Monday, November 26, 2012

እውነት እና የእውነት ኃይል


እውነት ሲያሸማቅቅ ለማየት ከፈለጋችሁ  የፎክስ ኒውስ ቻናል ጋዜጠኛ እውነትን ሲሸሻት መመልከት ትችላላችሁ።

እውነት አርነት ያወጣችኋል የሚለው ከአንዳንድ የዜና ሰዎች የጠፋ ይመስላል፤ ቃለ መጠይቅ ተደራጊውን ጋዜጠኛ ግን ልናደንቃቸው ይገባቸዋል። የጋዜጠኝነት ከፍተኛ ሽልማት የሆነውን የPulther ሽልማት ያገኙት አለምክንያት አይደለም። 

Tuesday, June 19, 2012

የሕጉ ተግባር ምንድነው? ካለፈው የቀጠለ



19 እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ።20 መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።21 እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤22 ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል። 23 እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር።24 እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤25 እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም።26 በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤27 ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።28 አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።29 እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።
የሕጉ ዓላማ ምንድነው? 
ስለ ሕጉ ጳውሎስ የሚመልሰውን ከማየታችን በፊት ሕጉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሚና ምንድነው? ለዚህ ሦስት ዓይነት አስተያየቶች በዘመናችንም ሆነ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰጥተዋል::
1. የክርስቶስ መምጣት ሕጉን ሙሉ በሙሉ ሽሮት የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ታውጆአል የሚል ነው:: 
ይህ ብዙ ጊዜ ከነ መርቅያን (ማርስዮንና) ከሌሎች አንቲኖሚያንስ ጋር ቢያያዝም የተወሰነ ክርስቲያናዊ እውነት አለው:: 
2. ሕጉ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር የተገለጠው ፈቃድ ቢሆንም የተሙዋላ (ፍጹሙ) ፈቃዱ ግን አይደለም:: የእግዚአብሔር ፈቃድ ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ ተገልጦ ለእኛ ደግሞ በአዲስ ኪዳን ትምህርት በመንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶአል:: 
3. የሙሴ ህግ ለቤተ ክርስቲያንም የተሰጣት የተገለጠው የእግዚአብሔር ሕግ ነው:: ሆኖም የሕጉን ፈቃድ መፈጸም የሚቻለው በክርስቶስ በማመን በምንቀበለው በክርስቶስ መንፈስ ነው የሚል ነው:: 
ሕግ ምንድነው? 
1. በኅብረተሰብ መካከል ሥነ ምግባርን የሚያስጠብቅ መመሪያ ነው:: 
2. በታሪክና በሰው ሕይወት ኃጢአትን በመግለጥ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ጸጋ የሚመራ የእግዚአብሔር መሣሪያ ነው:: 
3. በቤተ ክርስቲያን የክርስቲያን ሥነ ምግባር መመሪያ ነው:: 
ይህ ሦስተኛው የሕግ አጠቃቀማችን (ሰርሺየስ ዩዘስ ሌጊስ ) ነው ብዙ ጊዜ ክርክር ውስጥ የሚያስገባን:: 
1. የሕጉ ዓላማ ምንድነው? 
1.1. በበደል ምክንያት የተጨመረ ነው:: 
ይህም ኃጢአት በመግባቱ መጨመሩን ወይም ኃጢአት ስለገባ ኃጢአትን ለመግለጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመግለጽ የተጨመረ ነው:: 
1.2. የተስፋው ዘር እስኪመጣ የተሰጠ ነው:: 
1.3. በፍጡራን መካከለኛነት (በሙሴና በመላእክት) የተሰጠ ነው:: 
2. ሕጉ ለአብርሃም የተሰጠውን ተስፋ ይቃወማልን? አለበለዚያ ለምን ተሰጠ? 
3. ሕጉ ሕይወትን የሚሰጥ ሕግ አልሆነም:: 
4. በክርስቶስ ያመንን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል:: ምክንያቱም በክርስቶስ ያመንን እኛ ክርስቶስን ስለለበስን ነው:: 
5.በክርስቶስ ያመኑ ጾታ ዘር ወገን ሳይለያቸው ሁሉም አንድ ናቸው እውነተኞቹ የአብርሃም ዘር ወራሾች ናቸው:: 

ልጆች ነን   4:1- 31 
እዚህ ላይ ስለልጅነታችን ይህ መልእክትና እንዲሁም ሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስተምሩንን መመልከት ይገባል:: 
1.ልጅነታችን የተመሠረተው እግዚአብሔር ለእኛ ባለው የዘላለም ፍቅር ነው:: ኤፌሶን 1:4-6:: 
1.1 እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር በዘላለም ፍቅር ወደደን 
1.2 እግዚአብሔር ወልድ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ እርሱ ሰው ሆነ ሮሜ 8:29
1.3 እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በማደር አባ አባት የምንልበት የልጅነት መንፈስ ሆነን:: ሮሜ 8:1-11:: 
2. ይህን ልጅነታችንን የምናገኘው በክርስቶስ በማመን ነው::ዮሐ 1:12::  ኤፌሶን 2:1-10:: 
3. ይህ ልጅነት ዘር ወገን ጾታ የማይለይ ለሁሉም የተሰጠ ነው:: 
ይህ ልጅነት በመንፈስ ቅዱስ የታተመ ስለሆነ ዋስትና ያለው ልጅነት ነው:: ሮሜ 8:16:: 
ሀ.  በክርስቶስ የተገኘው ልጅነትና የልጁ መንፈስ 4:1-7

1 ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥2 ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው።3 እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤4 ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤5 እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ።6 ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።7 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።
1. የሕጻንነት ዘመን በሕግ ሞግዚትነት የነበርንበት ዘመን ነው:: 
2. ከሕግ በታች ያለነውን ይዋጀን ዘንድ እግዚአብሔር ልጁን ላከልን:: 
3. ልጅነታችንን ያስረግጥ ዘንድ የልጁን መንፈስ በልባችን ላከው:: 
4. ልጆች እንጂ ባሮች አይደለንም:: ልጆች በመሆናችን በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ነን:: 
ለ. እውነተኛ አምላክና ሐሰተኛ አማልክት 4:8-11
ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤9 አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?10 ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ።11 ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ።
1. ዓላማውን የፈጸመውን ሕግ እንደገና የአምልኮ መንገድ ማድረግ ወደባርነት መግባት ነው:: 
2. የገላትያ ክርስቲያኖች በወንጌል የተሰጣቸውን ነጻነት ወይም ባርነትን ይመርጡ እንደሆነ ምርጫቸውን ማስተካከል አለባቸው:: 
  1. እስራኤላውያን ከነጻነት ይልቅ ባርነትን መምረጣቸው ምን እንዳስከተለባቸው ያሳስባቸዋል:: ዘጸአት 14:11-12:: 16:3:: 17:3:: ዘኁልቍ 14:1-4:: 
  2. ጳውሎስን ያሳዘነው የገላትያ ክርስቲያኖች የአይሁድን በዓላት ማክበራቸው ሳይሆን የሚያከብሩበት መንገድ ነው:: ሐዋ 20:6;1 ቆሮ 16:8:: 
ሐ. የጳውሎስ ልመና 4:12-20

12 ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና። እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም።13 በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥14 በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ።15 እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ።16 እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?17 በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ።18 ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው።19 ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል።20 ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ።
1. ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ለእርሱ የነበራቸውን የቀደመ ፍቅራቸውን እንዲያስቡ ያሳስባቸዋል:: 
2. አሁን እያሳሳቱአቸው ያሉ ሰዎች ዓላማ እነርሱን ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጭ ለማስቀረት ነው:: 
3. የጳውሎስ ጭንቀት ደግሞ ክርስቶስ በእነርሱ ሕይወት ክርስቶስ እስኪሳል ነው:: 
መ. ይስሐቅና እስማኤል የአብርሃም ሁለት ልጆች 4:21-31

21 እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ።22 አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና።23 ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል።24 ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት።25 ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና።26 ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት።27 አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል።28 እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። 29 ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው።30 ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት።31 ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።
ሕግ                              ወንጌል 
የአጋር ቃል ኪዳን        የሳራ ቃል ኪዳን 
እስማኤል  (ሥጋ)        ይስሐቅ (ተስፋ) 
አሳዳጅ                     ተሳዳጅ
የባርነት ልጆች            የነጻነት ልጆች 
ሲና ተራራ                 ጽዮን ተራራ (ጎልጎታ? መንግሥተ ሰማይ 
ምድራዊቱ ኢየሩሳሌም  ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም 
አሮጌው ኪዳን             አዲሱ ኪዳን
1.  ሁለቱ ሴቶች አንደኛዋ ባሪያ ሌላዋ ጨዋ ተደርገው ተገልጠዋል:: 
2. የሁለቱ ልጆች አንደኛው በተስፋ የተወለደ ሁለተኛው ደግሞ ባለማመን በሥጋ የተወለደ ተደርጎ ተወስዶአል:: 
3. ጳውሎስ በአጋር ታሪክ ደብረ ሲናንና ኢየሩሳሌምን በማያያዝ በሕጉ ሥር ለሚኖሩ የባርነት ምሳሌ አደረጋቸው:: 
4. ሳራን ደግሞ ከሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ጋር በማገናኘት ከእርሱዋ የሚወለዱ የመካኒቱ ልጆች (ኢሳ 51:2 እና 54:1 ተመልከቱ) ከሕጉ ነጻ የሆኑ የነጻነት ልጆች አደረጋቸው:: 
5. የአጋር ልጅ የሳራን ልጅ እንዳሳደደው ወደ ይሁዲነት ለመውሰድ የሚፈልጉ በክርስቶስ ያሉትን እያሳደዱ ናቸው:: 
ስንሰደድ ምን እናድርግ? 
1. ክርስቶስ ምሳሌያችን እንደሆነ እናስብ::
2. ከእኛ በፊት ብዙ ቅዱሳን እንደተሰደዱ እናስብ:: 
3. እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣ እናስብ:: 

Tuesday, June 5, 2012

የተቀበልነው ስጦታ 3:1-29



1. የእምነት በቂነት 3:1-5 
የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? 2 ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? 3 እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን? 4 በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? 5 እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?
1. የገላትያ ሰዎች የማያስተውሉ እንዲሆኑ በሌሎች ተጽዕኖ ሥር ወድቀዋል:: 
2. ባለማስተዋላቸው ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር መቃረን ጀምረዋል::  
3. ባለ ማስተዋላቸው በእነርሱ ውስጥ ያለውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መቃረን ጀምረዋል:: 
3.1 የክርስትናቸውን ጅማሬ ያገኙት በእምነት ከሆነ መስማት በሆነ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው:: ሮሜ 8:9:: 
3.2 መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው ሆኖ የሚሰራው ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው:: 
       ልጅነትን በማስረገጥ- ሮሜ8:15-16:: 
       ተአምራትን በማደረግ  
       ፍቅርንና የመንፈስ ፍሬዎችን በመስጠት 
4. ከእምነት በሚገኝ በመንፈስ ቅዱስ ከጀመራችሁ በሕግ ሥራ በሚገኝ በሥጋ አትፈጽሙ:: ሮሜ 8:13:: 
2. የአብርሃም ምሳሌነት 3:6-9
እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። 7 እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። 8 መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። 9 እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።
1. አብርሃም ጽድቅን ያገኘው በእምነት ነው:: ዘፍ 15:6:: 
2. የአብርሃም የሆኑት ሁሉ የአብርሃምን ጽድቅ የሚያገኙት በአብርሃም እምነት በኩል ነው:: ዘፍ12:2
3. አብርሃምንና በእምነት ልጆቹ የሆኑትን አሕዛብን የሚያገናኛቸው ሁለቱም ያመኑበት ወንጌል ነው:: 
3.1 የአብርሃም ልጆች መሆን ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተሰጠ ነው:: 
3.2 የአብርሃም ልጆች መሆን አብርሃምን መምሰል ከእኛ የሚጠብቅ ነው:: ዮሐ 8:39::
3.3 የአብርሃም ልጆች መሆን ማለት የአብርሃምን በረከት ወራሾች መሆን ማለት ነው:: ገላ 3:29:: 
4. በእምነት የሚገኘው ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ልጅነታችንን ለማግኘት መሰረት ነው:: 
4.1 ጽድቃችን የአብርሃም ልጆች በመሆናችን የምናገኘው ውርስ ነው:: ይህም የኃጢአትን ፍርሃት በማስወገድ እውነተኛ የሆነ ሕብረት ከእግዚአብሔር ጋር እንዲኖረን ያደርጋል:: 
4.2 ለቤዛ ቀን የሚያትመን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የአብርሃም ልጆች በመሆናችን የምናገኘው ውርስ ነው:: ይህም የሞትን ፍርሃት የዘላለምን ሕይወት ተስፋ በማድረግ ይተካዋል:: 
3. ከሕግ እርግማን ነጻ መውጣት 3:10-14
ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። 11 ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። 12 ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን። የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል። 13 በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ 14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
1. ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸው:: 
2. ክርስቶስ ከሕግ እርግማን ዋጅቶናል:: 2 ቆሮ 5:21:: ኢሳ 53:4-6
3. ክርስቶስ ከሕግ እርግማን የዋጀን የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል ነው::  
4. ዘርና መካከለኛ የሆነው ክርስቶስ 3:15-22
ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።16 ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር። ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን። ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። 17 ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። 18 ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል።19 እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። 20 መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 21 እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤ 22 ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል። 
1. ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው ተስፋ ዘላለማዊ ተስፋ ነው:: 
2. የአብርሃም ዘር የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: 
3. ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠውን ተስፋ ከ430 ዓመት በኋላ የመጣው የሙሴ ሕግ አልሻረውም::
3.1 ሕጉ የተሰጠው ኃጢአትን ለመግለጥ ነው::ሮሜ 4:15::
3.2 ሕጉ የተሰጠው የኃጢአትን አስከፊነት በማሳየት ሰዎችን ወደ ጸጋ ለማድረስ ነው:: ሮሜ 5:20:: 

