Read in PDF
« ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።» ኤፌሶን 1፥4።
በፍቅር የተሞላ አምላክ እኛን የመረጠን በፍቅሩ ነው። በዘላለም ፍቅሩ ነው። ወንጌላውያኑ ተባብረው እንዲህ ይላሉ። « ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ማርቆስ 3፥13። ዮሐንስ ደግሞ እንዲህ ይላል « ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። ዮሐንስ 13፥1። የመረጠን በፍቅሩ ነው።
ይህ ቃል በሚቀጥለው ቍጥር በሰፊው እንደምናየው ሰፊ አንድምታ አለው። ፍቅሩ ልጁ ነው። እግዚአብሔር እኛን ያድን ዘንድ ከፈጠረው ፍጥረት መካከል አንዱን አልላከም። የላከው የሚወደውን፥ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድ ልጁን ነው። በቅዳሴያችን፥ በማኅሌታችን «በፍቁር ወልድከ በውድ ልጅህ» እያልን የምንጸልየው የምናዜመው፥ የምናመሰግነው ለዚህ ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጠው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ነውና።
እንደገና የመረጠን በዚሁ ፍቅር እንመላለስ ዘንድ ነው። « በፍቅሬ ኑሩ» የእርሱ አቢይ ትእዛዝ ነው። ይህ ማለት እግዚአብሔር አለም ሳይፈጠር ላቀደልን ታላቅ ዓላማ ልጁን ወደመምሰል መድረስ የምንችለው በእርሱ ፍቅር ስንኖር ነው። ፍቅሩ የሕይወታችን የኑሮአችን ማዕከል ሲሆን ነው። «በፍቅር የሚሰራ እምነት» የሰጠንም ለዚህ ነው። እርሱን ሳንወድ ወይም በእርሱ ፍቅር ሳንኖር እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ልንሠራ አንችልም፤ በመላእክት ልሳን ብንናገር፥ ያለንን ሁሉ ለድሆች ብንመጸውት፥ ሰውነታችንን ለእሳት አሳልፈን ብንሰጥ፥ ተራራንን የሚያንቀሳቅስ እምነት ቢኖረን ፍቅር ከሌለን ከንቱ ነን። ( 1 ቆሮ 13)
ለቅድስና የመረጠን ጌታ በፍቅር እንድንኖር መርጦናል። አለምክንያት አይደለም ቅድስናና ፍቅር አብረው ይሄዳሉ። በፍቅር ውስጥ ያለ ሰው የሚያስበው በንጽሕና ራሱን ለሚያፈቅረው ማቅረብን ነው። ፍቅር ሳይኖር ቅድስናን ማሰብ አይቻልም። ሊኖርም አይችልም። ፍቅር በሌለበት ሕይወትና ቤት ውስጥ የመጀመሪያው የሚጠፋው ነገር ቅድስና ነው። እግዚአብሔርን ሳትወዱት በቅድስና መኖር አትችሉም። ወንድሞቻችንን ሳንወድ በቅድስና መኖር አንችልም። በፍቅር መኖርን ታላቅ የክርስትናችን መንገድ ማድረግ ያለብንም ለዚህ ነው።
ብዙዎች ለእምነት ታላቅ ትኩረት እንሰጣለን የሚሉ፥ ከቤተ ክርስቲያን የማይጠፉ፥ በቅዳሴው፥ በማኅሌቱ፥ በማናቸውም ሥራ የሚተጉ፥ ፍቅር አልባ በሆነ ሕይወት ሲመላለሱ ይታያሉ። እነዚህን ሰዎች ቀረብ ብላችሁ ሕይወታቸውን ስትመለከቱ፥ የሚታገሉት ፍቅር አልባ በሆነ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ቅድስና አልባ በሆነም ሕይወት ነው። እንደገና እደግመዋለሁ። ፍቅር ከሕይወታችን ከቤታችን ሲወጣ ቅድስናም ይከተላል። ቅድስና በሌለበት ሕይወትም ፍቅር የለም፤ የቱንም ያህል « የፍቅር ቃላት» ይደርደር እንጂ፥ ቅድስና የሌለበት ሕይወት ፍቅር የለውም። ለዚህ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም ዙሪያ ገባውን ማየት ብቻ ነው የሚያስፈልገው።
እኔና እናንተስ? በፍቅር በወደደን አምላክ ትእዛዝ ውስጥ ውስጥ ሆነን በእርሱ ፍቅር እየኖርን ነውን? ፍቅሩን የሕይወታችን ማዕከል አድርገነዋልን? በመስቀል ላይ ፍቅሩን የገለጠለን ጌታን ፍቅሩን፥ ውለታውን፥ ቸርነቱን በማሰብ ሕይወታችንን በእርሱ ላይ እንድናሳርፍ እግዚአብሔር ይርዳን።
No comments:
Post a Comment