Tuesday, June 25, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (ሰባተኛ ክፍል)

Read with PDF
ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት። ተሰብአ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል።  

ስለእኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ፤ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ፤ 

መግቢያ 
ባለፈው ሳምንት « ስለ እኛ ስለሰዎች» የሚለውን ኃይለ ቃል በመያዝ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ በኃጢአት መውደቁ ያመጣውን ውጤት አይተን ነበር፤ እንደተመለከትነው ኃጢአት ወደ ዓለም በገባበት ወቅት 
• ሰው ከእግዚአብሔር ተለየ 
• ሰው በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ሆነ 
• ሰው በኃጢአት ባርነት ሥር ሆነ 
• ሰው ራሱን ማዳን የማይችል ሆነ ብለን ነበር። በመሆኑም የኒቅያ አባቶች « ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ» በማለት የእግዚአብሔር ልጅን በሥጋ የመገለጥ ዓላማ ግልጥ አድርገውልናል። ማለትም የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ የተገለጠው በኃጢአት የወደቀውን የሰው ዘርን ለማዳን ነው። 

ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት። 
ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ 

ሀ. የአምላክ ልጅ ለምን ሰው ሆነ? 

1. ሰው በራሱ ራሱን ለማዳን ስላልቻለ፤ 
በኃጢአት ለመውደቁ የሰው ልጅ ያዘጋጀው መፍትሔ ቅጠል መልበስና በገነት ዛፎች መካከል መሸሸግ  ነበር። (ዘፍጥረት 3፥8) ቀደም ሲል እንዳየነው የሰው ልጅ ይህን ያደረገው እግዚአብሔር ለእርሱ ጠላት የሆነበት ስለመሰለው ነበር፤ እውነታው ግን በእግዚአብሔር ላይ ጠላት የሆነውና ያመፀው ሰው ራሱ ነበር። ሰው ማንነቱን ያገኘበትን እግዚአብሔርን በጠላትነት መመልከቱ እግዚአብሔርን እንዲጠላ ከማድረጉ በላይ ራሱን እንዲጠላው አደረገው፤ ሐፍረት ከውድቀት በኋላ የመጣ ሲሆን ራስን የመጥላት ምልክት ነው። ራሱን ስለጠላም የእርሱ የሆነውን ሁሉ ጠላ፤ የሕይወቱን አጋር « ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት» በማለት ከሰሳት፤ የገዛ ልጆቹ አንዳቸው አንዳቸው ስለጠሉ ተጋደሉ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ጠላት የሆነ፥ ከማንም ጋር እርቅ ሊኖረው ወይም እውነተኛ ፍቅርን ሊያገኝ አይችልም፤ በመሆኑም ሰው ለራሱ መፍትሔ ያደረገው ራሱን የሚከላከልበት ነገር ሁሉ መጥፊያው ሆነ፤ ኢሳይያስ በትንቢቱ እንደነገረን ሰውን የሚያድን « ሰው እንደሌለ» ስላወቀ አምላክ ራሱ ክንዱና ቀኝ እጁ የሆነውን ልጁን ለእኛ መድኃኒት እንዲሆን ላከው። (ኢሳይያስ 59፥ 16) 

