Tuesday, June 18, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት ( ስድስተኛ ክፍል)

    READ IN PDF
   ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም። ብርሃን ዘእምብርሃን አምላክ ዘእምአምላክ ዘበአማን። 
  ዘተወልደ ወአኮ ዘተገብረ ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ። ዘቦቱ ኲሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ ዘበሰማይኒ ወዘበምድርኒ። 
    

ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ከአብ ጋር የሚተካከል። ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለእርሱ ግን ምንም የሆነ የለም በሰማይም ሆነ በምድርም ሆነ 

በክፍል አምስት ትምህርታችን የግዕዙን አቀማመጥ ተከትለን   ቤተ ክርስቲያን ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ጌታ እንደተባለና ኢየሱስ እና ክርስቶስ የሚሉት ስሞቹ የሚያመለክቱት ምን እንደሆነ። ዛሬም ከዚያው በመቀጠል ዘለዓለማዊነቱንና ፈጣሪነቱን የሚናገሩትን ቃላት እናብራራለን። 

1. ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን፤ 

አርዮስ ከወደቀበት ስህተት አንዱ የወልድን ዘለዓለማዊነት መካድ ነው። በእርሱ እምነት ተወለደ እና ተፈጠረ የሚሉት አንቀጾች አንድ ስለሆኑ « ወልድ ያልነበረበት ጊዜ አለ።» በማለት ያስተምር ነበር  ። ሆኖም በኒቅያ የተሰበሰቡ አባቶች የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት አድርገው በሥጋ የተገለጠው ወልድ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ጋር እንደነበረ፥ ተቀዳሚ እና ተከታይ የሌለው የአብ ልጅ እንደሆነ አስተምረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ወልድ ከሥጋዌ በፊት ማለት ሰው ከመሆኑ በፊት በቅድምና በዘለዓለም ከአብ ጋር እንደነበረ በግልጥ ያስተምረናል። ዮሐንስ ስለዚህ ሲናገር  « በመጀመሪያ ቃል ነበረ።» ይለናል። ዮሐንስ 1፥1። ይህ ቃል ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር ጋር የነበረ መሆኑንም ሲነግረን « ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» ይለናል። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእመቤታችን ከመወለዱ በፊት ነዋሪ መሆኑን ሲናገር « አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ።» ወይም « አብርሃም ሳይወለድ እኔ ነኝ» በማለት አስተምሮአል። ዮሐንስ 8፥58።  

ስለ ጌታ ኢየሱስ ዘላለማዊነት የነቢያትን ምስክርነትም እናገኛለን። በትንቢተ ኢያሳይያስ ላይ ከቅድስት ድንግል ስለሚወለደው ሕፃን ሲናገር «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።» በማለት በሥጋ የተገለጠው አምላክ « የዘላለም አምላክ» እንደሆነ ገልጦአል።( ኢሳይያስ 9፥6። )  ዳዊትም ስለ ጌታ ዘለዓለማዊነትና፥ በሞት ላይ ድል አድራጊ ስለመሆኑ ስለትንሣኤውና ስለ ዘለዓለማዊ ክህነቱ በተነገረበት በመዝሙረ ዳዊት ላይ « ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ>> በማለት ተናግሮአል። መዝሙር 109፥3። ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ማለት በሌላ አነጋገር ከጊዜያት በፊት የነበረና ጊዜያትን የፈጠረ ማለት ነው። ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንደተናገረው «  የጊዜያት ባለቤት ለጊዜ አይገዛም።»። 

Tuesday, June 11, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (አምስተኛ ክፍል



ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ የምትመሰክራቸው እውነቶች 

በኒቅያ የተሰበሰቡት አባቶቻችን በአርዮስ የቀረበላቸውን የስህተት ትምህርት ፊት ለፊት በእግዚአብሔር ቃል ሲቃወሙት በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ተከትላ የምታስተምረውን ትምህርት በሚገባ መግለጥ ነበረባቸው።  በሚቀጥሉት ክፍሎች የምናገኛቸው ሐረጎችና ቃላት አባቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምራቸው እውነቶች ጠቅለል አድርገው የገለጡበት ክፍል ነው። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በመያዝ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ አምላክነቱን አስተምራለች ዋጋም ከፍላበታለች።  

1.  በአንዱ ጌታ እናምናለን።
(ወነአምን በአሐዱ እግዚእ፤) 
መጽሐፍ ቅዱስ በሥጋ የተገለጠውን እግዚአብሔር ወልድን ከሚጠራበት ስሞች አንዱ ጌታ ብሎ ነው። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችም « በአንዱ ጌታ» ብለው ተናግረዋል።   ጌትነቱን የምንናገረው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ነው። « በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። » (1 ቆሮንቶስ 12፥3) በአፋችን ጌትነቱን መናገራችን የደኅንነታችን ምክንያት ነው። « ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና » ሮሜ 10፥9። የአባቶችን ነገረ መለኮት በምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቅ የተመሰገነው ቶማስ ኦዴን እንዳሳሰበን ክርስቶስን በምድር ሲመላለስ ብቻ ጌታ ብንለው ኖሮ ምናልባትም አስተማሪ ወይም አለቃ መሆኑን ማስተዋወቂያ ነው። ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ ጌታ መባሉ በአሁኑ ዓለምም በሚመጣውም የእግዚአብሔር መንግሥት እርሱ ገዢ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሐምሳ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ « እናተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።» በማለት የተናገረው። (ሐዋ ሥራ 2፥6 ) ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በነገረ ጥምቀት ትምህርቱ እንዳለው « እርሱ ጌታ ነው፤ ጌትነቱም ደረጃ በደረጃ ያገኘው ሳይሆን በባሕርዩ ጌታ በመሆኑ ያገኘው ክብር ነው።» 

