እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።
ይህ ምሳሌ በተለምዶ << የጠፋው ልጅ ምሳሌ>> ተብሎ ነው የሚጠራው:: በነገራችን ላይ ስያሜው የመተርጉማን ነው እንጂ የወንጌል ወይም የጌታ አይደለም:: ጌታ ምሳሌውን የሚጀምረው አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት ነው የሚለው:: ይህ የምሳሌው መክፈቻ በታሪኩ ውስጥ ስላሉት ሦስት ዋና ገጸ ባህርያት ይነግረናል:: አንድ ስለአባት ሁለተኛ ስለታናሽ ልጅ እና በመጨረሻም ስለ ታላቁ ልጅ:: ስለሆነም ታሪኩን ለመዳሰስ ከአባትየው ብንጀምር ደስ ይለኛል::
ይህን ታሪክ ላይ ላዩን ስንመለከት የሁለቱ ልጆች ታሪክ ይምሰል እንጂ የታሪኩ ዋና እምብርት አባትየው ነው:: አባትየው ከ12 ጊዜ በላይ ሲጠቀስ በልጆቹ በኩል ደግሞ በተዘዋዋሪ በብዛት ተጠቅሶአል:: ሉቃስ በዚህ ታሪክ ላይ ከምንም በላይ ሊያጎላን የሚፈልገው ይህ አባት ለልጆቹ ምን ያህል ፍቅር እንዳለው እና ፍቅሩንም ለሁለቱ ልጆች እንደገለጠ ይነግረናል:: ታሪኩን በጥንቃቄ ከተከታተልነው ሁለቱ ልጆች እነማን እንደሆኑ እንመለከታለን:: መጀመሪያ የታናሹን ልጅ ታሪክ እንመልከት
12 ከእነርሱም ታናሹ አባቱን። አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው።
ይህን የመጀመሪያውን ክፍል በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ሲሰሙ ምን ያህል ድንጋጤ እንደሚሰማቸው አልነግራችሁም:: ምክንያቱም የታናሹ ጥያቄ ሁለት ታላላቅ ስህተቶችን የያዘ ነው:: በዚያን ዘመንም ሆነ አሁንም ውርስ ከሞት በኋላ ነው:: ስለሆነም አባት ገና በህይወት እያለ የሚደርሰኝን ስጠኝ ማለት ለአባት ታላቅ ስድብ ነው:: ይህ ማለት አባቴ ሆይ እስከ ዛሬ ብዙ ጠበቅሁኝ አንተ አትሞትም:: አሁን ግን አንተን ማየት ስለሰለቸኝ አንተን አልፈልግህም ገንዘብህን ግን ስጠኝ ማለት ነው:: አስተውሉ <<ገንዘብህ>> ነው ያለው: እንጂ ገንዘቤን ስጠኝ አላለም:: ገንዘቡ የአባቱ ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ይህ ታናሹ ልጅ የኖረን ይትበኻል ያፈረሰ ነው:: በዚያን ዘመን ይትበሃል የመጀመሪያው ወራሽ በኩር ልጁ ነው:: ታላቁ ልጅ ነው:: ሆኖም ታላቁ ልጅ እያለ ነው ታናሹ የጠየቀው:: ሌላ አባት ቢሆን ኖሮ በዚህ ልጁ ድርጊት አዝኖ እና ተናዶ ከልጅነት ይፍቀው ነበር ይህ አባት ግን እንዲ አላደረገም:: ምንም እንኳ አባቱን በጸያፍ ጥያቄ ቢያስነውርም ምንም እንኳ የታላቅ ወንድሙን ክብር ቢጋፋም አባትየው ግን አባቱ የልጁን ጥያቄ ሲፈጽምለት እናያለን::
13 ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ።
የአባቱ ቸርነት ግን ይህን ታናሽ ልጅ ወደ ማስተዋል አላመጣውም ነበር:: እንዲያውም በአባቱ ለጋስነት መጠን ኃጢአትን ማድረግን ፈለግ:: የአባቱን ጸጋ አባከነ በተነ:: ወደሩቅ አገር የሄደው ምናልባትም የአባቱን ተግሳጽ ላለመስማት ይሆናል:: ወደ ሩቅ አገር የሄደው አባቱ እንዳይመለከተው ይሆናል:: ለማንኛውም የሄደበት አገር ግን የፍሬ ሳይሆን የብክነት የማከማቸት ሳይሆን የመበተን አገር ነበር::
