Tuesday, July 30, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (አስራ አንደኛ ክፍል)



ስለ እኛ ተሰቀለ፤ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረም በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛ ሕያዋንን ሙታንንም ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም። 

  1. ስለ እኛ ተሰቀለ
አንዳንድ የመስቀሉ ቃል ያልተገለጠላቸው ሰዎች እንዴት ሰው የተገደለበትን መሣሪያ ታገኑታላችሁ ይሉናል። ነገር ግን ይህ የሞት መሣሪያ የሕይወት ምልክት የሆነው በእርሱ ላይ ከተከናወነው ነገር የተነሣ ነው። 
• መስቀሉ መርገም የተሻረበት ነው፤ 
በገነት መካከል ያለው ዛፍ እርግማንን ወደሰዎች ያመጣ ነው። የቀደመው ሰው አዳምና እናታችን ሄዋን አትብሉ የተባሉትን ሲበሉ በመርገም ውስጥ ነበር የወደቁት፤ በመስቀሉ ግን ያ እርግማናችን ነው የተደመሰሰው፤ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤» ይላል። ገላትያ 3፥19። 
• መስቀሉ ጥል የተገደለበት ነው፤ 
አሁንም በገነት መካከል ያለው ዛፍ በሰውና በእግዚአብሔር እንዲሁም በሰውና በሰው መካከልም ከዚያም አልፎ በሰው ሕይወት ውስጥ ጥልን የተከለ ነበር። በሰው ሕይወት ውስጥ ወዲያው የተገለጠው ራቁትነት፥ ፍርሃት፥ ራቁትነት እና ከእግዚአብሔር መሸሽ ነበር። ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጥል የሆነውን ነገር ማድረግ ጀመረ፤ ከራሱና ከሌላው አምሳያው ጋር መጣላት ጀመረ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን «እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።» ኤፌሶን 2፥14-16
• መስቀሉ የእርቅ ምልክት ነው። 
የእግዚአብሔር ልጅ ለእኛ ለሰው ልጆች የሰበከልን የእግዚአብሔር መንግሥት የተጠቃለለው በመስቀሉ ላይ ባሳየን የፍቅር መሥዋዕትነት ነው። ከዚህ በፊት በብሉይ ኪዳን ይሠዉ ስለነበሩት መሥዋዕቶች ስንነጋገር እንዳልነው፥ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ያከናወነልን እርቅ ነው። በመሆኑም መስቀል ሲባል ጌታ የሞተበት ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሰውን ከአምላኩ ለማስታረቅ ያከናወነው ድርጊት ነው። በመሆኑም ወንጌል ራሱ የመስቀሉ ቃል ተብሎአል። ሮሜ 1። 18። 
• መስቀሉ የእግዚአብሔር ጥበብ የተገለጠበት ነው። 
በመስቀሉ በኩል ያየነው እግዚአብሔር እጅግ አስደናቂ የሆነ ነው። ወደሰዎች መከራና ሥቃይ የቀረበ። የሰዎችን የልብ ስብራት የዳሰሰ እግዚአብሔር ነው። በትህትናና በዝምታ የመጣ እግዚአብሔር ነው። ክብሩን ሁሉ የተወ እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም ልክ ኤልያስ በእግዚአብሔር ተራራ ላይ በእሳት እና በአውሎ ነፋስ እንደፈለገው በዕውቀታቸው ወይም በዚህ ዓለም ከፍታዎች ውስጥ የፈለጉት አላገኙትም። እርሱ የተገኘው በመስቀል ላይ ከወንጀለኞች ጋር፥ በነዘኬዎስ ቤት ከኃጢአተኞች ጋር፥ በጌርጌሶን ከመቃብር አዳሪዎች ጋር፥ በመንገድ ደም ከሚፈሳቸው ጋር፥ በቤት ከታወቁ ኃጢአተኞች ጋር ነው። በዚህም የዓለምን ጥበብ ሁሉ ከንቱ አደረገው። ክብር ለእርሱ ይሁን

  1. ታመመ ( መከራ ተቀበለ) 

የክርስቶስን ሕማም በምናስብበት ወቅት የምናስባቸው የሕማማቱን ሳምንቶች ብቻ አይደለም። የሕማሙ ጉዞ ከልደቱ እስከሞቱ ያለው ሁሉ ነው። ታመመ የሚለው ቃል ጌታ በመከራ ወደ እኛ እንዴት እንደቀረበን የሚያመለክት ነው። ዕብራውያን ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ይላል። « ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።» በማለት በነገር ሁሉ እኛን እንደመሰለ ይነግረናል። በዚሁ አንቀጽ ላይ እንደገና ዝቅ ብሎ ሲናገር « ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም።» ይላል። ዕብራውያን 2፥17፤4፥15። ቅዱስ ጴጥሮስም የእርሱ መከራ ለእኛ መከራ የእርሱ ሕማም ለእኛ ሕማም የመጽናናት ምክንያት እንደሆነ ሲያስተምረን እንዲህ ብሎአል፦ « የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤» 1 ጴጥሮስ 2፥21-23 


