Wednesday, May 24, 2017

ውሉ የጠፋበት የበዓላት አከባበራችን፤እንደ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ትምህርትና እንደ እግዚአብሔር ቃል ከሆነ፥ የዛሬውን ቀን ክርስቲያን የተባለ በሙሉ በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ዕልልታ ሊያከብረው ይገባ ነበር። የጌታ ዕርገት ከዘጠኙ ዓበይት የጌታ በዓላት አንዱ ነውና። የጌታ በዓል ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ( ለምሳሌ ፌስ ቡክ ) መመዘኛ ከሆኑን ግን፥ ለበዓለ ዕርገት የአንዱ ቅዱስ የወር በዓል የሚሰጠውን ያህል ትኩረት አልሰጠነውም። የጥንቱ የቤተ ክርስቲያን የበዓል አከባበር፥ አሁን እንደምናየው በወረት ከፍና ዝቅ የሚል አልነበረም። ለምሳሌ በዓለ ሐዋርያት በታላቅ ክብር ነበር የሚታሰበው፤ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን ስንመለከት፥ የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በዓላት የሚውሉበት፥ በጥንቃቄ ተጽፎ እናገኛለን። ሕዝቡ በታላቅ ክብር ያከብረው ነበር፥ የግዝት በዓልም ነበር ። ዛሬ ስንቶቻችን በዓለ ታዴዎስን፥ ወይም በዓለ እንድርያስን እናስታውሳለን? ቀድሞ ነገር አስራ ሁለቱን ሐዋርያት በስም የምናውቅ ስንቶቻችን ነን። 

በዓላት አስፈላጊ ናቸው። በበዓላት ውስጥ ታሪካው ክስተቶችን ብቻ ሳይሆን በዚህ ዘመን ለእኛ ያላቸውን መልእክትም እናስተውልበታለን። በዕርገቱ፥ የወደቀው የሰው ልጅ ምን ያህል ክብር እንዳገኘ አስተውለናል። በተዋህዶ ነውና ያረገው።  በዕርገቱ፥ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በገዛ ደሙ በእጅ ወዳልተሠራች ወደ ሰማያዊት ድንኳን እንደገባ፥ዛሬ በአባቱ ዘንድ ስለ እኛ እንደሚታይልን እናስተውላለን። በዕርገቱ፥ ሞትንና መውጊያውን ድል ያደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ፥ አሁን በክብሩ እንዳለ፥ እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስና ንጉሥ እንደሆነ እናስተውላለን። በዕርገቱ ሰማይንና ምድርን ጠቅልሎአልና። በዕርገቱ፥ እነዚያ መላእክት እንደነገሩን፥ዳግመኛ የመምጣቱ ነገር እርግጠኛ ሆኖአል። « ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል» ተብለናል። ( ሐዋ ፩፥፲፩) በዚህም ምክንያት በኦርቶዶክስ የቅዱሳት ሥዕላት አሳሳል ( አይክኖግራፊ) የጌታ እርገትና ምጽአት አንድ ዓይነት ናቸው። 

በዓላትን እንዴት እናክብር? 
አባቶቻችን በዓለ ሰማዕታትን፥ በዓለ ቅዱሳንን፥ በዓለ ሐዋርያትን ሲያከብሩ፥ ቅዱሳኑ የሰበኩትንና የተሰየፉለት የክርስቶስ ክብር እንዳይጋረድ እንዳይሸፈን ተጠንቅቀው ነበር። አሁን ከዛሬ ጀምሮ ዘመነ ክረምት እስከሚገባበት ድረስ የሚነገረው የዕርገቱና የርደተ መንፈስ ቅዱስ ነው። ለምሳሌ በዚህ ሰሞን ከሚከበሩት በዓላት በብዙዎች ዘንድ ታዋቂ የሆነውን በዓለ ሚካኤልን እንውሰድ፤ ቀኑ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል የሚታሰብበት ቢሆንም አባቶቻችን በዚያ ቀን የሚያዜሙት የሚሰብኩት፥ ስለ ክርስቶስ እርገት ነው። ለምን? ምክንያቱም ቅዱስ ሚካኤል የሚያመልከው የሚሰግድለት፥ መላእክት ሁሉ የሚሰግዱለትና የሚቀኙለት ጌታ ስለ ሆነ፥ የክርስቶስ ክብር ቅድሚያ ይሰጠዋል። ለሁላችንም ታላቅ ትምህርት ይሆነን ዘንድ የሰኔ ሚካኤል የሚባለውን ቀለም ( ዜማ) እንመልከት፤ 