2. የሰዎች (የዕሩቅ ብእሲ) ደም ዓለምን ማዳን ስላልቻለ፤ 
የዕብራውያውን ጸሐፊ የአምላክን ልጅ ሰው መሆን በተናገረበት አንቀጹ ላይ « ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤» ብሎናል። ዕብራውያን 1፥1። ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ መንገድ ተናግሮአል። ነገር ግን ያ በነቢያትና በተለያየ መንገድ የመጣው መልእክት ዓለምን ለማዳን አልቻለም። ወይም በቅዳሴ መጽሐፋችን አባቶቻችን እንዳስቀመጡልን ጌታ በሥጋ የተገለጠው ከአቤል ደም ጀምሮ በእቃ ቤቱ መካከል እስከ ተገደለው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ የፈሰሰው ደም ዓለምን ማዳን ስላልቻለ ነው። ከአቤል ደም ጀምሮ በምድር ላይ የፈሰሰው የሰዎች ደም የሰዎችን ኃጢአት የሚገልጥና የሚከስ ደም ነው። ቃየን ወንድሙን አቤልን ከገደለ በኋላ እግዚአብሔር ቃየን  « የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።» ነበር ያለው። (ዘፍጥረት 4፥10) በመሆኑም የአቤል እና ከእርሱም በኋላ ደማቸው በምድር የፈሰሰ ሁሉ ደማቸው ወደ ሰማይ የሚጮህ ደም ነው። የአምላክ ልጅ ግን በሥጋ የተገለጠው በደሙ መፍሰስ ዓለምን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ነበር። ይህንን እንደገና የዕብራውያን ጸሐፊ ሲናገር « የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።» በማለት ገልጦታል። ዕብራውያን 12፥24። 


3.  ሰዎች እግዚአብሔር በባሪያዎቹ የላከውን መልእክት ማድመጥ ስላልቻሉ
ኃጢአት በሰው ሕይወት ውስጥ ማዕከላዊ ሥፍራ ከያዘ በኋላ፥ ሰው መፍትሔ አድርጎ የያዘው ከእግዚአብሔር መሸሽን እና በእግዚአብሔር ላይ ማመጽን እንደሆነ ተመልክተናል። እግዚአብሔር በብዙ መንገድን ጎዳና ይህን የወደቀውን ሰው ወደ እርሱ ክብር ቢጠራም ሰው ሊመለስ አልቻለም፤ እግዚአብሔር ስለዚህ ሲናገር « ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።» ሮሜ 10፥21፤ በመሆኑም ምንም እንኳ እግዚአብሔር የፍቅርና የሰላም የእርቅ መልእክት ወደ ሕዝቡ በብዙ መንገድ ቢልክም ሰው የእግዚአብሔርን ድምጽ አልሰማም፤ ይህን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ልብ በሚነካ ምሳሌ አስተምሮናል። « የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ።ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት።ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው።በኋላ ግን። ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። ( ማቴዎስ 21፥ 33-37) 

4. ለሰዎች መዳን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ በማስፈለጉ፤ 
ሰው በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት በጽድቅና በቅድስና ያለምንም ኃጢአት በመሆን በእግዚአብሔር ፊት ስለ ሰው ለመቆም የቻለ ማንም አልተገኘም፤ ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳን መካከል ሁለቱን ብንጠቅስ፥ አብርሃም ጻድቅ እንደሆነ በእግዚአብሔር የተመሰከረለት ነው፤ ሆኖም ጽድቁ በሰው ፊት እንጂ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይደለ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር « አብርሃም በሥራው ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም።» ብሎአል። ( ሮሜ 4፥2።) ማለትም አብርሃም በእምነቱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ ያልኖረባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ከታሪኩ እናያለን፤ ሁለተኛው ሰው ሙሴ ነው። ሙሴን የዕብራውያን ጸሐፊ የብሉይ ኪዳን መካከለኛ ይለዋል። ምክንያቱም ብሉይ ኪዳን ለእስራኤላውያን የተሰጠው በሙሴ አማካኝነት ነው። ሆኖም ግን የሙሴ መካከለኛነት ጉድለት ነበረበት፤ አንደኛው የተቀበለውን ተስፋ ሲፈጸም ለማየት አልቻለም ነበር፤ በምድረ በዳ የመራውን ሕዝብ ወደ ተስፋው ምድር ሊያገባው አልቻለም፤ ሁለተኛ ሙሴ በቤቱ አገልጋይ ነበር እንጂ ልጅ አልነበረም። ማለትም የእግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ሊገልጥ የሚችል አልነበረም። 

በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ የሚሆነው ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆን ነበረበት። ቅዱስ ጳውሎስ ለተወደደው ልጁ ለጢሞቴዎስ ስለዚህ ሲናገር « በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።» በማለት ሙሴና አብርሃም ያልቻሉትን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ መሆኑን ገልጦአል። መካከለኛ ማለት ምን ማለት ነው? በመካከል ሆኖ ሁለት ወገኖችን የሚያስታርቅ የሚያቀራርብ ማለት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚመለክና የሚሰገድለት ነው። በሰውነቱ ደግሞ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን የመሰለ ነው። የዕብራውያን መልእክት ግልጥ አድርጎ ሲነግረን እንዲህ ይላል። « እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።» ዕብራውያን 2፥ 14-18። እያለን ያለው መካከለኛው የሰውን ወገን ከሞት ፍርሃት ነጻ ያወጣ፥ የሚሞተውን ሥጋ መልበስ ነበረበት። በቅዳሴ ዲዮስቆሮስ እንደተጠቀሰው « የማይሞት እርሱ ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ። በቅርብ ጊዜ ወደ ያረፉት የእስክንድርያው ፓትርያርክ አንጻራዊ ትምህርተ መለኮት በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ስለ ክርስቶስ መካከለኛነት ሲናገሩ የሚከተሉትን ነጥቦች ተናግረዋል። 

« የክርስቶስ መካከለኛነት የቤዛነት መካከለኛነት ነው። ይህም ማለት መካከለኛነቱ ለኃጢአታችን ሥርየት ሲሆን፥ ዕዳችንን በመክፈል ስለእኛ ቤዛ በመሆን የተከናወነ ነው። በመስቀል ላይ ለአባቱ ያለው « እኔ በደላቸውን ተሸክሜአለሁና መተላለፋቸውን አትቁጠርባቸው» ነው። (ኢሳይያስ 53፥6) በመሆኑ እርሱ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል መካከለኛ ሆኖ ቆሞአል። ወይም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ብቸኛው መካከለኛ እርሱ ነው። የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ፍትሕ ያረካና ስለእነርሱ በመሞት ለሰው ልጆች የኃጢአት ይቅርታን የሰጠ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ « ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥  ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።» በማለት የተናገረው ይህንን ነው። 1 ዮሐንስ 2፥1። በዚህ ምንባብ ውስጥ የቤዛነት ዕርቅ ግልጥ ሆኖ ተገልጦአል። ለኃጢአተኛ የሆነ ቤዛነት ነው።« ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ»  ይህ ኃጢአተኛ ሥርየት ያስፈልገዋል። ይህን ሥርየት ማቅረብ የሚችለው፥ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። . . . ይህ ዓይነቱ መካከለኛነት ጥያቄ የማይቀርብበት መካከለኛነት ነው።» 

ይህ መካከለኛነት በአጭር ቃል፥ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በሆነው አምላክ ብቻ የተከናወነ ነው። ይህ መካከለኛነት በደም የሆነ ነው። ይህ መካከለኛነት ለኃጢአት ሥርየት የሆነ ነው። ይህ መካከለኛነት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አንድ ጊዜ ጊዜ ለዘለዓለም የቀረበ አሜን የሆነ ነው።  

ለ. ከሰማይ ወረደ ስንል ምን ማለታችን ነው? 

1. ከአባቱ መላኩን የሚያመለክት ነው። 
የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ባሕርይ በተመለክትንበት ርእሳችን እንደዳሰስነው፥ እግዚአብሔር በባሕርዩ ምሉዕ ነው። ማለትም በየትም ቦታ በሰማይም ሆነ በምድር በምልአት የሚገኝ አምላክ ነው። በመሆኑም ከሰማይ ወረደ የሚለው ቃል ከአባቱ መላኩን የሚያመለክት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆኑን ነገር በሚናገርበት ጊዜ ሁሉ ለደቀመዛሙርቱ የሚነግራቸው የሥጋዌው ምክንያት ከአባቱ መላኩ ነው። ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ በኃጢአት የወደቀውን የሰው ልጅ እንዲያድን አባቱ ልኮታል። ደቀ መዛሙርቱን ለወንጌል ተልዕኮ ሲልካቸው ያላቸው « አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ» ነበር። ዮሐ20፥21። 

