Thursday, December 19, 2013

ትዳርና አመለካከት

በቀሲስ ዳውድ ላሜይ  ( ካይሮ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን) 
ትርጉም በሊ.ኅ.መ.ባ
በጋብቻ ውስጥ ደስታን ለማግኘት የመጀመሪያው ቁልፍ ነገር ባልና ሚስት የሚኖራቸው « አመለካከት» ነው። በትዳር ውስጥ ያለ አመለካከት ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላቸውን፥ የራሳቸውን ሕይወትና በዙሪያቸው ያሉትን በሚመለክቱበት እይታ ላይ የተመሠረተ ነው። በራስ ሕይወት፥ በትዳር ጓደኛ፥ እኛን አንድ አድርጎ ባያያዘን ግንኙነትና በአጠቃላይ በሕይወት ውስጥ አዎንታዊ የሆነ ክርስቲያናዊ አመለካከትን ማዳበር ለጋብቻችን ስኬት ቁልፍ ነገር ነው። 

ባል ሚስቱን እግዚአብሔር በፀጋው የሰጠው የሕይወት ባልደረባ አድርጎ ሲመለከታት፥  አመለካከቱ እጅግ ጥልቅ የሆነ ምስጋና፥ ፍቅር፥ እንክብካቤና መሰጠት ይሆናል። በአንጻሩ ደግሞ ተፎካካሪሪውና ተገዳዳሪው ወይም ፍላጎቱንና ጥያቄውን ልታገለግልለት የተቀመጠች አንዲት ሴት አድርጎ የሚያይ ከሆነ፥ አመለካከቱ በትዕቢት፥ በቁጣ የተሞላ ከመሆኑም በላይ ጥላቻን ሳይቀር ማሳደግ ይጀምራል። 

ሚስትም በሙሉ ኃይልዋ እንድታፈቅረው ለእርሱና ለቤተሰቧ ሕይወቷን እንድትሰዋ እግዚአብሔር የሰጣት ስጦታ አድርጋ ባልዋን የምትመለከተው ከሆነ፥ አመለካከቷ የፍቅር፥ የመሰጠት፥ የድጋፍና የመሥዋዕትነት ይሆናል። ነገር ግን ባልዋን የሚጨቁናትና እርሱንና የተቀረውን ቤተሰብ ለማገልገል ያስቀመጣት አድርጋ የምታይ ከሆነ አመለካከቷ በምሬት፥ በእምቢተኝነት የተሞላ ይሆናል ቀስ በቀስም ይህ አመለካከት ወደ ዓመፅ ያድጋል። 

ባልና ሚስት በእርሱ ውስጥ ያለውን ዕቅድ ለማከናወን ፈቃደኞች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አድርገው ራሳቸውን የሚቆጥሩ ከሆኑ፥  ወደ እግዚአብሔር የመቅረብን አመለካከት ያዳብራሉ፤ አንዳቸው አንዳቸውን ለመርዳትና ለመቀራረብ እጅግ ይጥራሉ። ሰላምና ደስታ የተሞላበት የእርካታ ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልገውን ምግባር ያገኛሉ። 

ሁለቱ ገንዘብንንና ቁሳዊ ሀብትን እጅግ ዋና ነገር አድርገው መመልከት ከጀመሩ አንዳቸው ስለአንዳቸው ስለሌሎች ሰዎችና ስለሚገጥማቸው ሁኔታ የሚኖራቸው አመለካከት በራስ ወዳድነትና በጥላቻ የተሞላ ይሆናል። ነገር ግን የመኖራቸው ምክንያትና በጋብቻ መተሳሰራቸው  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅሩን ለሰዎች ሁሉ የሚያሳይበት መሣሪያ አድርገው የሚያስቡ ከሆነ፥   በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ጌታን የበለጠ እንዲያውቁ ለማገልገል ፈቃደኛ የመሆን አመለካከት ይኖራቸዋል። ቤታቸውም የጌታ ማረፊያ (ትንሿ) ቤተ ክርስቲያን ትሆናለች። 

በመሆኑም በመጀመሪያ በጋብቻ ሕይወታችሁ በእርግጥኝነት የሚያጋጥማችሁን ብዙ ተግዳድሮት ለመቋቋም፥ ደስታና እርካታ የተመላበት ሕይወት ለመምራት እንድትችሉ የሚረዳችሁን አዲስ አመለካከት ለማዳበር፥ አሳባችሁን፥ ራዕያችሁንና ዋጋ የምትሰጡትን ነገር መመርመር እጅግ አስፈላጊ ነው። 

ሌላው ልናስታውስ የሚገባን « አመለካከት» ከሰው ወደሰው የሚጋባ ነው። በመሆኑም የትዳር ጓደኛችሁ አዎንታዊ ያይደለ ወይም እጅግ አሉታዊ ያይደለ ቢኖራት ወይም ቢኖረው ከልብ በሆነ ጸሎቶቻችሁና በመልክካም በታጋሽነታችሁ እና በደስተኛ አመለካከታችሁ መለወጥ ይኖርባችኋል።  

ነገሮችን በአሉታ የሚመለከት  ወይም የሚትመለከት የትዳር ጓደኛ ቢያጋጥማችሁ አሉታዊ በሆነ መንገድ በመመለሳችሁ የምታሸንፉ አይምሰላችሁ።  በክፉ ስትመልሱ ነገሮችን የተሻለ የምታደርጉበትን እድል ከማጣታችሁ በላይ ዘላቂ ሰላማችሁን በማጣት « ክፉን በመልካም እንጂ በክፉ አታሸንፍ» በማለት ካዘዘ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚኖራችሁን ግንኙነት ታበላሻላችሁ። 


እስከአሁን ካልጀመራችሁ፥ ነገሮች ከእጃችሁ ከመውጣታቸው በፊት ስለ ትዳር ጓደኛችሁና ስለ ሕይወታችሁ ያላችሁን እመለካከት እንድትለውጡ እመክራችኋለሁ። ብዙ ሰዎች እድላቸውን ወርውረው ስለ ትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን አመለካከት ለመለወጥ ምንም ጥረት ሳያደርጉ የትዳር ጓደኛቸው ወደ ጌታ ሲሄዱ ወይም ትዳራቸው ወደ አልሆነ አቅጣጫ ሲሄድ በፀፀት እንዳይወሰዱ እፈራለሁ። 

No comments:

Post a Comment