የእስክንድርያ ትምህርት ቤት
በቀሲስ ቴድሮስ ማላቲ
ትርጉም በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ ተረፈ
መግለጫ፤
ከዛሬ ጀምሮ በየሁለት ሳምንቱ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚመለከቱ ጽሑፎችን እናወጣለን። በሚቀጥሉት ተከታታይ ብሎጎች የእስክንድርያ ትምህርት ቤትን በሚመለከት ግብጻዊው ቀሲስ ቴዎድሮስ ማላቲ የጻፉትን ተርጕመን እናወጣለን። አንዳንድ የግርጌ ማስታወሻዎችን እንደየሁኔታው ለማከል እንሞክራለን።
መግቢያ ስለ እስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን
ክርስትና ወደ እስክንድርያ ከመግባቱ በፊት ቀደም ብሎ፥ ከተማይቱ የዕውቀት መናኸሪያ በሆኑ ብዙ ትምህርት ቤቶቹዋ የምትታወቅ ናት። ከነዚህም ትምህርት ቤቶች መካከል ታላቁ «ሙዚየም» በመባል የሚታወቀውና በፕቶሎሚ የተመሠረተው ነው። ይህ ትምህርት ቤት በምሥራቁ ዓለም እጅግ የታወቀ ትምህርት ቤት ነው። ከ« ሙዚየም» ጋር « ሴራፒየም» እና « ሴባስቲዮን» የተባሉ ትምህርት ቤቶች ነበሩ። እነዚህ ሦስቱ ትምህርት ቤቶች በየራሳቸው ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት ነበራቸው። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው ጁስቶ ጎንዛሌዝ እንደዘገበው፥ በዓለም የታወቁ ምሑራን ይመሩት የነበረው የ« ሙዚየም» ቤተ መጻሕፍት፥ በአንድ ወቅት ከሰባት መቶ ሺ በላይ መጻሕፍት ያስተናግድ ነበር። ይህም ማለት በጊዜው እጅግ አስገራሚ የሆነ የዕውቀት ማህደር ነበር። « ሙዚየም» ስሙ እንደሚያመለክተው፥ ለግሪክ እና ሮማውያን አማልክት ለሙሰስ የተበረከተ፥ አያሌ ጸሐፍያን፥ ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች የተሰባሰቡበትና ምርምራቸውን የሚያከናውኑበት ዩንቨርስቲ ነበር። በእነዚህ ተቋማት ምክንያት እስክንድርያ በዕውቀት ማዕከልነቷ እጅግ ታዋቂ ከተማ ነበረች። በቁጥር የበዙ የአይሁድ ትምህርት ቤቶችም በከተማዋ ውስጥ በየቦታው ነበሩ።
የእስክንድርያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በከተማዋ ውስጥ ለሚሰጠው ትምህርት የተለየ ቃና ሰጥቶት ነበር። ይህ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ከእስክንድርያ የሚወጣው ምሑራዊ ሥራ፥ የዓለሙን ጥማት የሚያመለክት ነበር። ምሥጢራዊና የተሸሸገ ጥበብ ያዘለች አገር አ አድርገው በሚመለከቷት በጥንታውያን ግሪኮች ዘንድ ግብጽ እጅግ እጅግ የምትደነቅ አገር ነበረች። ከዚህም በላይ ከምሥራቅ የመነጩት የተለያዩ ትምህርቶችና አስተሳሰቦች ሁሉ ተሰብስበው የተለየ ክምችት ፈጥረው ነበር። ከነቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው የመጡት አይሁድ ብቻ አልነበሩም። ባቢሎናውያን ከነየሥነ ፈለክ ጥናታቸው፥ ፋርሳውያን ከምንታዌ አስተሳሰባቸው መጥተው ነበር። ብዙዎቹም ልዩ ከሆነውና ብዙውን ጊዜ ግራ ከሚያጋባው እምነታቸውና አስተሳሰባቸው መጥተው ነበር።
በሌላ ቋንቋ ብዙ ባህልና ቋንቋ በአንድነት የሚኖርባት (ኮስሞፖሊታን) የእስክንድርያ፥ከተማ፥ የግብጻውያን፥ የግሪክ፥ የአይሁድ ባህሎች ከምሥራቃውያን የተመስጦአዊ ትምህርት ጋር በአንድነት የሚኖሩባትና ለአዲስ ሥልጣኔ መነሻ ትሆን ዘንድ፥የትምህርት ማዕከል እንድትሆን የተመረጠች የተለየች የዕውቀታዊ ሕይወት ማዕከል ነበረች። ፊሊፕ ሻፍ እንደጠቆመው፥
« እያደገ የመጣ የንግድ፥ የግሪክ እና የአይሁድ ትምህርት ማዕከል እና በጥንታዊው ዓለም ታላቅ የነበረው ቤተ መጻህፍት መቀመጫ የነበረችውና ታላላቆች ከሆኑት የክርስትና ማዕከላት አንዷ የሆነችውና የሮምና የአንጾኪያ ተፎካካሪ የነበች እስክንድርያ፥ የግብጽ መጥሮጶሊስ ነበረች፥ የፍልስጥኤም የሃይማኖት ህይወትና የግሪክ የዕውቀት ይትበሃል አንድ ላይ ሆኖ ፍልስፍናዊ ውይይትና አስተርእዮአዊ እውነቶችን ማስረገጥን ዓላማው ያደረገው የመጀመሪያው የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት እንዲከፈት ጥርጊያ መንገድ ከፈተ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ ታላላቅ ትምህርት ቤቶች የከፈቱትን የአስተሳሰብ ጦርነት ለመቋቋም፥ የክርስቲያን ተቋም ከማቋቋም ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ አልነበራትም። በሐዋርያት ዘመን ምሁራን የሆኑ ክርስቲያኖች በእስክንድርያ እንደነበሩ በእርግጠኝነት መገመት ይቻላል። ለምሳሌ በሐዋ ሥራ 18፥24 ላይ አጵሎስ ስለተባለው ምሑርና መጽሐፍ ቅዱስ አዋቂ የእስክንድርያ አይሁድ ቅዱስ ሉቃስ ሲነግረን እናገኛለን። ምናልባትም አቂላንና ጵርስቅላን ሳይገናኝ በፊት ስለኢየሱስ የተማረው እና የተረዳው በእስክንድርያ ሊሆን ይችላል።
