Friday, December 20, 2013

ጋብቻና ድንበር (ወሰን)

ቀሲስ ዳውድ ላሜይ ( ካይሮ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን)
ትርጉም በሊ.ኅ.መ.ባ 

Read in PDF
ጋብቻችን በክርስቶስ የተጠበቀ እንዲሆን ከውጭው ዓለም ጋር በሚኖራችሁ ግንኙነት ላይ ድንበር ወይም ወሰን ማስቀመጥ መቻል አለባችሁ። ብዙ ጋብቻዎች ወደብዙ ችግር የሚገቡት፥ በእነርሱና በቤተሰቦቻቸው፥ በእነርሱና በአማቾቻቸው፥ በጓደኞቻቸው፥ በሥራ ባልደረቦቻቸው ሌላው ቀርቶ እርስ በእርሳቸው ባላቸው ሕይወት ይህን አስፈላጊ የሆነ ድንበርና ወሰን ለማስቀመጥ ባለመቻላቸው ነው። 

እናንተና የትዳር ጓደኛችሁ ወሰንና ድንበር የማታስቀምጡበት አንድ ነገር ቢኖር  ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላችሁ ሕይወት ነው። እናንተ [በፈቃዳችሁ ካልሆነ] ከማንም ጣልቃ ገብነት የተጠበቃችሁ በራሳችሁ ምሉዓን የሆናችሁ ሰዎች ናችሁ። 

ይህ ማለት ግን ራሳችሁን ሙሉ በሙሉ ከውጫዊው ዓለም መለየት አለባችሁ፤ በተባሕትዎ በብቸኝነት መኖር አለባችሁ ማለቴ አይደለም። ለማለት የፈለግሁት ከማናቸው ሰው ጋር የሚኖራችሁ ግንኙነት በጋብቻ ሕይወታችሁ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ እንድትጠነቀቁ ይገባል ነው።

ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ቃል የሚከተሉትን ምንባባት መርጣ የሚጋቡትን የምታሳስበው እንዲያው በግብታዊነት አይደለም። 
« ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ» ማቴዎስ 19፥5። 
« ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ» መዝሙር 45፥10። 

ስለራሳችን ስለቤተሰቦችንና ስለወላጆቻችን መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ያለ ምክር ከሰጠን፥ ከሌሎች ጋር ስላለንም ግንኙነት እንደዚሁ ልንጠነቀቅ እንደሚገባ የታወቀ ነው። 

« ወገንን የአባትን ቤት መርሳት» ወይም « አባትንና እናትን መተው» ማለት ምን ማለት ነው? 

መርሳት ወይም መተው ማለት ከጋብቻ በፊት እንደገፍባቸው ግንኙነቶችን «በመጣል»  ወደ ሌላ አቅጣጫ ትኩረትን ማድረግ ማለት ነው። የሚያስገርመው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ከአባቱና ከእናቱ ጋር እንደነበረው ያለ ጠንካራ ግንኙነት ከጋብቻ በኋላ ከሚስቱ ጋር ሊኖረው እንደሚገባ በአጽንኦት ለመግለጥ፥  መንፈስ ቅዱስ « አባትና እናቱን ይተዋል» ካለ በኋላ « ከሚስቱም ጋር ይተባበራል( ይጣበቃል)» አለ። ይህ ግንኙነት ከአባትና ከእናቱ ጋር ከነበረው ግንኙነት የተለየ ነው፤ ይህ ግንኙነት እስከ ሕይወት ፍጻሜ የሚዘልቅ ግንኙነት ነው። 

መተው (መጣል) 

መተው ( መጣል) ከዚህ ዓውደ ንባብ አንጻር በሚገባ የሚገልጠው ሕፃናት ልጆች ምግባቸውን ለማግኘት የእናታቸውን ጡት ሙሉ በሙሉ መደገፋቸውን ትተው ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ማለትም ምግባቸውን ከሌላ ሥፍራ ለማግኘት የሚያደርጉትን ሂደት ያመለክታል። ( ጡት ጣለ ( ተወ) የሚለውን የአገራችንን አባባል ያመለክቷል) 

መተው ( መጣል) የሚለው ቃል በራስ የመቆምንና የማንነትን አሳብ ያዘለ « ነፃነትን» የሚያመለክት ነው። ቀላል ሂደት አይደለም። በመጀመሪያ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። አስቸጋሪነቱ ለሕፃኑ ብቻ ሳይሆን ለእናትም ነው። ጡቱ መጥባቱን ሲተው እናት ሕፃኑ ከእርሷ ጋር ያለውን ቀረቤታ እንደተወ እና እንዳስለመደው በእርሷ መደገፉን እንዳቆመ ይሰማታል። 

መተው ( መጣል) ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱም ይታያል። ከወላጆቿቸው ሊለዩና ለረጅም ጊዜ ያለ እነርሱ ሊቆዩ መሆኑን ሲያውቁ ምርር ብለው ያለቅሳሉ። በተመሳሳይ መንገድ ሰው በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ሲገባ ሌላው መተው ( መጣል) ይከሰታል። 

በእኛ ባህል « መተው» ሁል ጊዜ እንዲዘገይ ይደረጋል። እናቶች ልጆቻቸውን ከሁለት ዓመት በላይ ዕድሜ ኖሮአቸው ለማጥባት ይፈልጋሉ።. . . 

