Tuesday, June 11, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (አምስተኛ ክፍል



ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ የምትመሰክራቸው እውነቶች 

በኒቅያ የተሰበሰቡት አባቶቻችን በአርዮስ የቀረበላቸውን የስህተት ትምህርት ፊት ለፊት በእግዚአብሔር ቃል ሲቃወሙት በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ተከትላ የምታስተምረውን ትምህርት በሚገባ መግለጥ ነበረባቸው።  በሚቀጥሉት ክፍሎች የምናገኛቸው ሐረጎችና ቃላት አባቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምራቸው እውነቶች ጠቅለል አድርገው የገለጡበት ክፍል ነው። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በመያዝ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ አምላክነቱን አስተምራለች ዋጋም ከፍላበታለች።  

1.  በአንዱ ጌታ እናምናለን።
(ወነአምን በአሐዱ እግዚእ፤) 
መጽሐፍ ቅዱስ በሥጋ የተገለጠውን እግዚአብሔር ወልድን ከሚጠራበት ስሞች አንዱ ጌታ ብሎ ነው። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችም « በአንዱ ጌታ» ብለው ተናግረዋል።   ጌትነቱን የምንናገረው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ነው። « በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። » (1 ቆሮንቶስ 12፥3) በአፋችን ጌትነቱን መናገራችን የደኅንነታችን ምክንያት ነው። « ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና » ሮሜ 10፥9። የአባቶችን ነገረ መለኮት በምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቅ የተመሰገነው ቶማስ ኦዴን እንዳሳሰበን ክርስቶስን በምድር ሲመላለስ ብቻ ጌታ ብንለው ኖሮ ምናልባትም አስተማሪ ወይም አለቃ መሆኑን ማስተዋወቂያ ነው። ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ ጌታ መባሉ በአሁኑ ዓለምም በሚመጣውም የእግዚአብሔር መንግሥት እርሱ ገዢ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሐምሳ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ « እናተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።» በማለት የተናገረው። (ሐዋ ሥራ 2፥6 ) ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በነገረ ጥምቀት ትምህርቱ እንዳለው « እርሱ ጌታ ነው፤ ጌትነቱም ደረጃ በደረጃ ያገኘው ሳይሆን በባሕርዩ ጌታ በመሆኑ ያገኘው ክብር ነው።» 

ጌታ ኢየሱስ ስንል ምን ማለታችን ነው? በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት ጌታ ኢየሱስ የሚለው ቃል ዋጋ የሚያስከፍል ቃል ነበር። ለሮም ግዛት (Roman Empire) በሰዎች ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ጌታ የነበረው ቄሣር ነበር። በመሆኑም ቄሣር ይሰገድለት ይመለክ ነበር።  በብሉይ ኪዳን የሰብአ ሊቃናትን ትርጕም (ሰብትዋጀንት) ከተከተልን ከስድስት ሺ ጊዜ በላይ ያህዌ የሚለውን የእብራይስጥ ቃል « ጌታ» ተብሎ ተተርጉሞአል። ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ ማለት ከቄሣር ተቃራኒ አድርጎ የሚያስቆም « ፓለቲካዊ አቋም» ብቻ ሳይሆን፥ ይህ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ሙሴን የተናገረው « እኔ ነኝ » ያለውና ነቢያቱን የላከው መሆኑን ነው። ይህ « እኔ ነኝ » ማለት አቻ ወይም ተቃራኒ አልባ ብቸኛ አምላክ ማለት ነው።በጥንት አማርኛ የተጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ጸሎተ ሃይማኖት ትርጓሜ ስለዚህ ቃል ሲናገር «በሐንድ ጌታ ምን አሰኛቸው፥ ሌላ ጌታ አለን ያሉ እንደሆን። ጌታስ መኰንንም፥ ካበላ ካጠጣ ጌታ ይልዋል። እርሱ ግን አጋዙን ቀድሞም ከሰው ያላመፃው፥ ኋላም ለሰው ያያሳልፈው፥ በባሕርዩ በጠባይዕ ገዢ በሐንድ አምላክ ነአምናለን አሉ።» ይለናል።  

