልብ ውስጠኛ ክፍል የሚገባና የሚኖር ቃል ብቻ ነውና። የሰው የጩኸት ድምፅ ቃልን ከሰው ጆሮ ያደርሳል። ድምፅ ከጆሮ ደጃፍ ይቆማል። ቃል ግን ከልብ ይገባል፥ ያለመለየትም ይዋሓዳል። ከልብ ይወጣል፤ በመጻሕፍት ውስጥም ይጻፋል። ቃል ወደ ሕሊና ይገባል፤ የማይጎድል ምሉእ ነውና በልብ ያድራል።  ለስም አጠራሩ ስግደት ይግባውና፥ ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ ነው። ትእዛዙን በምታደርግ ነፍስ ሁሉ፥ በሁሉ ያድራል፤ የምታገኝህም ነፍስ ሁሉ በክብርህ ደስ ትሰኛለች ሐሴትም ታደርጋለች። እኔም ይህችን ሕይወት አገኘኋት። የእግዚአብሔር ልጅ የልደቱ ምሥጢር እንዲህ ነው። ፈጣሪ በሆነው በአባቱ አምሳል፥ ዓለምን ይወልዳል። ይህ የቀደመው ሐዲስ ዓለም ነው። ይህ መንፈሳዊ ልደት፥ የጻድቃን ትንሣኤ ራስ ነው። እርሱም በዚህ ይኖራል። 

ምዕራፍ ፳፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ውሆችን ልትቀድስ ወደ ጥምቀት የመጣህ፥ እኔን አገልጋይህን እንደዚሁ ቀድሰኝ፤ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይልትጠመቅና ከሐዲስ ሕይወት ማኅፀን እንወለድ ዘንድ ለሰማያዊው አባት ልጆች ልታደርገን ለአንተም ወንድሞች ልታደርገን ወደ መጠመቂያ የመጣህ፥ ከዚያች እናት ውለደኝ መንፈሳዊ ሕይወት ወደሆነች ልደትም ከፍ ከፍ አድርገኝ።   

No comments:

Post a Comment