በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ
መግቢያ
በፕሮፌሰር ብራድሊ ናሺፍ የተጻፈውን ስለጳጳሳት ሐዋርያዊ ተልእኮ የሚያትተውን ጽሑፍ በጡመራ መድረካችን ላይ ካስቀመጥንበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አስተያየቶች ደርሰውናል። በዋናነት የሚጠቀሰው ግን ምንም እንኳ ፕሮፌሰር ናሺፍ ያነሡዋቸው ነጥቦች በወል ሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት የሚዳስሱ ቢሆኑም፥ የእኛን ቤተ ክርስቲያን ዐበይት ችግሮች በጥልቀት የሚዳስሱ ጽሑፎች ስለማስፈለጋቸው ነው ምንምን እንኳ ይህ የሁላችንንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም እኛ ቃል እንደገባነው በፕሮፌሰሩ መነሻ ነጥቦች ላይ በመመርኮዝ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ላይ የሚያጠነጥነውን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል አቅርበናል።
ወደጽሑፋችን ዋና ሐሳብ ከመግባታችን በፊት ግን የሚከተሉትን ነጥቦች ለማስጨበጥ እንሞክራለን። አንደኛ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ላለችበት ሁኔታ ተጠያቂ የምናደርገው አንድን ቡድን ወይም አካል ሳይሆን ሁላችንንም ነው። ይህን የምናደርገው ለይምሰል ወይም የዘመናዊ ሐሳብ ፍሰት አካሄድ ስለሆነ ሳይሆን፥ እነ ዳንኤል እነ ኤርምያስ ስለሕዝባቸው ስለአገራቸው ያላቸውን ጭንቀት በገለጡበት ወቅት የተከተሉትን መንፈስ ተከትለን ነው።
ሁለተኛ ይህን ለቤተ ክርስቲያናችን ይጠቅመናል የምንለውን ሐሳብ የምናቀርበው ለቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ ልጆች ነው። እውነተኛ ልጆቹዋ እነማን እንደሆኑ የሚያውቀው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ውጫዊ ምልክቶች ግን አሉዋቸው። ከእነዚህም ምልክቶች ዋነኛው ፍቅር ነው። አገልግሎት የሚመነጨው ከዚህ ፍቅር ነው። እምነታቸው እንኳ ለገላትያ ሰዎች ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው « በፍቅር የሚሠራ እምነት» ከዚህ የተነሣ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ስለሚጠፉት ሰዎች ይገዳቸዋል። በእንባና በጸሎት ያስተምራሉ ይመክራሉ የመድኃኔ ዓለምን ሞቱንና ትንሣኤውን ይመሠክራሉ።