3. ሞተ 
ቅዳሴያችን « የማይሞት እርሱ ሞተ፥ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ፤ በቃል ኪዳን ተስፋው እንደነገራቸው።» ይላል። (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ቍ. 35) እውነት ነው የሞተው ከዘላለም አነዋወሩ ሞት ለባሕርይው የማይስማማው የነበረ ነው። ነገር ግን የሰውን ባሕርይ ገንዘብ ሲያደርግ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ነሥቶ ሰው ሲሆን ዋና ዓላማው በሥጋው የሞትን መውጊያ ለማጥፋት ነው። የሞትን መውጊያ ወይም የሞትን የማስፈራራት ኃይል ለማጥፋት የእግዚአብሔር ልጅ ከሰዎች የሚፈለገውን የሞትን ዋጋ መክፈል ነበረበት፤ ምክንያቱም ኃጢአት ወደ ዓለም በመግባቱ ሞት ወደ ዓለም ገብቶ ነበር፤ «ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤» ሮሜ 5፥12፤ ዘፍጥረት 2፥17፤ « ነገር ግን ሥጦታው እንደበደሉ አይደለም» የተባለለት ልዑል እግዚአብሔር ልጁን በመላክ ከሞት ነጻ አደረገን። ሮሜ 5፥14፤ ከዚህ በፊት ደጋግመን እንዳየነው የጌታ ሰው የመሆን ምሥጢሩም ከዚህ የሞት ፍርሃት ነጻ ሊያወጣን ነው። «እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።» ዕብራውያን 2፥14። 

  1. ተቀበረ 

ጌታ ስለሕማሙ ስለሞቱ ትንቢት እንደተናገረ ሁሉ ስለመቀበሩም ትንቢት ተናግሮአል። « ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።» ማቴዎስ 12፥40

• በመቃብር ያደረው ሙስና መቃብርን ያጠፋ ዘንድ ነው። 
ሰው እጅግ ከሚፈራው ነገር አንዱ ርደተ መቃብርን ማለትም ወደመቃብር መውረድን ነው። የክርስቶስ ወደመቃብር መውረድ ግን ሰውን ከመቃብር ፍርሃት እና በመቃብር መበስበስ ነጻ አውጥቶታል። « እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።» ሐዋ ሥራ 2፥24-27። 

• በመቃብር ያደረው በሲኦል ላሉት ነጻነትን ለመስበክ ነው። 
ጌታ በመቃብር ስለማደሩ የተናገረውን ከቅዱስ ጴጥሮስ ቃል ጋር ስናነጻጽረው  ጌታ ለምን በመቃብር እንዳደረ ታላቅ መልእክት ይሰጠናል። ይኸውም ክርስቶስ በአካለ ነፍስ ወደሲኦል ወርዶ በዚያ ላሉት ነጻነትን አውጆላቸዋል።  «ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤» 1 ጴጥሮስ 3፥18-19  ይህንን ትምህርት ይዘው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰዓልያን የክርስቶስን ትንሣኤ በሚሥሉበት ወቅት አዳምንና ሔዋንን በቀኝና በግራው ይዞ ያሳያሉ። 

  1. በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ 

ሞት ይይዘው ዘንድ ስላልቻለ ጌታ በኃይሉና በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ። ከሙታን ሲነሣ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ አላለም። ከሙታን የተነሣው ከዚህ በፊቱ ከሙታን ተነሥተው ተመልሰው እንደሞቱት ሰዎች አይደለም። ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ሞትን ድል አድርጎ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን፥ ትንሣኤው የክርስትናችን እውነት ማዕከል ነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታ ትንሣኤ ምሥጢር በስፋት ባስተማረበት በ1ኛ ቆሮንቶስ 15 ላይ ሰፋ ያለ እውነቶችን አስቀምጦልናል። 
• የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስቶስን ወንጌል እውነተኛነት ያረጋገጠ ነው። 
• የክርስቶስ ትንሣኤ በክርስቶስ ያንቀላፉት ተስፋ እንዳላቸው የገለጠ ነው። 
• የክርስቶስ ትንሣኤ የኃጢአት ይቅርታን እንዳገኘን ያረጋገጠልን ነው። 
• የክርስቶስ ትንሣኤ በዚህ ዓለም ባለን ኑሮ ተስፋን የሰጠን ነው። 
• የክርስቶስ ትንሣኤ በመከራችን ለመጽናት ምክንያታችን ነው። 
• የክርስቶስ ትንሣኤ ከእኛ የተለዩንን ወገኖቻችንን ዳግመኛ እንደምናገኛቸው የሚያመለክተን ነው። 
• የክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛ ትንሣኤ ተስፋ ነው። 

