Saturday, October 29, 2011

የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እመስላታለሁ? ሉቃ 13:18-21

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአገልግሎቱ መነሻ ያደረገው መንግሥተ ሰማያት መቅረብዋንና በንስሐ ወደዚህች የእግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዳለብን በማወጅ ነው:: ይህች የእግዚአብሔር መንግሥት ያላትን ባህርይ ለማስረዳት ጌታ ኢየሱስ ሁለት ምሳሌዎችን ያቀርብልናል:: አንደኛዋ የሰናፍጭ ቅንጣት ናት:: ያች ታናሽ ዘር አድጋና ቅርንጫፎቹዋን ዘርግታ ለብዙዎች አዕዋፋት ማረፊያ እንደምትሆን እንዲሁ የእግዚአብሔር መንግሥትም የብዙዎች ሕይወት እረፍት ማግኝያ እንደምትሆን ነው:: ይህም ሊታወቅ በጌታ በትምህርቱ በፈውሱና በተአምራቱ ብዙዎች በሥቃይ የነበሩ አርፈዋል:: የነፍስ እረፍትን በትምህርቱ የሥጋ እረፍትንም በተአምራቱና በፈውሱ አግኝተዋል:: ሁለተኛው ምሳሌ የእርሾው ምሳሌ በዱቄት ውስጥ የተሽሽገ እርሾ ሊጡን በሙሉ እንደሚለውጥ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባትም የምድራዊ ድርጅት ጉዳይ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የባህርይ ለውጥ የሚያመጣ ነው:: ምን ዓይነት ባህርይ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ቢኖር በዚሁ በሉቃስ የሜዳው ስብከት የተባለውንና በማቴዎስ የተራራው ስብከት ተብሎ የሚታወቀውን ማየት ነው:: ጌታ በተራራው ስብከት ሊያሳይ የፈለገው የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች የሆኑ ሰዎች የሚኖራቸው የህይወት ለውጥን ነው:: በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሆነን አፍአዊ ክርስቲያን መሆን አንችልም:: በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሆነን በዓለማዊ አስተሳሰብ ውስጥ አንዳክርም:: እርሾው ማለትም ያ ሰማያዊ አሳብ ሙሉ በሙሉ ይለውጠናል::

No comments:

Post a Comment