ጌታ ኢየሱስ ስንል ምን ማለታችን ነው? በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት ጌታ ኢየሱስ የሚለው ቃል ዋጋ የሚያስከፍል ቃል ነበር። ለሮም ግዛት (Roman Empire) በሰዎች ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ጌታ የነበረው ቄሣር ነበር። በመሆኑም ቄሣር ይሰገድለት ይመለክ ነበር።  በብሉይ ኪዳን የሰብአ ሊቃናትን ትርጕም (ሰብትዋጀንት) ከተከተልን ከስድስት ሺ ጊዜ በላይ ያህዌ የሚለውን የእብራይስጥ ቃል « ጌታ» ተብሎ ተተርጉሞአል። ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ ማለት ከቄሣር ተቃራኒ አድርጎ የሚያስቆም « ፓለቲካዊ አቋም» ብቻ ሳይሆን፥ ይህ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ሙሴን የተናገረው « እኔ ነኝ » ያለውና ነቢያቱን የላከው መሆኑን ነው። ይህ « እኔ ነኝ » ማለት አቻ ወይም ተቃራኒ አልባ ብቸኛ አምላክ ማለት ነው።በጥንት አማርኛ የተጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ጸሎተ ሃይማኖት ትርጓሜ ስለዚህ ቃል ሲናገር «በሐንድ ጌታ ምን አሰኛቸው፥ ሌላ ጌታ አለን ያሉ እንደሆን። ጌታስ መኰንንም፥ ካበላ ካጠጣ ጌታ ይልዋል። እርሱ ግን አጋዙን ቀድሞም ከሰው ያላመፃው፥ ኋላም ለሰው ያያሳልፈው፥ በባሕርዩ በጠባይዕ ገዢ በሐንድ አምላክ ነአምናለን አሉ።» ይለናል።  

  1. ኢየሱስ ክርስቶስ  
 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሥጋ የተገለጠው ቃል የተጠራባቸው ብዙ መጠሪያዎች ቢኖሩም በዋናነት የሚታወቁት ሁለቱ ናቸው፤ እነርሱም ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ናቸው።  ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ያላቸውን የነገረ መለኮት አንድምታዎች በሚገባ በመተንተን ከጻፉ ቀደምት ጸሐፊዎች መካከል « የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት» (the father of church history)  ተብሎ የሚታወቀው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ ዋናው ነው። አውሳብዮስ ስለ ጌታ ስሞች ሲያብራራ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነገሮች ይነግረናል። አንደኛው ኢየሱስ እና ክርስቶስ የሚለው ስም ከጥንት ጀምሮ በነቢያት የተነገሩና በመላእክት የተበሠሩ ስሞች ናቸው። ሁለተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አምላክነት የሚያሳዩ ናቸው ሦስተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አዳኝነት የሚያመለክቱ ናቸው።   ለዚህ ዋና ምሳሌ አድርጎ የሚያነሣልን ሙሴን ነው። ሙሴ እስራኤልን በመሪነት ሲያስተዳድር ከእግዚአብሔር በተቀበለው ትእዛዝ መሠረት ከሾማቸው የአገልግሎት ሹመቶች መካከል ዋና የሚባሉት ሁለት እንደሆኑ ይጠቅስልናል፤ እነዚህም ሊቀ ካህናቱን አሮንንና ራሱን ሙሴን የተካውን ኢያሱን የሾመበት ነው። አውሳብዮስ እንደሚለን « « በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ» በማለት እንዳዘዘው ቃል የሰማያዊ ነገሮችን አምሳልና ምልክቶች፥  በመጠቀም ክርስቶስ የሚለውን ስም የተለየ ታላቅነት እና ክብር ያለው ስም እንደሆነ እንዲታወቅ በማድረግ የመጀመሪያው ሙሴ ነው። (ዘፀአት 25፥40)ከሰዎች ሁሉ ከፍ ያለውን  የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህን በገለጠበት ወቅት " ክርስቶስ" ወይም " የተቀባ" ብሎ  ጠርቶታል። በእርሱ እይታ ከሰዎች ሁሉ ክብር ከፍ ባለው በዚህ የሊቀ ካህንነቱ አገልግሎት  ሊቀ ካህኑ የክብርና የከፍታ ምልክት ይሆንለት ዘንድ ክርስቶስ የሚለውን ስም ሰጥቶታል። (ሌዋውያን 4፥5፡16፤ 6፥22) » 
  
ለኢያሱ ሲነግረንም፥ ራሱ « ኢያሱ» የሚለው ስም ኢየሱስ ከሚለው ስም ጋር እንዴት ዓይነት ግንኙነት እንዳለው ሲነግረን ኢያሱ « ወላጆቹ ባወጡለት በሌላ ስም አውሴ በመባል ነበር የሚታወቀው። ሙሴ ግን ከነገሥታት ዘውድ የሚበልጠውን፥ ገንዘብ የማይገዛውን እጅግ ክቡር የሆነውን ስም ሊሰጠው ኢየሱስ (ኢያሱ) ብሎ ጠራው።ከሙሴ በኋላና አምሳላዊው አምልኮ ለሰዎች ሁሉ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ከተፈጸመ በኋላ በእውነተኛው ንጹሕ በሆነው እምነት ላይ በመሪነት የተቀመጠው የነዌ ልጅ ኢያሱም የአዳኛችንን ምሳሌ ተሸክሞ ነበር።  » ይህ የአውሳብዮስ ትንተና መልክአ ኢየሱስን በጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ደራሲ በግልጥ ተቀምጦአል
   « አክሊለ ስምከ እንዘ ይትቄጸል በርእሱ፤ 
   « አኅጉረ ፀር ወረሰ ኢያሱ፤» 
       የስምህን አክሊል በራሱ ላይ አድርጎ 
      የጠላትን ሀገሮች ኢያሱ ወርሶአል።
      