የክርስቲያን ትምህርት ቤት
ቅዱስ ኢያሮኒሙስ (ጀሮም) እንደዘገበው፥ የእስክንድርያ ትምህርት ቤት የተመሠረተው፥ በራሱ በቅዱስ ማርቆስ ነው። ትምህርት ቤቱን የመሠረተው ክርስትናን ለማስተማርና በከተማይቱ ውስጥ ለአዲሱ እምነት ጠንካራ መሠረት ለመጣል ብቸናው መንገድ እንደሆነ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነው።
ትምህርት ቤቱ በክርስትና ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የነገረ መለኮት ትምህርት ማዕከል ሆነ። የመጀመሪያው አጠቃላይ የነገረ መለኮት ንድፍ የተቀመረውና የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎምና አፈታት ዘዴ መልክ የያዘው በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። በዚህ መሠረት ዶን ሪስ እንደጠቆመው፥ « በጥንቱ የክርስትና ዓለም ውስጥ እጅግ ታዋቂ የሆነ የእውቀትና የምርምር ተቋም ቢኖር ያለምንም ጥርጥር የእስክንድርያ ካታኪዝም ትምህርት ቤት ነው። ተቀዳሚ ዓላማውንም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በማድረግ ለመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ትውፊት ትልቅ ስም ተከሏል። የትምህርት ቤቱም የአተረጓጎም ዘዴም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ፊደላዊ ንባብ ባሻገር የሚገኘውን መንፈሳዊ ትርጉም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማናቸውም ሥፍራ ለማግኘት ነበር። »
የትምህርት ቤቱ አመሠራረት
የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ስንል፥ በዘመናዊ አስተሳሰብ የትምህርት ቤት ሕንፃ አናስብም፤ ሌላው ቀርቶ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እንኳ አናስብም። ትምህርቱ ይሰጥ የነበረው በአስተማሪው ትምህርት ቤት ነው። (ይህ አሁን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንደሚሰጠው ማለት ነው።)
ይህ የክርስቲያን ትምህርት ቤት በመጀመሪያ የተጀመረው እንደ ንዑሰ ክርስቲያን (ካታኪዝም) ትምህርት ቤት ነው። ማለትም የክርስትናን እምነት ተምረውና መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ለጥምቀት የሚዘጋጁ ከአረማዊነት ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች የሚማሩበት ነው። የትምህርት ቤቱ ዲን ንዑሰ ክርስቲያንን ለጥምቀት የሚያዘጋጁ ነበሩ።
ማስታወሻ
ንዑሰ ክርስቲያን (ካታኩሜን) የምንላቸው፥ ወደ ክርስትና ለመግባት ፍላጎት ኖሮአቸው በትምህርት ላይ ያሉ የክርስትናን እውነትና መጽሐፍ ቅዱስን የሚማሩ ናቸው። በቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት ለምሳሌ በቅዳሴው እነዚህ ሰዎች መካፈል የሚችሉት ሥርዓተ ቅዳሴውን (የትምህርት ጊዜውን) ብቻ ነው። መልእክታቱን ወንጌሉን አድምጠው ፍሬ ቅዳሴ (liturgy of the faithful) ላይ ሲደርሱ ዲያቆኑ ጻዑ ንዑሰ ክርስቲያን ንዑሰ ክርስቲያን ውጡ ይላል። አሁን ጸሎቱና ቅርጹ ብቻ ነው ያለው እንጂ አይሠራበትም። (ተርጓሚው)
ይቀጥላል።
It is not a bad idea, but it would have been better if you focused on our own church history. Do people know EOTC's history well? Definitely No. Yerasewa arobat yelelawin tamaselalech endemibalew endayhon. I am not an opponent of aybody's history! What I am saying is that we should know ourselves better. Then we can explore others very easily. It is like the importance of learning the Tewahedo faith before trying to learn comparative theorlogy, i.e.e Catholicism, Protestantism etc...
ReplyDeleteከነቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው የመጡት አይሁድ ብቻ አልነበሩም። ባቢሎናውያን ከነየሥነ ፈለክ ጥናታቸው፥ ፋርሳውያን ከምንታዌ አስተሳሰባቸው መጥተው ነበር። ብዙዎቹም ልዩ ከሆነውና ብዙውን ጊዜ ግራ ከሚያጋባው እምነታቸውና አስተሳሰባቸው መጥተው ነበር።
ReplyDelete