  1. ኢየሱስ ክርስቶስ  
 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሥጋ የተገለጠው ቃል የተጠራባቸው ብዙ መጠሪያዎች ቢኖሩም በዋናነት የሚታወቁት ሁለቱ ናቸው፤ እነርሱም ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ናቸው።  ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ያላቸውን የነገረ መለኮት አንድምታዎች በሚገባ በመተንተን ከጻፉ ቀደምት ጸሐፊዎች መካከል « የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት» (the father of church history)  ተብሎ የሚታወቀው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ ዋናው ነው። አውሳብዮስ ስለ ጌታ ስሞች ሲያብራራ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነገሮች ይነግረናል። አንደኛው ኢየሱስ እና ክርስቶስ የሚለው ስም ከጥንት ጀምሮ በነቢያት የተነገሩና በመላእክት የተበሠሩ ስሞች ናቸው። ሁለተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አምላክነት የሚያሳዩ ናቸው ሦስተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አዳኝነት የሚያመለክቱ ናቸው።   ለዚህ ዋና ምሳሌ አድርጎ የሚያነሣልን ሙሴን ነው። ሙሴ እስራኤልን በመሪነት ሲያስተዳድር ከእግዚአብሔር በተቀበለው ትእዛዝ መሠረት ከሾማቸው የአገልግሎት ሹመቶች መካከል ዋና የሚባሉት ሁለት እንደሆኑ ይጠቅስልናል፤ እነዚህም ሊቀ ካህናቱን አሮንንና ራሱን ሙሴን የተካውን ኢያሱን የሾመበት ነው። አውሳብዮስ እንደሚለን « « በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ» በማለት እንዳዘዘው ቃል የሰማያዊ ነገሮችን አምሳልና ምልክቶች፥  በመጠቀም ክርስቶስ የሚለውን ስም የተለየ ታላቅነት እና ክብር ያለው ስም እንደሆነ እንዲታወቅ በማድረግ የመጀመሪያው ሙሴ ነው። (ዘፀአት 25፥40)ከሰዎች ሁሉ ከፍ ያለውን  የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህን በገለጠበት ወቅት " ክርስቶስ" ወይም " የተቀባ" ብሎ  ጠርቶታል። በእርሱ እይታ ከሰዎች ሁሉ ክብር ከፍ ባለው በዚህ የሊቀ ካህንነቱ አገልግሎት  ሊቀ ካህኑ የክብርና የከፍታ ምልክት ይሆንለት ዘንድ ክርስቶስ የሚለውን ስም ሰጥቶታል። (ሌዋውያን 4፥5፡16፤ 6፥22) » 
  
ለኢያሱ ሲነግረንም፥ ራሱ « ኢያሱ» የሚለው ስም ኢየሱስ ከሚለው ስም ጋር እንዴት ዓይነት ግንኙነት እንዳለው ሲነግረን ኢያሱ « ወላጆቹ ባወጡለት በሌላ ስም አውሴ በመባል ነበር የሚታወቀው። ሙሴ ግን ከነገሥታት ዘውድ የሚበልጠውን፥ ገንዘብ የማይገዛውን እጅግ ክቡር የሆነውን ስም ሊሰጠው ኢየሱስ (ኢያሱ) ብሎ ጠራው።ከሙሴ በኋላና አምሳላዊው አምልኮ ለሰዎች ሁሉ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ከተፈጸመ በኋላ በእውነተኛው ንጹሕ በሆነው እምነት ላይ በመሪነት የተቀመጠው የነዌ ልጅ ኢያሱም የአዳኛችንን ምሳሌ ተሸክሞ ነበር።  » ይህ የአውሳብዮስ ትንተና መልክአ ኢየሱስን በጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ደራሲ በግልጥ ተቀምጦአል
   « አክሊለ ስምከ እንዘ ይትቄጸል በርእሱ፤ 
   « አኅጉረ ፀር ወረሰ ኢያሱ፤» 
       የስምህን አክሊል በራሱ ላይ አድርጎ 
      የጠላትን ሀገሮች ኢያሱ ወርሶአል።
      
