Tuesday, June 4, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት አራተኛ ክፍል

 Read in PDF
ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም። 
ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።

  

መግቢያ 

በነገረ መለኮት ትንታኔው የሚታወቅ አንድ ሊቅ ሲናገር የሃይማኖት ስህተቶች ሁሉ የሚጀምሩት የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ባለመረዳት ነው ብሎአል። በመሆኑም የጸሎተ ሃይማኖት መሰጠትንም ሆነ ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ ያለውን ጊዜ ተከትለው የተደረጉትን ጉባኤያት ብንመለከት በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚሰነዘሩት የስህተት ትምህርቶችን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ልንገልጣቸው ቶማስ አኵናስ የተባለው ሊቅ ይነግረናል። 

• ክርስቶስ ሰው ብቻ ነው የሚሉ፤ 
ለምሳሌ ፎጢኖስ የተባለው « ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፤ ነገር ግን መልካም ሰው ነው። በመልካም አነዋወሩና ሕይወቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማድረጉ በማደጎ (adoption) የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ተጠርቶአል» በማለት አስተምሮአል። ያ ብቻ አይደለም የክርስቶስ ሕልውና የሚጀምረው ከማርያም ከተወለደ በኋላ ነው በማለት ክርስቶስ በጊዜ የተወሰነ እንደሆነ አስተምሮአል። የእግዚአብሔር ቃል ግን እነዚህ አስተሳሰቦች ሐሰት እንደሆኑ በግልጥ ይመሰክራሉ። ዮሐንስ በወንጌሉ « እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለው አንድ ልጁ እርሱ ተረከው» በማለት ወልድ በቅድምና ከአብ ጋር እንደነበር ይናገራል። ዮሐንስ 1፥18፤ ኢየሱስም ራሱ « አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ» ብሎ ሲናገር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከመወለዱ በፊት ከአብርሃም በፊት መኖሩን ነግሮናል። ዮሐንስ 8፥58። 

• ክርስቶስ ራሱ አብ ነው የሚሉ፤ 
በዚህ ስህተቱ የታወቀው ሰባልዮስ የተባለው ሰው ነው። ሰባልዮስ ጌታ ቅድመ ዓለም መኖሩን ያምንና ነገር ግን በሥጋ የተገለጠው ቅድመ ዓለም የነበረው አብ ነው ብሎ ያስተምር ነበር። በእርሱ ትምህርት አብና ወልድ ሁለት አካላት ሳይሆኑ አንዱ አብ ነው በተለያየ መንገድ የተገለጠው። አሁንም የሰባልዮስን ስሕተት የእግዚእብሔር ቃል በግልጥ ይቃወመዋል። ጌታ ራሱ « የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁም» በማለት ከአባቱ እንደተላከ» በዮሐንስ 8፥16 ላይ ገልጦአል። 

• ልዩ ፍጡር ነው የሚሉ፤ 
አርዮስ የተባለው የስሕተት አስተማሪ ስለጌታ ያስተማረው ትምህርት ከቅዱሳት ጋር የሚቃረን ነበር፤ አንደኛ ክርስቶስ ፍጡር ነው። ሁለተኛ፥ ከዘለዓለም ያልነበረና ከሌሎች ፍጡራን ልዩ አድርጎ እግዚአብሔር የፈጠረው ነው ። ሦስተኛ፥ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ ስላይደለ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም እውነተኛ አምላክ አይደለም በማለት ያስተምር ነበር። አሁንም የአርዮስን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ሲሽርበት ጌታ « እኔና አብ አንድ ነን» በማለት በባሕርይ ከአባቱ ጋር አንድ መሆኑ ሲገልጥ እናያለን።  

እነዚህ ከላይ ያያናቸው በየዘመኑ ከተነሡት ለናሙና ያነሣናቸው ስህተቶች ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በክርስቶስ ላይ ለሚሰነዘሩት ስህተቶች መሠረቶች ናቸው። « የኑፋቄ አዲስ የለውም» የሚባለው ለዚህ ነው። ሆኖም ቶማስ አኵኖስ ይህ ሁሉ በየጊዜው የሚነሣው ስህተት  ወንጌላዊው ዮሐንስ  በወንጌሉ መክፈቻ ላይ ያስቀመጣቸው ዐረፍተ ነገሮች « በመጀመሪያ ቃል ነበር» የፎጢኖስን « ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» የሰባልዮስን፥ « ቃልም እግዚአብሔር ነበረ» የአርዮስን ስህተት ይደመስሰዋል ብሎአል ።   

ኢየሱስ ማንነው? 