ተጋቢዎች ከወላጆቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ያላቸውን « የመተው» ሂደት በጊዜ ካላደረጉት፥ በጋብቻ ሕይወታቸው ውስጥ ብስለትና ነጻነት ያለበት የአብሮነት ሕይወትን ለመኖር የማይችሉበት ነጥብ ላይ ይደርሳሉ። 

ይህ ቤተሰቦቻችንን የመተው ሂደት ልክ እንደሌሎቹ ሂደቶች ( ጡት እንደመተው፥ ትምህት ቤት እንደመግባት) አስቸጋሪና ለመጀመሪያ ከፍተኛ ሕመም የሚፈጥርብን ነው። ነገር ግን በጋብቻ ሕይወታችን ለማደግና ለመጠንከር ግዴታ ነው። በመሆኑም ይህን የነጻነት ኑሮ ለመኖር ከወሰኑበት ወቅት ጀምሮ ይህን ውሳኔአቸውን በተመለከት ሊመጣባቸው የሚችለውን ፈርጀ ብዙ የሆኑ ፈተናዎች በጋብቻ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ከእጮኝነት ሕይወታቸው ጀምሮ በሚገባ ሊገነዘቡት ይገባል። 

« ድንበር ማስቀመጥ» ማለት ሁለቱ ምክር ፈልገው ከሚቀርቡአቸው ንስሐ አባትና የጋብቻ አማካሪዎች  ውጭ የሁለት ባለትዳር ጓደኞች ግላዊ ሕይወት በሌሎች ሊደፈር አይገባም ማለት ነው።  በጋብቻ ያሉ የባልና የሚስት ዝርዝር የትዳር ሕይወት በወላጆች፥ በቤተሰብ አባላት፥ በጓደኞችና በቤተ ዘመዶች መካከል የወሬ ርእስ መሆን የለበትም። 

አንዳንድ ወላጆች የእነርሱ ጣልቃ ገብነትና ስለልጆቻቸው ጋብቻ የሚሰጡት አስተያየት በልጆቻቸው የጋብቻ ሕይወት ላይ ምን ያህል አደገኛ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አያስተውሉም። ልጆቻቸው የጋብቻ ሕይወታቸውን ለመጠበቅ ያስቀመጡትን ድንበር ወይም ወሰን ለማክበር  አንዳንድ ወላጆች በጣም ይቸግራቸዋል፤ ፈቃደኞችም አይደሉም። ልጆቻቸው ለእነርሱ ምንም እንደማያስቡና ታማኞች እንዳይደሉ አድርገው ቅሬታ ያሰማሉ። ያለመታደል ሆኖ ብዙዎች ባሎችና ሚስቶች በዚህ የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማቸው ወደዚህ ወጥመድ ይወድቁና በጋብቻ ሕይወታቸው ያለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በማድረግ የወላጆቻቸውን ፍላጎት ለማርካት ይሞክራሉ። 


ለወላጆቻችሁ ያላችሁን ታማኝነትና ለትዳራችሁ ያላችሁን ኃላፊነት ሚዛናዊ ማድረግ ለጋብቻ ሕይወታችሁ ዕድገትና ስኬት እጅግ አስፈላጊ ነው። በመልካም ትህትና፥ ለእናታችሁ ወይም ለአባታችሁ መቼና እንዴት « አይሆንም፤ አይደረግም» ማለት እንዳለባችሁ ማወቅ፤ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ያላችሁ ሕይወት ቅድሚያ ለመስጠት መወሰን ፤ ከሁሉም በላይ « አባትና እናታችሁን ተዉ፤ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተባበሩ» ላለው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ለመታዘዝ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ለመስጠት መወሰን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።  

1 comment:

  1. Kesis,

    May God bless your ministries. You have been a spiritual guide and teacher for me for a while now. I read every bit of your posts here and of course Sunday sermons. I thank my Lord for your.

    Reading your recent post about 'marriage', I was just wondering if you could write or bring us useful materials for myself and fellow singles who are neither married or not in any relationship. It's becoming a very challenging facet of life for me especially recently. I consider myself to be a 'good person' not so much to aggrandize myself but I would like to believe someone who deserves someone I can love/loved and be happy with but nothing seem to work.

    I have prayed and gave it to the Lord for last two years but I keep running into a dysfunctional relationships. It is very discouraging and quite honestly pretty frustrating. It's causing doubts in my faith and trust of the Lord.

    If you could please shade some light on 'pre marriage' and relationship matters and of course pray for me, I would greatly appreciate it.

    Thank you and God Bless you again,

    ReplyDelete