Thursday, January 31, 2013

የእስክንድርያ ትምህርት ቤት (ክፍል ሁለት )

Read in PDF
የትምህርት ቤቱ አመሠራረት

የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ስንል፥ በዘመናዊ አስተሳሰብ የትምህርት ቤት ሕንፃ አናስብም፤ ሌላው ቀርቶ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እንኳ አናስብም። ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በአስተማሪው ቤት ነው። (ይህ አሁን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጠው ማለት ነው።) 


ይህ የክርስቲያን ትምህርት ቤት በመጀመሪያ የተጀመረው እንደ ንዑሰ ክርስቲያን (ካታኪዝም) ትምህርት ቤት ነው። ማለትም የክርስትናን እምነት ተምረውና መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ለጥምቀት የሚዘጋጁ ከአረማዊነት ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች የሚማሩበት ነው። የትምህርት ቤቱ ዲን ንዑሰ ክርስቲያንን ለጥምቀት የሚያዘጋጁ ነበሩ። የትምህርት ቤቱ ዲን የነበረው አርጌንስ በመጻሕፍቱ ውስጥ ስለእነዚህ ንዑሰ ክርስቲያንን አስተማሪዎች (ካታኪስት) ዘግቦአል። አስተማሪው የክርስትናን አስተምህሮና ክርስቲያናዊ ሕይወት ያስተምር ነበር። « ጥምቀትን ለመቀበል ከፈለጋችሁ» ይላል አርጌንስ፥ « በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ቃል መማር አለባችሁ፤ ከቀደመው ከክፋት፥ የአሕዛባዊ ሕይወትና አነዋወር ሥር መለየት አለባችሁ፥ የዋህነትንና ትህትናን መለማመድ አለበኣችሁ። የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ለመቀበል የተገባችሁ የምትሆኑት ከዚህ በኋላ ነው፤»


ባርዲ ስለ እስክንድርያ ትምህርት ስናስብ ከንዑሰ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ይልቅ የፍልስፍና ትምህርት ቤትን እያየን እንደሆነ ሲያሳስበን፥ ሜሃት ደግሞ በሌላ ጎኑ  ካታኬሲስ ማለት ዝም ብሎ የጥምቀት ትምህርት ማለት ብቻ እንዳይደለ ይጠቁመናል። ጄ ፌርጉሰንም እነዚህ ሁለቱ ማለትም ካቴኪዝም እና ፍልስፍና ሁለቱን የማይጣጣሙ እንደሆኑ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ እንዳላየ ጠቁሞአል። 

ትምህርት ቤቱ ዕድሜ፥ባህል፥ እና የኑሮ ሁኔታን ሳይወስን ለሁሉም ሰው ክፍት ነበር። በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ትምህርት ቤቱ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ለመሆኑ በሚከተሉት ነገሮች እናያለን። 

