Thursday, April 1, 2010

የወደዳቸውን እስከመጨረሻ ወደዳቸው


ዮሐንስ ወንጌላዊ ከሐሙስ ማታ ጀምሮ የተከናወነውን አስደናቂ ክንውን የገለጠው በሚያስደንቅ መንገድ ነው።
ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። ዮሐ 13፥1

የወደዳቸውን እስከመጨረሻ ወደዳቸው። ምንኛ አስደናቂ አነጋገር ነው። ጌታችን የተቀበለው መከራ ድንገት የሆነ ሳይሆን በፍቅር የሆነ ነው። በሁኔታዎች ላይ ያልተመሠረተ ፍቅር! መለኮታዊ ፍቅር!
ጴጥሮስ እንደሚክደው፥ ይሁዳ እንደሚሸጠው ፥ ደቀመዛሙርቱ እርሱን ጥለው እንደሚሸሹ እያወቀ የወደዳቸውን እስከመጨረሻ ወደዳቸው።

ግሩም በሆነው በጸጋው ዙፋን ፊት በድፍረት እንድንቀርብ ድፍረት የሚሆነን ይህነው። የወደደን ያለምንም ምክንያት ነው። የወደደን ወሰን በሌለው ፍቅር ነው። ኦ ለዚህ ወሰን ለሌለው ፍቅር አንክሮ ይገባዋል።

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይህን ፍቅርህን ዕለት ዕለት ግለጥልኝ። ለእኔ ያለህ ፍቅር ወሰን የሌለው ቢሆንም እኔ ግን ውሱን በሆነው የዓለም ፍቅር እየተንገገላታሁ ነኝና።
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ያሳየኸኝን ድንቅ የሆነውን ትህትናህን እንዳልረሳው አሳስበኝ። ሽርጥ ታጥቀህ የደቀመዛሙርትህን እግር ያጠብከው ይህን ልታስተምረኝ ነውና።
አምላኬ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ህይወቴን በፍቅርህ ሙላው በጸጋህ እጠበኝ።

No comments:

Post a Comment