Tuesday, December 13, 2011

የሉቃስ ወንጌል 15 የጠፋው በግና የጠፋው ድሪም


1 ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር።2 ፈሪሳውያንና ጻፎችም። ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ።

ቅዱስ ጳውሎስ በሕይወቱ መጨረሻ ዘመን ላይ ለተወዳጁ ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱ ላይ የወንጌልን ማዕከላዊ መልእክት ከራሱ የሕይወት ታሪክ ጋር አነጻጽሮ ሲናገር << ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤>> ብሎ ነበር:: 1 ጢሞቴዎስ 1፥15:: የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ መገለጥ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ዓለም መምጣት ኃጢአተኞችን ለማዳን ነው:: ይህ አዳኝ የሆነው ጌታ በማህጸነ ማርያም ሳይጸነስ ይህ ተልእኮው በእግዚአብሔር መልአክ ተነግሮ ነበር:: << ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።>> ማቴዎስ 1:21:: አስተውሉ ኢየሱስ ወይም መድኃኒት የሚለው ስም ጌታ ኃጢአተኞችን ለማዳን መምጣቱን የሚያመለክት ነው::

በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ላይ እንደምናየው ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ያንጎራጎሩትና የተቆጡት ጌታ የመጣበትን ይህን ታላቅ ዓላማ ስላከናወነ ነበር:: ጌታ ኢየሱስ ባለበት ስፍራ የኃጢአት ሸክም የከበደባቸው የኃጢአት ደመወዝ ያስፈራቸው የኃጢአት ቀስት ያቆሰላቸው ይሰበሰቡ ነበር:: በድን ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ እንደተባለ ጌታ ባለበት ስፍራ ዓለም የናቀቻቸውና ያቃለለቻቸው በሃይማኖተኞች ዘንድ ስፍራ የሌላቸው ሰውዎች በጌታ ዙሪያ ይሰበሰቡ ነበር:: አጋንንት ያሰሩአቸው ነጻነትን ሽተው ይሰበሰቡ ነበር:: በኃጢአት ባርነት ያሉ እና መውጫ በሩ የጠፋባቸው መንገዱን በሩን ሽተው ይሰበሰቡ ነበር::

ባለፈው ሳምንት እንዳየነው ጌታ እግዚአብሔር ህዝቡን በህይወት መንገድ እንዲያሰማሩ የሾማቸው እረኞች ያደረጉትን አይተናል:: በሕዝቅኤል አፍ ራሱ እግዚአብሔር እንደነገረን እንደነገረን እረኞች ራሳቸውን ነበር ያሰማሩት:: እረኞቹ በጎቹን ይጠቀሙባቸው ነበር እንጂ በጎቹን አያሰማሩም ነበር:: <<ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።>> ሕዝቅኤል 34:3-4::

ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያደረጉትን ይህን ነበር:: የራሳቸውን ሕግና መመሪያ አውጥተው ራሳቸውን ከሕዝቡ ፍጹም ለይተው ነበር:: እነርሱ ባሉበት ዓለም ውስጥ ከሌለ ሰው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም ነበር:: እነርሱ ያወጡትን ሕግ የማይጠብቀውን ሰው << ያገሩ ሰው>> የሚል ስያሜ ሰጥተውት ነበር:: ስለዚያ ሰውም ያላቸው አመለካከት የሚያስገርም ነበር:: << ሰውየው ከአገሩ ሰው አንዱ ከሆነ ገንዘብህን በአደራ አታስቀምጥ:: ምንም አይነት ምስክርነት ከእርሱ አትቀበል:: ምስጢርህንም ለእርሱ አትንገር:: ወላጅ የሌላቸው ልጆች ባለአደራ አታድርገው:: ወገን የሚረዳበትን ገንዘብ በእርሱ ዘንድ አደራ አታስቀምጥ:: በመንገድ ከእርሱ ጋር አብረህ አትጓዝ::>> በአጭር ቃል ሰው አድርገህ አትቁጠረው እንደማለት ነው::