ዋዜማ ዘሰኔ ሚካኤል 
ሃሌ ሉያ፥ አርኅዉ ኆኃተ መኳንንት፥ ወይባዕ ንጉሠ ስብሐት ወረደ ህየ አምላክ ምስለ ኃይል ወሰበረ ኆኃተ ብርት ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘሐጺን፤ ነአምን ሕማሞ ለዘኢየሐምም ተገምረ ዘኢይትገመር፤ ኃጢአተነ ነሥአ፥ ዘአልቦ ኃጢአት፤ ዓርገ ወልድ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ 

በአማርኛ፤ 
ሃሌ ሉያ፥ መኳንንቶች ሆይ በሮችን ክፈቱ፤ የክብር ንጉሥ ይግባ፤ አምላክ በኃይል ወደዚህ ወርዶአልና፤የናስ ደጆችን ሰብሮአል፤ የብረት ሠንሰለቶችን ቆርጦአል [ ቀጥቅጦአል] የማይታመመው እንደታመመ፥ የማይወሰነው እንደተወሰነ እናምናለን። ኃጢአት የሌለበት ኃጢአታችንን ወስዶአል። ወልድ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። 

እግዚአብሔር ነግሠ ዘሰኔ ሚካኤል 
ዓርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤ ኵሎሙ መላእክቲሁ ትንሣኤሁ ሰበኩ ወዜነዉ እርገቶ ውስተ ሰማያት፤ 

በአማርኛ፤ 
እግዚአብሔር በዕልልታ ዐረገ፤ ጌታችን በቀንደ መለከት፤ መላእክቱ ሁሉ ትንሣኤውን ሰበኩ፤ ወደ ሰማይ ማረጉንም አወጁ። 

ይትባረክ ዘሰኔ ሚካኤል 
ክብሮሙ ለመላእክት ከመ መንኰራኰር ወረደ መልአከ እግዚአብሔር፤ ኀበ መቃብር ወአንኰርኰራ ለይእቲ ዕብን ወነበረ ዲቤሃ ዓቢይ መልአክ ስቡህ እምግርማሁ ተሀውኩ እለ የአቅቡ መቃብረ ተንሥአ ወልድ በሣልስት ዕለት ወዓርገ ውስተ ሰማያት፤ 

በአማርኛ
የመላእክት አለቃቸው የሆነው የእግዚአብሔር መልአክ፥ እንደ መንኰራኰር ወደ [ ጌታችን] መቃብር ወረደ፤ ያችንም ድንጋይ ገልብጦ ታላቁና ክቡሩ መልአክ ተቀመጠባት። ከግርማው የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁት ታወኩ፤ ወልድ በሦስተኛው ቀን ተነሣ ወደሰማይም አረገ፤ 

ዋዜማ ሰላም ዘሰኔ ሚካኤል  
ምሉዓ ሞገስ ፍጹመ ጸጋ ወጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ዘሐመ ወሞተ በእንተ ፍቅረ ሰብእ ወተንሥአ በሣልስት ዕለት። ወዓርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ ወተቀበልዎ መላእክት ወኵሎሙ ሊቃነ መላእክት ሚካኤል ወገብርኤል ሱራፌል ወኪሩቤል ይሴብሕዎ እንዘ ይብሉ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ለዘሠምሮ ለሰብእ፤ 

በአማርኛ 
ፍጹም በሆነ ጸጋና እውነት በሞገስ የተመላ፥ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ፍቅር ታመመ ሞተ በሦስተኛው ቀን ተነሣ። ወደ ሰማያትም አረገ፤ መላእክትና ሊቃነ መላእክት ሁሉ፥ ሚካኤልና ገብርኤል፥ ሱራፌልና ኪሩቤል እያመሰገኑት እንዲህ እያሉ ተቀበሉት፤ ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት፥ ሰላምም በምድር፥ ለሰው በጎ ፈቃድ። 


ምልጣን ዘሰኔ ሚካኤል 

አመ ይሰቅልዎ አይሁድ ለእግዚእነ፤ 
ሚካኤል አርመመ ወገብርኤል ተደመ፤ 
ጸሐይ ጸልመ፤ ወወርኅ ደመ ኮነ፤
ወሪዶ እመስቀሉ አብርሃ ለኩሉ፤ 

አማርኛ 
ጌታን አይሁድ በሰቀሉት ጊዜ፤ 
ሚካኤል ዝም አለ፥ ገብርኤል ተደነቀ፤ 
ጸሐይ ጨለመ፤ ጨረቃም ደም ሆነ፤ 
[ክርስቶስ] ከመስቀሉ ወርዶ፥ ለሁሉ አበራ፤ 

ይህን ሁሉ ያሳየነው፥ ኦርቶዶክሳውያን አበው፥ ክርስቶስን ለማሳየት ምን ያህል መጨነቃቸውንና መጠንቀቃቸውን ነው የምናየው፤ ዛሬ በዘመናችን ብዙ ነገር ተዘዋውሮአል። ይህም የሆነው ከትምህርት ጉድለት ነው፤ የመንደር ወሬ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተደርጎ ሲሰበክ፥ ቀዋሚው የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቦታ ያጣል። ለዚህ ነው ነገሮችን በጥንቃቄ ማድረግ ያለብን። 


ቀደምት ከሆኑት የአገራችን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አንደኛው፥ የአንድ ቅዱስ በዓል ለማክበር ወደ አንድ ስፍራ ሲሄዱ ቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ በሕዝብ ተጨናንቆ፥ ኮረብታው ሁሉ በሕዝብ ተሸፍኖ ይመለከታሉ። ተደንቀው በዓሉን አክብረው ይመለሳሉ። ከሁለት ወር በኋላ ሥላሴን ለማክበር እዚያው አካባቢ ወዳለ ታላቅና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ቢሄዱ፥ እፍኝ የማይሞላ ሰው ያገኛሉ፤ ተገረሙና « ፍጡርንና ፈጣሪን የማትለይ አይ አንተ ሕዝብ» አሉ ይባላል እያሉ ብዙዎች ተርከውልኛል። ይህ ተከናወነ የተባለው ከአርባ ዓመት በፊት ነው። ( ሊቀ ጳጳሱ የነበሩት በሃምሳዎቹ እና በስልሳዎቹ ነው፤) ጥያቄው ግን ዛሬስ ይህን ቀይረነዋል ወይ?  ዛሬ አብያተ ክርስቲያናት ሲታነጹ የሚሰየሙት በምንድነው? ሕዝባችንስ የሚነጉደው ወደየት ነው? የጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን? በሻማ ተፈልጎ የሚገኘው፥ የቅዱስ እንድርያስ ቤተ ክርስቲያን የማይገኘው፥ የቅዱስ ቶማስ የሌለው ለምንድነው?  መልሱን ለቤተ ክርስቲያን ይገደኛል የምንል በጥልቀት ልናስብበት ይገባል። 

1 comment:

  1. ጥሩ መልዕክት ነው። እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን

    ReplyDelete

ጸሎት

የአባቶቼ አምላክ፥ አምላከ ቅዱሳን አምላከ አበው ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ከፍ ካሉት ሁሉ በላይ ከፍ ያልህ ነህ፤ ሥራህ ከአእምሮ በላይ ነው። ኃይል ከመነገር በላይ ነው። ኃጢአተኛ እና በደለኛ የሆንኩትን እኔን ልጅ...