Saturday, May 13, 2017

መናፍቅነት ምንድነው፤ የውግዘት ፖለቲካና የቤተ ክርስቲያናችን እጣ ፋንታ ( ክፍል ሁለት)

መናፍቅነት ምንድነው? 

በዚህ ዘመን በዘፈቀደ በየጋዜጣውና በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚዘራ ቃል ቢኖር መናፍቅ የሚለው ቃል ነው። በክፍል አንድ ትምህርታችን ስለውግዝት ምንነት ተመልክተናል። ስለ ውግዝት በዚህ ዘመን ሲነሣ አብሮ ጎን ለጎን የሚነሣው « እገሌ መናፍቅ ስለ ሆነ ተወገዘ» የሚለው አዋጅ ነው። በመሆኑም አንድን ሰው የሚያስወግዘው ምንድነው የሚለውን በሰፊው ከመመልከታችን በፊት ፥ ስለ መናፍቅነት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረንና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥም ይህ ቃል በምን መንገድ ጥቅም ላይ እንደዋለ መመልከት ይኖርብናል። ልክ እንደውግዘቱ የዚህን ቃል ትርጉም ከተረዳን ለሚረባውም ለማይረባውም ትልቁንም ትንሹንም መናፍቅ ብሎ ከመናገር እንቆጠባለን። 

መናፍቅነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ

መናፍቅነት ወይም ኑፋቄ በግሪኩ « ሔረሲስ» ይለዋል። ቃሉ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ልዩ ልዩ ትርጉሞች ተሰጥቶት እናገኛለን። ለምሳሌ በሐዋ ፭፥፲፯ ላይ፥  ሔረሲስ የሚለው ቃል ቡድን፥ ወገን  ተብሎ ተተርጉሞአል።  « ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ( ሔረሲስ) ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ ቅንዓትም  ሞላባቸው።» ይላል። በሐዋ ፲፭፥፭፤፳፮፥፭ ላይ በተመሣሣይ መንገድ ቃሉ  « ወገን» ተብሎ ተተርጕሞአል።  በ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፲፱ ላይ ደግሞ ወገን ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም የተቃራኒ ቡድንን  ( faction)፥ ወይም የተፎካካሪ ፓርቲን የሚያመለክት ነው። ይህም መለያየትን መከፋፈልን የሚያመለክት ነው። ይህ መከፋፈል ደግሞ የሚመጣው፥ እምነትን ከፍሎ ገምሶ በማመን በመጠራጠር ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ ቃሉ ከክርስቶስና ከሐዋርያቱ ትምህርት ውጭ የሆነውን ወይም ጎዶሎ የሆነውን ትምህርት ኑፋቄ ተብሎ ይጠራል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ ሲናገር «ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤» ይላል ( ፪ ጴጥ ፪፥፩)። በዚህ የሐዋርያው ቃል መሠረት እነዚህ በኑፋቄ ውስጥ የገቡ ሰዎች የዋጃቸውን ጌታ የካዱና ፈጣን በሆነ መንገድ ጥፋትን በራሳቸው ላይ የሚስቡ ናቸው። 

እነዚህን የቃሉን መሠረታዊ ትርጕሞች ስንመለከት « መናፍቅነት» ወይም « ኑፋቄ» በሁለት ወገን አደገኛነቱ ይገለጣል። አንደኛው፥ መናፍቅነት ማለት የክርስቶስን ጌትነትና፥ የእርሱን ቤዛነት መካድ ስለሆነ፥ መሠረታዊ ከሆነው የክርስትና እውነት የሚያርቅ ነው። ሌላው ደግሞ፥ መናፍቅነት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚንድ ነው። ቤተ ክርስቲያንን አንድ የሚያደርጋት ራሷ የሆነው ክርስቶስ ነው። ኑፋቄ ደግሞ ያን ስለሚክድ በምእመናን መካከል መለያየትና መከፋፈል ሾልኮ እንዲገባ፥ አንድነት እንዲዳከም ያደርጋል።  

ከዚህ የተነሣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላ፭፥፲፱-፳፩  ላይ የሥጋ ሥራዎች ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል መናፍቅነት አንደኛው ነው። «የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው።» በሐዋርያትም ዘመን ሆነ አሁንም መናፍቅነት ክርስቲያኖች ሊጠነቀቁአቸው ከሚገቡአቸው ኃጢአቶች መካከል እጅግ አስፈሪው ነው። ምክንያቱን ሐዋርያው ሲገልጥ «አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።» ይላል ገላ ፭፥፳፩። ይህ ማለት መናፍቅነት ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት እንዳይኖረን ከሚያደርጉን ምድራዊና ሥጋዊ ባሕርያት መካከል አንዱ ነው።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተነሡ መናፍቃን እና አካሄዳቸው 

ቤተ ክርስቲያን በመንገድ ላይ የተገኘውን ሁሉ መናፍቅ ስትል አልተገኘችም። አንድን ትምህርት ወይም አሳብ ኑፋቄ ብላ የምትናገረው የመልእክቷን ዋና ማዕከል የሚነካ ሲሆን ነው። ከላይ ያተትነውን፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ቃሉ ያለውን ፍቺ በጥቃቄ ስንመለከት፥ እንዲሁም  በመጀመሪያዎቹ አራት ክፍለ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን የተጓዘችውን ጉዞ ስናጠና የምንደርስበት ድምዳሜ፥ አብዛኛዎቹ ኑፋቄዎች የሚያጠነጥኑት በእግዚአብሔር ልጅ ሰው መሆን ላይ ነው። እስከ ዛሬ የተነሡትን ኑፋቄዎች ጠቅልለን እናስቀምጥ ብንል፥ በሦስት ተርታ የሚቀመጡ ናቸው። ገሚሶቹ አምላክነቱን ( ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን አንድነት) የሚክዱ ናቸው፤ ገሚሶቹ ሰውነቱን የሚክዱ ናቸው። ገሚሶቹ በአምላክነቱና በሰውነቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ( ተዋህዶን) የሚክዱ ናቸው። በሚቀጥሉት ክፍሎች ውስጥ እነዚህን በዝርዝር እንመለከታለን። 