ይህ እንግዲህ ሕጉን አልጠበቁም ለተባሉት ለተራው ሕዝብ ነው:: በእነርሱ ላይ ይህን ያህል ልዩነት ካለ ቀራጮች ላይ ሊኖር የሚችለውን አመለካከት ከዚህ መገመት እንችላለን:: ቀራጮች ህዝባቸውን የከዱና አገሪቱን በቅኝ ገዢነት ከያዘው የሮማውያን መንግሥት ጋር የተባበሩ ባንዳዎች ናቸው:: በዚህ ብቻ አያበቃም ከሮማውያን ቀረጥ አስገባሪነታቸው ሌላ ባላቸው ሥልጣን ተጠቅመው ህዝቡን የሚበዘብዙ ነበሩ:: ኃጢአተኞችም እንዲሁ በሴተኛ አዳሪነት በሌብነት በሌላው ተሰማርተው የነበሩ ናቸው:: እነዚህ በሃይማኖተኞቹ ዘንድ ቦታ የሌላቸው ነበሩ:: በጌታ ዙሪያ ግን የሚሰበሰቡ ነበሩ::

ጌታ የፈሪሳውያንን ማጉረምረም እንደሰማ መልስ ይሆናቸው ዘንድ ሦስት ምሳሌ ሰጣቸው::
1. የጠፋው በግ ምሳሌ
2 የጠፋው ድሪም ምሳሌ
3. የጠፉት ልጆች ምሳሌ::

ባለፈው ሳምንት የጠፋው በግን ምሳሌ የእረኛውን መምጣት አስፈላጊነት እረኞች ተብለው ከተሾሙት አንጻር አይተናል::

እረኛው ዘጠና ዘጠኙን በጎች ትቶ አንዱን ለመፈለግ እንደሚሄድ ሁሉ የእረኞች አለቃ የሆነው ጌታ የጠፉት ለመፈለግ እንደመጣ ገልጦላቸዋል:: በዚህ ምሳሌ ላይ የእረኛውን ድርጊት በማየት ጌታ ለእኛ ያደረገው ነገር አብረን ልናሰላስል እንችላለን::

እረኛው የጠፋውን በግ ሊፈልግ መጥቶአል::
በአገራችንም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ የእረኞች አስቸጋሪ ስራ ከብቶቻቸውን የሚያሰማሩት እንደአሜሪካ ካው ቦይስ ሰፊ በሆነ ሜዳ ላይ በፈረስ ሆነው ሳይሆን በገደል በተከበበች ታናሽ ሜዳ ላይ ነው:: በመሆኑም ሁል ጊዜ ዓይኖቻቸው ከብቶቻቸው ላይ መሆን አለበት:: ከብቶቻቸው ሲጠፉ ደግሞ እነርሱን ለማግኘት ከባድ የሆነ የጉልበትና የህይወት ዋጋ ይከፍላሉ:: አንዳንዴ ገደል ገብቶ መሰበርና መሞትም አለ::

ጌታ ለእኛ ያደረገው ምንድነው?
ሀ. መልካሙ እረኛ የጠፋውን በግ የሰው ልጅ ሊፈልግ መጥቶአል::
ጌታ ሰውን ለመፈለግ መምጣቱ ለሰው ልጆች ያለውን ወሰን የሌለው ምህረትና ቸርነት የገለጠ ነው:: አስተውሉ እረኛው ዘጠና ዘጠኝ በጎች አሉት:: በሌላ ቋንቋ ጌታ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ፍጥረቶች አሉት:: አንድ ታዋቂ የሆነ ሳይንቲስት እንደተናገረው የከዋክብቱ ቁጥር በውቅያኖሶች ዳርቻ ያሉት አሸዋዎች ቁጥር ጋር እኩል ነው:: ማለትም እንኳን የእርሱ ህልውና ፍጥረቱን እንኳ ለማሰብ የሚያስቸግር ነው :: ታዲያ ይህ ጌታ ለክብሩ ይህን ታላቅ ዓለም (ዩንቨርስ) እንኳ አያስፈልገውም:: ግን የሰው ዘርን ለመፈለግ መጣ:: የጠፋውን ለመፈለግ መጣ::
በእረኝነት የኖሩ እንደሚነግሩን በጎች ለማገድ የሚያስቸግሩ ፍጥረታት ናቸው:: አንዴ ከጠፉ ደግሞ መንገዳቸውን በቀላሉ አያገኙም:: እንደፍየል አይደሉም:: ወይም በብዙ ርቀት ውሃ እንደሚያሸቱ ግመሎች አይደሉም:: ሰውም እንደዚሁ ሆኖ ነበር:: ማቴዎስ እንደነገረን ጌታ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ የሰው ልጅን ያገኘው በዚህ ሁኔታ ነበር:: <<ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።>> ማቴዎስ 9:36:: ጴጥሮስም ስለነበርንበት ሁኔታ ሲናገር << እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር>> ብሎናል:: 1 ጴጥሮስ 2:25:: ጌታ ይህን የጠፋውን የሰው ልጅ ሊፈልገው መጣ::

ይህ የጠፋውን በግ ለማግኘት እረኛው ዋጋ ከፍሎአል:: ጌታ << መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።>> በማለት በዮሐንስ 10:11 እንደተናገረው እኛን የጠፋነውን ለማግኘት ሕይወቱን ሰጥቶናል:: ይህም እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር በግልጥ ያሳየ ነበር:: << ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።>> ዮሐንስ 15:13:: ስለሆነም ፍለጋው በፍቅር የተሞላ ፍጹም ዋጋ የተከፈለበትና የጠፋው እስኪገኝ ድረስ የቀጠለ ነበር::

እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።

ጠፍቶ የነበረው በግ መገኘት ታላቅ ደስታን ፈጥሮአል::

ይህ ለፈሪሳውያን ታላቅ ህመም የሆነ ቃል ነው:: በተለይ በዚህ ዘመን አክራሪነት የመንፈሳዊነት ምልክት በሆነበት አለም ላይ ይህ ታላቅ መሰናክል ነው:: ለአክራሪዎች (ለሙስሊም አክራሪዎች ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያን አክራሪዎች) ኃጢአተኛ ሲታይ የመጀመሪያ የሚታያቸው ነገር ሰይፍና ድንጋይ ነው:: አክራሪ ሙስሊሞች ከቁርዓን እንደሚጠቅሱ ሁሉ አክራሪ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አያጡም ጌታ ጅራፍ ይዞ መቅደስ መግባቱን ድርጊታቸውን ማጽደቂያ ያደርጉታል:: የማይጠቅሱት ግን ጅራፉ ለሰው መግረፊያ ሳይሆን እንሳሳቱን ከመቅደስ ለማባረሪያ መሆኑን ነው:: የማይጠቅሱት ሰይፍ መዝዞ ጀግንነቱን ሊያሳይ የነበረውን ደቀመዛሙር ሰይፍህን ወደሰገባው መልስ ማለቱን ነው:: የማይጠቅሱት ከሁሉም በላይ የማይጠቅሱት ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ሊያድን መምጣቱን ነው:: ለነገሩ ጌታ ኃጢአተኞች የሚላቸውና ፈሪሳውያን ወይም የዛሬዎቹ አክራሪዎች ኃጢአተኞች የሚሉዋቸው የተለያዩ ናቸው:: ጌታ ኃጢአተኞች የሚላቸው ከእግዚአብሔር መንገድ የወጡትን ነው:: ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ያሉትን ነው:: የዛሬዎቹ አክራሪዎች ሌሎችን ኃጢአተኞች የሚሉዋቸው እነርሱ ያወጡን ሕግ ሰዎች ስላልተከተሉላቸው ነው:: ሳውዲ ያለው አክራሪ ሴቱዋ መኪና ስለነዳች በድንጋይ ትወገር ሲል የኛው አክራሪ ደግሞ ሴቱዋ ጸጉርዋን ስላልተከናነበች በድንጋይ ትወገር ይላል:: ልዩነቱ አንደኛው ከቁርዓን ሌላው ከወንጌል መጥቀሳቸው ነው እንጂ ልዩነት የላቸውም:: መንፈሳቸው አንድ ነው:: ደም በማፍሰስ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት::


ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።

በአክራሪዎች መንደር በአንድ ኃጢአተኛ ነው ብለው በሚያስቡት ሰው መሞት መወገር በጩቤ መወጋት ታላቅ ደስታ ነው:: በሰማያውያን መላእክት ግን በአንድ ኃጢአተኛ ንስሐ መግባት ታላቅ ደስታ ነው::

የጠፋው በግ መገኘት በጌታ ዘንድ በሰማያውን መላእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ በመሆኑ አክራሪዎቹ ፈሪሳውያን በዚያች ሴት ኃጢአት ሲጠቋቆሙ ጌታ አምልኮዋን ስግደትዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሰረየልሽ ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ አላት:: ሌሎች እርኩስ ያሉዋትን እርስዋን እርሱ እግሩን እንድትስመው ፈቀደላት:: ሌሎች ቆሻሻ ያሉዋትን እርሱ በጸጉርዋ እንድታብሰው ፈቀደላት:: ሽቱዋን ብቻ አልወሰደም:: ሰውነትዋን ሊከብርበት ወደደ:: ክብር ይግባውና::

