Thursday, March 7, 2013

የእስክንድርያ ትምህርት ቤት (ክፍል አምስት )

 የእስንድርያ ነገረ መለኮት ባህርያት (ካለፈው የቀጠለ። )


ክርስቶስ ሁሉ በሁሉ የሆነበት አሐዳዊ ሕይወት ( ONENESS OF LIFE) 


የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ለእኛ ያስተላለፉልን ዋና ነገር ቢኖር በአንዱ በክርስቶስ ያለውን ሕይወት ነው። ርዕሰ መምህሩም ሆነ ተማሪዎቹ የሃይማኖት፥ የፍልስፍናና እና የሳይንስ ጥናታቸውን ከቤተ ክርስቲያናቸው ሕይወት ወይም ከየዕለቱ ኑሮአቸው ነጥለው አያዩትም ነበር። በአንዱ በክርስቶስ ሕይወትነት ያምኑ ነበር። ይህም በጥናታቸው፥ በአምልኮአቸው፥ በአኗኗራቸው፥ በስብከታቸውና በምስክርነታቸው የተገለጠ ነበር።

አርጌንስ ስለ ክርስትና ሕይወት የነበረውን እይታ ሮውን ኤ ግሪር ጠቅለል አድርጎ ሲያቀርበው « የክርስቲያን ሕይወት የመለኮታዊ አስተርእዮ divine revelation) ምላሽ ነው። እግዚአብሔርን በማወቅ እንጀምርና ከእርሱ ጋር ያለንን ኅብረት ፍጹም ወደሚያደርገው ፊት ለፊት ወደሚሆን ራዕይ እንሻገራለን። የዚህ (እግዚአብሔርን የማወቅ) ሕይወት ገጽታዎችም  ሥነ ምግባራዊ፥ ዕውቀታዊ፥ መንፈሳዊ ሲሆኑ   እኛንም በቤተ ክርስቲያን ሕይወታችንና በዓለም ውስጥ በሚኖረን ተግባራችን ውስጥ እንድንሠማራ የሚያደርጉ ናቸው። 

መላ ዘመኑን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በመመስከር የኖረው ቅዱስ አትናቴዎስ፥ ከነባራዊው ዓለም የተለየና በአመክንዮአዊ ክርክር ላይ ያተኮረ ክርስቲያናዊ ፈላስፋ ወይም ዝም ብሎ የዶግማ ቴዎሎጂያን አልነበረም። ዋና የመከራከሪያ ነጥቡ አበ ነፍሳዊ ( pastoral ) ነበር። የእርሱ ዋና ምኞት የሰዎችን መዳን ማቅረብ ነበር። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና የክርስትና ሕይወት ምን ዓይነት የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው አሳየ ። እንዲህም በማለት አስተማረ፥ 
 « እምነትና እግዚአብሔርን መምሰል እርስ በእርሳቸው የሚተባበሩ እኅትማማቾች ናቸው። በእርሱ የሚያምን እርሱን በመምሰል የሚኖር ነው። እርሱን በመምሰል ሕይወት የሚኖር ደግሞ በእምነቱ የበረታ ነው።» አርዮስን በተከራከረባቸው ጦማሮቹ ሁሉ ያሳየው ነገር ቢኖር በተሰቀለው የእግዚአብሔር ልጅ፥ የእኛ ባሕርይ መቀደሱን፥ መታደሱንና ዳግም መወለዱን ነው። ይህን ሲያመለከት እንዲህ ብሎአል። « 
 እርሱ ራሱን ስለእኛ ከቀደሰ (ዮሐ 17፥18፡19) እና ይህንንም ያደረገው ሰው ሆኖ ከሆነ፥ እንግዲያውስ በዮርዳኖስ በእርሱ ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ በእኛም ላይ እንደወረደ ግልጽ ነው። የእኛን ሥጋ ገንዘብ አድርጎአልና። እርሱ በተጠመቀ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ እንደተቀባ ከተነገረለት፥ እርሱ ሲጠመቅ በእርሱ እኛም ስለተጠመቅን፥ በእርሱ የተቀባነውም እኛ ነን። » 


የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን እና ተማሪዎች አብዛኛዎቹ የድንግልና ሕይወትንም የሚመሩ መላ ሕይወታቸውን ለክርስቶስ የሰጡ ናቸው። እንደምሑራን ብቻ ሳይሆን እንደእውነተኛ መንፈሳውያን፥ ገዳማውያንና ሰባክያን የሚኖሩ ነበሩ። ሕይወታቸውን ለመስጠትና ስለ ክርቶስ የመመስከርና እርሱን የማገልገል ኃላፊነታቸውን ሳይረሱ የእግዚአብሔር ቃል በማጥናት ስለእግዚአብሔር ለማሰላሰል በጣም ይጓጉ ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ሕይወቱን የሰጠው አርጌንስ ብዙ አሕዛብን በትምህርቱ በመሳብ ወደ ክርስትና እንዲገቡ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የገቡት ኋላ በሰማዕትነት ማለፋቸው እንግዲያውስ  አለምክንያት አይደለም። ይህ ክርስቶስ ሁሉ በሁሉ የሆነበት ሕይወት ብዙዎች የትምህርት ቤቱ ርዕሳነ መምህራን ፓትርያርክ ሆነው በመመረጥ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ እንዲመሩ አስችሎአቸዋል። 1 comment:

  1. ሰላም ለከ ቀሲስ በጣም ጥሩ ጅምር ነው ይግፉበት፤ ከእናንተ ብዙ ይጠበቃል፤ ይዘቱን ወድጄዋለሁ

    ኢየሱስ ሞኦ
    ከአትላንታ

    ReplyDelete