Tuesday, July 16, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (አሥረኛ ክፍል)

Read in PDF
ባለፈው ክፍል ትምህርታችን ላይ ስለ ሊቀ ካህኑ አገልግሎት የሚመለከቱ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ማለትም መሥዋዕቱን፥ ዕርቅንና ቡራኬን ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ላይ እንዳልነው በብሉይ ኪዳን የሚሠዉት  መሥዋዕቶች በሙሉ የሚያመለክቱት ክርስቶስን ነው። ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ከተባለው የሊቀ ጉባኤ አበራ አበራ መጽሐፍ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን በዚህ ርእስ ዙሪያ ያስቀምጣል። በመሆኑም ስለ ክርስቶስ መሥዋዕትነት የሚያትተንውን ምዕራፍ ለጥናታችን እንዲያመች በአርእስት በመከፋፈል እቅርበነዋል። 

1. የኃጢአት አደገኛነት
« ኃጢአት ከእግዚአብሔር መጣላትን መከራና ሞትን እንዳመጣብን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። ሆኖም አንዳንድ የሃይማኖት ወገኖች በሰው ሰውኛ አስተሳሰብ እየተመሩ የኃጢአት ሥርየት የለም፥ ከኃጢአታችንም የሚያድነን፥ ከእግዚአብሔርም የሚያስታርቀን አያስፈልግም ብለው ያምናሉ። እንደ እግዚአብሔር ቃል ከሆነ የኃጢአት ሥርየት ከሌለ ማንም ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ከቶ አይችልም። እውነትኛውም አምልኮ በዚህ ላይ ተመሠረተ ነው። በኦሪት ሕግ የመሥዋዕቱና የቁርባኑ ሥርዓት ሁሉ የሚያስተምረን ስለ ኃጢአት ሥርየት ነው።»

2. ደም ሳይፈስ ሥርየት የለም
« ደምም ሳይፈስ ሥርየት የለም» እንደ ተባለ በኦሪት ሥርዓት መሠረት የእንስሳት ደም በመሠዊያው ላይ እየፈሰሰ የሰዎችን ኃጢአት ሁሉ ለአማናዊው መሥዋዕት ምሳሌ በመሆን ያስተሠርይ ነበር። (ዕብ 9፥6_22፤ ዘሌዋ 17፥11) እውነተኛው የእግዚአብሔር በግ በመሠዊያው ላይ ደሙን እስኪያፈስ ድረስ በኦሪቱ የፈሰሰው የእንስሳት ደም ሁሉ ምሳሌና ትንቢት ነበር። የእግዚአብሔር በግ ክርስቶስ የሰዎችን ልጆች ሁሉ ኃጢአት ለማስተሥረይ በመስቀል መሠዊያ ላይ ደሙን አፍስሶ የኃጢአት ሥርየትን አስገኝቶልና።

3. በመሥዋዕቱ የሚገኘው እርቅ
« እንግዲህ ሰዎች ፍጹም ቅዱስ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር ሊታረቁና ሊቀርቡ የሚችሉት በክርስቶስ መሥዋዕትነት ባገኙት የኃጢአት ሥርየት ነው።«  ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው። » በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስገነዝበናል። . . . እንግዲህ በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል አንድ መካከለኛ ሆኖ ክርስቶስ እንዳስታረቀን ማመን አለብን፤ ያለ እርሱ . . . ማንም ወደቅዱስና ፍጹም አምላክ ሊደርስ አይችልም። አንዳንድ የሃይማኖት ወገኖች ወገኖች ወይም የፍልስፍና ሰዎች የሚሉትን በመከተል ማንም  ሰው ብቻዬን ወደ እግዚአብሔር እደርሳለሁ ቢል እርሱ ገና የሃይማኖትን ነአር አላወቀም፤ የኃያል አምላክን መልዕልተ ባሕርይ ገና አልተረዳም። « ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው፤ ካለ በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመቀጠል፦ አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ ነው፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ» ብሏል። ( 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥3_6) መካከለኛ መሆን ወይም አስታራቂነት በክርስቶስ የማዳን ሥራና ቤዛነት ላይ የተመሠረተ ነገር እንደ ሆነ ከሐዋርያው ቃል ለመረዳት እንችላለን። »

