Tuesday, June 18, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት ( ስድስተኛ ክፍል)

    READ IN PDF
   ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም። ብርሃን ዘእምብርሃን አምላክ ዘእምአምላክ ዘበአማን። 
  ዘተወልደ ወአኮ ዘተገብረ ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ። ዘቦቱ ኲሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ ዘበሰማይኒ ወዘበምድርኒ። 
    

ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ከአብ ጋር የሚተካከል። ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለእርሱ ግን ምንም የሆነ የለም በሰማይም ሆነ በምድርም ሆነ 

በክፍል አምስት ትምህርታችን የግዕዙን አቀማመጥ ተከትለን   ቤተ ክርስቲያን ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ጌታ እንደተባለና ኢየሱስ እና ክርስቶስ የሚሉት ስሞቹ የሚያመለክቱት ምን እንደሆነ። ዛሬም ከዚያው በመቀጠል ዘለዓለማዊነቱንና ፈጣሪነቱን የሚናገሩትን ቃላት እናብራራለን። 

1. ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን፤ 

አርዮስ ከወደቀበት ስህተት አንዱ የወልድን ዘለዓለማዊነት መካድ ነው። በእርሱ እምነት ተወለደ እና ተፈጠረ የሚሉት አንቀጾች አንድ ስለሆኑ « ወልድ ያልነበረበት ጊዜ አለ።» በማለት ያስተምር ነበር  ። ሆኖም በኒቅያ የተሰበሰቡ አባቶች የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት አድርገው በሥጋ የተገለጠው ወልድ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ጋር እንደነበረ፥ ተቀዳሚ እና ተከታይ የሌለው የአብ ልጅ እንደሆነ አስተምረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ወልድ ከሥጋዌ በፊት ማለት ሰው ከመሆኑ በፊት በቅድምና በዘለዓለም ከአብ ጋር እንደነበረ በግልጥ ያስተምረናል። ዮሐንስ ስለዚህ ሲናገር  « በመጀመሪያ ቃል ነበረ።» ይለናል። ዮሐንስ 1፥1። ይህ ቃል ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር ጋር የነበረ መሆኑንም ሲነግረን « ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» ይለናል። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእመቤታችን ከመወለዱ በፊት ነዋሪ መሆኑን ሲናገር « አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ።» ወይም « አብርሃም ሳይወለድ እኔ ነኝ» በማለት አስተምሮአል። ዮሐንስ 8፥58።  

ስለ ጌታ ኢየሱስ ዘላለማዊነት የነቢያትን ምስክርነትም እናገኛለን። በትንቢተ ኢያሳይያስ ላይ ከቅድስት ድንግል ስለሚወለደው ሕፃን ሲናገር «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።» በማለት በሥጋ የተገለጠው አምላክ « የዘላለም አምላክ» እንደሆነ ገልጦአል።( ኢሳይያስ 9፥6። )  ዳዊትም ስለ ጌታ ዘለዓለማዊነትና፥ በሞት ላይ ድል አድራጊ ስለመሆኑ ስለትንሣኤውና ስለ ዘለዓለማዊ ክህነቱ በተነገረበት በመዝሙረ ዳዊት ላይ « ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ>> በማለት ተናግሮአል። መዝሙር 109፥3። ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ማለት በሌላ አነጋገር ከጊዜያት በፊት የነበረና ጊዜያትን የፈጠረ ማለት ነው። ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንደተናገረው «  የጊዜያት ባለቤት ለጊዜ አይገዛም።»። 


 ይህ ዘላለማዊ አምላክ በቅድምና ከአብ ጋር የነበረ የአብ አንድያ ልጁ ነው። ለአብ እርሱን የሚመስልና የሚተካከል ሌላ ልጅ የለውም፤ አዳም ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ልጅ ቢባልም ይህ በባሕርይ የሆነ ሳይሆን በጸጋ የሆነ ነው። ይህ የአባትና የልጅ ግንኙነት ግን የዘመን መቀዳደምን አላመጣም፤ ወልድ የማያውቀውና ያልነበረበት የአብ ዘመንና ጊዜ የለም። « ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም» ማቴዎስ 11፥27። ይህ የወንጌል እውነት የሚያሳየን አብ በምልዓት ወልድን እንደሚገልጠው ሁሉ ወልድም በምልዓት አብን መግለጥ የሚችል መሆኑን ነው። የቅዳሴ ሕርያቆስን ምሳሌ ለመጠቀም፥ አብርሃም ከይስሐቅ እንደሚቀድም ወይም ይስሐቅ የማያውቀው ወይም ያልኖረበት የአብርሃም ሕይወት እንዳለ አይደለም። በአብና በወልድ እንዲህ ያለ መቀዳደም የለም፤ ለምን በምንልበት ጊዜ ቀደም ሲል ምሥጢረ ሥላሴን ባየንበት ወቅት እንደተመለከትነው ምንም እንኳ በሥላሴ ዘንድ የአካልና የግብር እንዲሁም የስም ሦስትነት ቢኖርም ሦስቱ አካላት አንዳቸው በአንዳቸው ሕልዋን የሆኑበት አንድነት አላቸው፤ ወልድ የአብ ዘላለማዊ ቃሉ ነው። ለዚህም ነው በዮሐንስ 17፥5 ላይ « አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ፤» ያለው። ከአብ ጋር ዓለም ሳይፈጠር ከዘላለም በክብር የኖረ አምላክ ነውና። በዚሁ በጠቀስነው ክፍል ላይ ጌታ ስለደቀ መዛሙርቱ የጸለየው ጸሎት በአብና በእርሱ መካከል ከዘላለም የነበረው አንድነትና ሕብረት በደቀመዛሙርቱ ሕይወት እንዲገለጥ ነው። ዮሐንስ 17፥20-23። 

2. ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል። ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለእርሱ ምንም የሆነ የለም በሰማይም ሆነ በምድርም ሆነ 

ከአብ የተወለደው ዘላለማዊ ቃል፥ አርዮስ እንዳለው « ልዩ ፍጡር» ሳይሆን ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ ነው። በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ ስለሆነ፥ በመለኮቱም ከአብ ጋር እኩል ነው። ይህ እውነት ሐዋርያቱ እንዳስተማሩን የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት የእውነት መሠረታችን ነው። ዮሐንስ በመልእክቱ እንደነገረን « ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።» 1 ዮሐንስ 4፥15። ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ሁሉ የተፈጠረበት ነው። ጳውሎስም « መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እናም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።» በማለት የእግዚአብሔር ልጅ በባሕርዩ ከአብ ጋር በመተካከል ያለ መሆኑን ነግሮናል። 1 ቆሮንቶስ 8፥6። 

የእግዚአብሔር ልጅ በምንልበት ወቅት ወይም ስለአብ(አባት) እና ስለወልድ (ልጅ) የምንናገረው የባሕርይ ልዩነትን አይደለም፤ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንደተናገረው « አብ የባሕርይ ስም አይደለም፤ ነገር ግን አብ ከወልድ ጋር ወልድ ከአብ ጋር ያለው የግንኙነት(የግብር) ስም ነው።» ምክንያቱም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ አንድ ናቸውና።  በመሆኑም ከአብ ተወለደ የሚለው ቃል የአንድ ጊዜ ክስተት ወይም ከጊዜ በኋላ የመጣ አይደለም።  የአርዮስ ስህተት ይህ ነው። በዚህም ምክንያት የባሕርይ ልዩነት ያለ ስለመሰለው ወልድ በባሕርይ ከአባቱ ጋር አንድ አይደለም ለማለት ሞከረ። ሆኖም የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ እንደ አስቀመጠልን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ያ አካላዊ ቃል፥ ያው ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ «ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ ብለን እንመሰክራለን። 

ከላይ እንደተናገርነው፥ አዳም የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎአል። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸው የልዑል ልጆች ተብለዋል፥ እኛም በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለናል። « አንድያ» የሚለው ቃል በቅዱስ ቃሉ መጻፉም ይህን የእኛን ልጅነት በባሕርዩ የአብ ልጅ የሆነውን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ልጅነት ከእኛ ልጅነት ለመለየት ነው። እንዳልነው የእኛ ልጅነት በጸጋ የሆነ ነው። በሥጋ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ልጅ ከመቀበላችን የተነሣ ያገኘነው ክብር ነው። « ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤» ዮሐንስ 1፥12። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም የላከው የልጅነትን ሥልጣን እንድናገኝ ነው። ገላትያ 4፥5፤ የወልድ ዋና ተልእኮ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደነገረን የሰውን ዘር ከአብ ጋር ወደ እርቅ ግንኙነት ማምጣት ነው። ወደ ልጁ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የተጠራነውም ለዚህ ዓላማ ነው። 1 ቆሮንቶስ 1፥9፤ ወደዚህ ሕብረት የምንገባውም በእምነትና በፍቅር ነው። 1 ዮሐንስ 1፥3፤ ወደዚህ ሕብረት ከመግባታችን የተነሣ እግዚአብሔር አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ልኮልናል። « ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።» ገላትያ 4፥6። 

ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት።
ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለ መዳናችን ከሰማይ ወረደ 

1. ስለ እኛ ስለሰዎች ስለመዳናችን 
ቀደም ሲል እግዚአብሔር የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረ አምላክ መሆኑን የጸሎተ ሃይማኖት ትምህርታችን ሦስተኛ ክፍል ላይ፥ ስለ ሰው አራት ዋና ዋና ነጥቦችን አይተን ነበር ። እነዚህም አንደኛ ሰው የሚታየውና የማይታየውን ዓለም ጠቅልሎ  የያዘ ነው። ሁለተኛ ሰው በፍጥረትና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ ነው። ሦስተኛ ሰው እኔ ነኝ ባይ አካል ነው።  አራተኛ ሰው በእግዚአብሔር ዓርአያ እና አምሳል የተፈጠረ ነው ብለናል። በተለይ አራተኛውን ጽንሰ ሐሳብ ስንዘረዝርም በእግዚአብሔር አርአያ እና አምሳል የተፈጠርን በመሆናችን ከእግዚአብሔር ልዩ ፍቅር የተቀበልን መሆኑን፥ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ዋጋ ያለን መሆኑንን እና ልዩ ኃላፊነት ያለብን መህኑን ተመልክተናል። 

ሆኖም በዚህ የጸሎተ ሃይማኖት ክፍል እንደምንረዳው ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ልዩ ጸጋ በሚገባ አልተረዳውም። እግዚአብሔር ያሰበለትን ወይም እግዚአብሔር ያቀደለትን በማስተዋል ለመጓዝ አልቻለም። ይህ የሆነው ሰው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመጣስ በኃጢአት በወደቀ ወቅት ነው። የሰውን ውድቀት ለመረዳት የኃጢአትን ምንነት እና በእኛ ሕይወት ያመጣውን ተፅዕኖ መረዳት አለብን። 

ኃጢአት ማለት ምን ማለት ነው? 
ኃጢአት የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የሚያመለክተው « አቅጣጫ መሳት» ወይም « ጉድለት» ነው። የመጀመሪያው ከእግዚአብሔር መንገድ እንዴት እንደወጣን የሚያመለክት ሲህን ሁለተኛው የእግዚአብሔር ክብር እንዴት እንደጎደለን የሚያመለክት ነው። በኢሳይያስ 55፥8 ላይ የሚገኘው እውነት የሚያሳየን በኃጢአት መጓዝ እንዴት አቅጣጫ እንደሚያስት ነው። « ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር፦
ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።»  እነዚህ ሁለቱ ጉዳቶች በግላዊና በማኅበራዊ ሕይወታችን ላይ ታይተዋል። 

ኃጢአት አፍአዊ ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ እንደሆነ የሰውን ልብንም እንዴት እንደሚመርዝ ያየነው ወዲያው የሰው ልጅ እንደወደቀ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ዘፍጥረት 6፥ 5 ላይ ሲናገር « እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።» ይለናል። የሰው የልቡ አሳብ ክፉ እስኪሆን ድረስ ነው ኃጢአት ሰውን የለወጠው። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ላይም እንደምናየው ኃጢአት የሰው የእኔነቱ ማዕከል የሆነውን ልቡን እንዴት እንደመረዘው በማርቆስ 7፥14-23 እና በማቴዎስ 12፥33-37 እናያለን። ይህ ከልብ የጀመረው ነገር የሰውን ሁለንተና ሁሉ ሲበክለው እናያለን። ሮሜ 7፥18፤ ኤፌሶን 2፥3 ፤ ኤርምያስ 17፥9፥ 


ኃጢአት በሰው ሕይወት ውስጥ የሚያመጣውን ጉዳት በዝርዝር በመተንተን የሚታወቀው ቅዱስ ጳውሎስ የኃጢአትን በሰው ሕይወት የሚያመጣውን ተጽእኖ እንደሚከተለው ገልጦታል። አንደኛ ኃጢአት ልብን እንዳያስተውል በማድረግ ያጨልመዋል። ስለዚህ ነገር የሮሜ መልእክት ሲናገር « ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ፤ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፤» ይላል። 1 ቆሮንቶስ 1፥21።  
ሁለተኛው ኃጢአት አእምሮን እንዲበረዝ ወይም እንዲጠፋ ያደርገዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለንተናው በኃጢአት የተያዘና ለእግዚአብሔር ቃል ስፍራ የሌለው ሰው የሚኖረውን ሕይወት ለጢሞቴዎስ ሲገልጥለት «በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ።» ይላል። 1፥ጢሞቴዎስ 6፥5። 
ሦስተኛው በኃጢአት የተመረዘ ልብ ችግር መንፈሳዊ እውነትን ለመረዳት አይችልም፤ 1 ቆሮንቶስ 2፥14 እንዲህ ይላል፤ « ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም።» 
አራተኛው የኃጢአት ውጤት ስሜትን ለተለያዩ ኃጢአቶች ባሪያ ማድረጉ ነው። « እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን።» ቲቶ 3፥3። በተለይ ስለዚህ አስከፊ ሁኔታ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር « ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው።» ብሎአል። ዮሐንስ 8፥34። 

ይህ ሁሉ በግል ሕይወታችን በኩል ያለ ነው። በሌላ በኩል ኃጢአት እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ ሲፈጥረን የሰጠንን ኃላፊነት አለመወጣትም ነው። በሌላ መልኩ ኃጢአት ማለት እኛነታችንን አለመሆን ነው። የተፈጠርንበት የእግዚአብሔርን ባሕርይ አለማንጸባረቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት አለማድረግ ኃጢአት ነው። 

ኃጢአት እንዴት መጣ? 
ለዚህ ጥያቄ ቅዱስ ጳውሎስ መልስ ሲመልስ «ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት» ይለናል ሮሜ 5፥12በዚህ ምክንያት « ሁሉ በአዳም ይሞታሉ» 1 ቆሮንቶስ 15፥22።  ነገር ግን የአዳም ኃጢአት እንዴት የእኛ ሆነ? ወይም የአዳም ኃጢአት እንዴት ወደዘሮቹ ወረደ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በማስተዋል የነገረ መለኮት ሊቃውንት የተለያዩ አሳቦች አቅርበዋል። አንደኛው አዳም የእኛ ተወካይ ስለሆነ ነው። የሚል ነው። አዳም የአምላኩን ትእዛዝ ቢከተል ኖሮ በዘላለም ሕይወት ይኖር ነበር፤ እኛም ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንኖር ነበር። ነገር ግን ባለመታዘዙ ምክንያት ሞትን ተቀበለ እኛም በእርሱ ሥር ያለን እንደመሆናችን ከእርሱ ጋር ሞትን ተቀበልን። 
ሁለተኛው አዳም የሰው ዘር ሁሉ መገኛ ስለሆነ ነው የሚል ነው። ማለትም እርሱ በሚበድልበት ወቅት እኛም በእርሱ ዘር ውስጥ የታቀፍን እንደመሆናችን መጠን በእርሱ ውስጥ ነበርን። ይህ ባዕድ የሆነ አሳብ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናገኘው አሳብ ነው። ለምሳሌ በዕብራውያን 7፥4-10 አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ አስራት ሲያወጣ ሌዊ በአብርሃም ወገብ ስለነበረ አስራት የሚቀበለው የሌዊ ዘር ለመልከ ጼዴቅ አስራት እንዳወጣ ይናገራል። በመሆኑም አዳም በሚበድልበት ወቅት በአዳም ወገብ ስለነበርን የአዳም መተላለፍ የእኛ መተላለፍ ነው። 
በሌላ በኩል የአዳም ታሪክ የእኛ የየዕለት ታሪካችን ነው። ማለትም አዳም የተባልነው እኛ ነን።  ሙሴ ለእስራኤል፥ ኢያሱም ለመራቸው ሕዝቦች እንዲሁም ሲራክ ለተማሪዎቹ እንደተናገረው በየዕለቱ የሞትና የሕይወት ምርጫ በፊታችን ይቀርብልናል። እንደምናየው አዳም የመረጠውን ምርጫ ዛሬም የሰው ልጆች ሲመርጡ እናያለን። 

ኃጢአት በሰው ግላዊና ማኅበራዊ ሕይወት ያመጣው ጉዳት አስከፊ ውጤት በሥጋም በመንፈሳዊ ሕይወትም አምጥቶአል።

መለየት 
የመጀመሪያው የኃጢአት ውጤት ሰው ከእግዚአብሔር ፍጹም እንዲለይ አድርጎታል። የእግዚአብሔር ልጅ ከዚያም በላይ የእግዚአብሔር ወዳጅ እንዲሆን የተፈጠረው የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ጠላት ሆነ (ሮሜ 5፥10) ከእግዚአብሔር መለየታችን ራሳችንን ለፍርሃት እና ለጭንቀት አሳልፎ ሰጠን፤ እግዚአብሔር ጠላታችን እንደሆነ አድርገን መገመት ስለጀመርን በእግዚአብሔር ላይ የበለጠ ማመጽ ጀመርን (የቃየንን፥ የሰናዖር ግንብን ይመለከቷል።) ከእግዚአብሔር መለየታችን ከሌላውም ሰው እንድንለይ አደረገን። አንዳችን ከአንዳችን ለመብለጥ አንዳችን አንዳችንን ለመግዛት መሽቀዳደም ጀመርን። ከፍጥረት ጋርም በስምምነት እንድንኖር የፈጠረን ቢሆንም ያ አንድነት በኃጢአት ምክንያት ስለፈረሰ ከፍጥረትም ተለየን። ፍጥረትን የእግዚአብሔር የእጁ ሥራዎች አድርገን ከማየት ይልቅ የእኛ መጠቀሚያዎች ስለሆኑ እንደፈለግን መጠቀም ጀመርን። 

ፍርድ
በኃጢአት ሥር በመኖራችን፥ በጻድቁ ፈራጅ ፊት በፍርድ ሥር ሆንን። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ተሸካሚዎች እንድንሆን የተፈጠርን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር « በእግዚአብሔር ጽድቅና ቅድስና የተፈጠረው» ይለናል። ኤፌሶን 4፥24። ሆኖም ይህን የተፈጠርንበትን  ዓላማ በመዘንጋታችን ጥፋተኞች ሆነን በእግዚአብሔር ፊት እንድንቆም አደረገን። እግዚአብሔር ግን በጸጋው ይህን ፍርድ ወዲያው ተግባራዊ አላደረገብንም። 

ባርነት 
ቀደም ሲል እንዳየንው ኃጢአት ሰውን ባሪያ ነበር ያደረገው። ኃጢአት ገዢ ከመሆኑ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ ያልመረጥነውን እንድናደርግ ያስገድደናል። ስለዚህ ጉዳይ ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች ያስተማረው ትምህርት የኃጢአት ባርነትን አስከፊ ገጽታ ያሳየናል (ሮሜ 7፥21_23) 

ችሎታ ማጣት 
ይህ ማለት ኃጢአት ሰው ወደቀደመ ክብሩ በራሱ ችሎታ ለመመለስ እንዳይችል አድርጎታል። የፖለቲካ ተሃድሶ፥ ወሲብ፥ ገንዘብ፥ ቴክኖሎጂ፥ ሰውን ወደቀደመ ክብሩ ሊመልሱት አልቻሉም። 
የሰው ልጅ በኃጢአት መውደቅ ውጤቶች እነዚህ ከሆኑ እግዚአብሔር ያዘጋጀለትን መዳን በሚቀጥሉት ክፍሎች እናያለን።  ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ የወረደው ጌታ የወደቀውን ሰው ችላ አላለውምና።  

No comments:

Post a Comment