እርሱ ልጁን መፈወስ ስለፈለገ ከመንገዱ ቆሞ የልብሱን ዘርፍ የዳሰሰችውን ሴት ፈለገ:: አስራ ሁለት ዓመት የተደበቀችን አስራ ሁለት አመት የተሰደበችን አስራ ሁለት አመት እርኩስ የተባለችን ሴት ነይ ከጓዳሽ ውጪ አላት:: የድብቅ አምልኮዋን ወደ አደባባይ አወጣው:: የድብቅ ህይወት ይብቃሽ አላት:: እርኩስ እርኩስ መባል ይብቃሽ አላት:: እየተንቀጠቀጠች በፊቱ ቆመች:: እርሱ ግን በሰላም አሰናበታት:: እየፈራች በፊቱ ቆመች:: እርሱ ግን በማረጋጋት ላካት::

ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል::

አክራሪዎች ኃጢአተኛ ሲያዩ ድንጋይ ነው የሚፈልጉት:: ለዚያውም እነርሱ ኃጢአተኛ ላሉት:: ጌታ ግን ኃጢአተኛ ሲያይ እምባ ነው የሚቀድመው:: አክራሪዎች እግዚአብሔር ከእነርሱ ጎን እንደሚሆንና ሐሳባቸውን እንደሚያጸድቅ ነው የሚያስቡት:: አንድ ቀን እንኳ ቆም ብለው የራሳቸውን መንፈሳዊ ሕይወት ለመመርመር ጊዜ የላቸውም:: ለዚህም ነው ያች በዝሙት የተያዘችውን ሴት ለመውገር ድንጋይ ይዘው የመጡት:: በነገራችን ላይ ወንዱን ይዘው አልመጡም:: ከእነርሱ አንዱ ነዋ:: ያችው መከረኛዋን ሴት ይዘው አመጡ ስለኃጢአተኝነትዋ እርግጠኞች ነበሩ:: የረሱት ነገር ግን ስለራሳቸው ነበር:: ጌታ ግን ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት ይውገራት አላቸው:: ኃጢአት የሌለበት ይውገራት::

ጌታ በወንጌል እንዳደረገው በዚህም ዘመን መንፈስ ቅዱስ በህይወታችን ሲሰራ የመጀመሪያው ተግባር እውነተኛ ማንነታችንን እንድናስተውለን ያደርጋል:: ከሰው ኃጢአት ይልቅ የእግዚአብሔርን ምህረትና ፍቅር እንድንፈልግ ያደርጋል:: ከዚያም ለሰዎች ጌታ ያደረገልንን ምህረትና ቸርነት መንገር እንጀምራለን::

እነዚህም ሰዎች ከተሳሳተ መንገዳቸው ሲመለሱ እግዚአብሔር ያደረገልን ትዝ ስለሚለን ከሰማያውያኑ ጋር አብረን በኃጢአተኞች ንስሐ መግባት ደስ ይለናል::


ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት?9 ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ። የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች።10 እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።

ስለዚህ አስር ድሪም ብዙዎች ብዙ ጽፈዋል::
በመጀመሪያ ልንገነዘበው የሚገባን በዚያ ወቅት ገንዘብ እጅግ ውድ ነው:: በእድሜ እጅግ የበለጠጉ አባቶች አንዳንዴ በጨዋታ መካከል ደመወዜ በአመት አምስት ብር ነበር ብለው ሲያወጉ መስማት ለዘመናችን ጆሮ ምን ያህል እንግዳ እንደሆነ እና በዚያን ወቅት ገንዘብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገባናል::

በሁለተኛ ደረጃ የዚያን ዘመን ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ስለሆነ አንድ ነገር ቢከሰት መጠባበቂያ የለም:: በመሆኑም በማያቋርጥ የረሃብ ስጋት ላይ ናቸው:: በዚህ ምንባብ የምናገኘው አሥር ድሪም ደግሞ የአስር ቀን ደመወዝን ስለሚያሳይ የችግር ቀንን ሊያስገፋ የሚችል ነው:: እነዚህ ሁለቱ ምክንያቶች ብቻ ይህች ሴት ለምን ይህን አስር ድሪም አጥብቃ እንድትፈልግ እንዳደረጋት ያሳየናል::

ከዚህም በተጨማሪ የዘመኑን ይትበሃል ያጠኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ያገቡ ሴቶች ተቀጣጥሎ የተሰራ ድሪም የራስ ጌጥ አድርገው ያስሩ ነበር:: ይህ ጌጥ በሰርጓ ዕለት አባቷ ለሙሽሪት የሚሰጣት ነው:: ተራ ጌጥ አይደለም:: በጋብቻ ውስጥ ያለች ሴት መሆኑዋን ይገልጣል:: አንዳንድ ጊዜ በዝሙት የተያዙ ሴቶች የራስ ጌጡ ስለሚወሰድባቸው የራስ ጌጡ መጥፋት ለዚህች ሴት አስቸጋሪ ነበር::


ይህን ምሳሌ ጌታ ለፈሪሳውያን ሲነግራቸው እያላቸው ያለው እናንተ የምታንቋሽሹዋቸው ቀራጮችና ኃጢአተኞች ለኔ የክብሬ መገለጫዎች ናቸው:: ልክ ያች ሴት በጥንቃቄ መብራትዋን አብርታ ቤትዋን ጠርጋ ድሪሞቹዋን እስክታገኝ ድረስ አጥብቃ እንደምትፈልግ እነዚህንም አጥብቄ ለመፈለግ መጥቼአለሁ እያለ ነው::

ይህ ምሳሌ ከእግዚአብሔር የተለየ ሰው የሚኖርበትን ኑሮ የሚገልጥ ነው::
ድሪሙን ለመፈለግ ሴትየዋ መብራት ማብራት ነበረባት:: ይህ ማለት ድሪሙ የጠፋው በጨለማ ውስጥ ነው::የቱንም ያህል የዚህን ዓለም ዕውቀት ቢያሰባስብም ከእግዚአብሔር የተለየ ሰው በጨለማ ውስጥ ነው:: ለዚህም ነው የጠፋውን ሊፈልግ የመጣው አዳኝ << እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም >> ያለው:: ዮሐንስ 8:22 ኢሳይያስ መሲሁ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ስለርሱ መምጣት ሲተነብይ ያለው ይህን ነበር:: << ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። 2 በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።>> ኢሳይያስ 9:1-2:: ማቴዎስም ይህንኑ ጠቅሶ በጨለማ ላሉት ጌታ ብርሃን እንደሆነ መስክሮአል:: ማቴዎስ 4:14::

ድሪሙን ለማግኘት ሴትየዋ ቤትዋን መጥረግ ነበረባት:: ቆሻሻውን ለማስወገድ:: በሰው ልጆች ላይ የተከመረውን የኃጢአት ቆሻሻ ለማስወገድ የበግ የላምና የጊደር ደም አልበቃም ነበር:: የአዳኙ ደም ያስፈልግ ነበር:: ወደቀደመ ክብራችን ወደቀደመ ውበታችን እንድንመለስ የእግዚአብሔርን ክብርና የእግዚአብሔርን ሐሳብ ከሸፈነን ግርዶሽ መውጣት ነበረብን:: << እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም 2 ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።>> ብሎ ነቢዩ ኢሳይያስ በም.59:1-2 እንደተናገረው ከዚህ ግርዶሽ ለመውጣት የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ፈስሶልናል::

የጠፋው አስር ድሪም ምንም እንኳ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ቢሆንም እስከጠፋ ድረስ አቧራ ከመሰብሰብ ውጭ ለምንም አይጠቅምም:: በተገኘ ጊዜ ግን ጥቅሙ ይገለጣል:: የሰውም በኃጢአት መውደቅ ያመጣው ነገር ቢኖር ይህን ነው:: በክብር የተፈጠረውና ለዘለዓለም ከአምላኩ ጋር እንዲኖር የተመረጠው የሰው ልጅ በጨለማ ተዋጠ ለኃጢአት ባሪያ ሆነ:: በመሆኑም ስለሰው ልጆች እግዚአብሔር በቃሉ ሲናገር << ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። >> አለ:: ሮሜ 3:11-12::

ድሪሙ አቧራ ከመሰብሰብና በጨለማ ውስጥ ከመዛግ ከመበስበስ ያመለጠው ሲገኝ እንደሆነ ሁሉ እኛም በአምላካችን በመገኘታችን የተፈጠርንበትን መልካሙን ሥራ የምናደርግ ሆነናል:: ኤፌሶን 2:10::

No comments:

Post a Comment