4. በመሥዋዕቱ የተከፈተው መንገድ
« በወንጌል ያለ ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ እንደ ሌለ ተጽፏል። እርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ እውነተኛ መንገድና በር ነው። ያለ እርሱ መንገዱም በሩም በኃጢአት ግርግዳ የተዘጋ ነው። በእርሱ ባገኘነው የኃጢአት ሥርየት የጥሉ ግርግዳ ስለፈረሰ ወደ ወደ እግዚአብሔር የሚያገናኘው መንገድ ተከፍቶአል። እርሱ ራሱ መንገድም፥ እውነትም፥ ሕይወትም፥ ነውና በእርሱ በኩል ካልሆነ ወደ አብ የሚመጣ የለም ። (ዮሐንስ 14፥6) በእርሱ ሥጋዌ (ሰው መሆን ) በማመን እርሱ በከፈተው የጽድቅ መንገድ፥ እርሱ በመስቀሉ ባስገነው ቤዛ ካልሆነ በቀር በገሐድ በሥጋዌ (ሰው በመሆን) ያልተገለጠውን አብን የሚያገኘው የለም ማለት ነው። (ዮሐንስ 14፥6 ትርጓሜውን ተመልከት፤

5. በደሙ የተመረቀልን መንገድ
ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰን አማናዊው መንገድ (ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት) የተባለው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። እግዚአብሔር ወደ አለበት ወደ ቅድስት ለመግባት የምንችለው በክርስቶስ ሥጋ በኩል አንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውን ክርስቲያኖች ሲጽፍ፦ እንግዲህ ወንድሞች ሆይ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት እንዳለንና እንዲሁም « በእግዚአብሔር ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን » እንዳለን ገልጾናል። « ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን» የሚለውን የሐዋርያውን ቃል ትርጉም ወይም ምሥጢር የምንገነዘበው ሰው በሠራው በደልና ኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ በፍርሃትና በጭንቀት ሲኖር ሳለ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ደሙን አፍስሶ ኃጢአቱን አስወግዶ ከራሱ ጋር አስታርቆ « ወደ ቅድስት የሚወስደውን መንገድ»  እንዲከፈት አድርጐ ወደ ሰማያዊው መቅደስ ወደ ጸጋው ዙፋን ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት ለመግባት መብትን « ድፍረትን እንዲሁም የጸጋ ልጅነትን እንዲያገኝ ሥልጣንን እንደሰጠው በማመን ነው። (ዕብራውያን 10፥19-22፤ 9፥8-28፤ 4፥16፤ ዮሐንስ 1፥12) የቀድሞው የብሉይ ኪዳን መንገድ ወይም ሥርዓት የሰውን ኃጢአት ስለ ማያስወግድ ከእግዚአብሔር ስለ ማያስታርቅ እግዚአብሔር በፈቀደውና በወደደው « በአዲስና በሕያው መንገድ» ወደ እርሱ እንድንመጣ አድርጎናል። ይኸውም መንገድ በኦሪቱ ሊቀ ካህናትነት እንደሆነ ሐዋርያው ለዕብራውያን በጻፈው መልእክቱ አረጋግጦልናል። እንግዲህ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው መንገድ በኦሪቱ  ሥርዓት በቤተ መቅደሱ መጋረጃ ተዘግቶ የነበረውን በዕለተ ዓርብ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ በሥጋው በፈጸመው መሥዋዕትነትና አስታራቂነት አስወግዶታል። ያን ጊዜ መጋረጃው ተቀዷል (ማቴዎስ 27፥51) በክርስቶስ ለሚያምኑት ሁሉ ወደ ፈጣሪያቸው የሚያደርሱበት የእርቅና የሰላም የጽድቅና የሕይወት መንገድ ተከፍቶላቸዋል።»

6. የአዲስ ኪዳን አስታራቂ
« በመሠረቱ ሰው ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚቻለው ሰው በሆነው በክርስቶስ በኩል ነው። ከዚያ በፊት ግን ሰው መጀመሪያ ወደ ክርስቶስ ለመቅረብና እርሱን ለማመን የሚቻለው የእግዚአብሔር ረድኤት፥ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ወደ ክርስቶስ ሲስበው ነው። በመሆኑም ክርስቶስ፦ የላከኝ አባቴ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ካልሰጠኝ በኔ ማመን የሚቻለው የለም ብሏል ( ዮሐንስ 6፥44) እንግዲህ ራሱ እግዚአብሔር እኛ ሰዎችን ኃጢአተኞችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅና ለማቅረብ ያሰበውና ያዘጋጀው የጽድቅ መንገድ፥ የሕይወት መንገድ በልጁ ሰው መሆን ማለት በምሥጢረ ሥጋዌና በነገረ መስቀል እንደተገለጸው ተፈጽሟል።  በሥጋዌ፥ ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ የሰውን ባሕርይ ባሕርዩ በማድረጉ ያን ጊዜ ባሕርያችንን ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቋል። ስለዚህ ነው <« የአብ ሊቀ ካህናት የሚሆን እርሱ የሰውን ባሕርይ ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ» እያልን በሐዋርያት አመክንዮ እምነታችንን የምንገልጸው ። (ሥርዓተ ቅዳሴ፤ ቍጥር 43 ተመልከት)  በመስቀሉ ደግሞ ነፍሱን ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጎ በመስጠቱ ሰውን ከእግዚአብሔር አጣልቶና አርቆት የነበረውን ኃጢአትን አስወግዶ እርቅና ሰላምን አስገኝቶልናል። ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን መሥዋዕት በመሆኑ እውነተኛ አስታራቂአችን ሆኗል። ቤተ ክርስቲያንም በእርሱ ስም በእርሱ መሥዋዕት የማስታረቁን ሥራ እርሱ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ በኃላፊነት እንድትሠራ ታዛለች። (2 ቆሮንቶስ 5፥18-21፤ 1 ቆሮንቶስ 11፥23-26፤ ማቴዎስ 28፥19-20)

7.  እንደመልከ ጼዴቅ ባለ ክህነት የዘለዓለም ካህን የሆነ
« እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት የዓለም ካህን እንደሆንክ» የተባለለት « እርሱ. . . ለዘለዓለም ይኖራል ክህነቱ አይሻርምና። ዘወትር በእሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል፤ ለዘለዓለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል። እንዲህ ያለ የካህናት አለቃ ይገባናል. . . ከሰማያት በላይ የሆነ . . . ኦሪትስ የሚሞት ሰውን ሊቀ ካህናት አድርጋ ትሾማለች፤ ከኦሪት በኋላ የመጣው የእግዚአብሔር የመሐላ ቃሉ ግን ዘለዓለም የማይለወጥ ፍጹም ወልድን ካህን አድርጎ ሾመልን። ( ዕብራውያን 7፥20-28)  ክርስቶስ መካከለኛ የተባለበት አዳምና ልጆቹ ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተው፥ ተለይተውና ርቀው የነበሩን በማስታረቁና በማቅረቡ ነው። « ለወንጌል ሊቀ ካህናት ለመንግሥተ ሰማት አስታራቂ ሆነ . . . በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳናቸው አነጻቸው ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ ዕብራውያን 12፥24  በቅድሚያ እርሱ ራሱ በሥጋ ተዛምዶ ማለትም ሰው በመሆኑ ወደ እኛ ቀርቧል፤ ከእኛም ጋር ታርቋል። እንግዲህ እርሱ ራሱ በሰውነቱ ቀርቦ አቅርቦናል፤ ታርቆ አስታርቆናል።No comments:

Post a Comment