Tuesday, May 28, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት ካለፈው የቀጠለ (ሦስተኛ ክፍል)

Read in PDF
ነአምን በ፩ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኵሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ

ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። 

እስከ አሁን እግዚአብሔር በገለጠልን መጠን ስለ አንድነቱና ስለሦስትነቱ ማለትም ስለምሥጢረ ሥላሴ ተምረናል። ምሥጢረ ሥላሴ ማለት የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት እንደሆነ፥ ይህም ማለት አንዱ እግዚአብሔር ሦስት እኔነት ሦስት እኔ ነኝ ባይ አካላት እንዳሉት አይተናል። የእግዚአብሔር የሦስትነት ስሙም አብ ወልድ መንፈስ ነው። እርስ በእርሳቸውም የሚገነዛዘቡበት የኵነት ስማቸውም ልብ፥ ቃል እስትንፋስ ነው። ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ለዚህ ትምህርታቸው መሠረት ያደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትንና አገላለጾችን ነው። 

ሆኖም ከዚህ በፊት እንዳልነው ምሥጢረ ሥላሴን ገልጦ ለመጨረስ መሞከር አይቻልም። ወይም የአባቶቻችንን አገላለጥ ለመጠቀም ውቅያኖስን በዕንቁላል ቅርፊት ጨልፎ ለመጨረስ እንደመሞከር ነው። ባለፉት ክፍሎች ያነሣናቸው ነጥቦች ለጊዜው ደብዘዝ ቢሉብን ብዙ አንጨነቅ፤ የበለጠ ስለ ራሳችን ማንነት ባየን ወቅት የበለጠ ስለመዳናችን ስንወያይ፥ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ግልጥ ይሆንልናል። ይህ ግን እምነታችን ነው። « በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን። አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ናቸው። በአካል ሦስት ናቸው። በመለኮት በአገዛዝ በሥልጣን አንድ ናቸው። አብ እኛን ከመውደዱ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ አንድያ ልጁን ወልድን ሰዶልናል። ወልድ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖአል። በመሰቀል ተሰቅሎ ሞቶ ተነሥቶ አድኖናል። አሁን በክብር አርጎ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦአል። መንፈስ ቅዱስ ቀድሞ ፍጥረትን ያስተናበረ ሕይወትና ውበት የሰጠ (ዘፍጥረት 1፥2) አሁን ደግሞ በክርስቶስ የተከናወነው የማዳን ሥራ እውን እንዲሆን በሞተው ሕይወታችን ውስጥ ሕይወት ሰጥቶናል። ቀድሶናል። 

ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ ፤ 

ሀ.  ሥነ ፍጥረት 

አባቶቻችን ይህን የሚታየውንና የማይታየውን  ዓለም ሰማዩንና ምድሩን እግዚአብሔር የፈጠረበትን መንገድ በሃይማኖት (በሳይንስ አይደለም) ያጠኑበት ትምህርት ሥነ ፍጥረት ይባላል። እነቅዱስ ባስልዮስ፥ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ያስተማሩበት ሄክሳሜሮስ ወይም አክሲማሮስ በሚል ይታወቃል። ስድስቱን የፍጥረት ቀናት የሚያመለክት ነው።   ዛሬ ሳይንሱ ከፍተኛ ርቀትና ጥበብ ውስጥ ባለበት ወቅት የአባቶቻችንን የሥነ ፍጥረት መንገድ የምናጠናው ለምንድነው ተብሎ ይነሣ ይሆናል። ዛሬ ከመቼውም በበለጠ ስለ ፍጥረት እያየን ባለንበት ወቅት የእግዚአብሔርን ታላቅነት የኑሮአችንና የምርምራችን ማዕከል ልናደርገው ይገባል። 

ስለፍጥረት ስንመምረምር የሚከተሉትን ነጥቦች ልንረዳ ይገባል። 

1. እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው በሦስትነቱ ነው። 

እግዚአብሔር አብ በልብነቱ አስቦና ፈቅዶ ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ፥ ፈቀደ፥ ፈጠረ (ራዕ 4፥10_11
እግዚአብሔር ወልድ ዓለም የተፈጠረበት ቃል ነው። እግዚአብሔር አብ ዓለምን የፈጠረው በቃሉ ነው። ዮሐንስ በወንጌሉ እንደነገረን ሁሉ በእርሱ (በቃል) ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ (ያለ ቃል) አልሆነም። ዮሐንስ 1፥3። ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ወልድ ሲናገር « በሰማይና በምድር በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።» ቆላ 1፥16። 
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለፍጥረቱ መልክና ቅርጽ፥ ሕይወት የሰጠ ነው።  ሙሴ የፍጥረትን ታሪክ ሲጽፍ « « የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር» ይለናል። ዘፍጥረት 1፥2። 

2. እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው በሉዓላዊ ፈቃዱ ነው። 
እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው ማንም አስገድዶት አይደለም። ወይም ለሕልውናው አስፈልጎት አይደለም። ዓለማትን የፈጠረው በፈቃዱ ነው። ራዕ 4፥10 


3. እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው በፍቅሩ ነው። 
ዓለምን ያዳነበት የቤዛነት ሥራው ብቻ ሳይሆን ፍጥረትን የፈጠረበትም መንገድ የፍቅርና የጸጋ መንገድ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚናገሩት፥ ፍጥረት በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ያለው ከመጠን በላይ « ሞልቶ የተትረፈረፈው» ፍቅር ውጤት ነው። 

የስድስቱ ቀን ፍጥረታት 

« ቀን የሚለው ቃል (yom) የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። 1. ሃያ አራት ሰዓታት።   2. እግዚአብሔር የወሰነው የጉብኝት ወይም ፍርድ ሰዓት ወይም ያልተወሰነ ዘመንን  ያመለክታል።  ኢሳይያስ 2፥11፤ ኤር 11፥4። ቀን የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሃያ አራት ሰዓትን ብቻ ነው ብሎ መሟገት አንድ የነገረ መለኮት ሊቅ እንደተናገረው « በገጸ ንባቡ ላይ ሾልኮ መግባትና ጥቅሱ ቅኔያዊ አምሳላዊ አነጋገር እንዳይኖረው ማድረግ ነው።» ፖፕ ሺኖዳ ስለዚህ ሲናገሩ  ሲናገሩ « የእኛ ማብራሪያ ይህ ነው። የሥነ ጽጥረት ቀኖች በፀሐይ የቀን አቆጣጠር መሠረት ማለት አንድ ቀን 24 ሰዓት እንደምንለው አይደለም። እግዚአብሔር ፀሐይን በአራተኛው ቀን ፈጠረ። ይህም ማለት የመጀመሪያዎቹ አራት ቀኖች በፀሐይ የሚቆጠሩ ቀኖች አልነበሩም። ከዚህም በላይ ቅዱሳት መጻሕፍት ሰባተኛው ቀን እንደ ተፈጸመ አይገልጹም። ስለሆነም ከአዳምና ከሔዋን ጊዜ ጀምሮ በሰባተናው ቀን እንኖራለን። ይህም ጊዜ የሚያበቃው በትንሣኤ ዘጉባኤና በዓለም ፍጻሜ  ይሆናል።  ስለዚህ የሥነ ፍጥረት ቀኖች ያልተወሰኑ ክፍለ ጊዜያት (ዐረፍተ ዘመናት) ናቸው ። ይኸውም አንድ ቀን ማለት አንድ አፍታ ወይም ሚሊዮን ዓመታት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ያም ሆነ ይህ ያልተወሰነው ክፍለ ጊዜ መጀመሪያውና መጨረሻው « ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ" በሚለው ቃል ይጠራል።» 

እግዚአብሔር በስድስቱ ቀናት የፈጠራቸው ፍጥረታት የሚከተሉት ናቸው። 
እሑድ፥ 
በዕለተ እሑድ የተፈጠሩት ፍጥረታት አራቱ ባሕርያት የተባሉት መሬት ውኃ ነፋስና እሳት፥ ብርሃን ፥ ሰማያት፥ እና መላእክት ናቸው። ሰባቱ ፍጥረታት ተብለው የሚታወቁት እነዚህ ናቸው። 

ሰኞ፤ 
በዚህ ዕለት የተፈጠረው ጠፈር ነው። 

ማክሰኞ 
በዚህ ዕለት የተፈጠሩት እግዚአብሔር የብሱንና ውቅያኖስን በመለየት የሚበሉ እና የማይበሉ አዝርእትን አትክልትና ዕፅዋትን ማለትም እነዚህን አራት ፍጥረቶች ከአራቱ ባሕርያት ፈጥሮአል። 

ረቡዕ 
በዚህ ዕለት እግዚአብሔር ሦስት ፍጥረታትን ማለትም ፀሐይን ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጥሮአል። 

ሐሙስ 
በዚህ ዕለት አባቶቻችን << ዘመደ እንስሳ» ብለው የሚጠሩአቸው በባሕር የሚኖሩት ዓሣዎችና የመሳሰሉት፥ ሁለተኛው « ዘመደ አራዊት» ዐዞ ጉማሬ የመሳሰሉት በውኃም በመሬትም የሚመላለሱ ናቸው። ሦስተኛው « ዘመደ አዕዋፍ» የሚባሉት ናቸው። እነዚህ በባሕር ላይ የሚኖሩ ነገር ግን በክንፋቸው የሚበሩትን ያመለክታል። 

ዓርብ 
በዚህ ዕለት የተፈጠሩት እንደገና በሦስት ታላላቅ ክፍሎች እናያቸዋለን። « ዘመደ እንስሳ»  በሬና ፈረስ የመሳሰሉት ፤ « ዘመደ አራዊት»  አንበሳና ነብር የመሳሰሉት « ዘመደ አዕዋፍ »  ርግብና አሞራ የመሳሰሉት ናቸው። በመጨረሻም ሰው የተፈጠረው በዚሁ ቀን ነው። በአጠቃላይ ሃያ ሁለቱ ፍጥረታት የተባሉት እነዚህ ናቸው። 


ለ. ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው?  

ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ስለ ሰው ማንነት ሲያስተምሩን አጠንክረው የሚነግሩን ነገር ቢኖር በፍጥረት ውስጥ ሰው ያለውን ልዩ ቦታ ነው። ዛሬም በቢሊዮን ጋላክሲዎች መካከል ሰው በዕውቀቱ በችሎታው የሚያደርጋቸውን ነገሮች ስናይ ሰው በእርግጥም በፍጥረት መካከል ልዩ ቦታ ያለው ነው። ይህን የሰውን ሚና አባቶች በአራት ዋና ዋና ነጥቦች አስገንዝበውናል። 

1. ሰው የሚታየውና የማይታየው ዓለምን ጠቅልሎ የያዘ 

እግዚአብሔር አምላክ የፈጠረው ግዘፉን ዓለም ብቻ ሳይሆን « ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውንም» ነው። የማይታየው ዓለም (ሰማያዊው ዓለም)  መንፈሳዊ እና ኢቁሳዊ (nonmaterial) የሆነ ዓለም ነው። መላእክትና መናፍስት የሚመደቡት ከዚህ ዓለም ነው። የሚታየው ዓለም ደግሞ ቁሳዊው ዓለም ነው። በዚህ ውስጥ የሚመደቡት ደግሞ ከዋክብት፥ ፕላኔቶች፥ ዕፅዋትና እንስሳት ናቸው። እነዚህ ሁለቱ ዓለማት፥ ግኖስቲኮችና የምሥራቁ ዓለም ፍልስፍና አስተማሪዎች እንደሚያስተምሩት እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ አይደሉም። ሁለቱም በአንዱ በእግዚአብሔር የተፈጠሩ ናቸው። 

በኦርቶዶክሳውያን መምህራን መሠረት፥ በፍጥረት ውስጥ የሚገኝ ማናቸውም ነገር ሁሉ ከእነዚህ ክፍሎች ማለትም ከሚታየውና ከማይታየው፥ ከቁሳዊውና ከመንፈሳዊው ዓለም በአንዱ ይመደባል። ከሰው በስተቀር። 
ሰው በመንፈሳዊና በቁሳዊው የተፈጠረ ነው። በዚህም ሰው ፍጥረትን ጠቅልሎ የያዘ ነው። በፍጥረት ውስጥ ይህን የሰው ልዩ ቦታ የያዘ ሌላ ማንም የለም። የጫካው ንጉሥ የሆነው አንበሳ የመንፈሳዊና የዕውቀት ዓለም የለውም። መላእክት የመንፈሳዊና የዕውቀታዊው ዓለም ባለቤት ቢሆኑም ቁሳዊ ወይም ግዘፋዊ በሆነው ዓለም ምንም ተፈጥሮ የላቸውም። ከምድር አፍር ተበጅቶች የእግዚአብሔርን እስትንፋስ የተቀበለ ሰው ብቻ ነው። 