Tuesday, May 29, 2012

ክፍል ሁለት ሕይወትን የሚለውጥ መልእክት 1:11-2:21



ይህን ከመጀመራችን በፊት ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን ነገር ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቴ ያለው ቦታ ምን ያህል ነው:: የክርስቶስ ወንጌል ሕይወቴን ምን ያህል ለውጦታል? ይህን የእግዚአብሔርን ቃል መማሬ በተግባሬ በኑሮዬ አካሄድ እና እርምጃ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ አምጥቶአል? ክርስትና የለውጥ ሃይማኖት ነው:: በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ በሚገርም ሁኔታ የእርሱን ሕይወት በጥንቃቄ እንድንመለከት ይነግረናል:: ገላትያ 4:12:: 1ቆሮ 4:16:: 11:1:: ፊል 3:17:: 4:8-9:: 

ሀ. ጳውሎስ የጸጋውን ወንጌል በቀጥታ ከጌታ ስለመቀበሉ:: 1:10-12
ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤12 ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።
1. ጳውሎስ ወንጌሉን የሰበከው በሰዋዊ መንገድ አይደለም። 
2. ጳውሎስ ወንጌሉን  ከሰው አልተማረውም ወይም አልተቀበለውም።
<< እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም>>


ለ. የጳውሎስ የቀደመው የይሁዲነት ሕይወት ለጸጋው ወንጌል መነሻ አለመሆኑ 1:13-14
በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥14 ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።

ሐ. ጳውሎስ ወንጌሉን የተቀበለው ከሰው አይደለም:: 1:15-24:: 
በቍጥር 11-12 ላይ የጀመረውን ወንጌሉን በትምህርትና በሰው ትውፊት እንዳልተቀበለው ይልቁኑም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገለጠለትና ይህንንም ወንጌል ለማስተማር ሲነሳ ከማንም ሰው ጋር እንዳልተመካከረ በመግለጥ የእርሱ ወደ ክርስትና መግባት በይሁዳ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት (ማኅበሮች) መካከል እንዴት አድናቆትን እንደፈጠረ ይነግረናል:: 

1. እግዚአብሔር የክርስቶስን የጸጋ ወንጌል ለጳውሎስ የገለጠበት ሁኔታ
 ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥

2. ጳውሎስ ከሐዋርያት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘበት ሁኔታ 
ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። 18 ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤19 ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። 20 ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።21 ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። 22 በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ 23 ነገር ግን ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ 24 ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።

መ. ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተቀባይነት ስለማግኘቱ 2:1-10
በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረውን ወንጌልና የሐዋርያነቱን ተልዕኮ ከተቀበለ በኋላ ለሚቀጥሉት 14 ዓመታት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደነበረ ይገልጥልናል:: በዚህ ክፍል ቅዱስ ጳውሎስ  ከአሥራ አራት አመት በኋላ እንደገና ከሐዋርያት ጋር ሲገናኝ የነበረውን ሁኔታ እናያለን:: በአስራ አራተኛ ዓመት በኋላ የሚለው የትኛውን ነው? ወደክርስትና ከገባ በኋላ ነው ወይስ ከመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ጉብኝት በኋላ ነው ለሚለው በሊቃውንቱ መካከል የተለያየ አስተያየት አለ:: አብዛኛው ሊቃውንት የሚስማሙበት ይህ አስራ አራት ዓመት ጳውሎስ ወደ ክርስትና ከገባ በኋላ ጀምሮ ያለውን ነው::  
የጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ 
መነሻ                ቀን             ማስረጃ                     ትይዩ                     ምክንያት  
ደማስቆ             35                  9:22-30             ገላ1:18-24          ጴጥሮስን ለማነጋገር 
የሶርያ አንጾኪያ   46            11:30;12:25          ገላ 2:1-3,6-10    ለድሆች እርዳታ
                                                                                                     የአሕዛብ ጉዳይ 
የሶርያ አንጾኪያ   49            14:26-15:29                                    የአሕዛብ ወደ ክርስትና       
                                                                                                      መግባት
ቆሮንቶስ            52             18:1,18,22                                         የፋሲካ በአል
                                                                                                      የድሆች እርዳታ 
ግሪክ                57             20:2-3;21:17                                       ለድሆች እርዳታ 
                                       ሮሜ15:25-31

1.ጳውሎስ ከበርናባስና ከቲቶ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ:: 
1ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤2 እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ 
በርናባስ በአገልግሎቱ << የመጽናናት ልጅ>> ተብሎ በሐዋርያት የተጠራ (ሐዋ ሥራ 4:36) የማርቆስ አጎት (ቆላ 4:10) ነው:: ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዙ እና ሰዎችን በማበረታታትና በማጽናት ለአገልግሎት ማብቃቱ እና በመንፈስ ቅዱስ መመራቱ  በሁሉም ዘንድ የታወቀለት ሐዋርያ ነው:: ሐዋ 4:36-37:: 9:26-30:: 11:22-26:: በሐዋርያነት ከጳውሎስ ጋር በአንድነት ያገለገለ ነው:: 14:14::15:12,25::  በዚሁ በገላትያ መልእክት በምናገኘው በጴጥሮስ ድርጊትና እና በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት በማርቆስ ምክንያት ጳውሎስ እና በርናባስ ተጋጭተዋል:: (ገላ 2:11-21:: ሐዋ ሥራ 15:39-40::) ሆኖም ይህ ግጭት በስተመጨረሻ በእርቅ ተቋጭቶአል:: 1ቆሮ 9:6:: ሁለተኛ ከበርናባስ ጋር ይዞ የወጣው ቲቶን ነው:: ቲቶ ጳውሎስ ወደ ክርስትና ካመጣቸው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አንዱ እና በመንፈሳዊ ሕይወቱና በክርስትና እውቀቱ ለታላቅ የመሪነት አገልግሎት የበቃ ነው::  ቲቶ 1:4:: 
2. ጳውሎስ የሚሰብከውን ወንጌል ገለጠላቸው:: 
ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው።

3. የኢየሩሳሌም መሪዎች ቲቶ ይገረዝ ዘንድ አላስገደዱትም:: 
3ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤ 

4. ሐሰተኞች ወንድሞች ወደ ኦሪት ባርነት ሊያስገቡዋቸው ሞከሩ:: 
ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።5 የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።

5. ሐዋርያት ጳውሎስ ለሚሰብከው ወንጌል አንድነታቸውን ገለጡ:: 
6አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥7ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤8 ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። 9ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤10 ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።

ሠ. ጳውሎስ ኬፋን (ጴጥሮስን) ስለመገሰጹ 2:11-14
ይህ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መገኘቱ ቅዱሱ መጽሐፋችን ምን ያህል የእውነት መጽሐፍ እንደሆነ የሚያሳየን ነው:: የሙሴ አለመታዘዝ የዳዊት በኃጢአት መውደቅ የጴጥሮስ ክህደት እንደተመዘገበበት ሁሉ በዚህም ቦታ በሁለት ወይም በርናባስን ከጨመርን በሦስት ታላላቅ መምህራን መካከል የተፈጠረውን ግጭት እና ይህም ለምን እንደሆነ እናያለን:: 

11 ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።12 አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። 13 የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። 14 ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት። 

ረ.  በሥራ ሳይሆን በእምነት ስለሚሆን ጽድቅ 2:15-21
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ራሱ ሕይወት በመመለስ በአይሁዳዊነቱ የጽድቁ መሠረት የሆነው አይሁድነቱ ሳይሆን በክርስቶስ ማመኑ እንደሆነና ይህም ለምን እንደሆነ ያብራራልና:: 
1. የጽድቃችን መሠረት በክርስቶስ ማመናችን ነው:: 
15 እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ 16 ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። 
2. በክርስቶስ በማመን መጽደቅ ማለት ምን ማለት ነው? 
17 ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። 18 ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና።19 እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። 20 ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። 21 የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።
1. በክርስቶስ በማመን ጸድቀናል በክርስቶስ መንፈስ እንመራለን ማለት ነው:: 

2. በክርስቶስ በማመን ጽደቀናል ማለት ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለናል ማለት ነው:: 

3. በክርስቶስ በማመን ጽድቀናል ማለት ክርስቶስ በእኛ ይኖራል ማለት ነው:: 

Tuesday, May 22, 2012


ወንጌልና ተጽዕኖ  1:1-10

1-2 በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤3 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።4 ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።5 ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። 6 በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤7 እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ።8 ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።10 ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
ሀ. የመልእክቱ ምክንያት 

ለ. የጳውሎስ የሥልጣኑ ምንጭ 
<< በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ>>

ሐ.የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የተቀበሉት ጸጋ 

  1. ወንጌል ጌታ ኢየሱስ ከርስቶስ ነው::    << በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ...>>
  2.  ወንጌሉ ጸጋና ሰላም  ነው::   << 3 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።>> 
  3. ወንጌል ከክፉው ዓለም ሊያድነን ራሱን አሳልፎ ስለሰጠው ስለ ክርስቶስ ነው። << ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። >> 
  4.  ወንጌሉ ወደ ክርስቶስ ጸጋ የሚጠራን ነው። <<  በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ....

መ. የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት የገቡበት ወጥመድ አስፈሪነት 
  1. በክርስቶስ ጸጋ ከጠራቸው ወንጌል ወደ ልዩ ወንጌል ፈጥነው አልፈዋል። << 6 በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤>> 
  2. ይህ ልዩ ወንጌል ወንጌል ያይደለ የተጣመመና ከክርስቶስ ጸጋ የሚያናውጥ ነው።  <<7 እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ።>>
  3. ይህ ልዩ ወንጌል ወደ እርግማን የሚወስድ ነው። << ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። >>
ሠ. የጳውሎስ ቁርጠኝነት 
ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
      



የቅዱስ ጳውሎስ አጭር ታሪክ 

ስለ ጳውሎስ ማንነት በጥልቀት የምናገኘው ሉቃስ ከጻፈልን ከሐዋርያት ሥራ እና ከራሱ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ነው።
1. በጠርሴስ ተወለደ 
ቅዱስ ጳውሎስ በአሁኑ ዘመን በደቡብ ምሥራቅ ቱርክ በምትገኘውና በዚያን ዘመን የትምህርት ማዕከላት ከሆኑት ከአቴንስ እና ከእስክንድርያ ጋር በእኩልነት ከምትጠራው ታዋቂ ከተማ በጠርሴስ ተወለደ። ወላጆቹ ከብንያም ነገድ ወገን የፈሪሳውያን ወገን ሲሆኑ ልጃቸውንም ከብንያም ወገን ታዋቂ በሆነው በንጉሥ ሳኦል ሰይመውታል። ምንም እንኳ የጳውሎስ ወላጆች አጥባቂ ፈሪሳውያን ቢሆኑም በዜግነት ሮማውያን እንደሆኑ በሐዋ ሥራ 21: 39 ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ጠቅሶአል። ሐዋ ሥራ 16:37፤ 22:25፤ 25:11። 
2. በገማልያል እግር ሥር ተማረ:: 
የተወለደባት የጠርሴስ ከተማ በግሪክ ፍልስፍና በተለይም በስቶይክ ፍልስፍና ትምህርት ማዕከልነትዋ የታወቀች ቢሆንም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ እንደነገረን የተማረው በገማልያል እግር ሥር ነው። ሐዋ ሥራ 22:3። ገማልያል ታዋቂ የሆነው የሂለል የረበናት ትምህርት ቤት መሪ የነበረ ሲሆን በጥበቡና በአስተዋይነቱ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በረበናት ትምህርቱ ከብዙዎች ጓደኞቹ የበለጠ ዕውቀት እንደነበረው በዚሁ በምናጠናው መልእክቱ ውስጥ ገልጦልናል። ገላ 1:14። 
3. ክርስቲያኖችን አሳዳጅ ነበረ ::
ምንም እንኳ በገማልያል እግር ሥር ሆኖ ቢማርም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሕጉና ስለሃይማኖቱ እጅግ ቀናኢና ከገማልያል ይልቅ የክርስትና መልእክትን ተጽዕኖ የተረዳ ይመስላል። ሐዋ ሥራ 5:34-39። በመሆኑም ገና የተመሠረተችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ ያሳድዳት ነበር። ገላ 1:13። በሐዋ ሥራ ላይ የምናየው ደብዳቤም ይህ ክርስቲያኖችን ማሳደዱ በኢየሩሳሌም ባሉት የአይሁድ መሪዎች ይሁኝታን ያገኘ ነበር። ሐዋ ሥራ 8:3። 
4. ለሐዋርያነት መጠራቱ:: 
ከሊቀ ካህናቱ ተልእኮ ተቀብሎ በኢየሱስ የሚያምኑትን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ በጉዞ ላይ ሳለ ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ለጳውሎስ እንደተገለጠለት በሐዋ ሥራ 9 ላይ እናገኛለን። ጌታ ኢየሱስ በደማስቆ ላይ የጳውሎስን ሕይወት መቀየር ብቻ ሳይሆን ለታላቅ የወንጌል አገልግሎትም ነበር የጠራው። እስከዚያች ሰዓት ድረስ እንደመልካም የኦሪት ተማሪ ጳውሎስ የሚያምነው በእንጨት የሚሰቀል ሰው የተረገመ እንደሆነና በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሞተ ሰው መሲህ (ክርስቶስ) መሆን እንደማይችል ነበር። ነገር ግን የተሰቀለውን ኢየሱስ ፊት ለፊት ተገናኘው። የኢየሱስ ተከታዮች የሚሉትም እውነት እንደሆነ ተመለከተ። ጳውሎስን ከሁሉ በላይ ያስደነገጠው ነገር ቢኖር እየተከተለው ያለው መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ያ ሕይወቱን የሰጠለት የኦሪቱ ሕግ አለማሳየቱ ነበር። ከዚያ ይልቅ ወሰን የሌለው የክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ በምህርቱ እንደጠራው አስተዋለ። በመሆኑም ለእርሱ ከዚያች ቀን ጀምሮ << ሕይወት ክርስቶስ >> እንደሆነ አወጀ። ፊል1:21። ሕይወቱን ሁሉ ለክርስቶስ ለመስጠት ወሰነ።
5. የአሕዛብ ሐዋርያ መሆን 
ቅዱስ ጳውሎስ ለሐዋርያነት ከጌታ ኢየሱስ የቀረበለትን ጥሪ ምላሽ የሰጠው ወዲያው ነበር። መጀመሪያ ወደ አረቢያ (ገላ 1:17) በመቀጠልም ወደ ደማስቆ  ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ በመሄድ በዚያም ጴጥሮስን እና የጌታ ወንድም ያዕቆብን አግኝቶአል። (1ቆሮ 15:5) ወደ ተወለደበት ወደ ተርሴስ በመሄድም ሊያጠፋው የሞከረውን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ሰብኮአል። (ገላ 1:21-24)  ቀድሞ ወደ ሐዋርያት ያመጣው በርናባስ እንደገና ወደ አንጾኪያ ሄደው በዚያ እንዲያገለግሉ ጋበዘው።ሐዋ 11:19-26። የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የገቡ ሰዎች በብዛት ያሉባት ነበረች። 
6. የኢየሩሳሌም ጉባኤ 
የአንጾክያ ምዕመናን በሃይማኖት የበረቱና ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተብለው የተጠሩ ነበሩ። አገልግሎታቸውም በአሕዛብ መካከል ወንጌልን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን መርዳት ነበር። ይህን እርዳታ ለማድረስ ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም በወጡበት ወቅት በኢየሩሳሌም ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ይመሩ የነበሩት ጴጥሮስ ዮሐንስና የጌታ ወንድም ያዕቆብ በአንጾኪያ ያለውን አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ለበርናባስና ለጳውሎስ ድጋፋቸውን ገለጡ። (ቀኝ እጃቸውን ሰጡ።) ሐዋ 11:27-30። ገላ 2:1-10። ሆኖም በኢየሩሳሌም በአይሁድ መካከል ያለችው ቤተ ክርስቲያን እና በአንጾኪያ በአሕዛብ መካከል ያለችው ቤተ ክርስቲያን ሊከተሉት ስለሚገባቸው መንገድ የተለያየ አቀራረብ ነበራቸው። በመሆኑም ከኢየሩሳሌም ወደአንጾኪያ የሚሄዱ አንዳንዶች ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የገቡትን የኦሪትን ሥርዓት መቀበል እንዳለባቸው ማስገደድ ስለጀመሩ በኢየሩሳሌም እንደገና ወንጌልን በአሕዛብ መካከል እንዴት መስበክ እንደሚገባ የሚወስን የሐዋርያት ጉባኤ ወይም የሐዋርያት የመጀመሪያው ሲኖዶስ ተካሄደ። ሐዋ 15:1-29። ቅዱስ ጳውሎስ ከጉባኤው በኋላ አገልግሎቱን በማስፋት በብዙ ቦታዎች ላይ አብያተ ክርስቲያናትን የመሠረተ ሲሆን ከኢየሩሳሌሙ ጉባኤ በኋላ ለሁለት ጊዜ ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶአል:: በመጨረሻም የተያዘውና በእሥር ወደሮም የተወሰደው ከኢየሩሳሌም ነው።
ጳውሎስ በዘመናት ውስጥ 
33    ለሐዋርያነት ተጠራ:: ወደ ዓረብ ምድር ሄደ 
35    ወደኢየሩሳሌም ለአጭር ጉብኝት ሄደ 
35-45 ኪልቅያ ሶርያ አንጾኪያ 
46    ከአዕማድ" መሪዎች ጋር  በኢየሩሳሌም መገናኘቱ (ገላ 2:1-10) 
       ከአንጾኪያ ይዞት የሄደውን እርዳታ ለኢየሩሳሌም ቅዱሳን ማድረሱ (ሐዋ ሥራ 11:27-30) 
47-48 ጳውሎስ እና በርናባስ የመጀመሪያውን ሕዋርያዊ ጉዞ ማድረጋቸው (ሐዋ 13:4-14:28)
48/49 የሐዋርያት ጉባኤና ውሳኔ 
49-51/52  ጳውሎስና ሲላስ በመቄዶንያና በአካይያ:: የፊልጵስዩስ በተሰሎንቄ በቤሪያ እና በቆሮንቶስ 
                አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ:: (ሐዋ ሥራ 16:9-18:18) 
51/52 ጳውሎስ በኢየሩሳሌም አስቸኳይ ጉብኝት አደረገ 
52-55 ጳውሎስ በኤፌሶን (ሐዋ ሥራ 19:1-20:1) 
55-57 ጳውሎስ በመቄዶንያ በእልዋሪቆን እና በቆሮንቶስ 
57      ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ኢየሩሳሌምን መጎብኘቱ::መያዙ እና መታሠሩ:: 
57-59  በቂሳርያ መታሠሩ (23:35-26:32) 
59-60 ወደኢጣሊያ ጉዞ 
60-62 በቁም እስር በሮም መቀመጡ 
62      ጳውሎስ በቄሳር ፊት 
64      የሮም መቃጠል 
65      የጳውሎስ ሰማዕትነት 

Tuesday, May 15, 2012


በክርስቶስ የጸጋ ወንጌል የተገኘ ነፃነት 
የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች 
1. ወንጌልና ተጽዕኖ  1:1-10
2. ሕይወትን የሚለውጥ መልእክት  1:11-2:21
3. የተቀበልነው ስጦታ 3:1-29
4. ልጆች ነን   4:1- 31 
5. ነጻነትና መንፈሳዊ ሕይወት 5:1-1-26
6.በወንጌል የምንኖረው የነጻነት ሕይወት 6:1-18::
የገላትያ መልእክት ዝርዝር አርእስት 
ሀ. መግቢያ 
1. ሰላምታ 1:1-5
2. ስለገላትያ ሰዎች የቅዱስ ጳውሎስ ሐዘን  1:6-9
ለ. የጳውሎስ የሕይወቱ ምስክርነት 1:10-2:21
1. ጳውሎስ የጸጋውን ወንጌል በቀጥታ ከጌታ ስለመቀበሉ:: 1:10-12
2. የጳውሎስ የቀደመው የይሁዲነት ሕይወት ለጸጋው ወንጌል መነሻ አለመሆኑ 1:13-14
3. ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተቀባይነት ስለማግኘቱ 2:1-10
4. ጳውሎስ ኬፋን (ጴጥሮስን) ስለመገሰጹ 2:11-14
5. በሥራ ሳይሆን በእምነት ስለሚሆን ጽድቅ 2:15-21
ሐ. የጸጋው ወንጌል ምንነት ትርጉም 3:1-5:12
1. የእምነት በቂነት 3:1-5 
2. የአብርሃም ምሳሌነት 3:6-9
3. ከሕግ እርግማን ነጻ መውጣት 3:10-14
4. ዘርና መካከለኛ የሆነው ክርስቶስ 3:15-22
5. የእምነት መምጣት 3:23-29
6. ወልድና መንፈስ ቅዱስ 4:1-7
7. እውነተኛ አምላክና ሐሰተኛ አማልክት 4:8-11
8. የጳውሎስ ልመና 4:12-20
9. ይስሐቅና እስማኤል የአብርሃም ሁለት ልጆች 4:21-31
10. በክርስቶስ የሚገኝ ነጻነት 5:1-6
11. ስለማመቻመች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 5:7-12
መ. በመንፈስ መመላለስ 5:13-6:10
1. ሕግና መንፈስ 5:13-21
2. የመንፈስ ፍሬ 5:22-26
3. አንዱ የሌላውን ሸክም ስለመሸከም 6:1-5
4. በቤተ ክርስቲያን ሊኖር ስለሚገባ መረዳዳት 6:6-10
5. በክርስቶስ መስቀል ስለመመካት 6:11-18