በዶ/ር ብራድሊ ናሲፍ
ትርጉም በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ
መግለጫ
ጸሐፊው ዶክተር ብራድሊ ናሲፍ የአንጾኪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባል ሲሆኑ በቺካጎ ኖርዝ ፓርክ ዩንቨርስቲ የነገረ መለኮት ፕሮፌሰር ናቸው። ጽሑፋቸው በዚህ ዘመን በኦርቶዶክሱ አለም ለሚታየው ከፍተኛ ቀውስ ቆም ብለን የምናስብበት ታላቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። እዚህ ላይ የተረጎምነውም ለኛዋ ቤተ ክርስቲያንም ታላቅ ትምህርት ይሰጣል ብለን በማሰብ ነው። መልካም ንባብ።
የዚህ አጭርና ያልተሟላ አስተያየት ዓላማ፥ በኦርቶዶክሳዊ ሊቀ ጳጳስ የወንጌል አገልግሎት ማዕከላዊነት ላይ ትኩረት ለመስጠት ነው። ይህ ጽሑፍ በጊዜያችን በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያለውን ችግር አንዱን ወገን ወግኖ ለማየት አይደለም። ዓለማው ሊቀ ጳጳሱ የተጠራለትን ሕይወት ለማሳየት ነው። በየትኛውም ሥፍራ ይሁን በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ፥ የሊቀ ጳጳሱ ተቀዳሚ ሥራ ሊሆን የሚገባውን ለማሳየት በአዎንታዊነት የቀረበ አስተያየት ነው። በእኛ መካከል ሊቀ ጳጳሱ በሚሰጠው አገልግሎት ውስጥ የክርስቶስ ወንጌል ማዕከላዊ እንደሆነ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።
በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሊቀ ጳጳሱ ሐዋርያዊ ተልዕኮ በአምስት ነጥቦች ሊጠቃለል ይችላል።
- ወንጌልን መስበክ።
ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት የክርስቶስን ወንጌል ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም ማወጅና መተርጐም አለባቸው። ጳጳሳት ሊመረጡ የሚገባቸው በይበልጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማወቃቸውና ለሌላው ለማስረዳት ባላቸው ችሎታ መሆን አለበት። ለእንዲህ ዓይነቱ ጳጳስ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችለው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው። ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ወንጌልን በታማኝነት ሊከተሉና የአገልግሎታቸው ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል።
ይህ ከሆነ ወንጌል ምንድነው? ወንጌል እግዚአብሔር ሰው የሆነበት፥ ወደ እግዚአብሔር ኅብረት ይመልሰው ዘንድ የወደቀውን የሰውን ልጅን ሰብእና ገንዘብ ያደረገበት፥ ኃጢአትን ድል ያደረገበትና ሞትን ያጠፋበት « መልካም ዜና» ነው። ይህን ያደረገው በክርስቶስ ሕይወት፥ ሞት፥ ትንሣኤና ወደሰማይ ማረግ ነው። ይህ መልካም ዜና በማናቸውም የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ሰጪ አገልግሎቶች ማለትም በምሥጢራት፥ በአምልኮትዋ፥ በጾምና በጸሎት ውስጥ መሠረት ሊሆን ይገባል።
ጳጳሳት ይህን መልካም ዜና ማለትም የክርስቶስን ሕይወት ሞትና ትንሣኤ ለቀሳውስቶቻቸውና ለምእመኖቻቸው ሊሰብኩ ይገባል። ሰዎችንም ወደንስሐና ወደእምነት ሊጠሩ ይገባል። ሰዎች በቤተ ክርስቲያን አጸድ ስለተገኙ ብቻ ክርስቲያኖች እንደሆኑ አድርገው መገመት የለባቸውም።
ላለፉት አራት አሠርት አመታት ስናገር ኖሬአለሁ። አሁንም እስከ ዕለተ ሞቴ እናገራለሁ። በኦርቶዶክሱ ዓለም ላይ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ዋና ነገር ቢኖር፥ በልማድ ብቻ ያሉ ዓለማውያን ኦርቶዶክሳውያን በክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖራቸው የማስተማርና የመስበክ ውስጣዊ ተልዕኮ እንዲኖረን ነው። ጳጳሳት በመጀመሪያ የወንጌል አስተማሪዎች፥ ሰባኪዎችና ወንጌላውያን ሊሆኑ ይገባቸዋል። የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ተግባራቸውም ይህ ነው።
እኛ ምእመናንም ከአስተዳደራዊና ከዕለት ተዕለት የሥራ አስኪያጅነት ተግባር በተወሰነ ደረጃ ነጻ ልናደርጋቸው ይገባል። እርግጥ ነው፥ አስተዳደራዊ ሥራዎችን ሊመሩ ይገባል። ነገር ግን እነዚህ አስተዳደራዊ ተግባራት ከወንጌል አገልግሎት ይልቅ ብዙ ትኩረትን ሲወስዱ፥ ምዕመናን በጳጳሳቶቻቸው ላይ ታላቅ ኃጢአት እያደረጉ ነው። ከሌሎች ተግባራት ነጻ በማድረግና በማስተማር፥ በመስበክና ሌሎችን በእግዚአብሔር ቃል በማገልገል፥ በሐዋርያዊ ተግባራቸው ላይ እንዲያተኩሩ ጳጳሳቱን መደገፍ የእኛ ኃላፊነትና ተግባር ነው።
2. ምሥጢራትን መፈጸም።
ጳጳሳት የቁርባን ምስጋናና በበላይነት መምራት፥ በየአጥቢያዎቹ የምስጢራት ንጽሕና የተበቀ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው። ቅዱስ ቍርባን በወንጌል ላይ የተመሠረተ ነው። « ይህን ኅብስት በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።>> (1 ቆሮ 11፥26) የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት፥ ትንሣኤና ዳግም መምጣት የዚህ ምሥጢር ውስጥ ዋነኛ ማዕከል ነው። ጳጳሱም ሊሰብከውና ሊያከናውነው የተጠራውም ይኸንኑ ነው። ጳጳሱ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አብዝቶ የሰጠውን የፍቅሩን መልካም ዜና ለመናገር የአዋጅ ነጋሪ ነው። ሕይወትየሚሰጠው እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢር፥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያመላክተውም ይህንኑ መልካም ዜና ነው። ለመንጋዎቹ ይህን የወንጌል ምሥጢር በታማኝነት መግለጥና የሕይወታቸው ማዕከል እንዲሆን ማድረግ የሊቀ ጳጳሱ ተግባር ነው። ወንጌሉን አለመግለጥና የሕይወት ማዕከል እንዲሆን አለማድረግ ዛሬ ብዙዎች ወጣቶችን በስም ክርስቲያን እንዲሆኑና ነገር ግን በሕይወት እንዲጠፉ አድርጎአቸዋል። ስለእግዚአብሔር ያውቃሉ። ምንም እንኳ ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ቢመላለሱም፥ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን እምነት፥ የሕይወታቸው እምነት እንዲያደርጉት ተጠይቀው አያውቁም። ጳጳሳት ( እንዲሁም ካህናትና ምእመናን ሁላችንም የወንጌልን አገልግሎት ልናከናውን ይገባል።
3. እምነትን፥ አንድነትን እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ
በአሁኑ ዘመን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ ኃላፊነትን መውሰድና ቆራጥነትን ይጠይቃል። የወንጌል ጠበቃ መሆን ማለት በቀላሉ « ትውፊትን ማጠብቅ» ማለት አይደለም። የወንጌል ጠበቃ መሆን ማለት ቤተ ክርስቲያንን ከመንፈሳዊ ድንቁርናና እርጅና መጠበቅም ነው። በዚህ ሰሞን በሌላ ሀገር የሚኖር አንድ ኦርቶዶክሳዊ ወንድሜ የኤፌሶን መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይገኛል ወይ ብሎ ጠየቀኝ። እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ በመጠየቄ በጣም አዘንኩ። ይህ ሰው ሊያደርገው የሚገባው ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስን መክፈትና ማውጫውን መመልከት ነበር። በኦርቶዶክሱ ዓለም ብዙዎች ያሉበት ደረጃ ያ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ « በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ክፋቶች ሁሉ ምንጭ ቅዱስ መጽሐፍን አለማወቅ ነው» ብሎ የተናገረው አለምክንያት አይደለም።
4. ለሥነ ምግባር ፥ ለቅድስናና ለሁለንተናዊነት ምሳሌ መሆን
ይህ የሚያመለክተው ጳጳስም፥ ቄስም ይሁን ምእመን ከአንድ በአብ፥ በወልድ፥ በመንፈስ ቅዱስ ከተጠመቀ ክርስቲያን የሚጠበቀውን የሕይወት አካሄድና መንፈሳዊነት ነው።
5. በጳጳሳትና በመንጋዎቹ መካከል ያለውን ክፍተት ማጥበብ
ዓለማዊው የቁስጥንጥንያ ቤተመንግሥት መንፈስ በጵጵስና አገልግሎት ውስጥ እየሾለከ ገብቶአል። ቁስጥንጥንያ በኦቶማን ቱርክ ሥር ከወደቀች በኋላ (1453 ዓ. ም) የቁስጥንጥንያ ጳጳሳት፥ የመንጋዎቻችን የፖለቲካና የመንፈሳዊ ሕይወት መሪዎች ነን ሲሉ የወደቁትን ነገሥታት አክሊሎች ማድረግ ጀመሩ። « ክቡር» « ርእስ» የሚል የማዕረግ ስሞችን መጠቀም ጀመሩ። የካቴድራሉ ሊቀ ጳጳስ ሹመትም « በመንበር (በዙፋን) መቀመጥ» ተደርጎ መገለጥ ጀመረ። ይህ ሁሉ ከቢዘንታይን ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው።
ዛሬ ግን ራሳችንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያገኘነው ነው። በአንድ በኩል ጳጳሳቶቻችንን ማክበር እንፈልጋለን። በሌላ በኩል ደግሞ ዓለማዊና ፖለቲካው ሕይወት አንፈልግም። ጌታ ኢየሱስ በዚህ ዘመን ቢኖር ስለዚህ ልምምዳችን ምን ይል ይሆን? « የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን» ምናልባት ጳጳሳቶቻችንን በተሻለ መንገድ የምናከብርበት ክርስቲያናዊ መንገድ ይኖር ይሆን?
እውነተኛ የጵጵስና አገልግሎት ጥሪ ወንጌልን መግለጥና በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ማዕከላዊ አድርጎ መጠበቅ ነው። ይህ ከሆነ እንግዲያውስ ክርስቲያናዊ አመራር ስላለው የአገልጋይነት ባህርይ ምእመናን በተሳሳተ መንገድ እንዲረዱ ያደረጉ፥ ከጵጵስና አገልግሎቶች ጋር የተለጠፉ በየዘመናቱ የተከማቹ ሥልጣኖችን እንደገና ልንመረምር ይገባል።
እነዚህ ከላይ የዘረዘርኋቸው አምስት ነጥቦች ያልተሟሉ ቢሆኑም እዚህ ያቀረብኳቸው አይናችንን ዋና ከሆነው ነገር ላይ እንዳናነሳ ነው። ዋናውም ነገር በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያለው የክርስቶስ ወንጌል መልካም ዜና ነው። ግቡ ወንጌል ከሆነ ወንጌልን ግልጥና ማዕከላዊ ማድረግ የኦርቶዶክሳዊ ጳጳስ ሐዋርያዊ ተልእኮ ነው ማለት ነው።
ከተርጓሚው
ዶር ናሲፍ ባስቀመጡት ነጥብ ላይ በመንተራስ አሁን ቤተ ክርስቲያናችን ካለችበት አደጋ ልትወጣ የምትችልበትን ነጥቦች በሚቀጥሉት ቀናት እናብራራለን።
Can you post the link for the original article? Some folks may want to read the original english version...
ReplyDeleteቀስስ ቃለ ሄወት ያሰማልን።
ReplyDeleteቀሲስ ጽሑፍዎን ኢንተርኔት የሚጠቀም ብቻ ባያነበው ምን ይመስልዎታል ስለዚህ በመጽሔቶች ላይ በፍጥነት የሚወጣበት መንገድ ቢፈለግ መልካም አይመስልዎትምን?
ReplyDeleteኒቆዲሞስ