በጊዜው  በሥጋ ያዩት የሃይማኖት መሪዎች፥  የሕዝብ አስተዳዳሪዎች፥ ደቀ መዛሙርቱ እና ሌላውም ሕዝብ  በአንድነት የጠየቁትን ጥያቄ እርሱ ማንነው? የሚል ነው። እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው በማለትና  በመጠየቅ ስለ አዳኛችን ስለመድኃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥልቀት እናጠናለን።

ሽባውን ሰው « ኃጢአትህ ተሰረየችልህ» ሲለው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ያሉት « ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?  ብለው ያስቡ ጀመር።» ሉቃስ 5፥21። እንደገና ኃጢአተኛዋን ሴት « ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል» ሲላት በማዕድ ከርሱ ጋር ተቀምጠው የነበሩት « ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?» ብለው ነበር። ሉቃስ 7፥48-49።  ዮሐንስን ያስገደለው ሄሮድስም  « ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው?  » በማለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማየት አጥብቆ ይሻ እንደነበረ ሉቃስ ይነግረናል? ሉቃስ 9፥9። ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባና ከተማዋ ስትናወጥ ሕዝቡ « ይህ ማነው?» በማለት ነው የጠየቁት። ደቀ መዛሙርቱም በብዙ ቦታ ስለጌታ የበለጠ ለማወቅ ፈልገው በፍርሃት ዝም እንዳሉ እናያለን? ሉቃስ 9፥45።   
በእነዚህ ሁሉ ሰዎች እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከሁን በተነሳውም ትውልድ ይህ ማነው የተባለውን፥  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በኒቅያ የተሰበሰቡ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች የገለጡበትን መንገድ ለመረዳት በወንጌል ላይ ጌታ ስለራሱ የተናገረውን መረዳት ይገባል።

1. እርሱ ራሱ የነቢያት ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ገልጦአል፤

ወዳደገበቱ ወደ ናዝሬት ከተማ በመሄድ ወደ  ምኩራብ ገብቶ ኢሳይያስ 41፥1-2ን ሲያነብብ ስለሆነው ሉቃስ ሲነግረን « የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር።እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር። » ይለናል።  ሉቃስ 4፥18-21። እዚህ ላይ   ቁልፉ ቃል « ዛሬ . . . ተፈጸመ» የሚለው ቃል ነው። ይህም የነቢዩ ትንቢት ፍጻሜ እርሱ መሆኑን የሚያመላክት ነው።  በሌላም ሥፍራ ላይ  ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ማየታቸው የትንቢት ሁሉ ፍጻሜ የዘመናት ምኞት መሆኑን ሲናገር  « የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው።እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም»  በማለት ተናግሮአል። ሉቃስ 10፥23-24። ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎተ ወንጌል ላይም ይህን የነቢያት ምኞት የሆነውን የወንጌልን ቃል ለመስማት እግዚአብሔር ስለአበቃን አምላካችንን ማመስገን እንዳለብን ይህኑ ቃል በመጥቀስ ታሳስበናለች። 

2. በእርሱ እንድናምን አስተምሮአል። 

« በአባቴ እመኑ» ብቻ ሳይሆን « በእኔም እመኑ» በማለት ነበር ተከታዮቹ ተስፋቸው በአባቱና በእርሱ ላይ እንዲሆ ን የጠየቀው። (ዮሐንስ 14፥1።) በእርሱ ማመን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲናገርም « በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ  አይደለም፤ እኔንም የሚያይ የላከኝም ያያል። በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር  እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።» ብሎአል።  ዮሐንስ 12፥44-46። በእርሱ ማመን ወይም አለማመን የሞትና የሕይወት ያህል ልዩነት ያለው ነው። « በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።» ዮሐንስ 3፥15-17። 

