ፈሪሳውያን ለጌታ ኢየሱስ በማሰብ (አንዳንድ ደግ ፈሪሳውያን አይጠፉምና) ሄሮድስ ሊግድልህ ስለሚፈልግ እባክህ ከዚህ ዘወር በል ብለውት ሲመክሩት እናያለን:: ነገሥታት በምድራዊ ሥልጣናቸው ሥር ብዙ የሚታዘዝ ኃይል ስላላቸው የሚያስፈሩ ሊመስሉ ይችላሉ:: ሆኖም ግን የሥልጣናት ሁሉ ጌታ የሆነው እርሱ ሥልጣን ላላቸው የሚናገር ነው:: በመሆኑም ሄሮድስ በጌታ ኢየሱስ ሕይወት ላይ ሥልጣን እንደሌለውና ነገር ግን በአባቱ ፈቃድና በራሱ ፈቃድ ሞቱ በኢየሩሳሌም እንደሚሆን ይናገራል:: ሆኖም ግን የጌታን ልብ የሰበረው በተንኮሉና በክፋቱ በነፍሰ ገዳይነቱ ቀበሮ የተባለው የሄሮድስ ጌታን ለመግደል መሞከሩ ሳይሆን የኢየሩሳሌም መሲሁንና አዳኟን አለመቀበልዋ ነበር:: ዶሮ ጫጩቶቹዋን ከጭልፊት እንደምትሰውር በክንፎችዋ ከብርድ ሰውራ ሙቀት እንደምትሰጥ ጌታም ኢየሩሳሌምን ከሚመጣባት ፍርድ ለመሰወር ምን ያህል እንደፈለገና ነገር ግን ኢየሩሳሌም የጌታን ፍቅርን ለመቀበል እምቢተኛ እንደሆነች ይነግረናል::
ኢየሩሳሌም የአምላኩዋን ፍቅር እምቢ ብላ መግፋትዋ በስተኋላ በ70 ዓም ፍራሽ በፍራሽ እንድትሆን ልጆቹዋም በመላው ዓለም እንዲበተኑ አድርጎአል:: የጌታንም ልብ የሰበረው ይህ ሊመጣ ያለው የእግዚአብሔርን ፍርድ ለማየት አለመቻላቸው ነበር::
በአመዛኙ በሃይማኖታዊ ህይወታችን ብዙ የምንጨነቀው እግዚአብሔርን የምናስድስትባቸው ብለን ስላዘጋጀናቸው ነገሮች ነው:: ይህ ሁሉ ጥሩ ሆኖ ግን እኛው ባቆምናቸው ህጎች ወጎችና ሥርዓቶች ተውጠን ስንቀር ግን እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን መልካም ነገር ለማየት ያቅተናል:: ዋናውን ነገር እንረሳዋለን:: ሌት ተቀን በጾም ሰውነታቸውን የሚያደክሙ ነገር ግን ወንድማቸውን ይቅር ለማለት የማይችሉ ሰዎች ብዙዎች ናቸው:: እንደ አገሬ ደብተራ ማኅሌተ እግዚአብሔርን አደርሳለሁ ብሎ በአምላኩ ፊት ቆሞ እርሱ ግን በዜማው ወዝ ምክንያት ከጓደኛው ጋር በመቋሚያ ይደባደባል:: ዋናውን ነገር መርሳት በትንሹ ነገር ላይ ዋጋ መክፈልን ያመጣል::
አምላኬ ከልቤ ይልቅ ቅርብ እንደሆነ ሳስተውል ከምንም በላይ ላደርግ የሚገባኝ ነገር ቢኖር የእርሱን ፍቅር የእርሱን ምህረት ለመቀበል ልቤን ማዘጋጀት ነው::
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
-
የቅዱስ ጳውሎስ አጭር ታሪክ ስለ ጳውሎስ ማንነት በጥልቀት የምናገኘው ሉቃስ ከጻፈልን ከሐዋርያት ሥራ እና ከራሱ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ነው። 1. በጠርሴስ ተወለደ ቅዱስ ጳውሎስ በአሁኑ ዘመን በ...
-
እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ይህ ምሳሌ በተለምዶ > ተብሎ ነው የሚጠራው:: በነገራችን ላይ ስያሜው የመተርጉማን ነው እንጂ የወንጌል ወይም የጌታ አይደለም:: ጌታ ምሳሌውን የሚጀምረው አንድ ሰው...
-
የጌታን ልደት ከማክበራችን በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላቅ ሥፍራ አላቸው። ከዘጠኙ ንዑሳን የጌታ በዓላት መካከል የሚቆጠሩም ናቸው። የመጀመሪያው ሳምንት ስብከት፥ ሁለተኛው ብርሃን፥ ሦስተኛው ...
No comments:
Post a Comment