2.1 አምላክነቱን የሚክዱ፦  ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ካጋጠሟት መናፍቃን መካከል ዋናዎቹ የክርስቶስን አምላክነት የሚክዱ ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ትምህርታቸው በተለያየ መንገድ ይለያይ እንጂ በዋናነት በሥጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ፥ የባሕርይ አምላክ እንዳይደለ፥ ይልቁንም እሩቅ ብእሲ ( ሰው ብቻ) እንደሆነ የሚያስተምሩ ናቸው ከእነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹን እንመለከታለን። 

ኢቦናይቲዝም ( Ebionitism) 

እነዚህ ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የገቡ ቀደምት ክርስቲያኖች የነበሩ ሲሆን፥ ይሁዲነትነት በማጥበቅ፥ ( ግዝረትና ሌሎች የኦሪት ሕጎች መጠበቅ አለባቸው በማለት)፥ እንዲሁም በድህነትና በተባህትዎ በመኖር የሚታወቁ ናቸው። ከናዝራውያን ጋርም በብዙ የሚያመሳስላቸው አለ። ስማቸውንም ያገኙት በድህነት መኖርን ዋና መመዘኛ በማድረጋቸው ነው። የሐዋርያት ተከታያቸው የሆነውና በ2ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ቅዱስ ሄሬኔዎስ ስለ ኢቦናይት ሲናገር እንዲህ ይላል። « ኢቦናይት የሚባሉት  ዓለም በእግዚአብሔር እንደተፈጠረ ያስተምራሉ፤ ስለ ጌታ ግን ያላቸው አመለካከት ልክ እንደ ሴሪንተስ እና ካርፖክራተስ ነው። እነዚህ የሚቀበሉት ወንጌል የማቴዎስን ሲሆን፥ ቅዱስ ጳውሎስን ከሕግ ፈቀቅ ያለ ስሑት ብለው አይቀበሉትም ነበር።» በማለት ጽፎአል። ( በእንተ መናፍቃን 1፡26፡2)  በሌላም ሥፍራ ላይም ስለእነዚሁ መናፍቃን ሲናገር፥ የማቴዎስን ወንጌል ብቻ የሚቀበሉ ስለነበሩ ስለ ክርስቶስ የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው። ስለዚህ ሲናገር ቅዱስ ሄሬኔዎስ እንዲህ ይላል። « እግዚአብሔር ሰው ሆነ ጌታ ራሱ አዳነን፤ ምልክት ይሆነን ዘንድም ድንግልን ምልክት አድርጎ ሰጠን።» ይልና ኢቦናይትና አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱስን እንተረጉማለን የሚሉ ኢሳ ፯፥፲፬ ላይ « እነሆ ድንግል ትጸንሳለች» የሚለውን « እነሆ ሴት ትጸንሳለች» በማለት፥ እንደሚያነቡ፥ ይህን ተከትለው ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ   እንደሆነ እንደሚያስተምሩ ይነግረናል። ( 3፡21፡1) 

ተርቱልያን ( ጠርጡልያን) የተባለውና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የላቲን የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊ  የክርስቶስን ሥጋዌ ባተተበት ክፍል ውስጥ « ከመላእክት ጥቂት አሳነስከው»  የሚለውን ሲተረጉም ኢቦናይት « ኢየሱስ ሰው ብቻ እንደሆነ፥ ከዳዊት ዘር ከመሆኑ በቀር ሌላ ምንም እንደሌለው፥ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን እርሱን የእግዚአብሔር ልጅ እንዳይደለ፥ » ይናገሩ እንደነበረና፥ መልአክ አድሮበታል ብለው ያስተምሩ እንደነበረ ጽፎአል።  ( ተርቱልያን በእንተ ሥጋዌ 14 )  ከእነዚህ ቀደምት ጸሐፊዎች በተጨማሪ፥ አርጌንስ፥ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ፥ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘደሴተ ቆጵሮስ ( ሰላሚስ) እና ጀሮም ( ኢያሮኒሙስ) ስለእነዚህ መናፍቃን ጽፈዋል። 

በቅዱስ ሄሬኔዎስ ምስክርነት እንደተመለከትነው፥ ቤተ ክርስቲያን ይህን የኢቦናይትን ኑፋቄ የተከላከለችው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው የክርስቶስን ፍጹም ሰውነትና ፍጹም አምላክነት አምልቶና አስፍቶ በማስተማር ነው። ሁለተኛ የሐዋርያትን ትምህርት እና በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉትን ጠብቆ በማቆየት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው የእነዚህን ክህደት ለመገደብ ነው። ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደሚስማሙበት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የቆላስይስ መልእክትን የጻፈው፥ ይህን መሰሉን  « የቆላስይስ ኑፋቄ» በመባል የሚታወቀውን ለመቃወም ነው። 

No comments:

Post a Comment

ጸሎት

የአባቶቼ አምላክ፥ አምላከ ቅዱሳን አምላከ አበው ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ከፍ ካሉት ሁሉ በላይ ከፍ ያልህ ነህ፤ ሥራህ ከአእምሮ በላይ ነው። ኃይል ከመነገር በላይ ነው። ኃጢአተኛ እና በደለኛ የሆንኩትን እኔን ልጅ...