Wednesday, November 13, 2013

ምን ያህል ዕዳ አለባችሁ?

የአሜሪካንን የመካከለኛ መደብ ማኅበረሰብን እግር ከወርች ቀይዶ የያዘው የዕዳ ጉዳይ ነው። ሕይወት ማለት ለብዙ አሜሪካውያን የባንክ ወለድ መገፍገፍ ሆኖአል። የክሬዲት ካርድ ያላማረረው ማን ነው? ከመካከለኛ መደብ እጅግ በባሰ ሁኔታ ደግሞ መጤውንና ( immigrants) ደኃው ኅብረተሰብ በሆነ ባልሆነው እያባበሉት ከማይወጣበት የዕዳ ሐዘቅት ውስጥ እያስገቡት ነው።

Occupy Wall Street
" የኛ ዋና ዓላማ ይህን የሁለተኛ ዕዳ ገበያ (Second Debt Market) መረጃን ማሰራጨት ነው።   Photograph: Spencer Platt/Getty Images
ሆኖም ግን የ2011 ዓም በባንኮች ላይ የተካሄደውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ የመራው አካል ( Occupy Wall Street) ይህን የባንኮች በስስት ላይ የተመሠረተ አይጠግቤነትና ኅብረተሰቡን በወለድ አግድ በዕዳ መያዙ አምርሮ መቃወሙ ይታወቃል። በመሆኑም ይህ እንቅስቃሴ የወለደውና  የግለሰቦችን ዕዳ በማስወገድ ላይ በዋናነት ያተኮረው Rolling Jubilee ተባለው ቡድን የግለሰቦችን ዕዳ ከባንኮች እጅግ በቅናሽ ዋጋ በመግዛት ከ15 ሚሊዮን በላይ የግለሰቦችን ዕዳ ለማስወገድ ችሎአል። 
ዕዳውን ከባንኮች እጅግ በቅናሽ ዋጋ ስለሚገዛው ቡድኑ የ14,734,569.87 ዶላር የግለሰቦችን ዕዳ 400,000 ዶላር በማውጣት  ማቃለል ችሎአል። እንደ አንድሪው ሮስ የቡድኑ አባልና በኒዮርክ ዩንቨርስቲ የማኅበራዊና ባህላዊ ትንታኔ ፕሮፌሰር ገለጻ ከሆነ  ዕዳው እንደዚህ ሊቀል የቻለው የሁለተኛ ዕዳ ገበያ ካለው ባህርይ የተነሣ ነው። ባለዕዳዎች ብዙ ጊዜ ስለማይከፍሉ፥ ባንኮች ዕዳውን ለሌላ ሦስተኛ ወገን የሚሸጡት እጅግ ርካሽ በሆነ ሁኔታ በአብዛኛው ለአንድ ዶላር  ዕዳ እምስት ሳንቲም ያህል በመጠየቅ ነው። በመሆኑም የዕዳ አስወጋጁ አካል ዕዳውን በርካሽ ከባንኮች በመግዛት ግለሰቦችን የዕዳ ኪሳራ ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋቸዋል። ዕዳ አስወጋጁ አካል በዋናነት ያተኮረው የሕክምና ዕዳ ላይ ነው። 
ሮስ እንደሚለው ከሆነ ዕዳቸው በዕዳ ሰብሳቢዎች (debt collectors) ምን ያህል በርካሽ እንደተገዛ የሚያውቁ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ሲሆን ይህን ማወቅ ደግሞ ስለ ዕዳ ሥነ ልቡናዊ ለውጥ ይሰጣል ። በመሆኑም ዕዳ ሰብሳቢዎች ሲደውሉና ዕዳችሁን በሙሉ እንድትከፍሉ ሲጠይቁ፥ ዕዳ ሰብሳቢዎች ዕዳችሁን እጅግ በጣም በጣም ርካሽ በሆነ መንገድ ገዝተውት እንደሆነ ታውቃላችሁ ማለት ነው። ይህም ከዳ ሰብሳቢዎች ለምታደርጉት ንግግር የሞራል ብርታት ይሰጣችኋል 
በመልካም ነገር ሕዝቡን የሚያስተምርና ነጻ የሚያወጣ አዎንታዊ ተቃውሞ ማለት ይህ ነው። 
  ምንጭ፦ ዘጋርዲያን 

Tuesday, November 12, 2013

አዘክሪ ኵሎ


ታላቁ ባለቅኔና ደራሲ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፥ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ልጇ ወዳጇን ይዛ በስደት ወደ ምድረ ግብጽ መሄዷን አነጻጽሮ በፋሽሽት ጣልያን ለስደትና ለስቃይ የተዳረጉትን እያሰበ የተቀኘው ቅኔ ሰሞኑን በስደት ዓለም ሳሉ ሕይወታቸው በስቃይ ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን የበለጠ የምናስብበት ይሆናል። ዘመኑም የጌታችንን ከእናቱ ጋር ስደት የምናስብበት ስለሆነ፤ አሁንም ወገኖቻችንን ወደ አገራቸው በሰላም ያግባልን። 

ድንግል ሀገሬ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ
ሕፃናቱም ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ
ልጅሽ ተሰደደ አንቺን ተከትሎ፣
የሕፃናቱን ደም አዘክሪ ኩሎ፡፡
አስጨነቀኝ ስደትሺ፣
እመቤቴ ተመለሺ፣ ተመለሺ…

ተአምራት በሥራ ገበታ፤ የኤቢሲ ጋዜጠኛ ማሞግራምና ውጤቱ

በጥቂቱም በብዙም ማዳን የሚቻለው እግዚአብሔር አድኅኖቱን የሚያሳይበት መንገድ ብዙ ነው። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ተአምራቱን የሚያሳየው በዕለት ተግባራችን በምናሳየው ታማኝነት ነው። በዚህ በአሜሪካ የአሜሪካ ዜና ማሰራጫ ድርጅት ( abc) ጋዜጠኛ የሆነችው አሚ ሮባክ አለቃዋ አንድ ነገር እንድታደርግ ይጠይቃታል። የካንሰር ቀንን ምክንያት በማድረግ በሚሊዮን ተመልካቾች ፊት አሚ የጡት ካንሰር ምርመራ ( ማሞግራም) እንድታደርግ ይጠይቃታል። እርሷም እሺ ትላለች፤ ምርመራውን ለGood moring America ካቀረበች በኋላ ዶክተሮች ዱብ እዳ ይነግሩአታል። የጡት ካንሰር በሽተኛ መሆኗን። ሆኖም ግን አስደሳች ነገር ይነግሯታል። ያ በሥራዋ ምክንያት ለቴሌቪዥን ማስታወቂያ ያደረገችው ምርመራ ሕይወቷን አድኖአታል። ምክንያቱም ገና በመጀመሪያ ደረጃው ነበር ካንሰሩን ያገኙት።   አሚ በጻፈችው መጣጥፍ ላይ እንደገለጠችው ይህ በእርሷ ሕይወት ያጋጠማት ድርጊት ለብዙ እህቶች ትምህርት ሆኖ በጊዜ የጡት ምርመራ እንዲያደርጉ እንደሚያነሣሣ ተስፋዋ ነው። እኔ ይህን ተአምር ብዬዋለሁ በእለት ተእለት ሕይወታችን በሚኖረን ታማኝነት የምናገኘው በረከት።

ምንጭ ABC News


የአባትንና የእናትን ምክር መስማት


ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ 
የእናትህንም ሕግ አትተው
ለራስህ የሞገስ ዘውድ 
ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና።      
መጽሐፈ ምሳሌ 1፥8


ከ1960ቹ ጀምሮ እንደባህል የተያዘው ወላጆች ኋላ ቀር እንደሆኑና ምንም ሊያስተውሉ እንደማይችሉ፤ ወጣቱንም ሊረዱት እንደማይችሉ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አባቶችን እናቶቻችንን መናቅና እንዳላዋቂ ማየት ሊቅነት ሆኖአል። በመሆኑም በዕድሜ የበለጸጉት አባቶቻችንና እናቶቻችን ከዕድሜያቸው የተማሩትን ከቀደመው ሕይወት የያዙትን  ጥበብና የኑሮ ብልሃት እንደያዙ ተለይተውናል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተነሣው ትውልድ አቅጣጫ ጠቋሚ ያጣ ትውልድ ነው። ይህ በአጠቃላይ በመላው ዓለም የታየ ክስተት ነው። 

እኛን በመሰሉ አዲስ መጤ ማሕበረሰቦች ( Imgrant communities) ደግሞ ችግሩ ሰፊ ነው። ልጆቻችን ከእኛ ቀድመው ቴክኖሎጂውን ቋንቋውን ይይዙታል። በዚህን ወቅት በቤተሰብ ውስጥ ሳናውቀው ሚና እንቀይራለን። ልጆች ራሳቸውን እንደ አዋቂ መቁጠር ይጀምራሉ። ወላጆቻቸውን መስማት ያቆማሉ። በወላጆቻቸው የቋንቋ ችሎታ መሳቅ ሲጀምሩ ሁሉ ነገር እዚያ ላይ ያቆማል። ወላጆችም አውቀውት ይሁን ሳያውቁት ልጆቻቸውን እግዚአብሔር ያስተማራቸውን የኑሮ ብልሃት ማሳየት ያቆማሉ። ለምን ተብለው ሲጠየቁ « እኔን የሚያስተምሩኝ እነሱ ናቸው» ይላሉ። የአውራ ጎዳናውን መውጫ መግቢያ ሊያሳዩን ይችላሉ። ቋንቋውን እንደ አገሬው ተወላጅ (እነርሱም እዚህ ተወልደው ሊሆን ይችላሉ) ሊያንበለብሉት ይችላሉ። ነገር ግን የሕይወትን ጥበብ ከየት ይማራሉ። 
ሕይወት ከቋንቋ በላይ ነው። ሕይወት ከtexting, surfing, driving በላይ ነው። ሕይወት ጥበብ ይጠይቃል። የዚያ ጥበብ መጀመሪያ ደግሞ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።  ልጆች እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ችሎታ አለ። አንዳንዱን በዚያ በብሩህ አእምሮአቸው ከአካባቢያቸው ቀስመውት ያገኙታል። ነገር ግን ከሌላ ከማንም  የማያገኙት ከእኛ የሚማሩት ብዙ ነገር አለ። በሕይወታቸው እጅግ ወሳኝ የሆነ ነገር። 
እግዚአብሔርን መፍራት ከእኛ ይማራሉ። 
ኑሮን በጸጋና በምስጋና መቀበልን ከእኛ ይማራሉ። 
በትንሹ ማመስገንን ከእኛ ይማራሉ። 
ለሌላው መኖርን ከእኛ ይማራሉ። 
በጥንቃቄ መመላለስን ከእኛ ይማራሉ።
የመጀመሪያው የልብ ስብራት ሲያጋጥማቸው፥ የመጀመሪያውን ቼክ ሲቀበሉ፥ የመጀመሪያ ጓደኛ ሲይዙ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ውጪ ሲያመሹ፥ የሚጠቅማቸው ከወላጆቻቸው የተማሩት መሠረታዊ የሆነው የኑሮ ጥበብ ነው። 
አባትና እናት ካለፈው ስኬታቸውም ሆነ ስህተታቸው ተምረው አደጋን ወይም ጥፋትን ከሩቅ ያስተውላሉ። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ ወላጆችን  እንደ smoke detector ወይም ወይም እንደ ውሻ አፍንጫዎች እመስላቸዋለሁ። የጢስ አመልካቹ መሣሪያ በተለይ እንደኔ ላላችሁት ቡና ለምትወዱ እሪታው መንደር ላትወዱት ትችላላችሁ። ሆኖም ቤትን ከመቃጠል ያድናል። እሳት ያሸታል፤ ከእሳት ያድናል።።  በዚያ በክረምቱ በአዲስ አበባ ብዙዎች  በከሰል ጢስ (ካርቦን ሞኖኦክሳይድ)  ታፍነው ያለቁት ጢስ አመልክቴ (smoke detector)  በቤታቸው ስለሌለ ነው። የውሻ አፍንጫ የተቀበረ ፈንጂ  በማነፍነፍ ሰዎችን ከዕልቂት የሚያድን ሆኖአል።  ወላጆች እንደዚህ ናቸው። ዕድሜ፥ ኑሮ፥ የራስ ስህተትና ስኬት ያስተማራቸውን ይዘው ይመክራሉ። ለልጆችና ለወጣቶች የምላቸው ይህን ነው። ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ የእናትህንም ህግ አትተው። 

Monday, November 11, 2013

የተሰባበሩ መስተዋቶች ምሽት (Kristallnacht)

 በመላው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሳውድ አረቢያ ለሚሰቃዩት እኅቶቹና ወንድሞቹ ድምጹን ሲያሰማ፥ በአውሮፓ አንድ ታሪካዊ ዝክር እየታሰበ ነው። በአውሮፓ አቆጣጠር ኖቬምበር 10 ቀን የተሰባበሩ መስተዋቶች ምሽት ወይም በጀርመንኛው Kristallnacht ይባላል። ይህ በናዚ ፓራሚሊተሪዎችና የናዚ ደጋፊዎች የተቀነባበረ ዘመቻ በጀርመንና በኦስትሪያ በሚገኙት አይሁድ ላይ ጥቃትና ድብደባ የተካሄደበት ምሽት 75ኛ ዓመት መታሰቢያ ነው። 
በዚያች አስጨናቂ ምሽት ከ90 በላይ አይሁዶች የተገደሉ ሲሆን ከ30,000 በላይ የሚሆኑ ወደ ማሰቃያ ካምፖች ተወስደዋል። ይህን አሳዛኝ የሆነውን ታሪካዊ ምሽት ለማክበር ክርስቲያኖችና አይሁድ በጋራ ጸሎት አድርገዋል። በኢንግሊዝ አገር በዌስት ሚኒስተር አቤይ ለተሰበሰቡ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ንግግር ያደረጉት ራባይ እንደተናገሩት ይህ ቀን መታሰብ ያለበት በተስፋ መልእክት ነው ብለዋል። 
A boy cleans the street after Kristallnacht in November, 1938.
 አይሁዳውያኑ ሱቆች ተሰባብረው 
A boy cleans the street after Kristallnacht in November, 1938.Photo courtesy Wikimedia Commons/Public Domain

እኚ ራባይ ሲናገሩ « ያን ሽብር፥ ግድያና፥ ውድመት፥ የወላጅ የቤተሰብ የጓደኛ እጦት ስናስብ፥ ዛሬ ክርስቲያኖችና አይሁድ በጋራ ሆነን ተራ የሆኑ ሰዎች አስደናቂ ነገር ማድረግ እንደሚችሉ በማሰብ እናክብር፤. . .  እኛ  ዛሬ በሕይወት ያለነው በመላው ዓለም ላይ ስለሕይወታቸው ፈርተው ያሉትን ልንረዳ ጠመዝማዛውን የቢሮክራሲ ሰንሰለት አልፈን አንድ ነፍስ እንኳ ብንረዳ ብለዋል። በትውፊታችን እንደተጻፈው አንድ ነፍስ ያዳነ አለምን ሁሉ እንዳዳነ ነው» ብለዋል። 
እውነት ነው፤ ራባዩ ያነሱት የአይሁድ ትውፊት ላይ የአንድ ሰውን ሕይወት የገደለ የሰው ዘርን በሙሉ እንደገደለ እንደሚቆጠርም ይነገራል። 
ዛሬ ይህን ታሪካዊ ምሽት ስናስብና 6 ሚሊየን የሚሆኑ አይሁድ ላይ የደረሰውን ሰቆቃ ስናስብ ዛሬም ለአንድ ሰው ሰብአዊ ሕይወት፥ መብትና ነጻነት የመቆም ታላቅ ኃላፊነት አንዳለብን ማስታወስ ይገባናል። 
ይህ አሳዛኝ ድርጊት በአገሩ ላይ ሲደረግ በዝምታ በመመልከቱ ጸጸት ውስጥ የገባው የጀርመን ሉተራን ቄስ ያለውን እዚህ ላይ ማስተዋል አለብን። « መጀመሪያ ወደ ኮሚንስቶች መጡ፥ እኔ ኮሚንስት ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። ቀጥሎ ወደ ሠራተኛ ማኅበራት መጡ የሠራተኛ ማኅበራት አባል ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። ወደ አይሁድ መጡ አይሁድ ስላልሆንኩ ምንም አልተናገርኩም። በመጨረሻ ወደ እኔ መጡ። ስለ እኔ የሚናገርልኝ አንድም የተረፈ አልነበረም። 
 ምንጭ፦Religion News Service 

የሰው ያለህ


“ ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው” 
አለ ያ ታላቁ አርበኛ  ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ 
ባንዳ አገሩን ቢወር ሊያሰማ ኤሎሄ 
ዓይኔን ሰው ራበው አለ እየተጣራ 
በድዮጋን መንፈስ ጮኸ በጠራራ
ጸሐዩዋን ሳያምናት ፋናውን አብርቶ 
ሰው ባይኑ ፈለገ ከገበያው ገብቶ 
እያለ ተጣራ ጮኸ አሰምቶ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው 

ከዚያ ካምደ ወርቁ ከአውደ ምሕረቱ  
ከቤተ ልሔሙ ከቅኔ ማኅሌቱ 
በንባብ በቅኔው በመወድስ ዜማው 
በአራራይ፥ በዕዝል፥ በግዕዝ ቅላጼው 
እያለ ተጣራ ጮኸ አሰምቶ 
ማንም ዞር አላለ የለም የሚሰማ  
« ከመ እንስሳ»  ሆኖ የዕለቱ ዜማ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔ ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው 

ከዙፋን ችሎቱ ከአደባባዩ 
ከሥልጣን ሠገነት ከልፍኝ አስከልካዩ 
አሰምቶ ጮኸ  ዓይኔን ራበው ብሎ 
ያጣውን የሰው ዘር ዓይኑ ተከትሎ 
ከቤተ መንግሥቱም ከተኮለኮሉ 
ሰው አጣ በዓይኑ እንስሳ ነው ሁሉ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የሰው 
የሰው ያለህ የሰው 

ገባ ከጉባኤው ከሊቃውንቱ መንደር 
ሰው ሚገኝበትን ጥበብ ሊመረምር 
ምስክር የሆኑት የመጣፉ መምር 
ቢያነጋግራቸው  የመጣበትን ነገር 
ካፋቸው ቢጠብቅ የሰውነትን ሕግ 
ለካስ ችሎታቸው ሰው እንስሳ ማድረግ 
ዓይኔን ሰው ራበው 
ዓይኔን ሰው ራበው 
የሰው ያለህ የስው 
የሰው ያለህ የሰው 

ከሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ 


Sunday, November 10, 2013

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ሶርያ ክርስቲያኖች

በሶርያ በመካሄድ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ ሕልውናቸውን የማጣት አደጋ ውስጥ የገቡት የአገሪቱ ቀደምት ነዋሪዎች የሆኑትና ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ሶርያን ቤታቸው አድርገው የኖሩት የሶርያ ክርስቲያኖች ናቸው። ብዙዎች ተንታኞች እንደሚናገሩት በዚህ በጦርነቱ ክርስቲያኖች በሁለት በኩል አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል።

በአንድ በኩል እነርሱን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ እስላማውያን « ነጻ አድራጊዎች» ተደርገው በምእራባውያን ሁሉ ሲደገፉ፥ በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራባውያኑ ዘንድ አምባ ገነን ተብሎ የሚታወቀው የአሳድ አገዛዝ ከሚከተለው ዓለማዊ ( secular) አስተዳደር አንጻር ለክርስቲያኖች ውሱን የሆነ ነጻነት ሰጥቶአቸዋል።
« የሚያውቁት ሰይጣን፤ የሶርያ ክርስቲያኖች ለምን ባሽር አልአሳድን ይደግፋሉ » በሚል ግሩም መጣጥፉ ላይ  ገብርኤል ሰኢድ ራይኖልድ የተባለ ጸሐፊ፥ ገና በጦርነት ላይ ያሉት እስላማውያን ተዋጊዎች በያዙዋቸው አንዳንድ ከተማዎች ላይ በክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን በደል በዝርዝር ገልጦአል።

አብያተ ክርስቲያናትን ከመመዝበር አልፎ ተርፎ፥ ካህናቱን በገጀራ እስከማረድ ድረስ ዛሬ በሶርያ የሚታይ ድርጊት በመሆኑ፥ በዚያ ያሉት ክርስቲያኖች ምንም እንኳ ባሽር አልአሳድ የሚያኮራ የሰብአዊ መብት ሪኮርድ የሌለው ቢሆንም ከእርሱ ጋር መወገንን መርጠዋል።

ከሁሉ የሚያሳዝነው የምዕራባውያን መንግሥታት ነው። እንኳን በሶርያ ላሉት ክርስቲያኖች ቀርቶ፥ በቍጥር በዛ ያሉና በምዕራባውያን መንግሥታትም ዘንድ ተሰሚነት ይኖራቸዋል የሚባሉት የግብጽ ክርስቲያኖች በእስላማውያኑ እየደረሰባቸው ያለውን መከራና ስቃይ እንዴት በዝምታ እንዳለፉት ዓለም የሚያውቀው ነው።

ዛሬ ስለ ኢራቅ ክርስቲያኖች የሚያወራ ማን ነው። ነገር ግን የኢራቅ ክርስቲያኖች ላለፉት ሁለት ሺ ዓመታት በኢራቅ ውስጥ የኖሩ ከኢራቅ ቀደምት ነዋሪዎች መካከል የነበሩ ናቸው። ከሳዳም መውደቅ በኋላ ግን እስላማውያኑ የኢራቅ ክርስቲያኖችን ከኢራቅ እንዲጠፉ ነበር ያደረጉአቸው። ይህ አይነቱ ድርጊት በእነርሱ የሚደገም ስለመሰላቸው የሦርያ ክርስቲያኖች ስደትን በመምረጥ ፓስፖርታቸውን እያዘጋጁ መሆናቸውን ብሉምበርግ የተባለው የዜና ማሰራጫ ገልጦአል።

በጎረቤት አገር በኬንያ ስላለው እስላማዊ እንቅስቃሴና በእኛም አገር ቢሆን በዲያስፖራውም ሆነ በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ያለውን እይታ በሰፊው መጣበታለሁ።