2. ባሕርያችንን ገንዘብ ማድረጉን የሚያሳይ ነው። 
ወረደ የሚለው ቃል የእኛን ባሕርይ ገንዘብ ማድረጉን የሚያመለክት ነው።በሁሉ ምሉዕ የሆነ ጌታ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ፍፁም ሰው መሆኑን የሚያመለክት ነው። 

3. ከሰማይ ወረደ የሚለው ቃል ራሱን ባዶ ማድረጉን ትሕትናውን የሚያመለክት ነው። ይህ ማለት ከጽንሰቱ ጀምሮ፥በምድር መመላለሱ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል መውረዱ ድረስ ያለውን ነው። በአምላክነቱ ሁሉን ማድረግ ሲችል ራሱን ባዶ አድርጎ በማኅፀን ተወሰነ፥ በየጥቂቱ አደገ፤ ተራበ፥ተጠማ፥ ተሰደበ፥ ተገፋ፥ ታሠረ፥ ተመታ፥ ተሰቀለ፥ ሞተ፥ ወደ ሲኦል ወረደ። ይህ ርደት ወይም ( መውረድ) ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲናገር « እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።» ፊልጵስዩስ 2፥6-8

ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ፤

1. ሰው የመሆኑ ምሥጢር የሥላሴ ሥራ ነው። 
ወልድ በተለየ አካሉ የሰውን ባሕርይ ገንዘቡ ያደረገው፥ በፍቅሩ ታላቅ በሆነው በአባቱ ተልኮ፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። የእግዚአብሔር መልአክ ለቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገራት፥ « መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።» ነበር ያላት። ሉቃስ 1፥35። 

2. በነገር ሁሉ እንደ እኛ ሆነ፤
ከፍጥረት በፊት በቅድምና የነበረ፥ አሁን ከአንዲት ታናሽ ብላቴና ተወለደ፤ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረው፥ የፈጠረውን ሥጋ ለበሰ፤ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት፥ በሰማይና በምድር የመላ እርሱ በማኅፀን ተወሰነ። ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚሰገድለትና የሚመለክ ሐረገ ትውልድ ተቆጠረ።  « በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው» ዕብራውያን 2፥12። 

3. ቃል ሥጋ ሆነ፤ 
« ቃል ሥጋ ሆነ» ዮሐንስ 1፥14። ቃል የተባለው የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋን ገንዘቡ አደረገ፤ ሥጋም የቃልን ማለትም የአምላክነትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ። ሥጋ ሆነ ስንል ራሱን ለውጦ ሥጋ በማድረግ፥ ወይም ሥጋ ይዞ ከሰማይ በመውረድ ሳይሆን የእኛን ሥጋ፥ ነፍስ በመውሰድ ነው። አምላክነቱን ሳይለውጥ ከሰማይ ወረድ፤ በቅዳሴያችን አባቶቻችን እንዳስተማሩን « ከአባቱ ዘንድ ሳይለይ መጣ።» 

4. ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ፤ 
ይህ አስደናቂ የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢር የተከናወነው በቅድስት ድንግል ማርያም ነው። የሰው የመዳን ታሪክ በሚነገርበት ወቅት ሁሉ እግዚአብሔር እኛን ለማዳን የእኛን ባሕርይ ገንዘቡ ለማድረግ የመረጣትን እናት እናያለን። የመዳናችንን ታሪክ ስንናገር « ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል» የተባለላትን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብንዘነጋ፥ አንደኛ የራሳችንን የመዳን ታሪክ እንዘነጋለን። ሁለተኛ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ተቃራኒዎች እንሆናለን። በመሆኑም በሚቀጥለው ክፍል ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም እናያለን። 
No comments:

Post a Comment