Saturday, December 15, 2012

ቃልና ተግባር በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ





በእድሜ እየበሰልኩ ስመጣ፥ ሰዎች ለሚናገሩት ነገር ትኩረት አልሰጥም፤ ለሚያደርጉት እንጂ። 
አንድሪው ካርኒጌ 


በማናቸውም ቀን ስብከት ከመስማት ይልቅ ማየት እወዳለሁ። 
ኤድጋር ገስት 

ልጆች ከቤተሰቦቻቸው የሚቀስሙትን ታላላቅ እውነታዎች የሚረከቡት፥ በንግግር  ወይም በጽሑፍ ሳይሆን በማየት ነው። እንዲያውም ከአባት ከእናት ወደልጅ የሚተላለፉ እሴቶችን በንግግር መግለጽ ወይም በጽሑፍ መገልጥ አዳጋች ነው። የእናትን ፍቅር ወይም የአባትን ምቾት ማን ይገልጠዋል? ቃላትን በመቅረጽ ባለሙያዎች ለሆኑት ባለቅኔዎችና ጸሐፍት እንኳ ይህ ታላቅ ተግባር ነው።

ምዕራቡ ዓለም የመቻቻል መንፈስ ብዙ የሚደሰኮርበት ስለሆነ ብዙዎች በቃላቸው ሰውን እንዳይጎዱ በጣም የሚጠነቀቁበት ዓለም ነው። በልምምድ የተገኘ ከሚመስለው ፈገግታ ጀምሮ ሐሰተኛ እስከሆነው ትህትና ድረስ፥  የሰውን ጓደኝነት መግዣ መንገዶች ተደርገው በመወሰዳቸው፥ እውነተኛ የሆነ ውይይት ለመፍጠርና የልብ ጓደኛ ለማግኘት ከባድ ነው። ይህ የኑሮ ፈሊጥ ወደቤተሳባዊ ሕይወት ዘልቆ ከመግባቱ የተነሣ፥ በአባትና በልጅ ወይም በእናት እና በልጅ መካከል ያለው ቅርርብ ከልብ ያይደለ ከስሜት የራቀና ባዶ ሆኖ እናገኘዋለን።

በመሆኑም በዚህ ዘመን ልጆች ወላጆቻቸውን ከሚኮንኑበት ነገር አንዱ ግብዝነት የሆነውም ለዚህ ነው። ግብዝነት ምንድነው ብለን ስንጠይቅ ቃልና ተግባር ያልተዋሃዱበት መንታ ሕይወት ማለት ነው። የወንጌሉን ቃል ከወሰድን፥ ግብዝነት ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚከለክለን ሕይወት ነው። ማለት በሌላ መልኩ በልጆችና በወላጆች፥ ወይም በሕይወት አጋሮች፥ ወይም በጓደኞች መካከል እውነተኛ የሆነ የፍቅርና የእውነት ሕይወት እንዳይኖረን የሚያደርግ ነው።

በቤተሰብ መካከል ሊኖር ስለሚገባው መንፈሳዊ ሕይወት ስንነጋገርም፥ የምናገኘው ከዚህ የራቀ አይደለም። ለምሳሌ በዲያስፖራ ባለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጎልተው ከሚታዩት ጥያቄዎች መካከል፥ ክርስትናችንን ለቀጣይ ትውልድ እንዴት ማስተላለፍ አለብን የሚለው ነው። በቤተ ክርስቲያን አደባባዮች ስለልጆቻችን የሚነገሩት ቃላት ትርጕም የለሽ ሆነው ተንነው የሚቀሩት፥ ንግግራችን ከተግባራችን ጋር የተቀራረበ ባለመሆኑ ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ሕይወትን ለማስተላለፍ የተሰጠ ሕይወት አላቸው ወይ? ከልጆቻቸው ጋር አብረው ይጸልያሉ?  ለልጆቻቸው ቃለ እግዚአብሔር ያነቡላቸዋል? ወላጆች የዕለት ችግሮቻቸውን ወይም ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግጭቶች ሲፈቱ፥ መንፈሳዊ እሴቶችን የኑሮአቸው መመዘኛ ያደርጋሉ? እነዚህ ነገሮች በልጆቻችን ዓይን ፊት የክርስትናችን መስፈርቶች ናቸው።  ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነት ብንተርክላቸው፥ ልጆቻችን የሚመለከቱት የእኛን መንፈሳዊ ሕይወት መሠረት ነው።

አንድ ባልንጀራዬ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ካህን ጻፉት ብሎ የነገረኝ ይህን እውነታ ያጸናልናል።  ወላጆች ለልጆቻቸው እምነት ማጣት ምን ያህል ምክንያት እንደሚሆኑ ሲናገሩ  « ብዙዎች ልጆች እግዚአብሔር የለሽ የሚሆኑት ከቤተ ክርስቲያን ሲመለሱ  እሁድ ጠዋት ነው» ብለው ነበር ።  ወላጆች አብረው በአምልኮ የተሳተፉትን ወገኖቻቸውን ስም ጠርተው በሐሜት ሲያነሱዋቸው፥ ወይምየካህኑን ስብከት ሲያጣጥሉ የሃይማኖት አባት የሆነውን ካህን በንቀት ሲያጣጥሉት፥  ከቅዳሴው ውበት ይልቅ የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካና አተካራ የንግግራቸው ማዕከል ሲሆን፥ ልጆች ያዳምጣሉ። ያዳምጡና የወላጆቻቸውን ቃልና ተግባር ይመዝናሉ። ወላጆቻቸውን ይመዝናሉ ቀልለውም ያገኙአቸዋል። እግዚአብሔር በጸጋው ካልሰወራቸው የወላጆቻቸውን የለብታ ሕይወት በማየት << ክርስትና እውነተኛ ሕይወት (authentic life) የማይሰጥ በግብዞች የተሞላ እምነት ነው>>  ብለው ከቤተ ክርስቲያን ይርቃሉ። በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው ታላቅ ክስም ይህ የሆነው ለዚህ ነው።



1 comment: