Tuesday, May 21, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (ክፍል ሁለት) ካለፈው የቀጠለ

Read in PDF
ባለፈው ትምህርታችን ስለ ጸሎተ ሃይማኖት መጻፍ ታሪካዊ ምክንያቱን አትተን ስለ እግዚአብሔር አንድነት ሦስትነት በመጠኑ አትተን ነው ያቆምነው።  ዛሬ ከዚያ በመነሣት በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርታችን ላይ ሊነሡ የሚችሉትን ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን እናያለን። በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ያሉትን ቃላትና ሐረጎች በመተንተን መንፈሳዊ ትርጉማቸውንም እናያለን። 

1. ምሥጢረ ሥላሴ ማለት ምን ማለት ነው?

በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተማርነው መሠረት አንድ አምላክ በሦስት አካላት እንዳለ የምናምንበት የምንማርበት እውነት ነው።

2. ምሥጢረ ሥላሴ በሃይማኖት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ( የበቁ) ሰዎች የሚማሩት ነው?

አይደለም። እንዲያውም ገና ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች ሊማሩት የሚገባቸው ነገር ቢኖር አንዱ እግዚአብሔር በሦስትነት እንደተገለጠ ነው። ምሥጢረ ሥላሴ በፍልስፍና የምንማረው ሳይሆን በእምነት የምንቀበለው ስለሆነ። ዘዳግም 29፥29

3. የሥላሴ ትምህርት ለምን ምሥጢር ተባለ?

በኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ዘንድ ምሥጢር የተባለው የሥላሴ ትምህርት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ  እምነታችን ነው። ምሥጢር ሲባል የተደበቀ የተሰወረ ማለት ሳይሆን

•    አንደኛ ራሱ እግዚአብሔር የሰው አእምሮ ተመራምሮ የማይደርስበት፤ 1 ጢሞቴዎስ 6፥16። ኢዮብ 11፥7_12፤

« እስመ እግዚአብሔር ኢይትረከብ በሕሊና እጓለ እመሕያው ወሕሊና እጓለ እመሕያው ኢይረክብ መለኮተ፤ ወህላዌ መለኮት ርኁቅ እምሕሊና እጓለ እመሕያው ወይትሌዐል ኵሎ ሕሊናተ ፈድፋደ።   እግዚአብሔር በሰው ልጅ አስተሳሰብ ውስጥ አይገኝም። የሰው አስተሳሰብም መለኮትን ሊያገኝ አይችልም። የመለኮት አነዋወር (ሕላዌ መለኮት ከሰው ልጅ ሕሊና የራቀና ከህሊናት ሁሉ እጅግ ከፍ ያለ ነውና። ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ

• ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ማንም በማይደርስበት ብርሃን ቢሆንም ራሱን ለፍጥረቱ ገልጦአል። መጀመሪያ ራሱን በፍጥረቱ በኩል ገልጦአል። መዝሙር 32፥6፤ ሐዋ 17፥24_28። ሮሜ 1፥20_21። በቃሉ ራሱን ገልጦአል። ቃሉን በባሪያዎቹ በኩል እየላከ እግዚአብሔር ማንነቱ በብዙ መንገድ ገልጦአል። 2 ጴጥሮስ 1፥21። መጨረሻም ራሱን በልጁ ገልጦአል። ዮሐ 1፥14፡18፤ ዕብራውያን 1፥1።

•  ሦስተኛ፥ ወደዚህ ዕውቀትም ስንመጣ በዚህ ዕውቀት ለዘለዓለም ስለምንኖር ወደአምልኮ ይመራናል እንጂ አያስታብየንም። ምክንያቱም የምናመልከው አምላክ ሁል ጊዜ አዲስ ነውና። ሐዋርያም እንደተናገረው « ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና» የአምላካችንን ግርማውንና ጌትነቱን እያየን እናመሰግነዋለን። 


4.  የእግዚአብሔር አንድነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሷል?

አዎን፤ በብሉይ ኪዳን በዘዳግም 6፥4 ላይ የተጠቀሰውን ቤተ አይሁድ የሃይማኖታቸው መግለጫ ወይም
አንቀጸ ሃይማኖት አድርገው ተጠቅመውበታል። በኢሳይያስ 44፥8 ላይም እግዚአብሔር «ከኔ ሌላ አምላክ አለን?» በማለት ሲጠይቀን? በዚሁ በኢሳይያስ 45፥22 ላይ « ከእኔ በቀር ማንም የለም» በማለት ይመልሳል።  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በማርቆስ 12፥29 ላይ የዘዳግም 6፥4ን ቃል ማለትም « ሼማ»ን ጠቅሶ ሰለእግዚአብሔር አንድነት አስተምሮበታል። በቅዳሴያችን ጊዜ የምንዘምረው መዝሙር 85፥8፡10 « አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም። አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።» ይላል። ጳውሎስም በ1፥ ቆሮ 8፥6 ላይ «ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥»  በሎአል። 

5. እግዚአብሔር አንድ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው?

እግዚአብሔር « በአገዛዙ (በመንግሥቱ) በመለኮት (በአምላክነቱ) በባሕርይ(በህላዌ) በፈቃድና በሥልጣን አንድ ነው።

6.  የእግዚአብሔር የአንድነት ስሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሰዋልን?

አዎን ተጠቅሰዋል። አምላክ መዝሙር 17፥31።  መለኮት ሮሜ 1፥2  ኤልሻዳይ ዘፍጥረት 17  ይሆዋ፥ ዘጸአት 6፥3_8። አዶናይ (በአማርኛ ጌታ እየተባለ ተተርጕሟል) (ሕዝቅኤል 7፥2_5)፤ ፀባዖት    (ኢሳይያስ 6፥3) ፤  ኤሎሂም መዝሙር 21፥1፤ እነዚህ ስሞች በአንድም መንገድ ሆነ በሌላ የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚገልጡ ናቸው።

7. ሥላሴ የሚለው ቃል ምንን የሚያመለክት ነው"
ሥላሴ የሚለው ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ያለችውን የተቀደሰች ሦስትነት « ቅድስት ሥላሴ» የሚያመለክት ነው።

7. የእግዚአብሔር የሦስትነት የሥላሴነቱ ስሞቹ እነማን ናቸው?

የሦስትነት ስሞቹ በሦስት መልክ ተገልጠው እናያለን
_ በስም፤ አብ ፥ ወልድ፥ መንፈስ፥ ቅዱስ፥ ማቴዎስ 28፥20፤ 2 ቆሮንቶስ 13፥13፤ ማቴዎስ 3፥17
_ በኩነት፤ ልብ፥ ቃል፥ እስትንፋስ መዝሙረ ዳዊት 32፥6፡11። ዮሐ 1፥1_30፤
_ በግብር፤ ወላዲና አሥራፂ፥ ተወላዲ፥ ሠራፂ። መዝሙረ ዳዊት 2፥7 ፤ 109፥3፤ ዮሐ 15፥26፤
እነዚህ የአካል፥ የኩነት፥ የግብራት ስሞች የእግዚአብሔር ሦስትነት የሚያመለክቱ የሦስትነቱ ስሞች ናቸው።

8. የኵነታት ሦስትነት ምን ዓይነት ነው?
አካላት መቀላቀልና መጠቅለል ሳይኖርባቸው በመለየት በመከፈል በየራሳቸው የሚቆሙ ናቸው። ማለትም ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው። ለወልድ ፍጹም አካል፥ ፍጹም ገጽ፥ ፍጹም አለው። ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል፥ ፍጹም ገጽ፥ መልክ አለው።  ይህ ማለት አብ አብ ነው እንጂ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይደለም። ወልድ ወልድ ነው እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ አብ ወይም ወልድ አይደለም። ለምሳሌ ሥጋ ለብሶ እኛን ያዳነን በተለየ አካሉ ወልድ ነው እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ ነው።

ሆኖም ይህ በአካላት ያለው ሦስትነት በአንድነት ውስጥ የሚገለጠው በኩነታት ነው። ኵነታት መለየትና መከፈል ሳይኖርባቸው በተዋሕዶና በአንድነት በሥላሴ ዘንድ ያለችን የአካል ሦስትነትን በሥላሴ ዘንድ ካለች አንዲት ሕልውና (አነዋወር) የሚያገናዝቡ ናቸው። ይህም ለአብ፥  በአብ መሠረትነት ራሱ ልብ (ለባዊ) ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ዕውቀት መሆን ነው። ለወልድም፥ በአብ መሠረትነት ወልድ ለራሱ ቃል (ነባቢ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው መሆን ነው። ለመንፈስ ቅዱስም በአብ መሠረትነት መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ሕይወት(ሕያው) ሆኖ፥ ለአብና ለወልድ ሕይወት መሆን ነው። (አለቃ ሕሩይ ፍኖተ እግዚአብሔርን ተመልከቱ)

9. አካል ስንል ምን ማለታችን ነው?

ራሱን የቻለ ለራሱ የበቃ፥ እኔ የሚል ህላዌ፤ የስምና የግብር ባለቤት ነው። እኔ ባይ የሆነ ስንል « ዕውቀት ቀዋሚነት» ያለው ማለታችን ነው። ይህ እኔ ባይነት (አካልነት) ከእግዚአብሔር ሌላ የሚሰጠው ለመላእክት እና ለሰው ነው። በሌላ በኩል እኔ ባይ ስንል አእምሮ ፈቃድና ስሜት ያለው ማለታችን ነው። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላትን ተመልከቱ)
• እግዚአብሔር ይናገራል። (ዘፍጥረት 1፥3።
• እግዚአብሔር ይሰማል። መዝሙር 93፥9።
• እግዚአብሔር ይቆጣል፥ ይራራል ዘዳግም 1፥37፤ መዝሙር 110፥4፤
• እኔ ብሎ የሚናገር ነው።

10. ለምሥጢረ ሥላሴ ትምህርታችን ምሳሌ የሚሆኑን ምሳሌዎች አሉን?
ለምሥጢረ ሥላሴ ትምህርታችን አስረጅ የሚሆኑ ምሳሌዎች አሉን ወደምሳሌዎቹ ከመግባታችን በፊት ግን ማስጠንቀቂያ ማስቀመጡ መልካም ነው። ይኸውም በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርታችን ውስጥ እጅግ አስቸጋሪው ነገር የሰው ቋንቋ ውሱንነት ነው። የሰው ቋንቋ የሥላሴን ምሥጢር ሙሉ በሙሉ ለመግለጥ አይችልም። በመሆኑም ይህ የሰው ቋንቋ ውሱንነት በምናቀርበውም ምሳሌ ላይ ገደብ ይኖረዋል። ሆኖም እነዚህ ምሳሌዎች ይጠቅሙናል ብርሃን ያሳዩናል። በብርሃኑ የምንመላለሰው ግን በእምነት ነው።  ምሳሌዎቹም የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ ሰው
ቀደም ሲል ያየነው የኵነታት ሦስትነትን በግልጥ የሚያሳየን በሰው ሕይወት ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር አርአያ ነው። ሰውን ሰው ያሰኘው እኔ ባይ አካሉ ነፍሱ ናት። ነፍስ ደግሞ ለባዊት (ልብ) ነባቢት (ቃል) እና ሕያዊት (እስትንፋስ) ናት። በአንድ ሰው ውስጥ እነዚህ ሕያው ነፍስ የሚያሰኙት የነፍስ ግብራት ተገልጠው ይታያሉ።

2ኛ ፀሐይ
ፀሐይን ስንመለከት ሦስት ክፍሎችን እናያለን። ክበቡዋ፥ ብርሃኑዋ እና ሙቀቷ። ክበቡዋ ወይም ዐውዷ እግዚአብሔር አብን፥ ብርሃኗ እግዚአብሔር ወልድን፥ ሙቀቷ ደግሞ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ያመለክታሉ።   እነዚህ ሦስቱ የፀሐይ ክፍሎች አንዷን ፀሐይ እንደማይከፍሏት በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ሦስትነትት የእግዚአብሔርን አንድነት አይከፍለውም።

3ኛ እሳት
በእሳት ውስጥም ሦስት ክፍሎችን እናያለን። አካሉ ወይም ፍሕሙ፥ ብርሃኑ፥ ሙቀቱ ናቸው። በፍሕሙ አብ ይመሰላል፥ በብርሃኑ ወልድ በሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላል።

ሁሉን በያዘ 

እግዚአብሔርን ያወቅነው ራሱን በገለጠበት በባህርዩ መገለጫዎች ነው። ከእነዚህ ባህርያት ውስጥ የተወሰኑት የእግዚአብሔር የብቻው የሆኑ ባሕርያት ሲሆኑ በሌሎች ፍጥረቶቹ ማለትም በሰዎችም ሆነ በመላእክቱ የማይገኙ ናቸው ። እነርሱም

• የእግዚአብሔር ዘላለማዊነት ( The Eternal God)
ጅማሬ የለውም ፍጻሜ የለውም፤  የማይለወጥ ነው። ጅማሬ የሌለው ስለሆነ መጀመሪያን የሚፈጥር ነው። ዘመንም የማይቀይረው ነው። መዝሙር 89፥2፤ መዝሙር 101፥ 27፤ ኢሳይያስ 40፥28፤ ራዕይ 1፥8።