2. ሰው በፍጥረት እና በእግዚአብሔር መካከለኛ ነው። 


ሰው በፍጥረት መካከል ካለው ልዩ ቦታ የተነሣ፥ በፍጥረት መካከል እንደመካከለኛ ( mediator) እንዲያገለግል ተጠርቶአል። ሰው የተጠራው ፍጥረትን እንዲገዛ እና እንዲሰለጥንበት፥ በዓለም ውስጥ እየሠራ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲያቀርብ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ከሰጠው ፀጋ የተነሣ ሰው በጥበቡና በዕውቀቱ ፍጥረት የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጥበትን መንገድ ሲቀይስ እናያለን። ስለሆነም የሰው ግቡ ፍጥረትን ወደ እግዚአብሔር ክብር ማምጣት ነው። በምድር የእግዚአብሔር ወኪል ነውና በእግዚአብሔር ፊት ደግሞ የፍጥረቱ ሁሉ ተወካይ ነው። 

3. ሰው እኔ ነኝ ባይ  (personal being)ነው። 
ሰው የተፈጠረው እኔ ነኝ ባይ አካል ሆኖ ከአምላኩ ጋር ሕብረት እንዲኖረው ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ዘለዓለማዊ  ልዩ የሆነ ሕብረት እንዲኖረው ሆኖ የተፈጠረ ሰው ብቻ ነው። በመሆኑም ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ ተደርጎ የተፈጠረ አይደለም። ሰው በብቸኝነቱ ውስጥ ሳይሆን ሰብእናውን የሚያገኘው በሕብረት ውስጥ ነው። ከሌላው ሰው ጋር በሚኖረውና ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረው ሕብረት። « እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ሐሳብህ በፍጹም ነፍስህ ውደድ፤ ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገው ውደድ» ቃል ሰውን ወደተፈጠረበት ዋና ዓላማ የሚመራው ነው። 

4. ሰው በእግዚአብሔር ዓርአያ የተፈጠረ ነው። 

 በሰው ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ዓርአያ የምንለው ሰውን ከሌላው ፍጥረት የሚለየው ማናቸው ነገር ነው። ወይም ሰው የሚያሰኘን ተፈጥሮአችን (ባሕርያችን) ነው የእግዚአብሔር ዓርአያ የምንለው። 

4.1 በእግዚእብሔር ዓርአያ የተፈጠርን በመሆናችን የእግዚአብሔርን ልዩ ፍቅር የምንቀበል ሆነናል። እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሁሉ ይወዳል፥ አንድ ልጁን እስኪልክ ድረስ ይወደደው ግን ሰውን ነው። (ዮሐንስ 3፥16።) ይህን ለሚታየውም ሆነ ለማይታየው ፍጥረት አላደረገውም። 

4.2 በእግዚአብሔር ዓርአያ የተፈጠርን በመሆናችን በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ዋጋ ያለን ነን። 
ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ አለው። ነገር ግን ሰው ልዩ ዋጋ ያለው ነው። « ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?» ማቴ 6፥26። 
4.3 በእግዚአብሔር ዓርአያ የተፈጠርን በመሆናችን ልዩ ኃላፊነት አለብን። 
በእግዚአብሔር ዓርአያ የተፈጠርን ስለሆንን በምድር ላይ የእግዚአብሔር ወኪል ነን። በመሆኑም በምድር ላይ ለምናከናውነው ማናቸውም ድርጊት ኃላፊነት አለብን። ገና ለገና በፍጥረቱ ላይ ስልጣን አለን ብለን በምድር ላይ ያለውን መልካም የሆነውን ነገር የምናበላሽ ከሆነ በውስጣችን ያለውን ዓርአያ የሚጻረር ተግባር እያከናወንን ነው። የተሰጠንን ሥራ ተግባራዊ አላደረግንም (ዘፍጥረት 2፥15። 



የውይይት ጥያቄዎች 

1. ሰው በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሮአል ማለት ምን ማለት ነው? 

2. ሰውን ከእግዚአብሔር የእጁ ሥራዎች ልዩ የሚያደርገው ምንድነው? 

3.  ሥነ ፍጥረት ስለ እግዚአብሔር ምን ያስተምረናል?

4. እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረው በሥላሴነቱ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው?


























2 comments: