Monday, November 11, 2013

የሰው ያለህ


“ ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው” 
አለ ያ ታላቁ አርበኛ  ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ 
ባንዳ አገሩን ቢወር ሊያሰማ ኤሎሄ 
ዓይኔን ሰው ራበው አለ እየተጣራ 
በድዮጋን መንፈስ ጮኸ በጠራራ
ጸሐዩዋን ሳያምናት ፋናውን አብርቶ 
ሰው ባይኑ ፈለገ ከገበያው ገብቶ 
እያለ ተጣራ ጮኸ አሰምቶ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው 

ከዚያ ካምደ ወርቁ ከአውደ ምሕረቱ  
ከቤተ ልሔሙ ከቅኔ ማኅሌቱ 
በንባብ በቅኔው በመወድስ ዜማው 
በአራራይ፥ በዕዝል፥ በግዕዝ ቅላጼው 
እያለ ተጣራ ጮኸ አሰምቶ 
ማንም ዞር አላለ የለም የሚሰማ  
« ከመ እንስሳ»  ሆኖ የዕለቱ ዜማ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔ ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው 

ከዙፋን ችሎቱ ከአደባባዩ 
ከሥልጣን ሠገነት ከልፍኝ አስከልካዩ 
አሰምቶ ጮኸ  ዓይኔን ራበው ብሎ 
ያጣውን የሰው ዘር ዓይኑ ተከትሎ 
ከቤተ መንግሥቱም ከተኮለኮሉ 
ሰው አጣ በዓይኑ እንስሳ ነው ሁሉ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው 

ገባ ከጉባኤው ከሊቃውንቱ መንደር 
ሰው ሚገኝበትን ጥበብ ሊመረምር 
ምስክር የሆኑት የመጣፉ መምር 
ቢያነጋግራቸው  የመጣበትን ነገር 
ካፋቸው ቢጠብቅ የሰውነትን ሕግ 
ለካስ ችሎታቸው ሰው እንስሳ ማድረግ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የስው 
የሰው ያለህ የሰው 

ከሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ 


Sunday, November 10, 2013

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ሶርያ ክርስቲያኖች

በሶርያ በመካሄድ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ ሕልውናቸውን የማጣት አደጋ ውስጥ የገቡት የአገሪቱ ቀደምት ነዋሪዎች የሆኑትና ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ሶርያን ቤታቸው አድርገው የኖሩት የሶርያ ክርስቲያኖች ናቸው። ብዙዎች ተንታኞች እንደሚናገሩት በዚህ በጦርነቱ ክርስቲያኖች በሁለት በኩል አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል።

በአንድ በኩል እነርሱን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ እስላማውያን « ነጻ አድራጊዎች» ተደርገው በምእራባውያን ሁሉ ሲደገፉ፥ በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራባውያኑ ዘንድ አምባ ገነን ተብሎ የሚታወቀው የአሳድ አገዛዝ ከሚከተለው ዓለማዊ ( secular) አስተዳደር አንጻር ለክርስቲያኖች ውሱን የሆነ ነጻነት ሰጥቶአቸዋል።
« የሚያውቁት ሰይጣን፤ የሶርያ ክርስቲያኖች ለምን ባሽር አልአሳድን ይደግፋሉ » በሚል ግሩም መጣጥፉ ላይ  ገብርኤል ሰኢድ ራይኖልድ የተባለ ጸሐፊ፥ ገና በጦርነት ላይ ያሉት እስላማውያን ተዋጊዎች በያዙዋቸው አንዳንድ ከተማዎች ላይ በክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን በደል በዝርዝር ገልጦአል።

አብያተ ክርስቲያናትን ከመመዝበር አልፎ ተርፎ፥ ካህናቱን በገጀራ እስከማረድ ድረስ ዛሬ በሶርያ የሚታይ ድርጊት በመሆኑ፥ በዚያ ያሉት ክርስቲያኖች ምንም እንኳ ባሽር አልአሳድ የሚያኮራ የሰብአዊ መብት ሪኮርድ የሌለው ቢሆንም ከእርሱ ጋር መወገንን መርጠዋል።

ከሁሉ የሚያሳዝነው የምዕራባውያን መንግሥታት ነው። እንኳን በሶርያ ላሉት ክርስቲያኖች ቀርቶ፥ በቍጥር በዛ ያሉና በምዕራባውያን መንግሥታትም ዘንድ ተሰሚነት ይኖራቸዋል የሚባሉት የግብጽ ክርስቲያኖች በእስላማውያኑ እየደረሰባቸው ያለውን መከራና ስቃይ እንዴት በዝምታ እንዳለፉት ዓለም የሚያውቀው ነው።

ዛሬ ስለ ኢራቅ ክርስቲያኖች የሚያወራ ማን ነው። ነገር ግን የኢራቅ ክርስቲያኖች ላለፉት ሁለት ሺ ዓመታት በኢራቅ ውስጥ የኖሩ ከኢራቅ ቀደምት ነዋሪዎች መካከል የነበሩ ናቸው። ከሳዳም መውደቅ በኋላ ግን እስላማውያኑ የኢራቅ ክርስቲያኖችን ከኢራቅ እንዲጠፉ ነበር ያደረጉአቸው። ይህ አይነቱ ድርጊት በእነርሱ የሚደገም ስለመሰላቸው የሦርያ ክርስቲያኖች ስደትን በመምረጥ ፓስፖርታቸውን እያዘጋጁ መሆናቸውን ብሉምበርግ የተባለው የዜና ማሰራጫ ገልጦአል።

በጎረቤት አገር በኬንያ ስላለው እስላማዊ እንቅስቃሴና በእኛም አገር ቢሆን በዲያስፖራውም ሆነ በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ያለውን እይታ በሰፊው መጣበታለሁ። 

Saturday, November 9, 2013

ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነው።


የግእዙ ንባብ « አንሰ እመኒ ሐየውኩ ለክርስቶስ። ወእመኒ ሞትኩ ርቡሕ ሊተ፤ እኔስ በሕይወት ብኖር ለክርስቶስ ነው። ብሞትም የሚጠቅመኝ ነው።» ይላል። ግእዙ በሕይወት ብኖር ለክርስቶስ ነው» የሚለውን ግሪኩ « ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ነው» ብሎ ይናገራል።  ግእዙንም ሆነ የግሪኩን ንባብ  (አማርኛው የግሪኩን ተከትሎ ነው የሄደው) በጥንቃቄ ላስተዋለ ሰው  ጳውሎስ ስለ ስለእስራቱና አሁን ስለተጋፈጠው ችግር ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ ሕይወቱ ያለውን ትርጉም ይገልጣል። 

ጳውሎስ በዚህ ቦታ ላይ በሕይወትና በሞት መካከል ያለውን ትርጕም ይገልጣል። ለጳውሎስ « ሕይወት ክርስቶስ» ነው።» ይህም ማለት መኖር ማለት ለጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር መሆን ወይም በክርስቶስ መሆን ነው። ክርስቶስ ሕይወት የሆነበት ኑሮ ምን ይመስላል ስንል በ ቍጥር 22 የፊልጵስዩስ ሰዎችን ጨምሮ ለሌሎች ወይም ለቤተ ክርስቲያን በሙሉ ፍሬያማ የሆነ አገልግሎት መስጠት ነው።   

ሐዋርያው « ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ነው» ካለ በኋላ « ሞት ጥቅም ነው» አለ። ሞት እንዴት ጥቅም ይሆናል ብለን ስንጠይቀው ሞት የሚጎዳኝ የኃጢአት መሣሪያ መሆኑ አብቅቶአል። ይልቁንም ሞት ከክርስቶስ ጋር አንድ የምሆንበትና ለዘላለም ከእርሱ ጋር የምኖርበት መንገድ ነው ይለናል። በቍጥር 23 ላይም « ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና»  በማለት እንዲያውም ከሞት በኋላ ያለውን ኑሮ ከሁሉ ይልቅ የተሻለው መንገድ በማለት ይጠራዋል። 

ስለ ሕይወት ያለን እይታ በሕይወት ውስጥ የምናልፍበትን ነገር እንዴት አድርገን መቀበል እንዳለብን የሚወስን ነገር ነው። ሕይወትን የምናየው በምን መልኩ ነው? ወይም በሌላ ቋንቋ ለእኛ ሕይወት ምንድነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት የሚያስተምረን ምንድነው?

ጳውሎስ « ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ነው» በማለት  ከደማስቆ መንገድ ጀምሮ እስከዚያች ቀን ድረስ ክርስቶስ የገለጠለትን እውነት ቁጥብ በሆኑ ቃላት  አጠቃለለው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሕይወት የሚያስተምረን የሚከተለውን ነው። 

1. የሕይወት ምንጭ እግዚአብሔር ነው። 

ልበ አምላክ ዳዊት «የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።» ይላል።  መዝሙር 35፥9 አስቀድሞ በገነት መካከል የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ያለብን ራሱ እግዚአብሔር ራሱ ነው። ዘፍ 2፥7፤ ይህን ሕይወት ሲሰጠን ደግሞ ተመልሰን ወደ አፈር እንድንገባ አልነበረም። እኛን የፈጠረን ሞትን አዘጋጅቶልን አይደለም። ይልቁንም በገነት መካከል  የሕይወትን ዛፍ አዘጋጅቶልን ነበር። ዘፍ 2፥9። ሆኖም ግን ከእርሱ ይልቅ ጠላት ዲያብሎስ ያዘጋጀልንን መረጥን። 

ሕይወትን እንድንመርጥ የእግዚአብሔር አሳቡና ፈቃዱ ነው።
ሙሴ ለእስራኤላውያን በሞአብ ሜዳ « በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል።» ብሎአቸው ነበር ዘዳግም 30፥6። 

ሕይወትን መምረጥ የእኛ ድርሻ ነው። 
በዚሁ ክፍል ላይም እንደገና «በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ»  ዘዳግም 30፥19። 


ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 
ዮሐንስ በወንጌሉ እንደነገረን ያለእርሱ አንዳች የሆነ ነገር የለም። ሕይወት በእርሱ ዘንድ ነች። ማለትም ሕይወት ማለት እርሱ ነው።  የሕይወት ዛፍ እርሱ ነው። (ዘፍጥረት 2፥9፤ ራዕይ 22፥2) የሕይወት መንገድ እርሱ ነው። መዝ 15፥11፤ ዮሐንስ 14፥6)፤ የሕይወት ምንጭ እርሱ ነው። ( መዝ 35፥9) የሕይወት ውኃ እርሱ ነው። ( ዮሐንስ 4፥11፤ ራዕይ 22፥17 ) የሕይወት እንጀራ እርሱ ነው። ( ዮሐንስ 6፥35) የሕይወት ብርሃን እርሱ ነው። ( ዮሐንስ 8፥12) የሕይወት ራስ እርሱ ነው። (ሐዋ 3፥15) የሕይወት ቃል እርሱ ነው። ( ፊል 2፥16) የሕይወት ተስፋ እርሱ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 1፥1) የሕይወት ጸጋ እርሱ ነው። (1 ጴጥሮስ 3፥7) የሕይወት አክሊል እርሱ ነው። ( ያዕቆብ 1፥12፤ ራዕ 2፥10) 

Friday, November 8, 2013

የታላቁ መርማሪ ምሳሌ ( The Parable of the Grand Inquisitor)

የፊዮዶር ዶስቶዬቭስኪን « የካራማዞቭ ወንድማማቾች» ካነበብኩ ሰንብቼአለሁ፤ ሥነጽሑፍን በተመለከተ ካሉኝ ምኞቶች መካከል አንዱ በዚህ የልብ ወለድ መጽሐፍ ውስጥ ያለውንና « የታላቁ መርማሪ ምሳሌ» የተባለውን ክፍል መተርጎምና፥ ከዘመኑ ክርስትና አንጻር ትንታኔ መስጠት ነው። « የታላቁ መርማሪ ምሳሌ» ታሪካዊ በሆነው የስፔይን የሃይማኖት ሽብር ላይ የተመሠረተ ነው። ዶስቶዬቭስኪ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ስለእምነት፥ ስለሃይማኖት ተቋማት፥ ስለሰው ነጻነትና ስለሰው ሕልውናና ሰብእና ከፍ ያለ የፍልስፍና ጥያቄ ያነሳል።  ያን ምኞቴን እስከማደርስ ድረስ ለዛሬ ይህን ከወደ ሃገረ እንግሊዝ በድራማ የቀረበውን ልጋብዛችሁ።

Thursday, November 7, 2013

ሕይወት የሚገኝበትና ሕይወት የማይገኝበት ትምህርት


« ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም።» 2 ጢሞቴዎስ 4፥2-5 

ቅዱስ ጳውሎስ ከልጅነት እስከ እውቀት በወንጌል ኮትኩቶ ያሳደገውን መንፈሳዊ ልጁን ጢሞቴዎስን የወንጌል አደራውን እንዴት መፈጸም እንዳለበት በአጽንዖት የመከረው የአገልግሎትህ ግብ ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት ማቅረብ ነው። 

ሕይወት የሚገኝበት ትምህርት ማለት ምን ማለት ነው? በቅዱስ ጳውሎስም ሆነ የወንጌልን አደራ በሰጠው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት መሠረት ሕይወት የሚገኝበት ትምህርት ማለት የተቀበሉት ትምህርት የሰሚዎችን ሕይወት ሲለውጥና እግዚአብሔርን ወደመምሰል ሲያመጣ ነው። ጌታ የመንግሥቱን ወንጌል ለማስተማር መጀመሪያ ያደረገው « መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» የሚለውን ትምህርት ነው። ጌታ « ንስሐ ግቡ » ሲል ሕይወታችሁን ወደ እግዚአብሔር መልሱ የኑሮ አካሄድ ለውጥ አድርጉ ለማለት ነው። በጠፋው ልጅ ታሪክ ውስጥም የጠፋው ልጅ በንስሐ ወደ አባቱ መመለሱን የሚያመለክተው ቃል « ወደ ልቡ ተመልሶ» በሚል ሐረግ ተገልጦአል። 

ሐዋርያው ለመጨረሻ ጊዜ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት መልእክት ያስጨነቀው ነገር ቢኖር፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች ሕይወት የሚገኝበትን ማለትም የሕይወት ለውጥን የሚጋብዝን ትምህርት የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል የሚል ነው። ይህ በእኛ ዘመን ተከናውኖ ይሆን? የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት የሚገኝበት ትምህርትን ነው እያስተማረች ያለችው? 

እጅግ ጠንከር ያለ ቢመስልም ዛሬ ያለንበት እውነታው ይህ ነው። በቤተ ክርስቲያን አደባባዮች ፍቅር የለም፤ በአገልጋዮቿ መካከል ሰላም የለም። ኃጢአት ከመቅደሷ ጀምሮ እስከአደባባዮቿ ነግሶአል። እግዚአብሔርን መፍራት ሞኝነት መስሎ የታየበት፥ የአፍኒንና የፊንሐስ የድፍረት ኃጢአት የአግልግሎት ኩራት የሆነበት፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲራብ በማድረግ በተለያዩ ማታለያዎች ማወናበድ ሥራዬ ተብሎ የተያዘበት ጊዜ ላይ ነን። በዓለም አደባባይ፥ በየፍርድ ቤቱ የምንከራከር፤ ገበናችንን በየጋዜጣውና በየቴሌቪዢኑ የምናዝረከርክ፥ የሚወገዙልንን ወይም የሚወነጀሉልንን ወይም ገበናቸውን የምናጋልጣቸውን ወንድሞቻችንን፥ እህቶቻችንንን፥ ጳጳሳቶቻችንንና ካህናቶቻችንንን ስም ዝርዝር ይዘን ከቦታ ቦታ የምንከራተት ነን። በዚህ ሁሉ ግን እያስተማርን ነው። በስብከታችን እያስተማርን ነው፤ በመዝሙራችን እያስተማርን ነው። በማኅሌታችን እያስተማርን ነው። 

ሕይወት የማይገኝበት ትምህርት ምን ዓይነት ነው? ሕይወት የማይገኝበት ትምህርት የምንለው በክርስቲያናዊ አካሄዳችን ላይ አንዳችም ለውጥ የማያመጣ ሲሆን ነው። ወደ ንስሐ የማያመጣን ከሆነ፥ በፍቅር አንድ የማያደርገን ከሆነ፥ ለሰላምና ለይቅርታ የማይገፋፋን ከሆነ ያ ትምህርት ሕይወት የማይገኝበት ትምህርት ሊሆን ነው። እኛ ካልፈወስነው። 

ቤተ ክርስቲያን ማለትም እኛ በዚህ ዘመን ልንጠይቅ የሚገባን ነገር አለ።  አንድ የሚያደርገን ነገር ምንድነው? አንዳንዶች ላንቃቸው እስኪተረተር አየር እስኪያጥራቸው ድረስ ጩኸው የሚመልሱት « አንድ የሚያደርገን የቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ (ዶክትሪኗ) ነው» ይሉ ይሆናል። የኔ ጥያቄ ይህ ነው፤ ይህ ትምህርት ሕይወትን ገልጦአል ወይ? ይህ ትምህርት፥ ይህ የምንናገረው፥ የምንሰብከው ትምህርት ሕይወትን ገልጦአል ወይ? ማለትም አንድ አድርጎናል ወይ? ሰላምን ሰጥቶናል ወይ ? አፋቅሮናል ወይ?  

በዚህ ዘመን የትምህርት እንጂ የሕይወት አንድነት ስለሌለን በሕይወት የሚገለጠውን ክርስቶስን ለዓለም ለማሳየት አልቻልንም። ጉሮሮአችን እስኪዘጋ ድረስ ክርስቲያኖች መሆናችንን፥ የክርስቶስ ተልእኮ የተሰጠን መሆኑን እየተናገርን ነው። ዓለም ግን በእኛ ውስጥ ክርስቶስን ሊያይ ስላልቻለ ራሱን እየነቀነቀ ወደ ጥፋት ጎዳና እየሄደ ነው። 

የትምህርት እንጂ የሕይወት አንድነት ስለሌለን፥ በሕይወታችን ክርስቶስን ማሳየት ቢያቅተን በየጉራንጉሩ ተአምራት እየፈለግን ነው። ተአምራቶች ሕይወትን የሚያጸኑ እንጂ ሕይወትን የሚያመጡ አይደሉም፤ ከጥፋትም አያድኑም። 

ከአበው የመጣ ቢሆንም እንኳ በአንዳንድ ታዋቂ ሰባክያን ተደጋግሞ የሚነገር ነገር ግን በጥንቃቄ ልናየው የሚገባን ነገር አለ። አነጋገሩ እንዲህ የሚል ነው። አባቶች አንድን መጽሐፍ ደገኛ (ታላቅ መንፈሳዊ) መጽሐፍ ነው ብለው የሚቀበሉት፥ በእሳት አግብተው ሳይቃጠል ሲቀር፥ ወይም በውኃ ቢጥሉት ሳይረጥብ ቢወጣ፥ ወይም ደግሞ በበሽተኛ ላይ ቢጥሉ በሽተኛውን ቢፈውሰው ነው የሚል ነው። መልካም አባባል ነው። ነገር ግን ይህ ሁሉ መመዘኛ ከንቱ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። መመዘኛው አንድ ነገር ብቻ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ሕይወት። 

ጌታ በተራራው ስብከት  ላይ ስለዚህ ሲናገር « ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።» ብሎአል። ማቴዎስ 7፥20 - 23  


የቃላት ውበት፥ « ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ» ፥ ወይም የተአምራት ብዛት « ትንቢት መናገር፥ አጋንንት ማውጣት፥ ተአምራት ማድረግ » በጌታ ዘንድ መታወቅን አላመጣም። ነገር ግን ጌታ በተአምራቱ መካከል፥ በዝማሬው መካከል፥ በቅዳሴው መካከል፥ በስብከቱ መካከል፥ በሕዝቡ ብዛት መካከል አንድ ነገር ይፈልጋል። የሕይወት ፍሬን። 

ጌታ ሆይ አንተ በገለጥክልን ቅዱሳን ሐዋርያት እና እነርሱን ተከትለው የተነሱት አባቶቻችንና እናቶቻችን ባስተማሩን የሕይወት መንገድ ላይ ሆነን በሕይወታችን አንተን እንድንገልጥ እርዳን አሜን። 

Wednesday, November 6, 2013

« ኢየሱስ አለቀሰ» ዮሐንስ 11፥35


ዶክተር ሊሊያን አልፊ (ትርጉም ቀሲስ መልአኩ ባወቀ) 

የሚከተለው መጣጥፍ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን የሆኑ ዶክተር ሊሊያን አልፊ « የሰማይ መጽናናት» በሚለው መጽሐፋቸው ካስቀመጡት ጽሑፍ የተቀነጨበ ነው። 

ነዋሪዎቹ በብዙ ሥነ ምግባራቸው በሚታወቁበትና ጌታችን ኢየሱስ ራሱ እረፍት ማድረግ በሚወድበት በቢታንያ በሚገኘው በዚያ ቤት ሕይወት ሰላማዊ ነበር። ነገር ግን ያ ሰላም ብዙም አልዘለቀም። በአልአዛር ሕመም ምክንያት ሐዘን በዚያ ቤት አጠላ። ሁለቱ የአልአዛር እህቶች በፍቅሩና በርህራሄው ከሚያጥለቀልቃቸው ከወዳጃቸው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ የሚሄዱበት ሌላ ምንም የላቸውም ነበር። የርሱን እርዳታ ፈልገው ወደጌታችን ላኩ። መልእክቱን ሲልኩ « ጌታ ለጥሪው ምላሽ ሰጥቶ ቶሎ በመምጣት አልአዛርን ይፈውስ ይሆን ወይስ እርሱን በድንጋይ ለመውገር የሚጠባበቁትን የአካባቢውን ሰዎች ለመሸሽ ብሎ ይቀር ይሆን?» ብለው ሳይደነቁ አልቀረም። 

ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሜት ወይም በጥንቃቄ ላይ ተመሥርቶ ምንም እርምጃ አልወሰደም፤ ይልቁኑም ጌታ የተራመደው  በሰማያዊው ጥበብ ላይ ተመሥርቶ ነው፤ «  » መክብብ 3፥1 የሞት መልአክ በሩን በኃይል ሲያንኳኳ ፥ጌታ ግን መምጣቱን አዘገየ። ሴቶቹም  ጌታ በሰዓቱ መምጣቱን ለማጣራት ማዶ ማዶ ያዩ ነበር።   

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሞት ወደ እነዚህያ እህቶች ሕይወት ውስጥ ገባ፤ ያነቡት የነበረው የተስፋ በለቅሶ ወደተሸፈነ ምሬትና ውስጣዊ ጩኸት ተለወጠ። ውስጣዊ ማንነቱ በውስጡ እስክናልፍበት ድረስ የማናውቀው ሐዘን በእውነተኛ ቀለሙ ወደእነዚህ እህቶች መጣ፤ 

በወንድማቸው መቃብር ላይ የተቀመጠው ትልቁ ድንጋይ፥ በለቅሶአቸው የማይነቃነቅ፥ በልመናቸው የማይነሳ ነገር ግን በትከሻቸው ላይ መጥቶ የተቀመጠ መስሎ ተሰማቸው። የመጽናናቱ ቃል ሁሉ ከሕመማቸው ሊያሳርፋቸው አንዳች አላደረገላቸውም። ሌላው ቀርቶ፥ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ለነበሩት ሰዎች፥ ራሳቸው ይናገሩት የነበሩትን  ቃላት አሁን ሰዎች ለእነርሱ ቢደግሙላቸውም ለልባቸው ሊደርስ አልቻለም። 

ነገር ከረፈደ በኋላ ( ብዙዎች ያሰቡት እንደዚህ ነው) ጌታ ደረሰ። ለጌታ ከተናገሩት ንግግር እንደሚታየው ሁለቱ እህትማማቾች ተስፋቸውን ሁሉ አጥተው ነበር። « አንተ በዚህ ሆነህ ኖር ወንድማችን ባልሞተ ነበር» አሉት። ዮሐንስ 11፥22። 

ብዙ ሕዝብ እየተከተለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ መቃብሩ ወሰዱት፤ በአልአዛር መቃብርም አጠገብ፥ የለቀስተኞቹ እንባና የጌታችንና የመድኃኒታችን እንባ ተቀላቀለ።  እነርሱ ስለ አልአዛር ሞት ያለቅሱ ነበር፤ ኢየሱስ ግን  « ሞት» በሰው « ኃጢአት» በኩል በመግባቱ ያለቅስ ነበር። 

ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ግን አዎንታዊ የሆነ አስተሳሰብ ያለው ምእመን እንኳ የማይጠብቀው ነገር ተከሰተ. . .  የሞተው ሰው እየተራመደ ከመቃብሩ ወጣ። የሐዘኑ ጩኸት ወደ ደስታ ጩኸት፥ ለቅሶው ወደ እልልታ ተለወጠ። 

በዘመናት ሁሉ፥ ይህ ተአምር እየተደጋገመ ሲነበብ፥  በሐዘንተኞች ላይ የተስፋ ጥላ ውልብ ሳይልባቸው አይቀርም፦« ያ ተአምር ለምን ለኔ አይሆንልኝም?» የሚል። 

ሁሉን የሚችለውን ልዑል እግዚአብሔር ተእምራት እንዲያሳየን ለመጠየቅ ሙሉ መብቱ አለን። . . . ተአምራት በሕይወታችን እንዲከሰቱም ያለማቋረጥ መጸለይ አለብን። 

ነገር ግን ብዙ ተአምራት የመከሰታቸውን ያህል፥ ተአምራት አግዚአብሔር በልዩ መንገድ የሚሠራባቸው ልዩ ክስትቶች ናቸው እንጂ እግዚአብሔር ቀን በቀን ፍጥረቱን የሚያስተዳድርባቸው የተፈጥሮ ሕጎች አይደሉም። እምነታቸውን በተአምራት ላይ የሚያደርጉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ያዝናሉ። እነርሱ ሲጠብቁት የነበረው ተአምር ሳይሆን ሲቀር እግዚአብሔርን ያማርራሉ፥ በእርሱ ላይ ያንጎራጉራሉ፤ አልፎም ተርፎም ይክዱታል። 

እኛ ግን አንድያ ልጁን ስለ እኛ በመስቀል ላይ እንዲሞት አሳልፎ የሰጠንንና  ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ሌላ ተአምር የማያስፈልገውን አምላካችንን ልንታመነው ይገባል።  « በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።» የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል እንታጠቀው። ሮሜ 14፥8። በመሆኑም ጌታን እንዲህ እንበለው፦ የኔ ውዱ ጌታ በበሽታ ብሆንም፥ ፍትህ በማጣት መከራ ብቀበልም፥ ብሰደድም፥ ብከብርም ሁል ጊዜ የአንተ ነኝ። 

እርሱ በሚያውቀው መንገድ እግዚአብሔር ሦስቱን ወጣቶች ከሚነደው እሳት ለምክንያት ካዳናቸው፥  ብዙዎች ሌሎች ደግሞ በሚነድ እሳት መካከል ሕይወታቸውን ለአምላካቸው እንደሰጡ ማሰብ አለብን። የሰምርኔስ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ፖሊካርፕ በሽምግልና እድሜው  በእሳት ሲቃጠል በተአምራት ሊያድነው እግዚአብሔር ጣልቃ አልገባም። ያ ቅዱስም ያን እሳት አልፈራም። « ሰማንያ ስድስት ዓመት ክርስቶስን ሳገለግለው አንድም ቀን አልተወኝም። አሁን ታድያ ለምንድነው የምክደው? » ነበር ያለው። 

ይልቁኑ፥ መከራው በጸና መጠን ከእግዚአብሔር ጋር የመገናኘት እድላችን ሰፊ ይሆናል። እነዚያ ሦስቱ ወጣቶች ለእግዚአብሔር የቀረቡ ቢሆኑም፥ ከአምላካቸው ጋር ፊት ለፊት የተገናኙት የሚነደው እሳት ውስጥ ነው! እነርሱንም ሆነ ዛሬም በመከራ ውስጥ ያሉት ሌሎችን « በመከራ ውስጥ ባታልፉ ይሻላችሁ ነበር ወይ?» ብላችሁ ብትጠይቋቸው የሚሏችሁ « የሕይወታችንን ዋና ክፍል ልትነጥቁን ትወዳላችሁን? ሕይወት ምንድነው? ሕይወት እኮ ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ የእግዚአብሔርን ልጅ በሚነደው እቶን እሳት ውስጥ ያገኘንበት ጊዜ ነው»  ይሏችኋል።    

ስለሆነም በሚነደው የመከራ እሳት ውስጥ እንኳን ብትሆኑ በአምላካችሁ ታመኑ። እንዲህ ብሎ የተናገረውን፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም።እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ። ኢሳይያስ 43፥1-3። 


ወደ አልአዛር እንመለስና [ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ በትውፊት እንደምንረዳው] ከተአምራታዊ ትንሣኤው በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት እንደኖረ፤ በእርሱ ላይ የተከናወነው ተአምራት የጌታን አምላክነት የሚያሳይ ስለሆነ አይሁድ ያሳድዱትና ሊገድሉት ይሞክሩ እንደነበረ እናገኛለን። በመጨረሻም  ለሁለተኛ ጊዜ አርፎ ዓለም ሳይፈጠር ወደ ተዘጋጀለት ዘላለማዊ ቦታ ሄዶአል። በዚያም በሁለተኛው ተአምር ምክንያት የዘገየበትን እውነተኛ እረፍት አግኝቶአል። ለአላዛር ምርጫ ብንሰጠው ኖሮ [ቅዱስ ጳውሎስ እንደመረጠው] እንዲህ ይለን ነበር፦ « የእኔ ፍላጎት እንኳ መሄድ ከጌታዬም ጋር መሆን ነበር ነገር ግን እኅቶቼን ለማጽናናትና የጌታን አምላክነት ለማሳየት በእኔ ላይ የጀመረውን ሥራ ለመፈጸም በሥጋ እንደገና ተመልሻለሁ።» አሜን ። 

Tuesday, November 5, 2013

« አድካሚ አጽናኞች»

ዶክተር ሊሊያን አልፊ (ትርጉም ቀሲስ መልአኩ ባወቀ) 

የሚከተለው መጣጥፍ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን የሆኑ ዶክተር ሊሊያን አልፊ « የሰማይ መጽናናት» በሚለው መጽሐፋቸው ካስቀመጡት ጽሑፍ የተቀነጨበ ነው። 

ፈተና ኢዮብን ባጥለቀለቀው ጊዜ የኢዮብ ጓደኞች ጎብኝተውት ነበር። በደረሰበት ነገር በጣም ደንግጠው ስለነበር ሳምንት ሙሉ በዝምታ ተቀምጠው ነበር። እንደእውነቱ ከሆነ ዝምታቸው ከቃላቸው ይልቅ እጅግ የሚያጽናና ነበር። ለንግግር አንደበታቸውን በከፈቱ ወቅት፥ ይህ መከራ ለምን እንዳገኘው ለመናገር መሽቀዳደም ጀመሩ።
ቴማናዊው ኤልፋዝ « ኢዮብ ችግር ውስጥ የገባው በኃጢአቱ ምክንያት እንደሆነ» እርግጠኛ ነበር። ሹሐዊው በልዳዶስ ደግሞ ኢዮብ « ኃጢአት መሥራቱ ብቻ ሳይሆን፥ ኃጢአቱን አለማወቁና አለመናዘዙ» ችግር ውስጥ እንደጣለው በእርግጠኝነት መናገር ጀመረ። ነዕማታዊው ሶፋር ደግሞ « የኢዮብ ኃጢአት ከዚህ የከፋ መከራና ሐዘን ሊያመጣበት ይገባ ነበር» አለ። ቃላቸው በኢዮብ ላይ ሌላ ተጨማሪ ሐዘንን ነበር ያመጣበት፤ በመጨረሻ  ኢዮብ ይህን  ተናገረ 
ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ 
እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ።
በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን? 
ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው?
እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር 
ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥ 
እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ 
ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር።
በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር 
የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር። ኢዮብ 16፥1-5

የትዕግሥት አባት የሆነው ኢዮብ እነዚህን በምሬት የተሞሉ ቃላት ሲናገር፥ እኛም ልናስተውልና እንደእነርሱ እኛም አድካሚ አጽናኞች እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል። በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ያለፈ ሰው ሁሉ  እንደሚያስታውሰው አንዳንድ ሰዎች መጥተው ባይጎበኙን ሳንመኝ አንቀርም።  

የሕክምና ተማሪዎች የሚማሩት የመጀመሪያው ጠቃሚ ትምህርት « በሽተኛውን መርዳት ባትችሉ. . . . ሌላው ቢቀር እንዳትጎዱት» የሚል ነው። 

አንድ በሽተኛን፥ ባል ወይም ሚስትን በሞት የተቀሙ፥ ወይም ልጇ የሞተባትን እናት ከማጽናናታችን በፊት እንዴት ማጽናናት እንዳለብን ልንማር ይገባል። በመጀመሪያ በመከራ ያለ ሰውን ለማጽናናት ሰማያዊ ጥበብ እንደሚያስፈልገን ልንገነዘብ እና ለበለጠ ሐዘን ምክንያት እንዳንሆን  የስጦታ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔርን ልንለምን ይገባል።  በሁለተኛ ደረጃ ሌሎችን ለማጽናናት የሚፈልግ ሰው ርኅሩህ፥ ዝተኛና ጉዳታቸው የሚገባው መሆን አለበት። ያረጁ የነተቡ ቃላትን መደጋገም ወይም ጉዳታቸውን ሕመማቸውን የሚያናንቁ የታወቁ ቃላትን መጠቀም በፈተና ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን ልያስቆጣ ይችላል። 

በመከራ ውስጥ ያለ ወንድም ወይም እህት በመከራ ውስጥ ከቶውንም ባላለፉና በተንደላቀቀ የኑሮ ማማ ላይ ተሰቅለው በሚኖሩ ሰዎች ሲገጹና ሲወቀሱ የበለጠ ሊጎዱ ይችላሉ። ምክንያቱም መከራቸውን መረዳት ስለማይችሉ። 

በመሆኑም « ክብር ያለው ዝምታ» ከከንቱ ቃላት ይልቅ ይመረጣሉ። ፍቅርን የተመላ እይታ፥ ወይም የእጅ ሰላምታ  ብዙ ነገር ይናገራል። በዚህም ምክንያት ጠቢቡ « ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገር ጊዜ አለው።» ብሎአል። መክብብ 3፥1-7

ኢዮብ ጓደኞቹን እንደመከራቸው፥ በመከራ ያሉትን ሰዎች ሁኔታ ልናስብና ራሳችንን በእነርሱ ቦታ ለማስቀመጥ መሞከር አለብን። አንዳንድ ጊዜ « ችግርህ ይገባኛል» ወይም « ሐዘንህ ይገባኛል» የሚለው ቃል አደገኛ ቃል ስለሆነ ልንጠነቀቅ በተቻለ መጠን እንዲህ ያሉትን አነጋገሮች ከመጠቀም ልንከለከል ይገባል። « ልጅ ሞቶብህ ያውቃል?» ወይም ካንሰር ሕይወትሽን ሊወስድ ሞት አፋፍ ደርሰሻል?» ብለው ሊጠይቁን ይችላሉ። ዶክተር ሊሊያን እዚህ ላይ ይህን ያለችው የተስተካከለ ዕይታ እንዲኖረን እንጂ እነርሱ ያለፉበትን ልምምድ እናልፍበታለን ብላ አይደለም።  

አንድን ወንድም ወይም እህትን ለመጎብኘት ከመሄዳችን በፊት የሚከተሉትን ነገሮች ማሰላሰል አለብን። ለመጎብኘት ትክክለኛ ጊዜና ቦታ ነው? ከእኔ ቃላት ዕረፍት ያስፈልጋቸው ይሆን? የምጎበኛቸውስ መጎብኘት ስላለብኝ በግዴታ ነው ወይስ ከእውነተኛ ፍቅርና ያን ፍቅሬን ለወንድሜ ለእኅቴ ማካፈል አለብኝ ከሚል ነው? ልምዴን ለማካፈል እነርሱ ባለፉበት ተመሳሳይ መንገድ አልፌአለሁ? ወይስ እግዚአብሔር ታድጎኛል? በከበረ ዝምታ ፍቅሬን፥ ሐዘኔን ለመግለጥ የትኛው ሁኔታ ይመረጣል? 

በዚህ ሁሉ ግን ለማጽናናት ያሰብናቸውን ሰዎች በጸሎታችን ወደ እግዚአብሔር ልናቀርባቸው ያለማቋረጥ ልንጸልይላቸው ይገባል። ዓይናቸውን ልባቸውን ወደ ተሰቀለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያደርጉ፥ ከእርሱም መጽናናትን እንዲጠይቁ ልንመራቸው ይገባል። አንድ ልጇ በመስቀል ላይ በተንጠለጠለ ጊዜ  « ሰይፍ በነፍሷ ያለፈባትን» የቅድስት ድንግል ማርያምን ምልጃ ልንጠይቅ ይገባል። የመከራን ምሬት ስለምታውቀው የተናወጠችን ነፍስ ልታጽናና ትችላለች። 
« በአንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ
ወይም በሚያበረታታታ በአንድ ቃል 
የሌሎችን ሸክም በመሸከም እንደቀሬናዊው ስምዖን ለመሆን ሞክር፤ 
ይህን ባትችል ሌላው ቢቀር ስቃያቸውንና ሐዘናቸውን አታብዛባቸው።» 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሸኑዳ