Friday, September 12, 2014

ማንነቱን ያወቀ ክርስቲያን


የሰዎችን ይሁኝታ ለማግኘት የምንጥረው እግዚአብሔር የሰጠንን ማንነት ስላላወቅነው ወይም ለመቀበል ስላቃተን ነው። በመሆኑም ከውስጣችን ያጣነውን ከሰዎች ለማግኘት እንጥራለን። ከሁሉ የሚያዛዝነው ግን እንዲያ ጥረን ግረን ያገኘነው ነገር ለእኛ እርካታ አለመስጠቱ ነው። ምክንያቱም ያ ከሰዎች ያገኘነው  ማንነት፥ ሰዎች ስለ እኛነታችን የደረደሩት ቃላት ሁሉ ማንነታችንን ይሸፍነዋል እንጂ እንድናገኘው አያደርግም። ይህ ደግሞ እንደገና የሰዎችን ይሁኝታ ለማግኘት እንድንራብ ያደርገናል። እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ደግሞ ያደክማል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ባስተላለፈው መልእክቱ በምዕራፍ አንድ ላይ አጠንክሮ እንዳስቀመጠው በዓለም ላይ ክርስቶስን ለብሰን በድል አድራጊነት መመላለስ የምንችለው ሥፍራችንን ስናውቅ ነው። እግዚአብሔር አብ ዓለም ሳይፈጠር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ያዘጋጀልንን ሰማያዊ በረከት። በሰማያዊ ሥፍራ ተቀምጣችኋል፤ በሰማያዊ በረከት ተባርካችኋል ይለናል። ጠላት ዲያብሎስን የሚያስፈራው ማንነቱን ያወቀ ክርስቲያን ነው። . . . 

Thursday, September 11, 2014

እግዚአብሔርን በታመንኩበት መጠን

እግዚአብሔርን በታመንኩበት መጠን የሕይወት መሰናክሎቼን የምጋፈጥበት ኃይል ይኖረኛል። መዝሙረኛው በእግዚአብሔር የሚታመኑ ለዘለዓለም እንደማይናወጡ እንደጽዮን ተራራዎች ናቸው እንዳለ፥ በእርሱ መታመን ያለብን ሁሉ ሲያልቅብን ሳይሆን ሁሉንም ትተን ነው። ሁሉን የምናገኘው በእርሱ ስለሆነ።#አዲስዓመት

የሰዎች ይሁኝታ

የሰዎች ይሁኝታና ጭብጨባ የሕይወቴ ጉልበት ከሆነ ብርቱ ለመሆን ብዙ መልፋት አለብኝ። ሁሉን ለማስደሰት ስለማልችል ግን ልፋቴ ከንቱ ይሆናል። ነገር ግን ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ወይም የተሰኘበትን ለመኖር ብጥር ሕይወቴንና የሕይወቴን ትርጉም በዚያ አገኛለሁ።#አዲስዓመት

Wednesday, September 10, 2014

ክሮኖስና ካይሮስ

ጥንታውያን ግሪኮች ለጊዜ ሁለት ስም ነበራቸው። ክሮኖስ እና ካይሮስ ። ክሮኖስ አንድ ሁለት ብለን በሰከንድ፥ በደቂቃ፥ በሰዓት፥ በቀን፥ በወርና በዓመት የምንቆጥረውን ጊዜ ያመለክታል።ክሮኖሎጂ የሚለው ቃል ከዚህ የተገኘ ነው። ካይሮስ ደግሞ በእነዚያ ጊዜያት ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች ( ደስታም ይሁን ሐዘን) የተከሰቱበትን ወቅት ያመለክታል። ክሮኖስ ላይ ብቻ ካተኮርን ጊዜን ቆጥረን እንጨርሰዋለን። ሌላ ቀን ሌላ ወር ሌላ ዓመት ሲተካ ያው መቁጠራችንን እንቀጥላለን፤ ካይሮስ ላይ ካተኮርን ግን እግዚአብሔር የሰጠንን እያንዳንዱን ወቅት ወይም ቅጽበት በጥንቃቄ እናየዋለን። « በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ» ብሎ እግዚአብሔር የተናገረን፥ እግዚአብሔር ወደ እኛ ስለቀረበበት ወቅት ነው። ባሳለፈፍነው ዓመት ክሮኖስን ቆጥረን ጨርሰናል። ካይሮስን አይተነዋልን? አሰላስለነዋል? ተምረንበታል? ንስሐ ገብተንበታል። ያዘናችሁበትም ሆነ የተደሰታችሁበት ወቅት በአስተዋይ ዓይን ከተመረመረ የዕድገታችሁ ጊዜ ይሆናልና። በዚህ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ላይ ካሌንደር ( ክሮኖስ) ቆጣሪዎች ብቻ ሳንሆን የተሰጠንን ዕድል ( ካይሮስ) ነዋሪዎች እንድንሆን በጊዜ ባለቤት ፊት ቃል እንግባ። ብዙ ጊዜ የችግራችንን ወቅት የምሬት ወቅት እናደርገዋለን። የችግር ወቅት እንኳ ሳይቀር የበረከት ወቅት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከምንም ጊዜ በላይ ወደ እኛ የሚቀርብበት ጊዜ ነው። ዘመንን ዋጁት ያለንም ይህን ነው። ካይሮስን ማስተዋል። እግዚአብሔር ወደ እኛ የቀረበበትን ወቅት።