ኢየሱስ የሚለው ስሙ 
      
ይህ የአውሳብዮስም ሆነ የመልክአ ኢየሱስ ደራሲ ትንተና የሚያሳየን ኢየሱስ የሚለው ስም የእግዚአብሔር ሕዝብን ከማዳን ጋር የተገናኘ ስም መሆኑን የሚያመለክት ነው። ምክንያቱም በእብራይስጥ የሹኣ፥ ኢያሱ ወይም ኢየሱስ የሚለው ስም በእብራይስጡ « ያሕዌ መድኃኒት ነው» የሚል ትርጉም አለው።  ማቴዎስ ወንጌሉን በተለይ ለአይሁድ የጻፈ እንደመሆኑ፥ በአይሁድ ዘንድ ተስፋ የተነገረለትን የዚህን ስም ትርጉም በመልአክ እንደተነገረው በጽሑፍ አስፍሮታል። የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ሲነግረው « ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።  » ነበር ያለው። ማቴዎስ 1፥21። አውሳብዮስም ሆነ ከእርሱ በኋላ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የመልአኩ ቃል ያስተዋሉት፤ (ወንጌላዊውም ጭምር ማለት እንችላለን) የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ የነገረው ስም የእግዚአብሔር ስም መሆኑን ነው። እርግጥ ነው፥ በትንቢት፥ በምሳሌና በጥላ ቀድሞ ለተነሡት « አዳኞች» ኢያሱዎች ተሰጥቶአል። (ለምሳሌ ዘካርያስ 3፥1 ላይ የተጠቀሰውን ከምርኮ በኋላ እስራኤልን የመራው ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን ያስታውሷል።) 

Tuesday, June 4, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት አራተኛ ክፍል

 Read in PDF
ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም። 
ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።

  

መግቢያ 

በነገረ መለኮት ትንታኔው የሚታወቅ አንድ ሊቅ ሲናገር የሃይማኖት ስህተቶች ሁሉ የሚጀምሩት የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ባለመረዳት ነው ብሎአል። በመሆኑም የጸሎተ ሃይማኖት መሰጠትንም ሆነ ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ ያለውን ጊዜ ተከትለው የተደረጉትን ጉባኤያት ብንመለከት በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚሰነዘሩት የስህተት ትምህርቶችን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ልንገልጣቸው ቶማስ አኵናስ የተባለው ሊቅ ይነግረናል። 

• ክርስቶስ ሰው ብቻ ነው የሚሉ፤ 
ለምሳሌ ፎጢኖስ የተባለው « ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፤ ነገር ግን መልካም ሰው ነው። በመልካም አነዋወሩና ሕይወቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማድረጉ በማደጎ (adoption) የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ተጠርቶአል» በማለት አስተምሮአል። ያ ብቻ አይደለም የክርስቶስ ሕልውና የሚጀምረው ከማርያም ከተወለደ በኋላ ነው በማለት ክርስቶስ በጊዜ የተወሰነ እንደሆነ አስተምሮአል። የእግዚአብሔር ቃል ግን እነዚህ አስተሳሰቦች ሐሰት እንደሆኑ በግልጥ ይመሰክራሉ። ዮሐንስ በወንጌሉ « እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለው አንድ ልጁ እርሱ ተረከው» በማለት ወልድ በቅድምና ከአብ ጋር እንደነበር ይናገራል። ዮሐንስ 1፥18፤ ኢየሱስም ራሱ « አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ» ብሎ ሲናገር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከመወለዱ በፊት ከአብርሃም በፊት መኖሩን ነግሮናል። ዮሐንስ 8፥58። 

• ክርስቶስ ራሱ አብ ነው የሚሉ፤ 
በዚህ ስህተቱ የታወቀው ሰባልዮስ የተባለው ሰው ነው። ሰባልዮስ ጌታ ቅድመ ዓለም መኖሩን ያምንና ነገር ግን በሥጋ የተገለጠው ቅድመ ዓለም የነበረው አብ ነው ብሎ ያስተምር ነበር። በእርሱ ትምህርት አብና ወልድ ሁለት አካላት ሳይሆኑ አንዱ አብ ነው በተለያየ መንገድ የተገለጠው። አሁንም የሰባልዮስን ስሕተት የእግዚእብሔር ቃል በግልጥ ይቃወመዋል። ጌታ ራሱ « የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁም» በማለት ከአባቱ እንደተላከ» በዮሐንስ 8፥16 ላይ ገልጦአል። 

• ልዩ ፍጡር ነው የሚሉ፤ 
አርዮስ የተባለው የስሕተት አስተማሪ ስለጌታ ያስተማረው ትምህርት ከቅዱሳት ጋር የሚቃረን ነበር፤ አንደኛ ክርስቶስ ፍጡር ነው። ሁለተኛ፥ ከዘለዓለም ያልነበረና ከሌሎች ፍጡራን ልዩ አድርጎ እግዚአብሔር የፈጠረው ነው ። ሦስተኛ፥ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ ስላይደለ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም እውነተኛ አምላክ አይደለም በማለት ያስተምር ነበር። አሁንም የአርዮስን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ሲሽርበት ጌታ « እኔና አብ አንድ ነን» በማለት በባሕርይ ከአባቱ ጋር አንድ መሆኑ ሲገልጥ እናያለን።  

እነዚህ ከላይ ያያናቸው በየዘመኑ ከተነሡት ለናሙና ያነሣናቸው ስህተቶች ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በክርስቶስ ላይ ለሚሰነዘሩት ስህተቶች መሠረቶች ናቸው። « የኑፋቄ አዲስ የለውም» የሚባለው ለዚህ ነው። ሆኖም ቶማስ አኵኖስ ይህ ሁሉ በየጊዜው የሚነሣው ስህተት  ወንጌላዊው ዮሐንስ  በወንጌሉ መክፈቻ ላይ ያስቀመጣቸው ዐረፍተ ነገሮች « በመጀመሪያ ቃል ነበር» የፎጢኖስን « ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» የሰባልዮስን፥ « ቃልም እግዚአብሔር ነበረ» የአርዮስን ስህተት ይደመስሰዋል ብሎአል ።   

ኢየሱስ ማንነው? 

በጊዜው  በሥጋ ያዩት የሃይማኖት መሪዎች፥  የሕዝብ አስተዳዳሪዎች፥ ደቀ መዛሙርቱ እና ሌላውም ሕዝብ  በአንድነት የጠየቁትን ጥያቄ እርሱ ማንነው? የሚል ነው። እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው በማለትና  በመጠየቅ ስለ አዳኛችን ስለመድኃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥልቀት እናጠናለን።

ሽባውን ሰው « ኃጢአትህ ተሰረየችልህ» ሲለው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ያሉት « ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?  ብለው ያስቡ ጀመር።» ሉቃስ 5፥21። እንደገና ኃጢአተኛዋን ሴት « ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል» ሲላት በማዕድ ከርሱ ጋር ተቀምጠው የነበሩት « ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?» ብለው ነበር። ሉቃስ 7፥48-49።  ዮሐንስን ያስገደለው ሄሮድስም  « ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው?  » በማለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማየት አጥብቆ ይሻ እንደነበረ ሉቃስ ይነግረናል? ሉቃስ 9፥9። ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባና ከተማዋ ስትናወጥ ሕዝቡ « ይህ ማነው?» በማለት ነው የጠየቁት። ደቀ መዛሙርቱም በብዙ ቦታ ስለጌታ የበለጠ ለማወቅ ፈልገው በፍርሃት ዝም እንዳሉ እናያለን? ሉቃስ 9፥45።   
በእነዚህ ሁሉ ሰዎች እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከሁን በተነሳውም ትውልድ ይህ ማነው የተባለውን፥  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በኒቅያ የተሰበሰቡ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች የገለጡበትን መንገድ ለመረዳት በወንጌል ላይ ጌታ ስለራሱ የተናገረውን መረዳት ይገባል።

Tuesday, May 28, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት ካለፈው የቀጠለ (ሦስተኛ ክፍል)

Read in PDF
ነአምን በ፩ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኵሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ

ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። 

እስከ አሁን እግዚአብሔር በገለጠልን መጠን ስለ አንድነቱና ስለሦስትነቱ ማለትም ስለምሥጢረ ሥላሴ ተምረናል። ምሥጢረ ሥላሴ ማለት የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት እንደሆነ፥ ይህም ማለት አንዱ እግዚአብሔር ሦስት እኔነት ሦስት እኔ ነኝ ባይ አካላት እንዳሉት አይተናል። የእግዚአብሔር የሦስትነት ስሙም አብ ወልድ መንፈስ ነው። እርስ በእርሳቸውም የሚገነዛዘቡበት የኵነት ስማቸውም ልብ፥ ቃል እስትንፋስ ነው። ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ለዚህ ትምህርታቸው መሠረት ያደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትንና አገላለጾችን ነው። 

ሆኖም ከዚህ በፊት እንዳልነው ምሥጢረ ሥላሴን ገልጦ ለመጨረስ መሞከር አይቻልም። ወይም የአባቶቻችንን አገላለጥ ለመጠቀም ውቅያኖስን በዕንቁላል ቅርፊት ጨልፎ ለመጨረስ እንደመሞከር ነው። ባለፉት ክፍሎች ያነሣናቸው ነጥቦች ለጊዜው ደብዘዝ ቢሉብን ብዙ አንጨነቅ፤ የበለጠ ስለ ራሳችን ማንነት ባየን ወቅት የበለጠ ስለመዳናችን ስንወያይ፥ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ግልጥ ይሆንልናል። ይህ ግን እምነታችን ነው። « በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን። አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው። በአካል ሦስት ናቸው። በመለኮት በአገዛዝ በሥልጣን አንድ ናቸው። አብ እኛን ከመውደዱ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ አንድያ ልጁን ወልድን ሰዶልናል። ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖአል። በመሰቀል ተሰቅሎ ሞቶ ተነሥቶ አድኖናል። አሁን በክብር አርጎ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦአል። መንፈስ ቅዱስ ቀድሞ ፍጥረትን ያስተናበረ ሕይወትና ውበት የሰጠ (ዘፍጥረት 1፥2) አሁን ደግሞ በክርስቶስ የተከናወነው የማዳን ሥራ እውን እንዲሆን በሞተው ሕይወታችን ውስጥ ሕይወት ሰጥቶናል። ቀድሶናል። 

ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ ፤ 

ሀ.  ሥነ ፍጥረት 

አባቶቻችን ይህን የሚታየውንና የማይታየውን  ዓለም ሰማዩንና ምድሩን እግዚአብሔር የፈጠረበትን መንገድ በሃይማኖት (በሳይንስ አይደለም) ያጠኑበት ትምህርት ሥነ ፍጥረት ይባላል። እነቅዱስ ባስልዮስ፥ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ያስተማሩበት ሄክሳሜሮስ ወይም አክሲማሮስ በሚል ይታወቃል። ስድስቱን የፍጥረት ቀናት የሚያመለክት ነው።   ዛሬ ሳይንሱ ከፍተኛ ርቀትና ጥበብ ውስጥ ባለበት ወቅት የአባቶቻችንን የሥነ ፍጥረት መንገድ የምናጠናው ለምንድነው ተብሎ ይነሣ ይሆናል። ዛሬ ከመቼውም በበለጠ ስለ ፍጥረት እያየን ባለንበት ወቅት የእግዚአብሔርን ታላቅነት የኑሮአችንና የምርምራችን ማዕከል ልናደርገው ይገባል። 

ስለፍጥረት ስንመምረምር የሚከተሉትን ነጥቦች ልንረዳ ይገባል። 

1. እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው በሦስትነቱ ነው። 

እግዚአብሔር አብ በልብነቱ አስቦና ፈቅዶ ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ፥ ፈቀደ፥ ፈጠረ (ራዕ 4፥10_11
እግዚአብሔር ወልድ ዓለም የተፈጠረበት ቃል ነው። እግዚአብሔር አብ ዓለምን የፈጠረው በቃሉ ነው። ዮሐንስ በወንጌሉ እንደነገረን ሁሉ በእርሱ (በቃል) ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ (ያለ ቃል) አልሆነም። ዮሐንስ 1፥3። ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ወልድ ሲናገር « በሰማይና በምድር በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።» ቆላ 1፥16። 
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለፍጥረቱ መልክና ቅርጽ፥ ሕይወት የሰጠ ነው።  ሙሴ የፍጥረትን ታሪክ ሲጽፍ « « የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር» ይለናል። ዘፍጥረት 1፥2። 

2. እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው በሉዓላዊ ፈቃዱ ነው። 
እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው ማንም አስገድዶት አይደለም። ወይም ለሕልውናው አስፈልጎት አይደለም። ዓለማትን የፈጠረው በፈቃዱ ነው። ራዕ 4፥10 

Wednesday, May 22, 2013

መዝሙረ ዳዊት 9 ወይስ 10 ?



የእንግሊዘኛውን መዝሙረ ዳዊትና የአማርኛውን ወይም የግእዙን መዝሙረ ዳዊት ብትመለከቱ ወዲያው የምታስተውሉት ነገር ቢኖር፥ የምዕራፎቹ መለያየት ነው። ይህ የምዕራፎቹ መለያየት የሚጀምረው በመዝሙር 9 ላይ ነው። የግእዙና የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ የግሪክኛውን የሰብዓ ሊቃናቱን ትርጉም አከፋፈል ተከትሎ መዝሙር ዘጠኝን በ38 ቁጥሮች ሲያስቀምጥ፥ የእንግሊዘኛዎቹ ትርጉሞች ግን (ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትርጉሞች በስተቀር)  የዕብራይስጡን የማሶሬያቲክ ዘር ተከትለው መዝሙር ዘጠኝን ለሁለት ከፍለውት እናገኛለን።  አንዳንዶች ወገኖቻችን የዕብራይስጡ አከፋፈል ከፍ ያለ ክብር እንዳለው አድርገው ሊያሳዩን ይፈልጋሉ። ይህ ግን ልክ አይመስለኝም። እርግጥ ነው፥ መዝሙረ ዳዊት ከዕብራውያን ትውፊት የተገኘ ነው። ነገር ግን የማሶሬያቲክ ዘር ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመቶዎቹ ዓመታት ዘግይቶ የተሰባሰበ ሲሆን የሰባ ሊቃናቱ ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት የሆነ ነው። ለምሳሌ መዝሙር ዘጠኝን ከተመለከትን የዕብራይስጡን ፊደል ተከትሎ የተጻፈ ስለሆነ ምዕራፍ ዘጠኝና አስር የሆነው መሐል ላይ ተከፍሎ ነው። በመሆኑም ብዙዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋ መተርጉማን መዝሙሩ አንድ ምዕራፍ እንደህነ ይስማሙበታል። ያም ሆነ ይህ የምዕራፉ ልዩነት በአማርኛ ለሚያነበውም ሆነ ከእንግሊዘኛው ጋር ለሚያገናዝበው ግራ ማጋባቱ እርግጥ ነው። ይህ የምዕራፍ ልዩነት የሚጀምረው ምዕራፍ 9 ላይ ይሁን እንጂ በየቦታው ልዩነት ስላለው ልዩነቱን ለመገንዘብ የሚከተሉትን ማየት መልካም ነው።  በእንግሊዘኛ ስናነብም ሆነ አንዳንድ በዲጂታል የተጻፉትን ስናነብ ይህን የምዕራፍ ልዩነት ልናስተውል ይገባል።

የግሪኩ አቆጣጠርየእብራይስጡ አቆጣጠር
1-81-8
99 and 10
10-11211-113
113114 and 115
114116:1-9
115116:10-19
116-145117-146
146147:1-11
147147:12-20
148-150148-150

Tuesday, May 21, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (ክፍል ሁለት) ካለፈው የቀጠለ

Read in PDF
ባለፈው ትምህርታችን ስለ ጸሎተ ሃይማኖት መጻፍ ታሪካዊ ምክንያቱን አትተን ስለ እግዚአብሔር አንድነት ሦስትነት በመጠኑ አትተን ነው ያቆምነው።  ዛሬ ከዚያ በመነሣት በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርታችን ላይ ሊነሡ የሚችሉትን ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን እናያለን። በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ያሉትን ቃላትና ሐረጎች በመተንተን መንፈሳዊ ትርጉማቸውንም እናያለን። 

1. ምሥጢረ ሥላሴ ማለት ምን ማለት ነው?

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተማርነው መሠረት አንድ አምላክ በሦስት አካላት እንዳለ የምናምንበት የምንማርበት እውነት ነው።

2. ምሥጢረ ሥላሴ በሃይማኖት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ( የበቁ) ሰዎች የሚማሩት ነው?

አይደለም። እንዲያውም ገና ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች ሊማሩት የሚገባቸው ነገር ቢኖር አንዱ እግዚአብሔር በሦስትነት እንደተገለጠ ነው። ምሥጢረ ሥላሴ በፍልስፍና የምንማረው ሳይሆን በእምነት የምንቀበለው ስለሆነ። ዘዳግም 29፥29

3. የሥላሴ ትምህርት ለምን ምሥጢር ተባለ?

በኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ዘንድ ምሥጢር የተባለው የሥላሴ ትምህርት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ  እምነታችን ነው። ምሥጢር ሲባል የተደበቀ የተሰወረ ማለት ሳይሆን

•    አንደኛ ራሱ እግዚአብሔር የሰው አእምሮ ተመራምሮ የማይደርስበት፤ 1 ጢሞቴዎስ 6፥16። ኢዮብ 11፥7_12፤

« እስመ እግዚአብሔር ኢይትረከብ በሕሊና እጓለ እመሕያው ወሕሊና እጓለ እመሕያው ኢይረክብ መለኮተ፤ ወህላዌ መለኮት ርኁቅ እምሕሊና እጓለ እመሕያው ወይትሌዐል ኵሎ ሕሊናተ ፈድፋደ።   እግዚአብሔር በሰው ልጅ አስተሳሰብ ውስጥ አይገኝም። የሰው አስተሳሰብም መለኮትን ሊያገኝ አይችልም። የመለኮት አነዋወር (ሕላዌ መለኮት ከሰው ልጅ ሕሊና የራቀና ከህሊናት ሁሉ እጅግ ከፍ ያለ ነውና። ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ

• ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ማንም በማይደርስበት ብርሃን ቢሆንም ራሱን ለፍጥረቱ ገልጦአል። መጀመሪያ ራሱን በፍጥረቱ በኩል ገልጦአል። መዝሙር 32፥6፤ ሐዋ 17፥24_28። ሮሜ 1፥20_21። በቃሉ ራሱን ገልጦአል። ቃሉን በባሪያዎቹ በኩል እየላከ እግዚአብሔር ማንነቱ በብዙ መንገድ ገልጦአል። 2 ጴጥሮስ 1፥21። መጨረሻም ራሱን በልጁ ገልጦአል። ዮሐ 1፥14፡18፤ ዕብራውያን 1፥1።

•  ሦስተኛ፥ ወደዚህ ዕውቀትም ስንመጣ በዚህ ዕውቀት ለዘለዓለም ስለምንኖር ወደአምልኮ ይመራናል እንጂ አያስታብየንም። ምክንያቱም የምናመልከው አምላክ ሁል ጊዜ አዲስ ነውና። ሐዋርያም እንደተናገረው « ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና» የአምላካችንን ግርማውንና ጌትነቱን እያየን እናመሰግነዋለን። 

Tuesday, May 14, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (የሃይማኖት ጸሎት)



ነአምን በ፩ዱ፡ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኲሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ። 

ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። 

መቅድም 

ሀ. ስሙ 
1. ጸሎተ ሃይማኖት 
2. የኒቅያ የሃይማኖት መግለጫ (ውሳኔ ሃይማኖት፤ አንቀጸ ሃይማኖት) Nicene Creed 
3. የኒቅያ ቁስጥንጥንያ ውሳኔ ሃይማኖት Nicene-Constantinopolitan Creed

ለ.  ለምን አስፈለገ?
1. « መለኮታዊውንና ሐዋርያዊውን እምነት ጠቅልሎ ያስቀመጠ ስለሆነ።» ቅዱስ አትናቴዎስ 
2. ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ግልጥ በማድረግ ከክህደት ምእመናን ለመጠበቅ ነው። 
3. እያንዳንዱ ቃልና ሐረግ የክርስቲያንን እምነት የሚያጠነክር ስለሆነ ነው። 
4. ቤተ ክርስቲያን ልትሆነውና ልታደርገው የሚገባትን ነገር የሚያመለክት ነው። 

ሐ. በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ያለው ልዩ ቦታ 
1. በመላው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት ያለው አንቀጸ ሃይማኖት ነው። 
2 የክርስቶስን አምላክነት የመንፈስ ቅዱስ አምላክነት  በማብራራት ቤተ ክርስቲያንን ከታላቅ አደጋ የታደገ ነው።   
3. በኒቅያ በ325 ዓ.ም ላይ   እንደገና በ381 ዓ.ም ላይ በቁስጥንጥንያ በተከናወነው ኢኩሜኒካል ጉባኤ ላይ ተጨማሪ አንቀጾች ( መንፈስ ቅዱስን የሚመለከቱ) ገብቶለት ቤተ ክርስቲያንን በቀጥተኛ ሃይማኖት (ኦርቶዶክስ) የመራ ነው። 