ኢየሱስ የሚለው ስሙ 
      
ይህ የአውሳብዮስም ሆነ የመልክአ ኢየሱስ ደራሲ ትንተና የሚያሳየን ኢየሱስ የሚለው ስም የእግዚአብሔር ሕዝብን ከማዳን ጋር የተገናኘ ስም መሆኑን የሚያመለክት ነው። ምክንያቱም በእብራይስጥ የሹኣ፥ ኢያሱ ወይም ኢየሱስ የሚለው ስም በእብራይስጡ « ያሕዌ መድኃኒት ነው» የሚል ትርጉም አለው።  ማቴዎስ ወንጌሉን በተለይ ለአይሁድ የጻፈ እንደመሆኑ፥ በአይሁድ ዘንድ ተስፋ የተነገረለትን የዚህን ስም ትርጉም በመልአክ እንደተነገረው በጽሑፍ አስፍሮታል። የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ሲነግረው « ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።  » ነበር ያለው። ማቴዎስ 1፥21። አውሳብዮስም ሆነ ከእርሱ በኋላ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የመልአኩ ቃል ያስተዋሉት፤ (ወንጌላዊውም ጭምር ማለት እንችላለን) የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ የነገረው ስም የእግዚአብሔር ስም መሆኑን ነው። እርግጥ ነው፥ በትንቢት፥ በምሳሌና በጥላ ቀድሞ ለተነሡት « አዳኞች» ኢያሱዎች ተሰጥቶአል። (ለምሳሌ ዘካርያስ 3፥1 ላይ የተጠቀሰውን ከምርኮ በኋላ እስራኤልን የመራው ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን ያስታውሷል።) 

ሆኖም ግን እነዚህ « አዳኞች» ያዳኑት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ነው። ያዳኑትም የእግዚአብሔርን ኃይል እና ረድኤት አጋዥ በማድረግ ነው። ይህን የእግዚአብሔር ሕዝብ ያዳኑት ወይም የታደጉት ከምድራዊ ጠላቶቻቸው ስለሆነ ማዳናቸው ውሱን ነው። አማናዊው ኢያሱ አዳኛችን ግን ያዳነው « ሕዝቡን» ነው። የራሱን ሕዝብ ነው። ያዳነውም እግዚአብሔር ተጠቅሞበት ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ መድኃኒት ሆኖ ነው። ሕዝቡን ያዳነውም « ከኃጢአታቸው» ነው። ይህ አነጋገር የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። በመሆኑም እንደበፊቱ እግዚአብሔር በምሳሌና በጥላ ሳይሆን ራሱ   በመካከላችን በማደሩ « አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር » እንደ ሆነና በዚህም የነቢዩ የኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ እንዳገኘ ነበር የእግዚአብሔር መልአክ የገለጠው። ማቴዎስ 1፥23።  ቅዱስ ጴጥሮም በመንፈስ ቅዱስ ተመልቶ ስለዚህ ሲናገር « መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፤» ሐዋ 4፥12። ሉቃስም ልደቱን ለእረኞች ሲያበስር ይህን የአዳኝነቱን ስም ነበር የነገራቸው « ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና»  ሉቃስ 2፥11። 
     ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ማዳኑ የአምላክነቱ መገለጫ ነው። ከዚህ በፊት እንዳየነው፥ በማርቆስ 2፥3-12 ላይ  ሽባውን ሰው በፈወሰው ወቅት በመጀመሪያ ለዚያ ሰውነቱ በሕመም ለተጠቃው ሰው ያለው « ኃጢአትህ ተሠረየለችልህ»  ነበር፤ በዚህ ወቅት በዚያ የነበሩት ጻፎች ያሉት ነገር ቢኖር « ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሠርይ ማን ይችላል?» የሚል ነበር። ጻፎቹ ስለ እግዚአብሔር ያሰቡት አሳብ ትክክል ነበር፤ የተሳሳቱት ነገር ቢኖር የሚያዩት ራሱ በሥጋ የተገለጠውን እግዚአብሔርን መሆኑን አለማወቃቸው ነው። ኃጢአትን ይቅር የሚል አዳኝ ጌታ በሥጋ ተገልጦአልና። 
      
የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ኢየሱስ ለሚለው ስም ታላቅ ክብር ነው የነበራት፤ ለምሳሌ በበዓለ ሃምሳ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ስብከቱን የደመደመው «እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።»  በማለት ነበር ስብከቱን የሰሙ ሦስት ሺ ሰዎች በሰሙት ነገር ልባቸው ተነክቶ « ምን እናድርግ? » ብለው በጠየቁ ወቅት፥ « ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። » ነበር ያላቸው፤ (ሐዋ ሥራ 2፥3-38) ኢየሱስ የሚለው ስም የቤተ ክርስቲያን የስብከትዋና የአምልኮዋ ማዕከል እንደሆነ በዚህ የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስብከትና ምላሽ እናያለን።  

ገና ከመነሻው የአይሁድ ሊቃውንት ለሐዋርያት የነገሩዋቸው « በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ ነው።»( ሐዋ 4፥18) ሐዋርያት ግን ለዚህ አልታዘዙም ነበር።ከዚያ ይልቅ ስለ ስሙ መከራን መቀበልን ነበር የመረጡት። ሉቃስ ስለዚህ ሲነግረን «ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው።  እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤»  ሐዋ ሥራ 5፥40-41። ይህ ኢየሱስ የሚለው ስም የቤተ ክርስቲያን የጸሎትዋ ቁልፍ ቃል ነው። ራሱ ጌታ « ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። » በማለት እንደተናገረው (ዮሐንስ 14፥14) ቤተ ክርስቲያን የጸሎትዋ መደምደሚያ ኢየሱስ የሚለው ስም ነው። « በአሐዱ ወልድከ በአንድ ልጅህ» የሚለው ቃል የቤተ ክርስቲያናችን የተለመደው የጸሎት መደምደሚያ ነው። ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ እየተደበደበ የጠራው ይህን ታላቅ ስም ነበር፤ « ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፤» ( ሐዋ ሥራ  7፥59) ኢየሱስ የሚለው ስም የፈውስ ስም መሆኑን ቤተ ክርስቲያን የተገነዘበችው ገና ከመጀመሪያው ነው። አርባ ዘመን ሽባ ሆኖ የኖረውን ሰው ጴጥሮስ ያለው « ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ » (ሐዋ ሥራ 3፥ 6፤) ኢየሱስ የሚለውን ስም ዲያብሎስ እጅግ አጥብቆ የሚፈራው ስም ነው፤ ሉቃስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለተደረገው አስደናቂ ተአምራት ሲናገር እንዲህ ይለናል፤ « እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች። ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት።ክፉው መንፈስ ግን መልሶ፦ ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው።» ሐዋ 19፥ 11-15። 
         
ክርስቶስ የሚለው ስሙ 
   
ክርስቶስ ወይም መሲህ የሚለው ስም በሰባ ሊቃናቱ የብሉይ ኪዳን ትርጉም (ሰብቱዋጀንት)  ከ45 ጊዜ በላይ ተጠርቶ እናገኛለን። በብሉይ ኪዳኑ ትርጉም ክርስቶስ ወይም መሲህ ማለት ለተለየ አገልግሎት በእግዚአብሔር የተቀባ ወይም የተሾመ ማለት ነው። ቅብዓቱ እግዚአብሔር የመረጠውና  የጠራው ለመሆኑ ምልክት ነው። በመሆኑም በብሉይ ኪዳን ሦስቱ አገልግሎቶች ማለትም ካህንነት፥ ንግሥና እና ትንቢት በቅብዓት ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጥ ነበር። ቀደም ሲል የጠቀስነው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ እንዲሁም ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌምና ከእነርሱም በኋላ የተነሱ አባቶች እንደሚነግሩን እነዚህ ሦስቱ አገልግሎቶች በብሉይ ኪዳን የተሰጠቱ በምሳሌና በጥላ ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ግን ሦስቱም በአንዱ በክርስቶስ በምልዓት ተገኝተዋል። እነዚህ ሦስቱ አገልግሎቶች ለምን አስፈለጉ? ክርስቶስስ እነዚህን አገልግሎቶች እንዴት ፈጸመ?
    
     
በብሉይ ኪዳን ከምንመለከታቸው ዋና አገልግሎቶች አንዱ የትንቢት አገልግሎት ነው። ነቢይ ማለት በሕዝቡ ፊት የእግዚአብሔር አፍ ነው።  እግዚአብሔር ነቢያትን በየጊዜው እያስነሣ መልእክቱን ለሰዎች እንዲናገሩ ሲያደርግ እናያለን። ይህ ዓይነቱ አገልግሎት ለምን አስፈለገ ብለን ስንጠይቅ ኃጢአት በሰዎች ላይ ካመጣቸው ጉዳቶች አንዱ  ሰዎች « አእምሮአቸው እንዲጨልምና የእግዚአብሔርን እውነት በትክክል አንዳይመለከቱ፥ እና እውነተኛውን እና ትክክለኛውን በማስተዋል ክፉውንና ደጉን መለየት እንዳይችሉ» ማድረጉ ነው። በመሆኑም ነቢያት የእግዚአብሔርን እውነት በጨለማው ዓለም ላይ ለሰዎች የሚገልጡ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው። በቤተ ክርስቲያናችን ሙሴ ሊቀ ነቢያት ወይም የነቢያት አለቃ በመባል ይታወቃል ። ሙሴ ራሱ  ለእስራኤላውያን ስለሚመጣው የነቢያት ነቢይ ሲናገር « እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል እርሱንም ታደምጣለህ»  ብሎአል።(ዘዳግም 18፥15 )  ጴጥሮስም በኢየሩሳሌም ለነበሩት ሕዝቦች እንደሰበከው ያ « ከወንድሞችህ እንደኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል» የተባለለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሐዋ ሥራ 3፥22) 
     
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የነቢይነት አገልግሎት መዳን የሚገኝበትን የእግዚአብሔርን እውነትና፥ ለሰው ልጆች ያዘጋጀውን የመዳን እቅድ መግለጥ ወደዚህም መዳን ሰዎችን ሁሉ መጥራት ነው። ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን በምልዓት የገለጠው ማንም የለም። ዮሐንስ 1፥18፥ እግዚአብሔርን የገለጠው ደግሞ በእውነትና በጸጋ ነው። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ የነቢይነት አገልግሎቱ በናዝሬት ምኩራብ ባነበበው የኢሳይያስ ምንባብ ላይ በግልጥ አስቀምጦታል። ይኸውም ለድሆች ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ መቀባቱን ነው። (ሉቃስ 4፥21)ሆኖም እዚህ ላይ ልናስተውል የሚገባን ከእግዚአብሔር ተልከው የቀደሙት ነቢያት የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው እርሱ ግን ራሱ መልእክት ነው። የቀደሙት ነቢያት የመጡት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ነው  እርሱ ግን የመጣው « እኔ ግን እላችኋለሁ» በማለት ነው። (  ማቴዎስ 5፥22) ምክንያቱም ራሱ የእግዚአብሔር መገለጥ  የእግዚአብሔር ክብር እና እውነት ነው። 

      ሁለተኛው በብሉይ ኪዳን የምናገኘው አገልግሎት የክህነት አገልግሎት ነው። ካህን ማለት ስለ ሕዝቡ የሚቆም ማለት ነው። ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ከእግዚአብሔር ስለ ሕዝቡ ይቅርታ ለመጠየቅ ነው። ኃጢአታቸውን ለማስተሥረይ ( ለመክደን) ጸሎት፥ መባና መሥዋዕት ያቀርባል።  ይህ አገልግሎት ለምን አስፈለገ በምንልበት ወቅት አሁንም የምንመለሰው  ኃጢአት ወደ ዓለም በገባ ወቅት ወዳስከተለው ነገር ነው። የኃጢአት ጉዳት ሰዎች እውነትን እንዳይረዱ፥ ወይም ደግንና ክፉን መምረጥ እንዳይችሉ አእምሮአቸውን ማደብዘዝ ብቻ ሳይሆን፥ በኃጢአት ውስጥ በመውደቅ ጥፋተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ነበር። 

ይህ የኃጢአተኝነትና የጥፋተኝነት ሕይወት ያስከተለው ነገር ቢኖር ሰው ከእግዚአብሔር እንዲለይ ነበር፤ ኢሳይያስ ስለዚህ ሲናገር « በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።» ብሎአል። ኢሳይያስ 59፥1፤ በሌላም ሥፍራ « ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር፦ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።(ኢሳይያስ 55፥7-9።) በመሆኑም በብሉይ ኪዳን ይህን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ያለውን የኃጢአት ግድግዳ ለማፍረስ የእንስሳት መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። 

ነገር ግን ይህ የብሉይ ኪዳኑ መሥዋዕት በሦስት መንገዶች ፍጹም የሆነ የኃጢአት ሥርየት ሊያመጡ አልቻሉም። አንደኛ ሊቀ ካህኑ ራሱ በኃጢአት ተጽእኖ ሥር ያለ ስለሆነ፥ አስቀድሞ ስለ ራሱ መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ አገልግሎቱም በሞት የሚገደብ፥ ወይም ሞት የሚሽረው ነው ነው። ሁለተኛ መሥዋዕቶቹ ፍጹማን አይደሉም፤ ከሰው ወገን የሚቀርቡ እንጂ ከእግዚአብሔር በኩል የተዘጋጁ ስላይደሉ፥ መሥዋዕቶቹ ሥጋን ብቻ የሚቀድሱ ነበሩ።  ሦስተኛ ልክ እንደ ካህኑ መሥዋዕቶቹም ሞት የሚገድባቸው ስለሆኑ ሊቀ ካህኑ በየዓመቱ ደሙን ይዞ ወደቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት ነበረበት። 
     ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ሆኖ እንደመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጥ ይነግሩናል። ስለ ሊቀ ካህንነቱ በምልዓት በተነገረበት በዕብራውያን መልእክት ላይ እነዚህን ከላይ ያየናቸውን ሦስት የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ጉድለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንዴት ወደፍጻሜ እንዳመጣው ይነግረናል። 

አንደኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደመልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት የዘላለም ሊቀ ካህናት ነው። 
የእርሱ ሹመት እንደ መልከጼዴቅ የሆነበትን ምክንያት  የዕብራውያን ጸሐፊ  ሲናገር  « እንግዲህ ሕዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን እንደ አሮን ሹምት የማይቆጠር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ወደ ፊት ስለምን ያስፈልጋል?  ክህነታቸው ታልፍ ዘንድ አላትና፤ ክህነታቸው ካለፈችም ኦሪታቸው ታልፋለች. . .  ስለዚህ የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች። ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፈንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል  እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና። በመሐላ የሾመውን ግን « እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘልዓለም ካህን ነህ» አለው።  ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ ለእነዚያ  ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው ሞት ይሽራቸው፥ እንዲኖሩም አያሰናብታቸውም ነበርና። እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና። ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል።  » ዕብራውያን 7፥11-25 

ሁለተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ንጹሕ መሥዋዕት ሆኖ ራሱን ለዘላለም ያቀረበ ነው። 

«  ቅዱስና ያለ ተንኰል፥ ነውርም የሌለበት፥ ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል። እርሱም እነደ እንደ እነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።»  ዕብራውያን 7፥11-25 

ሦስተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹምና ሰማያዊ መሥዋዕት ስለሆነ በእግዚአብሔር ፊት የኃጢአት ይቅርታን አሰጥቶናል። 
« ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ የሰው እጅ ወደ አልሠራት፥ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው ከፊተኛይቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን የዘለዓለም መድኃኒትን ገንዘብ አድርጎ፥ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም፤» ካለ በኋላ « ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ በቀደመው ሥርዓት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ፤» ዕብራውያን 9፥11-15 ይህን የሊቀ ካህንነቱን ሥራ እንዴት አድርጎ በመስቀል ላይ እንደፈጸመ ሞትን በምንናገርበት ወቅት እናመጣዋለን። 

ሦስተኛው በብሉይ ኪዳን የምናገኘው አገልግሎት የንግሥና አገልግሎት ነው። ለንግሥና እግዚአብሔር የሚመርጣቸው ሰዎች በነቢያት ይቀቡ ነበር።  ይህ አገልግሎት ያስፈለገውም ልክ እንደሌሎቹ አገልግሎቶች ኃጢአት የእግዚአብሔር ሕዝብን ባሪያ አድርጎት ስለነበር፤ በኃጢአት ተመርተው በምድራዊ ነገር ባሪያ ካደረጉት ነጻ ለማውጣት እግዚአብሔር ነገሥታቱን ያስነሣ ነበር። ሆኖም እነዚህ ነገሥታት ራሳቸው በኃጢአት ተጽእኖ ሥር ስለሚሆኑ አንዳንድ ጊዜ ነጻ አወጣዋለሁ ያሉት ሕዝብ ለሌላ አደጋ ያጋልጡ ነበር፤ ሕዝባቸውንም ነጻ የማውጣታቸው ነገር በምድራዊ ነገር ብቻ የተወሰነ ነው። 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ተብሎ በብዙ ቦታ ተጠርቷል። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። አውሳብዮስ ዘቂሣርያ ስለዚህ ሲናገር ጌታ በተወለደበት ጊዜ ንግሥና ከአይሁድ የተወሰደበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አይሁዳዊ ያይደለ ሰው (ሄሮድስ) የአይሁድ ንጉሥ ተብሎ የተጠራበት ሊቀ ካህንነቱም የአገልግሎት ሹመት የሆነበትና ትንቢት በሙሉ የተቋረጠበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም እስራኤልን ከምድራዊ ባርነት ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊ ባርነት ነጻ የሚያወጣ ለዳዊት የተሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ንጉሥ እንደሚነሣ ሕዝቡ ይጠብቅ ነበር፤ ሰብአ ሰገልና የእነርሱን ዜና የሰሙ ጸሐፍት በአንድነት የተነጋገሩት ስለሚወለደው « የአይሁድ ንጉሥ» ነበር።(  ማቴዎስ 2፥1። )  የእግዚአብሔር መልአክ ለቅድስት ድንግል ማርያም ሲያበሥራት « እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።» ነበር ያላት( ሉቃስ 1፥32፡33) 

ጌታ በንጉሥነቱ ምን አድርጎአል ብለን ስንጠይቅ፥ ለዘመናት የሰው ልጆችን ባሪያ አድርጎ የነበረውን ሞትን ድል አድርጎአል። (1ኛ ቆሮንቶስ 15) ሁለተኛ በባርነት በዲያብሎስ ተይዘው የነበሩትን ነጻ አውጥቶአል። (ዕብራውያን 2፥10-18፤ እነዚህን የተዋጁትንና ነጻ የወጡትን  ወደ አባቱ መንግሥት አፍልሶአቸዋል። « እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።» ቆላስይስ 1፥13። ይህ በሞቱና በትንሣኤው የሆነውን የንጉሥነቱን ሥራ ወደፊት ትንሣኤውን በምናይበት ወቅት በሰፊው እንመለከታለን ። 

እንግዲህ እነዚህ ሦስቱ አገልግሎቶች ሳይነጣጠሉ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ውስጥ ታይተዋል ። ክርስቶስ የሚለው ስሙ የሚያመለክተውም ይህን ነው። እዚህ ላይ የዛሬውን ትምህርታችንን አንድ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ በተናገሩት ለምን አንደመድመውም፤  «  የወደቀው ሰው እውነትን በመማርና ለአእምሮ አብርሆትን በማግኘት ካልሆነ በስተቀር ራሱን ፍጹም ያድርግ ዘንድ በፍጹም አልቻለም። ኃጢአታችንን ከፍ ከፍ አድርጎ በመስቀል ላይ የሚጠርቅና እኛን የሚቀድስ ራሱን በመስቀል ላይ መሥዋዕት የሚያደርግ ሊቀ ካህናት ያስፈልግ ነበር።  ይህ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ  « ስለ ኃጢአታችን የሞተው»  ክርስቶስ ነው። . . . ይህ በክርስቶስ ሞት ቤዛነትን ያገኘው ሰው ሥልጣን ያለው ንጉሣዊ ቤዛ ያስፈልገው ነበር። . . . ሰው የሆነው አምላክ ትህትና በመስቀል ላይ ተፈጸመ ባለው ቃል ተደመደመ፤ በመስቀሉ ላይ ድል አድራጊነቱና ንጉሣዊው ሥልጣኑ አበራ፤ ክርስቶስ ወደሲኦል ወረደ፤ የሲኦልን ደጆች ሰባበረ፤ የሲኦልን መንግሥትና የሞትን ግዛት በታተነ፤ ለዘመናት በሞት ተዘግተው የነበሩትን አስነሣ፤ ከሙታን ሲነሣ ሁሉን ቻይ የሕይወትና የሞት ጌታ ሆኖ ተነሣ። « የሕይወት ባለቤት በሙስና መቃብር መያዝ አይችልምና።   ከሙታን ተነሥቶም ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ አለ። ( ማቴዎስ 28፥18) ወደ ሰማይ አረገ፤ እውነተኛ ንጉሥ ሆኖ በሰማይ ድል አድራጊ በምድር ደግሞ ተዋጊ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን እየመራ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦአል። በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ ዳግም ሲመጣ የሰው ልጆች ሁሉ የንጉሥነቱን ሥልጣን ያውቃሉ።  



1 comment: