Tuesday, December 18, 2012

የስምዖን ዓምዳዊ ጸሎት ( ክፍል አራት)

ምዕራፍ ፲፩፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ በጨርቅ የተጠቀለልክ ኃይልህን ስጠኝ፤ በጥበብህም ጠቢብ አድርገኝ፤ አንተ የሕይወት ጥበብ ነህና። ሕይወትን ሰጪ በሆነው ስምህ ታድነኝ ዘንድ፤ ወደ መዳን ወደብ ትመራኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።ብርሃናውያን ( መላእክት) ከአንተ ሕይወትን የሚመገቡ፥  ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጡቶች ወተትን የጠባህ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ነፍሴ ከአንተ ሕይወትን ትመገብ ዘንድ እለምንሃለሁ። የሁሉ ሕይወት ሆይ ሕያዋን የሆኑ ሁሉ በሕይወት የሚኖሩት በአንተ ነው።  አንተ ከሰማይ የወረደ ለፍጥረት ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ  የሕይወት ኅብስት ነህ። ሕይወትን ስጠኝ በጎ በሆነችውም ፈቃድህ መግበኝ።

ምዕራፍ ፲፪፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥  የአብርሃምን ቤት የተስፋ ማኅተም ለመቀበል፥ በአብርሃም ልጆች ላይ  የወሰንከውን ሕግ ለመፈጸም በስምንተኛው ቀን ወደ ግዝረት ቤት የገባህ፥ ቅድስት በምትሆን በሥላሴ ማኅተምኅ ልቡናዬን አትመኝ። ።ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ በመንፈስህ ሰይፍ ግዘረኝ፤ የጨለማ ኃጢአት የሆነችውን ሸለፈት ከእኔ  ቁረጥልኝ።

ምዕራፍ ፲፫፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ እኔ በምድር ላይ እሳትን ልጥል መጥቻለሁ እንድትነድም እፈልጋለሁ ያልክ፥ በእርሷ እነጻባት ዘንድ  በልቤ ውስጥ ትንደድ። ለአንተ ንጹሕና ቅዱስ ማደሪያ ይሆን ዘንድ ልቤንና ሕሊናዬን አንድ ታድርግልኝ። ሕይወትን በሚሰጥ በስምህ አንጻኝ፤ ሕይወትን ያፈልቅ ዘንድ የሕሊናየን ውስጥ አትመው። ስምህ የሕይወት ወንዝ ነውና፤ በውስጡ ስምህ ያለው ነፍስ ሁሉ በሕይወት ይኖራልና። 

No comments:

Post a Comment