• የእግዚአብሔር ሕያውነት ( The Living God)
እግዚአብሔር ከሌሎች አማልክት የሚለየው፥ ሌሎች አማልክት የሰዎች ምናብ ( imagination) ፈጠራዎች ሲሆኑ እግዚአብሔር ግን ሕያው አምላክ ነው። እርሱ ሕያው ስለሆነ ለፍጥረቱ የሕይወት መገኛ ነው። «እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው» ኤር 10፥10። የእግዚአብሔር ሕያውነት ከፍጥረቱ ጋር የተገናኘ አይደለም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው ይህ ዓለም ሲያልፍም እንኳ እግዚአብሔር ሕያው ነው። ሉቃስ 1፥33።

• የእግዚአብሔር ምሉዕነት ( The Omnipresent God)
ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው እግዚአብሔር  «ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም. . . በእርሱ ሕያዋን ነንና፤ እንንቀሳቀሳለን፥ እንኖርማለን።  »  ሐዋ 17፥28። ይኸው እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን « እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም።ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን?  » ኤርምያስ 23፥24። እግዚአብሔር በሁሉ የሞላ ነው ስንል ሙሉነቱ በምልዓት ነው። አንድ ሊቅ እንደተናገረው « የእግዚአብሔር ሐልዎት እንዳይታበት ትንሽ የሆነ የአቶሚክ ቅንጣት የለም። የእግዚአብሔር ሐልዎት እንዳይሸፍነው ሰፊ የሆነ ጋላክሲ የለም።» በሌላ ቋንቋ በቅንጣቱም በግዘፉ እግዚአብሔር በምልዓት ይገለጣል።

• የእግዚአብሔር ሁሉን ዓዋቂነት ( The Omnipresent God)
ፍጥረቱን ያለደረጃ፥ ያለመመዘኛ በምሉዕነት የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው። መዝሙር 93፥4፤ መዝሙር 138፤  ሁሉን አዋቂ ስለሆነ ሳይጀመር የነገሮችን ፍጻሜ ያውቃል። «በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ ምክሬ ትጸናለች » ኢሳይያስ 46 ፥10። ከዚህ ሁሉን አዋቂነቱ የተነሣ ሳንለምነው የሚያስፈልገንን እግዚአብሔር ያውቃል። ( ማቴዎስ 6፥8።) በእርሱ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተ ነው እንጂ የተሰወረ የለም። ( ዕብራውያን 4፥13)።

• የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ( The omnipotent God)
እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ነው። ለአብርሃምና ለሣራ እንደተናገረው እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ስለሆነ የሚሳነው ነገር የለም። (ዘፍጥረት 17፥1፡15_17፤ 18፥12 ) ኤርምያስ  በታላቅ መከራ ላይ ሳለ እንደተናገረው፥ ለእግዚአብሔር የሚያቅተው ነገር የለም። (ኤር 32፥17።)

እነዚህ ለእግዚአብሔር ብቻ የምንሰጣቸው ባህርያት ሲሆኑ፥ በፀጋው ለእኛ ያካፈላቸው ባህርያት ደግሞ አሉ። እነርሱም የእግዚአብሔር ጥበብ፥ ፍቅር፥ እውነተኛነት፥ ምህረት፥ ታማኝነት፥ መልካምነት፥ ትዕግሥት፥ ፀጋ፥ ጽድቅ ፍትህ ናቸው። እነዚህ በእግዚአብሔር ዘንድ በፍጹምነትና በምልዓት ሲገኙ ለእኛም በፀጋ ተሰጥተዋል።

የውይይት ጥያቄዎች

1. የኵነታትን  አሳብ የሚያብራራ አንድ ጥቅስ አንብባችሁ በራሳችሁ አሳብ ግለጡት፤

2. የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት በምናይበት ወቅት በፀሎታችን ሕይወት ውስጥ ለውጥ የሚያመጣ እውነት እናገኝበታለንን? ከሆነስ ምንድነው?

3. ለምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ አድርገን የተጠቀምንባቸው ምሳሌዎች ምን ምን ናቸው?

4. እግዚአብሔር አካል አለው ስንል ምን ማለታችን ነው?

5. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጡት የእግዚአብሔር የአንድነት ስሞች ምን ምን ናቸው።









1 comment: