Tuesday, October 21, 2014

እግዚአብሔር በክርስቶስ መረጠን

Read in PDF

እግዚአብሔር በክርስቶስ መረጠን ። 
ኤፌሶን 1፥4 
ሐዋርያው በዚህ በዛሬው ዕለት በምንመለከተው ክፍል የሚያነሳው ዋና አሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኛቸው አስደናቂ መለኮታዊ ክንውኖች መካከል ዋና የሆነውን ነገር ነው። እርሱም እግዚአብሔር እኛን የመረጠበት መንገድ ነው።  ምርጫ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን ቸርነት የምንመለከትበት እይታ እንጂ ደረቅ ስሌት አይደለም።  እኛን መርጦናል እነእገሌን አልመረጠም ብለን በትምክህት የምንጎራደድበት አይደለም።  ክርስቲያኖች የሆንን እኛ ሕይወታችንን ስንመለከት፥ እግዚአብሔር ያደረገልንን ቸርነት ስንረዳ ሕይወታችን  ሁሉ በጥልቅ አምልኮ ይመላል። ምክንያቱም የተደረገልን ሁሉ ከእኛ እንዳልሆነ እናውቃለንና። ከሌሎች የማንሻል ስንሆን አምላካችን ቸርነቱን ለምን አበዛልን? በምንስ ምክንያት ጠራን ስንል መልሱ እርሱ ስለወደደን፥ ስለመረጠን ነው የሚል ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ይህን አደረገ። እግዚአብሔር አሰበን፥ እግዚአብሔር ጎበኘን እንላለን።  

በዘዳግም 7፥6 ላይ ሙሴ ለእስራኤላውያን ያላቸው ይህን ነበር። «ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ።እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና» ሙሴ ለወገኖቹ እያለ ያለው፥ የእኛን ሁኔታ ስመለከተው አሁን ለበቃንበት ሁኔታ ያለኝ መግለጫ አንድ ብቻ ነው። እርሱም የእግዚአብሔር ምርጫ ወይም የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ «እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።» በማለት ተናግሮአል።  ዮሐንስ 15፥16። 

እግዚአብሔር እኛን መምረጡን ማሰብ ለምን ይጠቅማል ስንል መልሱ የክርስትናን ሕይወት ሁሉ የሚዳስስ ነው። በእግዚአብሔር መመረጣችንን ስናስተውል፥ የሰው ትምክህት ስፍራ ያጣል። ድካማችንን በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጠን በእግዚአብሔር ላይ ማረፍ እንጀምራለን። የምንደገፈው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ይሆናል። ምክንያቱም ከመጀመሪያውም በዚህ ጸጋ ወደ መንግሥቱ እንደተጠራን ተገንዝበናልና። በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት የጸና ይሆናል። በዚህ ዓለም ጣጣ ከመባከን እግዚአብሔርን በማመስገን መኖር እንጀምራለን።  ለመሆኑ እግዚአብሔር መቼ መረጠን? ለምንስ መረጠን? የምርጫውስ ግቡ ምንድነው? 


ዓለም ሳይፈጠር መረጠን 
ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።

እግዚአብሔር እኛን የመረጠን ዓለም ሳይፈጠር ነው፤ ይህ ዓለም ሳይፈጠር የሚለው ቃል እግዚአብሔር ስለእኛ ማሰብ የጀመረው፥ የእኛን የመዳን መንገድ ማዘጋጀት የጀመረው፥ እኛን ከመፍጠሩ በፊት፥ ዓለምን ሳይመሠርት በፊት እንደሆነ የሚያመለክት ነው። መዳናችን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። (ኤፌ 2፥8፡9) እንደእውነቱ ከሆነ ይህ የእግዚአብሔር ምርጫ የእኛን ማዳን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ሃሎ እግዚአብሔር በመንግሥቱ፤ ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር በመንግሥቱ ነበረ» በማለት አባቶቻችን በቅዳሴያቸው እንዳመሰገኑት እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር በክብሩ በሥልጣኑ፥ በመንግሥቱ ያለ አምላክ ነው። እኛን የፈጠረው ረዳት ሽቶ አይደለም። ወደፊት በሰፊው እንደምናየው እኛን መፍጠሩ እንኳ ከፍቅሩ የተነሣ ነው።  

እግዚአብሔር ሳይሆን ቀድሞ፥ ከዘመን በፊት አስቀድሞ ለእርሱ የሚሆኑትን እንደሚመርጥ፥ ለአገልግሎት እንደሚጠራ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን በነበሩት የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሕይወት ውስጥ እናየዋለን። ኤርምያስን «የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።።» ነበር ያለው። ኤር 1፥4፡5። ቅዱስ ጳውሎስም ለገላትያ ክርስቲያኖች ስለ ሕይወት ታሪኩ ሲተርክ እግዚአብሔርን «በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር» በማለት ነበር የጠራው። ገላ 1፥15። ሐዋርያው እያለ ያለው ከእናቱ ማኅፀን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንከን የለሽ እንደመራ አይደለም። ነገር ግን እያንዳንዱን የሕይወቱን ክንውን የሚያውቅ አምላክ ጳውሎስን አስቀድሞ ማወቁን፥ በኃጢአት እያለ እንኳ፥ በእግዚአብሔር የተወደደ መሆኑን ነው።  ልበ አምላክ ዳዊትም  «እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም።ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።» በማለት እግዚአብሔር የወደደው ያፈቀረው፥ በቸርነቱ ያሰበው ገና በእናቱ ማኅፀን ሳይሠራ እንደሆነ ገልጦአል።  መዝ 138፥15፡16። 


ብዙውን ጊዜ ስለማንነታችን ስናስብ ይህን ታላቅና ዘላለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን እቅድ ማሰብ ይኖርብናል። ዓለም ሳይፈጠር የመረጠንን አምላክ ስናስብ፥ የዛሬው ጉድለታችን፥ ውድቀታችን፥ ማግኘትችን ይሁን ማጣታችን ማንነታችንን እንደማይወስነው እንገነዘባለን። ሰዎች ስለእኛ የሚናገሩት በዛሬው ማንነታችን ላይ ተመሥርተው ነው። እግዚአብሔር ግን ስለእኛ የሚናገረው ዓለም ሳይፈጠር ባዘጋጀልን ዘላለማዊ ዕቅድ ላይ ሆኖ ነው፥ ክብርና ምስጋና ለዚህ የፍቅር ጌታ ይሁን። አሜን። 

No comments:

Post a Comment