የእኛን ሞት እንደሞተልን ሁሉ የእርሱን ሕይወት ደግሞ በትንሣኤው ሰጥቶናል። በሞቱ ኃጢአታችን እንደተሠረይልን ያወቅነው በትንሣኤው ባገኘነው ሕይወት ነው። በመሆኑም ሐዋርያው እንዳለው « ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤» ሮሜ 6፥5። ይህም የትንሣኤ ሕይወት ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ የምንኖርበት ሕይወት ነው። ይህም ወደሚቀጥለው እውነት ያመጣናል። ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱ እኛን ለአዲስ ሕይወት አብቅቶናል። በኃጢአት ላይ ኃይል እንዲኖረን፤ በሞት ላይ ኃይል እንዲኖረን፤ በሰይጣን ላይ ኃይል እንዲኖረን፤ አድርጎናል፤ ትንሣኤ ማለት አዲስ ሕይወት ነውና። 

  1. በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤

በአምላክነቱ የወረደው ጌታ በሰውነቱ አረገ፤ አረገ ወረደ የሚለው ቃል የአምላክን ልዩና አስደናቂ ክንውን የሚያሳይ ነው እንጂ እርሱ በሁሉ የመላ ሁሉን የያዘ አምላክ ነው። ወረደ ስንል የሰውን ባሕርይ ገንዘብ ማድረጉን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት መወሰኑን ሲሆን፤ አረገ በምንልበት ወቅትም ወደቀደመ ክብሩ መመለሱን ነው። ነገር ግን እርገቱ ከዚህ በላይም መልእክት አለው። 
• ያረገው በተዋሃደው ሥጋ ነው። 
ያረገው በረቂቅ መንፈስ አይደለም። ይህ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አንዳንዶች ክርስቶስ ዳግመኛ በመንፈስ መጥቶአል ያሉት በሆነ ነበር። ነገር ግን ያረገው በግልጥ ደቀመዛሙርቱ እያዩት ነው። እያዩት እንደሄደ ሁሉ በግልጥ ደግሞ ዓለም እያየው ይመጣል። 
• በእርገቱ የሰው ዘር ሁሉ ከብሮአል። 
ያረገው በተዋሃደው ሥጋ ስለሆነ በእርሱ ውስጥ እኛ አለን፤ ማለትም የተዋሃደው ባሕርያችን ዛሬ በአብ ቀኝ በክብር ተቀምጦአል። ዮሐንስ ዘደማስቆ ስለዚህ ሲናገር « ባህርያችን ከሙታን ተነሥቶ፥ አርጎ በአብ ቀኝ አለ በምንልበት ወቅት የሰው ዘር ሁሉ ተነስቶ በአብ ቀኝ አለ ማለታችን አይደለም። ነገር ግን የሰው ዘር በክርስቶስ ውስጥ ተሰውሮአል ለማለት ነው እንጂ፤» ይህም ከቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ጋር ይስማማል። 
• በአብ ቀኝ በመቀመጡ የቤተ ክርስቲያን ሁሉ ራስ ሆኖአል። 
እርገቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞትና በመውጊያው ላይ፥ በአለቆችና በሥልጣናት ላይ ድል አድራጊ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። «እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤» ዕብራውያን 1፥3  

ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት አንጻር ሲናገር እንዲህ ብሎአል።  «ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።» ኤፌሶን 1፥20-23 ይህ ምን ማለት ነው ብለን ስንጠይቅ « እግዚአብሔር አብ ክርስቶስን ከሙታን አስነስቶ በሰማያት በዙፋኑ ላይ አስቀመጠው፤ ዓለማትን ሁሉ ይገዛ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠው። ማንም ስምና ሥልጣን ከእርሱ አገዛዝ ውጭ አይደለም። ይህም ግዛቱ ለጊዜው ሳይሆን ለዘለላለም ነው። በሁሉ ላይ ሥልጣን አለው፤ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ እርሱ ነው። በዚህ ሁሉ መካከል ሆኖ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ይገዛል ማለትም ቤተ ክርስቲያን የዓለም ተቀጣይ ሳትሆን ዓለም የቤተ ክርስቲያን ተቀጣይ ናት። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ የሚናገርባትና ሥራውን የሚያከናውንባት ሁሉን በሁሉ የሚሞላባት የክርስቶስ አካሉ ናት ፤

No comments:

Post a Comment