Tuesday, June 25, 2013

ማንዴላና ኢትዮጵያ

በዚህ ሰሞን በመላው ዓለም ዜና የሆነው የፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ ( ማዲባ) በጠና መታመም ነው። የ95 ዓመት እድሜ ባለጸጋ አባት እንደመሆናቸው ብዙ የሚያስደንቅ ባይሆንም ለአፍሪካ ግን ታላቅ አባት የማጣት ነገር ስለሆነ ለአፍሪካ ወደ እግዚአብሔር ልንጸልይ ሌላ ማንዴላን እንዲያስነሳ ልንለምነው ይገባል። በዚሁ ግን የማንዴላ ነገር ከተነሣ አገራችን የነበራትን የቀደመ ክብርና ለአፍሪካ ነጻነት ያደረገችውን ውለታም ትውልድ ሊረሳው አይገባም። የሰሞኑ የአፍሪካ አንድነት የሃምሳ ዓመት መታሰቢያ ያን በመጠኑም ቢሆን የዘነጋ ስለመሰለኝ ነው።

ባለፈው ዓመት ደቡብ አፍሪካ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያናችን ባደረገችልኝ ጥሪ ለአገልግሎት ወደ ጆሃንስበርግ ባደረግኹት ጉዞ፥ በዚያ ያሉት አባቶች ካስጎበኙኝ ቦታዎች አንዱ የአፓርታይድ ሙዚየም አንዱ ነበር። በዚያ በክብር ከተቀመጡት ሰነዶች አንዱ ፕሬዚደንት ማንዴላ ገና የኤኤንሲ የትጥቅ ትግልን ሲመሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጣቸው ፓስፖርት ነበር። ኢትዮጵያዊው ስማቸው ዳዊት ሲሆን ጋዜጠኛ እንደሆኑ የሚጠቅስ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለታጋዩ ጀግና ሽጉጥ ሸልመዋቸው ነበር።


ታዲያ ማንዴላ፥ በእሥር ቤት ለረጅም ጊዜ ማቅቀው ከወጡ በኋላ እንኳ ይህን የኢትዮጵያን ውለታ አልረሱም ነበር። ብዙዎች እንደሚናገሩት ማንዴላ የኢትዮጵያ የነጻነት ታሪክ የራዕያቸው መሠረት ነበር። 
ለዚህም ነው ስለኢትዮጵያ ሲናገሩ «Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly  than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis. >» ብለው የተናገሩት። 
በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት የማያንቀላፋው ትጉሕ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር  ከታላቁ አፍሪካዊ አባት ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ይሁን። 

No comments:

Post a Comment