መ. በቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት ያለው ቦታ
1. በጸሎት ማለትም በቅዳሴ ጊዜ በካህናትና በምእመናን ይደገማል። 
2. የሚጠመቁ ሰዎች እምነታቸውን የሚገልጡት ጸሎተ ሃይማኖትን አሰምተው በመድገም ነው። (የክርስትና አባትና እናት ስለሕፃኑ ፈንታ ሁነው በጸሎተ ሃይማኖት እምነታቸውን መመስከር አለባቸው።  
3. የክርስትና መለያ ምልክት ስለሆነ በምኩራብ የእምነት መግለጫ የሆነው « እስራኤል ሆይ ስማ (ሼማ)በሚለው የአይሁድ አንቀጸ ሃይማኖት ትይዩ ሊታይ የሚችል ነው። 

መ. ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለው ግንኙነት 
1. ጸሎተ ሃይማኖት በተደነገገ ወቅት ገና የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ገና አልተቋጨም ነበር። 
2. ጸሎተ ሃይማኖት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የያዘ ስለሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ለመወሰን ማለትም የትኞቹ መጻሕፍት በቅዱሳት መጻሕፍት ቁጥር መግባት እንዳለባቸው ለመወሰን አገልግሎአል። 


ክፍል አንድ 
ነአምን በአሐዱ አምላክ እግዚአብሔር አብ


ሀ. እናምናለን።  (ነአምን) 

እምነት ደረቅ የሆነ የመረጃ ጥርቅም ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ የሚያመጣ የመዳን መንገድ ነው። እናምናለን የምንለው እውነት በጸሎታችን፥ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ እንዴት ባለ መንገድ መመራት እንዳለብን የሚያሳስብ ነው። የሰውን ሁለንተና የሚነካ ነው። 

• እምነት አእምሮን ይዛል፤ በመሆኑም « ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ እናምናለን» ብለን ስንናገር፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዓለምን የምናየው በተለየ መንገድ ነው። 
• እምነት ፈቃድን ይይዛል፤ እምነት ማለት በፈቃዳችን ወደ እኛ ለቀረበው ለእግዚአብሔር መስጠታችን ነው። 
• እምነት ስሜትን ይይዛል፤ እምነት ማለት ላዳነን ለእግዚአብሔር የምንሰጠው የፍቅር ምላሽ ነው። ይህ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ደግሞ ሌሎችን በመውደድ ይገለጣል። 

በመሆኑም እምነት አራት መልካም ነገሮችን በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያከናውናል። 

1. አንደኛው በእምነት በኩል ነፍስ ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት ይኖራታል። ሆሴዕ 2፥2። 
እምነት ሳይኖረው ማንም ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። (ማር 16፥16) 
ያለእምነት የሆነ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው። ሮሜ 14፥23 
« ዘላለማዊውንና የማይለወጠውን እውነት ማወቅ በሌለበት ሥፍራ በመልካም ምግባር የተጌጠ ሕይወት እንኳ ሐሰት ሊሆን ይችላል።» አውግስጢኖስ። 



2. ሁለተኛው የእምነት ውጤት የዘላለም ሕይወት ነው።
ያለ እግዚአብሔርን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ምንም ማለት አይደለም። ዮሐ 17፥3። ይህ እግዚአብሔርን ማወቅ የሚጀምረው በእምነት በኩሉ አሁን በዚህ ምድር ሳለን ነው።  ይህ እውቀት ፍጹም የሚሆነው ግን እግዚአብሔርን በሙላቱ ስናውቀው ወደፊት ነው።  እምነት ተስፋ የምናደርገውን ነገር የሚያስረግጥ ነው። ዕብራውያን 11፥1። በመጀመሪያ እግዚአብሔርን በእምነት በኩል ሳያውቀው ማንም ሰው ፍጹም ወደሆነው ወደሰማያዊ ደስታ እርሱም ወደ እውነተኛው እግዚአብሔርን ማወቅ መድረስ አይችልም። « ሳያዩኝ የሚያምኑኝ ብፁዓን ናቸው። ዮሐንስ 20፥29። 


3. ሦስተኛው ከእምነት የሚገኝ መልካም ነገር ለዛሬው ሕይወታችን ትክክለኛውን አቅጣጫ ይሰጠናል ወይም ያመላክተናል።
አንድ ሰው መልካም ኑሮ ለመኖር፥ በትክክለኛ መንገድ ለመኖር የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ አስፈላጊ ነው ። ይህን ለማወቅ ደግሞ በራሱ ጥረት ብቻ የሚደገፍ ከሆነ፥ ይህን እውቀት ሊያገኝ አይችልም ወይም ብዙ ድካም ይጠይቅበታል። እምነት ግን መልካም ሕይወትን እንዴት መኖር እንደሚቻል ያስተምረናል። « ጻድቅ በእምነት ይኖራል።» ያዕቆብ 2፥4። 


4. አራተኛው የእምነት ውጤት በእምነት ፈተናን ድል እናደርጋለን። 
« በእምነት ቅዱሳን መንግሥታትን ድል ነሡ» ዕብራውያን 11፥33። ማናቸውም ፈተና  ከዓለም ወይም ከሥጋ ወይም ከዲያብሎስ ነው። ዲያብሎስ ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ እንድናምጽበት ይሻል። 1 ጴጥሮስ 5፥8። ዓለም ደግሞ በብልጥግናዋ ከእርሷ ጋር እንድንጣበቅ በማድረግ ወይም ደግሞ በባላጋራነት በማስፈራራት ትፈትነናለች። ነገር ግን እምነት ግን የሚመጣውን እና የተሻለውን ሕይወት በማመን ይህን ድል ያደርገዋል።  « ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችሁ ነው። 1 ዮሐንስ 5፥4። ሥጋ ደግሞ በአንጻሩ የሚፈትነን ቶሎ ወደሚያልፉት የአሁኑ አለም እርካታዎች እንድንሳብ በማድረግ ነው። ነገር ግን እምነት ደግሞ በእነዚህ ጊዜያዊ ነገሮች ላይ ብንጠለጠል ዘላለማዊውን ደስታችንን እንደምናጣ ያሳየናል። « በሁሉም ነገር የእምነትን ጋሻ ውሰዱ። 

ለ. በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ  (በአሐዱ አምላክ እግዚአብሔር አብ )

በክርስትና እምነታችን ውስጥ ዋናውና ማዕከላዊው ነጥብ ምሥጢረ ሥላሴ ነው።
አንድ ሊቅ ሲናገር « ምሥጢረ ሥላሴን ካድ፥ መዳንህን ታጣለህ፤ ምሥጢረ ሥላሴን ጠቅልለህ ለማወቅ ሞክር አእምሮህን ታጣለህ።» ብሎአል።

1. ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መረዳት የምንችለው እግዚአብሔር  በቃሉ ማለትም በቅዱሳት መጻሕፍት ራሱን የገለጠበትን መንገድ በመረዳት ነው።

• የእግዚአብሔር አንድነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተብራርቶ ተጠቅሶአል። ዘዳግም 6፥4-5፤ 2 ሳሙኤል 7፥22፤ ኢሳይያስ 45፥18።
  • የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት በአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ተብራርቶ ተገልጧል። ዮሐንስ 1፥1፤ 20፥28፤ ሮሜ 9፥5፤ ቲቶ 2፥13፤ቅ
• ቃል በመጀመሪያ እንደነበረ፤ (ዮሐንስ 1፥1፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደነበረ  ዮሐንስ 1፥1፤ ቃልም እግዚአብሔር እንደሆነ (ዮሐንስ 1፥1) ቃልም ሥጋ እንደሆነ (ዮሐንስ 1፥14) ያ ቃል (ልጁ) በአባቱ ዘንድ ያለውን እንደተረከልን (ዮሐንስ 1፥18) ያስተምረናል። 
• መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ባመኑት ላይ ማደሩና ቤተ ክርስቲያንን መምራቱ በሰፊው በአዲስ ኪዳን ተገልጧል። ዮሐ 14፥15-17።

  1. ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጠው እውነት የሚያሳየን እውነት ምንድነው።

•  እግዚአብሔር በአንድነቱ አለ።
• እግዚአብሔር በሦስትነቱ አለ። ይህ አንዱ እግዚአብሔር ሦስት አካላት ማለትም አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ነው። ሦስቱም አካላት በመለኮት አንድ ስለሆኑ አብ እግዚአብሔር ነው፤ ወልድ እግዚአብሔር ነው። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። በአንድነቱ ውስጥ ሦስትነቱ አለ። በሦስትነቱ ውስጥ አንድነቱ አለ።
• እነዚህ ሦስቱ አካላት በሥማቸው እና በግብራቸው አንዳቸው ከሌላቸው ልዩ ናቸው።
አብ በአባትነቱ አብ ተብሎአል። ወልድ በልጅነቱ በልደቱ ወልድ ተብሎአል። መንፈስ ቅዱስም ከአብ የወጣ በመሆኑ ከአብ የወጥ ( ሠራፂ) ተብሎአል።

ቤተ ክርስቲያን በጸሎቱዋ « ለአብ፥ ለወልድ፥ ለመንፈስ ቅዱስ እሰግዳለሁ፤ አንድ ሲሆኑ ሦስት፤ ሦስት ሲሆኑ አንድ፥ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ለሚሆኑ» በማለት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በእምነት ትመሰክራለች። (ጸሎት ዘዘወትርን ተመልከት።
  1. ቤተ ክርስቲያን ጸሎትዋ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርቷን የሚያመለክት ነው።

• ጸሎታችንን የምናቀርበው ወደአብ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው።
 ___ አባታችን ሆይ ብለን እንጸልያለን።
___ በእንድ ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ብለን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንጸልያለን።
___ በመንፈስ ቅዱስ ተመልተንና ተመርተን እንጸልያለን።

  1. ቤተ ክርስቲያን ሕይወቷ ምሥጢረ ሥላሴን የሚያመለክት ነው።

• ምሥጢረ ሥላሴ የሚያስተምረን የመጀመሪያው እውነት የእኛ ማንነት ያለው ከክርስቶስ አካል ጋር ባለን ሕይወት እንጂ በግለኝነት በሚኖረን ሕይወት አይደለም።
• ሁለተኛው ትምህርት እግዚአብሔር ፍቅር ነው። የእግዚአብሔር ፍቅርም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል እንዲሁም ለፍጥረቱ በሙሉ እግዚአብሔር ባለው ፍቅር ታይቶአል። ይህ ፍቅር በሥላሴ የምናምን እኛም ለፍጥረት ሁሉ ፍቅርን እንድገልጥ ያስተምረናል።


ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ስጡ



1. ጸሎተ ሃይማኖት በስንት ዓ. ም ተወሰነ?ለምንስ ጸሎተ ሃይማኖት ተባለ? ሌላ ስሙስ ማን ይባላል? 

2. የጸሎተ ሃይማኖት አከፋፈል እንዴት ነው? 

3. እምነት በሕይወታችን ውስጥ  ምን ዓይነት ፍሬ ያፈራል? 

4. ስለ ምሥጢረ ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? 

5. ስለ እግዚአብሔር ወልድ  ወይም ስለእግዚአብሔር ቃል በተብራራ መልኩ የምናገኘው በየትኛው ወንጌል ነው። ምዕራፍና ቁጥር ጥቀሱ። 

6. ሥላሴን መርምረን በምልዓት ልንረዳ እንችላለን ወይ? አብራሩ።