እነዚህ ጥቅሶች ላይ ቆም እንድርግና እግዚአብሔር ለልጆቹ የሚሰጠውን ጸጋ እናስተውል:: በማቴዎስ 5:45 ላይ የሚገርም ነገር ይነግረናል:: << እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።>> ማለት እግዚአብሔር ጸጋውን ሲሰጥ ጸሎትን ሲመልስ ለሁሉም ልጆቹ ነው:: እደግመዋለሁ ለሁሉም ልጆቹ ነው:: ጥያቄው ግን በተሰጠን ጤንነት በተሰጠን የጸሎት መልስ በተሰጠን ዕድሜ ምን ሰራንበት:: ይህ ልጅ ሊሰጠው የማይገባውን ጸጋ ለእርሱ የማይገባውን ጸጋ እንደተሰጠው ተመልከቱ:: ነገር ግን የተባለው << ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ::>>
የእግዚአብሔርን ጸጋ መቀበል የጸሎትን መልስ ማግኘት: በእግዚአብሔር ክንድ መፈወስ አንድ ነገር ነው:: ታላቁ ነገር ግን ከባለጸጋው አምላክ ይህን ቸርነት ይህን ፍቅር ይህን ሰውን መውደድ ከተቀበልን በኋላ ምን አደረግነው ነው:: በእግዚአብሔር ቤት በቆየሁባቸው አጭር እድሜዬ ከእግዚአብሔር ታላላቅ ጸጋዎችን የተቀበሉ ሰዎችን አይቼአለሁ:: ሲቀድሱ ሰውን ወደሰማየ ሰማያት የሚወስዱ ማኅሌቱ ውስጥ ሲገቡ አንዱ የሃያና የሰላሳ ሰው ኃይልና ውበት ያላቸው:: ሲሰብኩ አፍ የሚያስከፍቱ:: ከምእመናንም አይቼአለሁ:: የፈውስ የትምህርት የእውቀት ጸጋ የሰጣቸው:: ነገር ግን በዚያው መጠን ደግሞ እንዚያ ሰዎች እንዴት እንደወደቁ አይቻለሁ:: በእግዚአብሔር ቤት ጸጋውን መቀበል ብቻ ሳይሆን በዚያ ጸጋ መኖር ታላቅ ነገር ነው::
14 ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር።
ይህ ልጅ መቀበሉን እንጂ መኖሩን አላወቀበትም:: ስለሆነም ከሰረ:: መቀበልን እንጂ መኖርን ያላወቁ ለማግኘት ሩቅ አትሂዱ ሎተሪ እጣ የደረሳቸው ሰዎችን ጠይቁ:: የሚበዙቱ መቀበልን ብቻ ያወቁ ናቸው:: ሃሊውድ በቢሊየኖች የሚንቀሳቀስ ኢንዱስትሪ ነው:: የሚበዙቱ ግን መቀበልን ብቻ የሚያውቁ ናቸው:: ብዙዎች የትረስት ፈንድ ልጆች መቀበልን ብቻ የሚያውቁ ስለሆኑ ህይወታቸው በሚያሳዝን ሁኔታ ተቀጥፎአል:: ወይም ከስሮአል::
ይህ ረሃብ መንፈሳው ረሃብን የሚያመልክት ነው:: የእግዚአብሔርን ቃል ረሃብ የሚያመለክት ነው:: << እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም።>> አሞጽ 8:11::
15 ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።16 እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።
ይህ ታሪክ እየተነገረ ያለው ለእስራኤላውያን ነው::በመሆኑም ይህን የልጁን ድርጊት ሲሰሙ ሳያስደነግጣቸው አይቀርም:: ምክንያቱም ልጁ ምን ያህል ችግር ውስጥ እንደገባ የሚገልጥ ነው:: በእነርሱ ዘንድ እሪያን መንካት እንኳ የሚያረክስ ነው:: በመሆኑም መብላት ብቻ ሳይሆን ማርባትም ክልክል ነው:: ከአባቱ ጸጋ ከአባቱ ቤት ስለወደቀ ይህ ልጅ የእሪያዎች እረኛ ሆነ:: ይህ ብቻ አይደለም አንዴ ከእግዚአብሔር ጸጋና ከእግዚአብሔር ፍቅር ሰው ሲወድቅ የሚሆነውን ተመልከቱ:: ጴጥሮስ ክሪሶሎጎስ እንዳለው << ይህ በአባቱ ላይ መታመንን እምቢ ያለና ራሱን ለባእድ ያስገዛ>> ነው:: በመሆኑም << ባለጸጋ መጋቢ ከሆነው አባቱ ሮጦ ከጽኑ ፈራጅ ዘንድ አደረ:: >> የኃጢአት አስከፊነት ሰውን ፍጹም ማንነቱን እንዲረሳ ማድረጉ ነው:: ያ ክብርና የባለቤትነት ክብር ፍጹም ስለተረሳ አሁን እሪያዎቹ ከሚበሉት መብላት እንዲመኝ አደረገው::
እሪያዎች ቅጠላ ቅጠል ብቻ ሳይሆን ያገኙትን ሁሉ የሚበሉ ናቸው:: ምግብ ፍለጋ መሬቱን ሁሉ ስለሚያነፈንፉ አካባቢያቸውን ሁሉ ያጨቀዩታል:: ያን የተጨማለቀ አሰር መመኘቱ ሳያንስ መጽሐፍ የሚለን እርሱን እንኳ << የሚሰጠው አልነበረም:: >>
17 ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ።
ቀደም ብለን እንዳልነው በኃጢአት ዓለም ውስጥ ያለ ሰው የሚለየው ከሰማያዊ አባቱ ብቻ ሳይሆን ከእውነተኛው ማንነቱም ነው:: በመሆኑም ጌታ በምሳሌው የጠፋው ልጅ የአባቱን ቤት ያሰበበትን ወቅት ወደልቡ የተመለሰበት ወቅት አደረገው:: በምን ምክንያት ወደ ልቡ ተመለሰ? እንዴት ተመለሰ ብለን ስንጠይቅ ፍሎክሴኒዩስ ወይም ፊልክስዩስ የተባለው የቤተ ክርስቲያን አባት እንደተናገረው ከሆነ ምንም እንኳ በኃጢአት አለም ቢሆንም እግዚአብሔር አባትነቱን አልነፈገውም:: ምንም እንኳ ከእርሱ ፊት ሸሽቶ ወደ ሩቅ አገር ቢሄድም አባቱ አልረሳውም:: ወደ እውነተኛ ማንነታችን ስንመለስ የመጀመሪያው የምንገነዘበው ነገር ቢኖር የሕይወታችንን ዓላማ ነው:: እስከዛሬ ይህ ልጅ የጠፋ ልጅ ነው:: ይህ ልጅ አባካኝ ልጅ ነው:: ይህ ልጅ በመጨረሻ የአሳማ እረኛ ነው:: አሁን ግን ወደ ልቡ ሲመለስ << አባቴ>> አለ:: ማለት የባለጸጋው የርህሩሁ አባት ልጅ እንደሆነ አስተዋለ::
18 ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥19 ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።20 ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ።
ይህ ክፍል የእውነተኛ ንስሐ ምንነትን የሚያመለክት ነው:: እውነተኛ ንስሐ ቁርጥ የሆነ ውሳኔ ኃጢአተኝነትን ማመንና መጸጸት እንዲሁም በመጨረሻ ፍጹም መመለስን የያዘ ነው:: በመጀመሪያ ያለው ተነሥቼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ:: ማለት ይህ ያለሁበት የውርደት ኑሮ ይብቃ:: ይህ ያለሁበት የሃዘንና የጭንቀት ኑሮ ያብቃ አለ:: ወደ አባቴ እመለሳለሁ::
ይህ ስለራሳችን ቆም ብለን የምናስብበት መሆን አለብን:: በምን አይነት ህይወት እንዳለን ራሳችንን እንመርመር :: እግዚአብሔርን በማያስደስትና የተፈጠርንበትን ታላቅ ዓላማ የማያገናዝብ ርኩሰትና ኃጢአት ውስጥ ካለን ግን ዛሬ የውሳኔ ጊዜ ይሁንልን::
ወደአባቴ ዘንድ እሄዳለሁ ብቻ ሳይሆን ይህ ልጅ አባቱን ምን ያህል እንደበደለው ተገንዝቦ ነበር በመሆኑ አባቱን << አባቴ ሆይ በሰማይና በምድር በደልሁህ >> እንደሚለው ተናገረ:: ምክንያተኝነትን መጣል አንዱ የንስሐ ምልክት ነው:: የኃጢአታችን ክብደት የሚሰማን የአምላካችንን ፍቅርና ውለታ ሲገባን ነው:: ለኛ ያለው ርህራሄው ቸርነቱ ሲገባን ነው:: ያን ጊዜ << አባቴ ሆይ በሰማይና በምድር በደልሁህ>> በዘመናችን ክልሼ ከሆነው << አበስኩ ገብርኩ >> ውጪ በእውነተኛ መንገድ ስህተቱን ኃጢአቱን የሚያምን እየጠፋ ስለመጣ ይቅርታን የሚጠይቅ የለም:: ይህ ልጅ ያደረገውን ግን ተመልከቱ:: ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ሲወስን አብሮ እውቅና የሰጠው ነገር ቢኖር ምን ያህል አባቱን መበደሉን ነበር::
ይህ ወደሚቀጥለው ክፍል ያመጣልናል:: እውነተኛ የሆነ የኃጢአት ወቀሳ በልቡ ስላረፈ ፍጹም ጸጸትም አድሮበት ነበር:: በመሆኑም << ልጅህ ልባል አይገባኝም>> እለዋለሁ አለ:: ይህን ንግግር እውነተኛ የሆነውን የልጁን ስህተት መጠን የሚያሳይ ነው:: ቀደም ብለን እንዳልነው አባቱ በፍቅሩ ባያልፈው ኖሮ የልጁ ድርጊት ከልጅነት የሚያስፍቀው ነበረ:: ይህ አሁን ስለገባው አባቴ ልጅህ ልባል አይገባኝም እለዋለሁ አለ:: ጸጸት ብቻውን የትም እንደማያደርስ ከይሁዳ ፍጻሜ አይተነዋል:: የዚህ ልጅ ጸጸት በአባቱ ፍቅር ዙሪያ ያጠነጠነ ነው::
ከወሰነ ኃጢአተኝነቱን ከተገነዘበና ከተጸጸተ በኋላ የመጨረሻውን እርምጃ ተጓዘ:: ያም ወደ ሸሸው አባቱ መምጣቱ ነበር:: ጌታ ይህን ሲነግረን << ተነስቶም ወደ አባቱ መጣ>> ይለናል:: ይህ እጅግ ወሳኝ የሆነ እርምጃ ነው:: ቁጭ ብለን ንስሐ ብንገባ ቁጭ ብለን ብንጸጸት የወሰንነውን ተግባራዊ ካላደረግን ማለትም ወደ እግዚአብሔር ካልቀረብን እውነተኛ የሆነውን የሕይወት ለውጥ አናገኝም:: ለዚህም ነው ያዕቆብ በመልእክቱ << እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤8 ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።>> በማለት የተናገረው:: ያዕቆብ 4:7-8::
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
-
የጌታን ልደት ከማክበራችን በፊት ያሉት ሦስት ሳምንታት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላቅ ሥፍራ አላቸው። ከዘጠኙ ንዑሳን የጌታ በዓላት መካከል የሚቆጠሩም ናቸው። የመጀመሪያው ሳምንት ስብከት፥ ሁለተኛው ብርሃን፥ ሦስተኛው ...
-
የአባቶቼ አምላክ፥ አምላከ ቅዱሳን አምላከ አበው ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ከፍ ካሉት ሁሉ በላይ ከፍ ያልህ ነህ፤ ሥራህ ከአእምሮ በላይ ነው። ኃይል ከመነገር በላይ ነው። ኃጢአተኛ እና በደለኛ የሆንኩትን እኔን ልጅ...
-
የቅዱስ ጳውሎስ አጭር ታሪክ ስለ ጳውሎስ ማንነት በጥልቀት የምናገኘው ሉቃስ ከጻፈልን ከሐዋርያት ሥራ እና ከራሱ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ነው። 1. በጠርሴስ ተወለደ ቅዱስ ጳውሎስ በአሁኑ ዘመን በ...
kale hiwot yasemalen
ReplyDelete