1. የእስክንድርያ ክርስቲያኖች የሃይማኖት ዕውቀት ጥማትን ለማርካት የቻለ ነበር። በተለያዩ መስኮችም ከፍተኛ የሆኑ ጥናቶችና ምርምሮች እንዲደረጉ የሚያበረታታ ነበር። ጂ ኤል ፕሬስቲጅ የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር የነበረው የአርጌንስ ተማሪዎች ስለነበሩት ሲናገር እንዲህ ብሎአል። 
« ትምህርታቸው በሁሉ አቅጣጫ ምሉዕ ነበር፤ ማናቸውንም ጥያቄ መጠየቅ ይችሉ ነበር፤ ማናቸውም ዕውቀት ከእነርሱ አይሸሸግም ነበር። የግሪክ ይሁን የሌላ ባህል፥ መንፈሳዊ፥ ማኅበራዊ፥ ሰዋዊ ወይም መለኮታዊ ማናቸውንም የትምህርት ክፍል ለማጥናት እድል ነበራቸው። (የአርጌንስ ተማሪ የነበረው ገባሬ መንክራት (ታማተርገስ) ጎርጎርዮስ ስለዚህ ሲናገር፥  « በዕውቀት ዓለም ውስጥ እንድንመላለስ እና እንድንመራመር፥ በተለያዩ ትምህርቶች ራሳችንን እንድናረካና ጣፋጭ በሆነችው ጥበብ እንድንደሰት፥ ሙሉ ነጻነት ተሰጥቶን ነበር።» ሲለን  በአርጌንስ የጥበብ መሪነት ሥር መሆን፥ ያለ ድካም የአእምሮ ፍሬ በሚበልቅበትና  በደስታና በሐሴት በሚኖሩበት በገነት እንደመኖር ነበር  « በእግዚአብሔር ገነት ምሳሌ፥ አርጌንስ ለእኛ እንደ ገነት ነበር፤»  ሲል እርሱን ትቶ መሄድም ልክ አዳም በውድቀቱ የሆነውን መሆን ነበር ብሎአል። እንዲህ ዓይነት ምስክርነት ከተማሪዎቻቸው ያገኙ አስተማሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው።»

2. ትምህርት ቤቱ በዘመናት ሁሉ እጅግ መንፈሳውያን የሆኑና የታወቁ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን  አፍርቶአል። ብዙዎቹም በቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ሊቀመጡ የተገባቸው ሆነዋል። 

3. ትምህርት ቤቱ ወንጌልን ለማስፋፋት ባለው ቅንዓት መሠረት ፥ በግብፅም ሆነ በሌሎችም አገሮች ብዙዎችን ነፍሳት ወደ ክርስትና ለመመለስ ችሎአል። 

4. በእውነተኛ የኢኩሜኒካል መንፈስም ኋላ በራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሆኑ ብዙዎች ተማሪዎችን ከሌሎች አገሮች ስቦአል። 

5. መሠረታዊ በሆነው የሃይማኖት መዋቅር ውስጥ የትምህርትን አስፈላጊነትን በሰዎች ውስጥ ያሠረጸ ነው። 

6. በዓለም የመጀመሪያው የሆነውን አጠቃላይ የነገረ መለኮት ጥናቶች ( Systematic theology) ያቀረበ ነው። 

7. የአሕዛብን ፍልስፍና ለመጋፈጥ ፍልስፍናን እንደመሣሪያ የተጠቀመና አሕዛብን በራሳቸው ሜዳ ያሸነፈ ነው። 

8. ምንም እንኳ የእስክንድርያ ትምህርት ቤት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤትና በሊቃነ ጳጳሳት በካህናትና እና  በምእመናን ላይ ከፍተኛ የሆነ ትምህርታዊና መንፈሳዊ ተጽእኖ ያለው፥ አብዛኛዎቹ ርእሰ መምሕራኖቹም ፓትርያርኮች ቢሆንም፥ ትምህርት ቤቱ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ላይ (በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ነበር። ጂ ኤል ፕሬስቲጅ ስለዚህ ሲናገር፦
በሮምና በእስክንድርያ ትምህርት ቤቶች መካከል ያለው ዋና ልዩነት በምስራቁ የክርስትና ዓለም ያለው በክርስትና ትምህርትና እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መካከል የቅርብ ግንኙነት ነው። የእስክንድርያ ፓትርያርኮች ምናልባትም ታላላቆቹን መምህራን ጥቅል በሆነ መንገድ በመረዳት፥ ሲመክሩአቸውና ሲቆጣጠሩአቸው የነበሩ ይመስላል። በሮም ክፍል እንደሚታየው የእስክንድርያዎቹ ፓትርያርኮች ካላቸው በራስ መተማመንና ምኞት የተነጃ የነገረ መለኮቱን ዓለም ሲጋፉ አልታዩም። በማንኛውም ሁኔታ፥ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በክርስትናው ዓለም እጅግ ማዕከላዊ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ነበረች።    

No comments:

Post a Comment