Wednesday, September 10, 2014

ክሮኖስና ካይሮስ

ጥንታውያን ግሪኮች ለጊዜ ሁለት ስም ነበራቸው። ክሮኖስ እና ካይሮስ ። ክሮኖስ አንድ ሁለት ብለን በሰከንድ፥ በደቂቃ፥ በሰዓት፥ በቀን፥ በወርና በዓመት የምንቆጥረውን ጊዜ ያመለክታል።ክሮኖሎጂ የሚለው ቃል ከዚህ የተገኘ ነው። ካይሮስ ደግሞ በእነዚያ ጊዜያት ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች ( ደስታም ይሁን ሐዘን) የተከሰቱበትን ወቅት ያመለክታል። ክሮኖስ ላይ ብቻ ካተኮርን ጊዜን ቆጥረን እንጨርሰዋለን። ሌላ ቀን ሌላ ወር ሌላ ዓመት ሲተካ ያው መቁጠራችንን እንቀጥላለን፤ ካይሮስ ላይ ካተኮርን ግን እግዚአብሔር የሰጠንን እያንዳንዱን ወቅት ወይም ቅጽበት በጥንቃቄ እናየዋለን። « በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ» ብሎ እግዚአብሔር የተናገረን፥ እግዚአብሔር ወደ እኛ ስለቀረበበት ወቅት ነው። ባሳለፈፍነው ዓመት ክሮኖስን ቆጥረን ጨርሰናል። ካይሮስን አይተነዋልን? አሰላስለነዋል? ተምረንበታል? ንስሐ ገብተንበታል። ያዘናችሁበትም ሆነ የተደሰታችሁበት ወቅት በአስተዋይ ዓይን ከተመረመረ የዕድገታችሁ ጊዜ ይሆናልና። በዚህ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ላይ ካሌንደር ( ክሮኖስ) ቆጣሪዎች ብቻ ሳንሆን የተሰጠንን ዕድል ( ካይሮስ) ነዋሪዎች እንድንሆን በጊዜ ባለቤት ፊት ቃል እንግባ። ብዙ ጊዜ የችግራችንን ወቅት የምሬት ወቅት እናደርገዋለን። የችግር ወቅት እንኳ ሳይቀር የበረከት ወቅት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከምንም ጊዜ በላይ ወደ እኛ የሚቀርብበት ጊዜ ነው። ዘመንን ዋጁት ያለንም ይህን ነው። ካይሮስን ማስተዋል። እግዚአብሔር ወደ እኛ የቀረበበትን ወቅት።

No comments:

Post a Comment