Thursday, June 20, 2013

የፖለቲካ ኑፋቄና የኑፋቄ ፖለቲካ (ክፍል አንድ)

ሰሞኑን በየአቅጣጫው የተለመደችው የፖለቲካ ኑፋቄ ከየአቅጣጫው ብቅ ብቅ ብላለች፤ የፖለቲካ ኑፋቄ ያልኩት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ወይም አንቀጸ ሃይማኖትን መነሻ ያላደረገ ከዚያ ይልቅ ፓለቲካ እንደኑፋቄና ኑፋቄ እንደ ፓለቲካ መሣሪያ የሚታይበትን ክስተት ለማተት ነው። ይህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሙሉ ሲታይ የኖረ ነገር ነው። የኒቅያ ጉባኤን ተከትሎ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የታየው ክስተት ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ትምህርት የሚሰጥ ቢሆንም፥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወነውን ላስተዋለ « ከታሪክ ያልተማረ እንዲደግመው ተፈርዶበታል» የሚለው ብሒል እየተፈጸመብን መሆኑን እንረዳለን። ለማንኛውም በወርቃማው የአባቶች ዘመን the Golden Patristic era ከነበሩት መካከል በሁለቱ ላይ የተከናወነውንና ቤተ ክርስቲያን ከዚያ ልትማር የሚገባውን እናያለን።

ቅዱስ አትናቴዎስ እና « ሦስተኛው እጅ»

የኒቅያ ጉባኤ የወልደ እግዚአብሔርን አምላክነት « ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፥ በመለኮቱ ከአብ የሚተካከል» የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጠቅልሎ የሚገልጠውን እውነት የወሰነ ታላቅ ኢኩሜኒካል ጉባኤ ነበር። የኛ አባቶች እንደሚሉት የኒቅያ አባቶች መንፈስ ቅዱስ እየመራቸው እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው የኒቅያ ጉባኤን ውሳኔ ሃይማኖት ወይም አንቀጸ ሃይማኖት ሲያጸድቁና አርዮስን ሲያወግዙ በቆስጠንጢኖስ ቤተ መንግሥት ሞገስ የነበራቸው እነ አውሳብዮስ ዘኒቆሞዲያ ደግሞ አርዮስን እና የአርዮስን ትምህርት እንዴት አድርገው በጓሮ በር ማስገባት እንደሚችሉ ይዶልቱ ነበር።

ይህን ለማድረግ ግን በጉሮሮ ላይ እንዳለ አጥንት ሆኖ ያስቸገራቸው አትናቴዎስ የክርስቶስ ሐዋርያ ነበር። በኒቅያ ጉባኤ ሊቀ ዲያቆን ሆኖ አርዮስን ከረታ በኋላ ሟቹን እለእስክንድሮስን ተክቶ በማርቆስ ወንበር ላይ ተቀመጠ። በመንበሩ ላይ የተቀመጠው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቅዶ የእስክንድርያ ምዕመናን በአንድ ቃል « ጻድቁን፥ ትጉሁን፥ እውነተኛ ክርስቲያኑን፥ ገዳማዊን አትናቴዎስን ስጡን፥ ፓትርያርካችን እርሱ ነው» በማለት በአንድ ቃል ጮኸውን ነው።

የኒቆሞድያ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚዶለተው ዱለት ግን አትናቴዎስን እንዴት አድርጎ ማስወገድ እንደሚቻል ማጠንጠን ነበር፤ የመጀመሪያው አርሳንዮስ የሚባል አንድ ጳጳስ በአስማት አስገድሎአል የሚል ክስ ነበር የቀረበበት። እርሱን ለማውገዝ በጢሮስ ጉባኤ ተጠራ፤ በዙሪያው እርሱን ለማውገዝ አሰፍስፈው የነበሩት አርዮሳውያን ጳጳሳት ነበሩ፤ ክስ ብቻ ሳይሆን የተገደለው ጳጳስ እጅ ብለውም አንድ የተቆረጠ እጅ አምጥተው ገድሎት በእጁ ያሟርትበታል ብለው በአትናቴዎስ ፊት ሲያስቀምጡ፥ ቤቱ በጩኸት ተቃጠለ፤ አትናቴዎስ ግን ምንም ሳይነዋወጥ « ለመሆኑ ይህ እጅ የአርሳንዮስ ለመሆኑ እርግጠኛ ናችሁ?» አላቸው። « አዎ! በሕይወት ሳለ በሚገባ እናውቀዋለን» ብለው መለሱለት። ከዚያ አትናቴዎስ ተከትሎት ወደመጣው አገልጋዩ መለስ ብሎ በዓይኑ ጠቀሰው፥ ያን ጊዜ በእድሜ የሸመገለ አባት ሰዎች ይዘው ወደ ጉባኤው ገቡ፤ ያን ጊዜ አትናቴዎስ « ለመሆኑ ይህ ማንነው? አርሳንዮስ ነው?» በማለት ጠየቃቸው። ሁሉም በአድናቆትና በጸጥታ ተዋጠ፤ ምክንያቱም ገድሎታል ተብሎ የተከሰሰበት አባት አርሳንዮስ በፊታቸው ቆሞ ነበር። በመቀጠል ጥያቄውን አቀረበ « እጁን አጥቶአል ያላችሁት ይህ ሰው ነው? ብሎ ጠየቀ። ቀስ ብሎ የሽማግሌውን የአርሳንዮስን እጅ ከፍ አድርጎ አሳያቸው፤ የአርሳንዮስ እጆች ሁለቱም በመልካም ሁኔታ ላይ ነበሩ። ፤ አትናቴዎስ ቀጠለ « እንደምታዩት አርሳንዮስ የተገኘው ከነሁለት እጆቹ ነው፤ አሁን ከሳሾቼ ሦስተኛው እጅ ከየት ቦታ እንደተቆረጠ ያሳዩኝ!» አላቸው። የሚያስገርመው እንዲህ ሐፍረት በከሳሾቹ ላይ ቢያጋጥማቸውም ሌላ ክስ ከየትም ፈልገው በዚያው በጢሮስ ባደረጉት ጉባኤ አትናቴዎስ ከመንበሩ እንዲሰደድ ወስነው ነበር፤ የሚያስቀው አትናቴዎስን ያሳደደውን ጉባኤ የመሩት፥ በጎልጎታ አዲስ የተሠራውን ቤተ ክርስቲያን ለመመረቅ በአንድነት ከንጉሡ ጋር ተያይዘው ነበር የሄዱት፤

የአትናቴዎስ ጥፋት ምን ነበር? ለእውነት መቆሙ ነበር። ለክርስቶስ እውነት፤ ኑፋቄ ሆኖ የተገኘበት ደግሞ ለቁስጥንጥንያ ፖለቲካ አለመመቸቱ ነበር፤ ኑፋቄው የፖለቲካ ስለሆነ በኑፋቄ ፖለቲካ መወገዝ ነበረበት፤ ታሪክ እንደሚነግረን አትናቴዎስ አብዛኛውን የሊቀ ጵጵስና የአገልግሎት ዘመኑን ያሳለፈው በስደት ነበር።

No comments:

Post a Comment