3. እኔ . . . ነኝ በማለት አምላክነቱን አሳይቶአል። 

ዮሐንስ በወንጌሉ በጥንቃቄ « እኔ ነኝ» በማለት ጌታ የተናገራቸውን ሰባት ንግግሮች መዝግቦአል።  አምስት ሺ ሰዎችን በመገበ ወቅት « እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ» (ዮሐንስ 6፥35)ለዕውሩ ማየትን በሰጠው ጊዜ « እኔ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ» (ዮሐንስ 8፥12 ) አልአዛርን ሲያስነሣ፥  « ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ» ብሎ ሲናገር።  (ዮሐንስ 11፥25) እንዲሁም በትምህርቱ « እኔ የበጎች በር ነኝ» (ዮሐንስ 10፥7) « እኔ መልካም እረኛ ነኝ»  (ዮሐንስ (10፥10) « እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ።» (ዮሐንስ 14፥6) « እኔ እውነተኛ የወይን ግንድ ነኝ» በማለት አስተምሮአል። እነዚህ ንግግሮች ምንን የሚያመለክቱ ናቸው ብለን ስንጠይቅ  በብሉይ ኪዳን ለሙሴ በምድረ በዳ በቁጥቋጦው መካከል « ያለና የሚኖር እኔ ነኝ» ያለው እርሱ በሥጋ መገለጡን የሚያመላክት ነው ። ዘጸአት 3፥14። 

4. በነቢያት የሰው ልጅና ክርስቶስ የተባለው እርሱ መሆኑን ገለጦአል። 

በትንቢተ ዳንኤል 7፥13 ላይ « የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ. . . ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው። ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።» የተባለለት እርሱ እንደሆነ ሲያመለክት ራሱን የሰው ልጅ (ወልደ እጓለ እመሕያው) እያለ ይጠራ ነበር። በአይሁድ ሸንጎ ፊት ሊቀ ካህናቱ « የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?» ብሎ ሲጠይቀው « እኔ ነኝ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ» በማለት ነበር ለሊቀ ካህናቱ የመለሰለት፤ « ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል ስድቡን ሰማችሁ ምን ይመስላችኋል?» በማለት የንዴት መልሱን ተናግሮአል። (ማርቆስ 14፥61-62)   የቤተ ክርስቲያን አባት በመባል የሚታወቀው አውሳብዮስ  የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፉ መግቢያ ላይ ኢየሱስና ክርስቶስ የሚለው ስም እንዴት ታላቅ የሆነ ስም እንደሆነ በስፋት አትቷል። ጥልቅ ምሥጢር ባለው በዚህ መግለጫው ላይ አውሳብዮስ ክርስቶስ  ስለሚለው ስም ሲናገር ክርስቶስ ማለት የተቀባ ማለት እንደሆነና እግዚአብሔር ለሙሴ በምሳሌና በጥላ ወደፊት ሊገለጡ ያሉትን ነገሮች ሲገልጥለት ታላቁን ሹመት ሊቀ ካህንነቱን ለአሮን ሲሰጥ « በቅብዓት» ስለነበረ» የአሮን ሹመት ክርስቶሳዊ ነበር።  ንግሥናና ትንቢትም እንዲሁ በቅብዓት ይመጡ እንደነበር ገልጦ። እነዚህ ሁሉ በምድራዊ ቅብዓት አማናዊውን የተቀባውን መሲህ (ክርስቶስን) ሊመስሉ ተሰጡ፤ ክርስቶስ ግን በምድራዊ ቅብዓት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ በሥጋ መገለጡን ገልጦአል። 

5. የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አስተምሮአል።
ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ መሆኑን ሲናገር « እኔና አብ አንድ ነን » ከአብ ጋር ከዘላለም የነበረ አምላክ መሆኑን ተናግሮአል። ፊልጶስም « አብን አሳየንና ይበቃናል» ብሎ በተናገረው ወቅት « እኔን ያየ አብን አይቶአል እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? በማለት መልሶለታል። ዮሐንስ 14፥9-10።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አባቱ ከሆነው ከአብ ጋር ያለውን ልዩ የሆነ ግንኙነት ሲገልጥም « ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፥ ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፥ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም አለ። » በማለት ተናግሮአል። ሉቃስ 10፥22 እውር ሆኖ የተወለደውን ያዳነውን ሰው ጌታ እንደገና ሲያገኘው  « አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው።እርሱም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ።ኢየሱስም፦ አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው።እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም።» ይለናል። ዮሐንስ 9፥35-38) የእግዚአብሔር ልጅ የተባለው ነቢያቱ የተነበዩለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከእኛ ደግሞ የሚጠበቀው በእርሱ ማመንና ለአምላክነቱ የሚገባው አምልኮ ነው። 

ቅዱሳት መጻሕፍት የክርስቶስን አምላክነት የመሠከሩት በምን መንገድ ነው? 

1. ለአምላክ ብቻ በሚሰጡ ስሞች ተጠርቶአል። 
« የእግዚአብሔር ልጅ» « ብርሃን» « እውነት መንገድ ሕይወት» ተብሎአል። ማቴዎስ «አማኑኤል»  ዮሐንስ «የእግዚአብሔር ልጅ» ፥ ጳውሎስ «ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ» (1 ቆሮንቶስ 8፥6)፤ የዕብራውያን ፀሐፊ « ሁሉን ወራሽ ያደረገው ደግሞም ዓለማትን የፈጠረበት ልጁ» ዕብራውያን 1፥2፤  ያዕቆብ « የክብር ጌታ»  (ያዕቆብ 2፥1) ዮሐንስ በራዕዩ « የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ»  ብለው ጠርተውታል።  (ራዕይ 19፥16።)  እነዚህ ስያሜዎች ለእግዚአብሔር ብቻ የሚሰጡ ናቸው። ጌታም በእነዚህ ስያሜዎች አልተቀየመም ወይም በዚህ ስያሜ አትጥሩኝ አላለም። 

2. የአምላክ ባሕርይ መገለጫዎች የነበሩት ለእርሱ ተሰጥተው ተነግረዋል። 
በቆላስይስ 1፥15 « ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።» በማለት የሁሉ ፈጣሪና ሁሉም ለእርሱ ክብር እንደተፈጠረ ገልጦልናል። « ትናንትናም ዛሬም ለዘላለም ያው ነው» በማለት ዘላለማዊነቱን ዕብራውያን 13፥8 በሰማይና በምድር ሥልጣን ያለው መሆኑን  ( ማቴዎስ 28፥20) መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሐዋርያትም ከጌታ ዕርገት በኋላ ወደ እርሱ ሲጸልዩ « የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ » በማለት  የሁሉን ልብ የሚያውቅ አምላክ መሆኑን ገልጠዋል። (ሐዋ ሥራ 1፥24) ፍቅሩም ከመታወቅ የሚያልፍ  እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጸለየው ጸሎት አስታውሶአል። (ኤፌሶን 3፥19) 

3. አምላክ ብቻ የሚያደርገውን ሥራ ሠርቶአል። 
ኃጢአትን ይቅር ብሎአል። ( ማርቆስ 2፥1-12። አዲስ ሕይወትን ሰጥቶአል። (ዮሐንስ 5፥21) ራሱም ከሙታን ተነሥቶአል። 

4. እግዚአብሔር ብቻ የሚቀበለውን አምልኮን  ከአብ ጋር በእኩልነት ተቀብሎአል። 
ሥጋውንና እንድንበላ ደሙን እንድንጠጣ ብቻ ሳይሆን በመሰባሰባችን ጊዜ ወቅት የአምልኮአችን ማዕከል እንዲሆንና ሞቱንና ትንሣኤውን እንድናስብ አዝዞናል፥ (1 ቆሮንቶስ 11፥24) የምንጠመቀው በአብ ስም ብቻ ሳይሆን በወልድም በመንፈስ ቅዱስም ነው። (ማቴዎስ 28፥20) የምናከብረው አብን እንደምናከብረው እንደሆነ ሲገልጥም « ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።»  በማለት ጌታ አስተምሮአል። ዮሐንስ 5፥24። በሮሜ 9፥5 እና በ2፥ቆሮንቶስ 13፥13 ላይም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በእግዚአብሔርነቱ ተመስግኖአል። 




2 comments:

  1. ሃይማኖት ስህተቶች ሁሉ የሚጀምሩት የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ባለመረዳት ነው kale hiwot yasemaln

    ReplyDelete