Friday, June 28, 2013

ጸሎተ ስምዖን ዓምዳዊ (ክፍል 13)

ምዕራፍ፴፱። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ለጠፋው በግ ያዘንክለት፥ በትከሻህ ላይ የተሸከምከው፤ ወደ በጎችህ ማደሪያ ያገባኸው እኔንም ከበጎችህ ቍጥር አንድ አድርገኝ፤ ቃልህን ከሚሰሙ፥ ትምህርትህንም በሥራ ከሚገልጡትና በማኅተምህ ከታተሙት ጋር አንድ አድርገኝ፤

ምዕራፍ፵። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ በፍጹም ልቤና በኅሊናዬ እከተልህ ዘንድ ፈቃድህን ከሚያደርጉ ጋር አንድ አድርገኝ፤ አንተ የሕይወት በር ነህና፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሕይወት ሰጪ ወደሆነች አደባባይህ እገባ ዘንድ በርህን ክፈትልኝ።

ምዕራፍ፵፩። ቸር እረኛ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ርኅራኄህ በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔን ባሪያህን በምሕረትህ ፈውሰኝ፤ እኔ በወንበዴዎች መካከል የወደቅኹ፤ ያቆሰሉኝና ጥላቻን የጨመሩብኝ ነኝ፤ ቸር እረኛ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ቍስሎቼን ፈውስ፥ በእኔም ላይ ከወይኑ፥ ከዘይቱና ከቅቡ አፍስስብኝ፤ በምሕረትህ ተሸከመኝ፤ አንጻኝ፥ ሕይወት ሰጪ ወደሆነችው ማደሪያህ አግባኝ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ተኩላዎች አቆሰሉኝ፤ በጥርሳቸውም ነከሱኝ፤ አንተ ግን በምሕረትህ ከእነርሱ አድነኝ። አንተ ቸር እረኛ ነህና። አሜን (ይቀጥላል።  

Tuesday, June 25, 2013

ማንዴላና ኢትዮጵያ

በዚህ ሰሞን በመላው ዓለም ዜና የሆነው የፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ ( ማዲባ) በጠና መታመም ነው። የ95 ዓመት እድሜ ባለጸጋ አባት እንደመሆናቸው ብዙ የሚያስደንቅ ባይሆንም ለአፍሪካ ግን ታላቅ አባት የማጣት ነገር ስለሆነ ለአፍሪካ ወደ እግዚአብሔር ልንጸልይ ሌላ ማንዴላን እንዲያስነሳ ልንለምነው ይገባል። በዚሁ ግን የማንዴላ ነገር ከተነሣ አገራችን የነበራትን የቀደመ ክብርና ለአፍሪካ ነጻነት ያደረገችውን ውለታም ትውልድ ሊረሳው አይገባም። የሰሞኑ የአፍሪካ አንድነት የሃምሳ ዓመት መታሰቢያ ያን በመጠኑም ቢሆን የዘነጋ ስለመሰለኝ ነው።

ባለፈው ዓመት ደቡብ አፍሪካ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያናችን ባደረገችልኝ ጥሪ ለአገልግሎት ወደ ጆሃንስበርግ ባደረግኹት ጉዞ፥ በዚያ ያሉት አባቶች ካስጎበኙኝ ቦታዎች አንዱ የአፓርታይድ ሙዚየም አንዱ ነበር። በዚያ በክብር ከተቀመጡት ሰነዶች አንዱ ፕሬዚደንት ማንዴላ ገና የኤኤንሲ የትጥቅ ትግልን ሲመሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጣቸው ፓስፖርት ነበር። ኢትዮጵያዊው ስማቸው ዳዊት ሲሆን ጋዜጠኛ እንደሆኑ የሚጠቅስ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ለታጋዩ ጀግና ሽጉጥ ሸልመዋቸው ነበር።


ታዲያ ማንዴላ፥ በእሥር ቤት ለረጅም ጊዜ ማቅቀው ከወጡ በኋላ እንኳ ይህን የኢትዮጵያን ውለታ አልረሱም ነበር። ብዙዎች እንደሚናገሩት ማንዴላ የኢትዮጵያ የነጻነት ታሪክ የራዕያቸው መሠረት ነበር። 
ለዚህም ነው ስለኢትዮጵያ ሲናገሩ «Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly  than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis. >» ብለው የተናገሩት። 
በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት የማያንቀላፋው ትጉሕ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር  ከታላቁ አፍሪካዊ አባት ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ይሁን። 

ጸሎተ ሃይማኖት (ሰባተኛ ክፍል)

Read with PDF
ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት። ተሰብአ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል።  

ስለእኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ፤ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ፤ 

መግቢያ 
ባለፈው ሳምንት « ስለ እኛ ስለሰዎች» የሚለውን ኃይለ ቃል በመያዝ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ በኃጢአት መውደቁ ያመጣውን ውጤት አይተን ነበር፤ እንደተመለከትነው ኃጢአት ወደ ዓለም በገባበት ወቅት 
• ሰው ከእግዚአብሔር ተለየ 
• ሰው በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ሆነ 
• ሰው በኃጢአት ባርነት ሥር ሆነ 
• ሰው ራሱን ማዳን የማይችል ሆነ ብለን ነበር። በመሆኑም የኒቅያ አባቶች « ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ» በማለት የእግዚአብሔር ልጅን በሥጋ የመገለጥ ዓላማ ግልጥ አድርገውልናል። ማለትም የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ የተገለጠው በኃጢአት የወደቀውን የሰው ዘርን ለማዳን ነው። 

ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት። 
ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ 

ሀ. የአምላክ ልጅ ለምን ሰው ሆነ? 

1. ሰው በራሱ ራሱን ለማዳን ስላልቻለ፤ 
በኃጢአት ለመውደቁ የሰው ልጅ ያዘጋጀው መፍትሔ ቅጠል መልበስና በገነት ዛፎች መካከል መሸሸግ  ነበር። (ዘፍጥረት 3፥8) ቀደም ሲል እንዳየነው የሰው ልጅ ይህን ያደረገው እግዚአብሔር ለእርሱ ጠላት የሆነበት ስለመሰለው ነበር፤ እውነታው ግን በእግዚአብሔር ላይ ጠላት የሆነውና ያመፀው ሰው ራሱ ነበር። ሰው ማንነቱን ያገኘበትን እግዚአብሔርን በጠላትነት መመልከቱ እግዚአብሔርን እንዲጠላ ከማድረጉ በላይ ራሱን እንዲጠላው አደረገው፤ ሐፍረት ከውድቀት በኋላ የመጣ ሲሆን ራስን የመጥላት ምልክት ነው። ራሱን ስለጠላም የእርሱ የሆነውን ሁሉ ጠላ፤ የሕይወቱን አጋር « ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት» በማለት ከሰሳት፤ የገዛ ልጆቹ አንዳቸው አንዳቸው ስለጠሉ ተጋደሉ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ጠላት የሆነ፥ ከማንም ጋር እርቅ ሊኖረው ወይም እውነተኛ ፍቅርን ሊያገኝ አይችልም፤ በመሆኑም ሰው ለራሱ መፍትሔ ያደረገው ራሱን የሚከላከልበት ነገር ሁሉ መጥፊያው ሆነ፤ ኢሳይያስ በትንቢቱ እንደነገረን ሰውን የሚያድን « ሰው እንደሌለ» ስላወቀ አምላክ ራሱ ክንዱና ቀኝ እጁ የሆነውን ልጁን ለእኛ መድኃኒት እንዲሆን ላከው። (ኢሳይያስ 59፥ 16) 

2. የሰዎች (የዕሩቅ ብእሲ) ደም ዓለምን ማዳን ስላልቻለ፤ 
የዕብራውያውን ጸሐፊ የአምላክን ልጅ ሰው መሆን በተናገረበት አንቀጹ ላይ « ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤» ብሎናል። ዕብራውያን 1፥1። ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ መንገድ ተናግሮአል። ነገር ግን ያ በነቢያትና በተለያየ መንገድ የመጣው መልእክት ዓለምን ለማዳን አልቻለም። ወይም በቅዳሴ መጽሐፋችን አባቶቻችን እንዳስቀመጡልን ጌታ በሥጋ የተገለጠው ከአቤል ደም ጀምሮ በእቃ ቤቱ መካከል እስከ ተገደለው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ የፈሰሰው ደም ዓለምን ማዳን ስላልቻለ ነው። ከአቤል ደም ጀምሮ በምድር ላይ የፈሰሰው የሰዎች ደም የሰዎችን ኃጢአት የሚገልጥና የሚከስ ደም ነው። ቃየን ወንድሙን አቤልን ከገደለ በኋላ እግዚአብሔር ቃየን  « የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።» ነበር ያለው። (ዘፍጥረት 4፥10) በመሆኑም የአቤል እና ከእርሱም በኋላ ደማቸው በምድር የፈሰሰ ሁሉ ደማቸው ወደ ሰማይ የሚጮህ ደም ነው። የአምላክ ልጅ ግን በሥጋ የተገለጠው በደሙ መፍሰስ ዓለምን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ነበር። ይህንን እንደገና የዕብራውያን ጸሐፊ ሲናገር « የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።» በማለት ገልጦታል። ዕብራውያን 12፥24። 

Monday, June 24, 2013

ጸሎተ ስምዖን ዓምዳዊ (ክፍል 12)

ምዕራፍ ፴፮፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ወደ ቃና ዘገሊላ ሠርግ የተጠራህ፤ ውኃውን ለውጠህ መልካም መዓዛ ያለው የሚያረካ ወይን ያደርግኸው፤ ኅቡእ የሆነው እይታህ፥ ወደእነዚያ የድንጋይ ጋኖች የወረደ፤ የውኃውን ጠባይ የቀየረ፥ ጣዕሙ መልካም የሆነ ወይን ያደረገው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ያ ኅቡእ የሆነው እይታህ ወደ ሕሊናዬ ውስጥ ይውረድ፤ ከንቱ ከሆነውና ከሚጠፋው ከዚህ ዓለም አሳብ ወደ አዲሱ ዓለም አሳብ ይለውጠው። ከእኔም ላይ አሮጌውን ሰው ይግፈፈው አዲሱን ሰው ያልብሰኝ።

ምዕራፍ ፴፯፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ አዲስ ምርጥ ዕቃ እንድሆን አድርገኝ፥ አዲሱንም ወይን በውስጤ ጨምር በምሕረትህም አድሰኝ።

ምዕራፍ ፴፰፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ዓለምን አዲስ ልታደርግ የመጣህ፥ ቅዱስ በሆነው ስምህ አድሰኝ፤ ኅሊናዬ ሆይ ተጓዝ፥ እንደ ለምጻሙ ሰው በመንገድ ቁም፤ እንዲፈውስህም [አዳኝህን] ጥራው፤ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ለምጻሙንና ሕመምተኛውን፥ ከለምጹና ከሕመሙ  የፈወስከው፥ ከኃጢአት ለምጽና ከቁስሉ ፈውሰኝ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ኃጢአቴ ከወዳጆችህ መካከል አሳደደችኝ፤ አንተ ግን በምሕረትህ መልሰኝ፤ ቁስልና ለምጽ ያለበትን ሰው ከከተማ እንዲያስወጡት ሙሴ አዘዘ፤ አንተ ግን በምሕረትህ ፈወስከው፥አስገባኸው፥ ተቀበልከው።ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ኃጢአቴ አሰደደችኝ፤ አንተ ግን በቸርነትህ ወደ አጸድህ መልሰኝ። 

ለዚህ ያደረሰንን አምላክ በኅብረት እናመስግነው።


The Wisdom of little Dorrit

O, Mrs Clennam, Mrs Clennam,' said Little Dorrit, 'angry feelings and unforgiving deeds are no comfort and no guide to you and me. My life has been passed in this poor prison, and my teaching has been very defective; but let me implore you to remember later and better days. Be guided only by the healer of the sick, the raiser of the dead, the friend of all who were afflicted and forlorn, the patient Master who shed tears of compassion for our infirmities. We cannot but be right if we put all the rest away, and do everything in remembrance of Him. There is no vengeance and no infliction of suffering in His life, I am sure. There can be no confusion in following Him, and seeking for no other footsteps, I am certain.

Charles Dickens, Little Dorrit 

Thursday, June 20, 2013

መንፈስ ቅዱስ


ይህ ስብከት ባለፈው ዓመት በድንግል ማርያም ካቴድራል በዓለ ሃምሳን ወይም በዓለ መንፈስ ቅዱስን ባከበርንበት ወቅት የተሰበከ ነው።  እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ  ወደ እውነት ሁሉ ይምራን። 

ራስ ከራስ ( ማሰላሰል)


ነፍሴ ሆይ በገናናው ዙፋኑ ፊት ራስሽን አዋርጂ፥ የታረደልሽ ጌታ ሕያውና በክብር ያረገ ነውና፤ በዚህ ዓለም ኹከትና ብጥብጥ ላይ ታች አትበይ፤ ኃጢአትሽን የተሸከመልሽ የቀራንዮው በግ በሰማይም በምድርም ጌታና አዳኝ ነውና ተስፋሽን በእርሱ ላይ አድርጊ፤ ታላቁ አባት ስምዖን አምዳዊ ይህን ጌታ እንዳመሰገነው አመስግኚው፥ አግንኚው አምልኪው፤

ነፍሴ ሆይ ውለታውን ተናግረሽ አልጨረሽም፤ እንኳን ውለታውን ተናግረሽ ለመጨረስ፥ የተደረገልሽን ገና ሙሉ በሙሉ አላስተዋልሽም፤ ገና በድንግዝግዝ ነሽ፤ ከዕውቀት ገና ከፍለሽ ነው ያወቅሽው፤ በዕውቀቱ እስክትሞይ ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ እስክትደርሺ፤ የጸጋው ሙላት እስክትዋኚ አክብሪው፥ አንግሽው፤

ነፍሴ ሆይ በዚህ ሰዓት በመላው ዓለም በብዙ ችግር ውስጥ ሆነው ለአምላካቸው ስም በጽንዓት የቆሙትን አስቢያቸው፤ በሦርያ ያሉትን ክርስቲያኖች፥ በኢራቅ ያሉትን ክርስቲያኖች፥ በግብጽ ያሉትን ክርስቲያኖች፥ መኖራቸው እንኳ ምስክር የሆነውን በሞታቸው ዋጋ የሚከፍሉትን አስቢያቸው፤ እናም ነፍሴ ሆይ ለአምላክሽ ዛሬ እንዴት ሆነሽ ዋልሽ፡ . . . .

ጸሎተ ስምዖን ዓምዳዊ (ክፍል 12

ምዕራፍ ፴፪፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ በገዳም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት የጾምክ፤ ከፈታኙ ዘንድ የተፈተንክ፥ ፈተናውንና ክፋቱን  ሁሉ ድል ያደረግህ፤ ከአንተ ዘንድ ረድኤትንና ድል ማድረግን ስጠኝ፤ ወደ መንፈሳዊ ተጋድሎና ምስክርነት ለተጓዘ ሰው፥ አንተ ከእርሱ ጋር ትሆናለህ፤ ድል አድራጊነትንም ትሰጠዋለህ።

ምዕራፍ፴፫፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ የጨለማ አለቃ የሆነው ዲያብሎስ የጻፋትን የኃጢአትን ሥርዓት ከሕሊናዬና ከልቤ ደምስስልኝ፤ ቅዱስና አምላካዊ የሆነውን የአንተን ሥርዓት በኅሊናዬ ውስጥ እንዲገባ በሰውነቴ ውስጥ ጻፈው፤ ከልቤ ጋር ከሚዋጋው ከክፉም አድነኝ።

ምዕራፍ፴፭፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ የክፉውን የዲያብሎስን ኃይል የሰበርክበትን ኃይህን ስጠኝ፤ አንተን ደስ አሰኝበት ዘንድ በጥበብህ አስተዋይ አድርገኝ። ስለ ቅዱስ ስምህ ስትል ይህን ኃይልህን እንዲያው በፀጋህ ስጠኝ። ኅሊናዬ ሆይ ለዓለማት ሕይወት ከሚሰጥ ጌታ ጋር ሁን፤ ለራስህ ሕይወትን ታገኝ ዘንድ ተከተለው። ከእርሱ ጋር ወደ ቃና ዘገሊላው ሠርግ ተሻገር። አሜን (ይቀጥላል።) 

የፖለቲካ ኑፋቄና የኑፋቄ ፖለቲካ (ክፍል አንድ)

ሰሞኑን በየአቅጣጫው የተለመደችው የፖለቲካ ኑፋቄ ከየአቅጣጫው ብቅ ብቅ ብላለች፤ የፖለቲካ ኑፋቄ ያልኩት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ወይም አንቀጸ ሃይማኖትን መነሻ ያላደረገ ከዚያ ይልቅ ፓለቲካ እንደኑፋቄና ኑፋቄ እንደ ፓለቲካ መሣሪያ የሚታይበትን ክስተት ለማተት ነው። ይህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሙሉ ሲታይ የኖረ ነገር ነው። የኒቅያ ጉባኤን ተከትሎ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የታየው ክስተት ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ትምህርት የሚሰጥ ቢሆንም፥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወነውን ላስተዋለ « ከታሪክ ያልተማረ እንዲደግመው ተፈርዶበታል» የሚለው ብሒል እየተፈጸመብን መሆኑን እንረዳለን። ለማንኛውም በወርቃማው የአባቶች ዘመን the Golden Patristic era ከነበሩት መካከል በሁለቱ ላይ የተከናወነውንና ቤተ ክርስቲያን ከዚያ ልትማር የሚገባውን እናያለን።

ቅዱስ አትናቴዎስ እና « ሦስተኛው እጅ»

የኒቅያ ጉባኤ የወልደ እግዚአብሔርን አምላክነት « ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፥ በመለኮቱ ከአብ የሚተካከል» የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጠቅልሎ የሚገልጠውን እውነት የወሰነ ታላቅ ኢኩሜኒካል ጉባኤ ነበር። የኛ አባቶች እንደሚሉት የኒቅያ አባቶች መንፈስ ቅዱስ እየመራቸው እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው የኒቅያ ጉባኤን ውሳኔ ሃይማኖት ወይም አንቀጸ ሃይማኖት ሲያጸድቁና አርዮስን ሲያወግዙ በቆስጠንጢኖስ ቤተ መንግሥት ሞገስ የነበራቸው እነ አውሳብዮስ ዘኒቆሞዲያ ደግሞ አርዮስን እና የአርዮስን ትምህርት እንዴት አድርገው በጓሮ በር ማስገባት እንደሚችሉ ይዶልቱ ነበር።

ይህን ለማድረግ ግን በጉሮሮ ላይ እንዳለ አጥንት ሆኖ ያስቸገራቸው አትናቴዎስ የክርስቶስ ሐዋርያ ነበር። በኒቅያ ጉባኤ ሊቀ ዲያቆን ሆኖ አርዮስን ከረታ በኋላ ሟቹን እለእስክንድሮስን ተክቶ በማርቆስ ወንበር ላይ ተቀመጠ። በመንበሩ ላይ የተቀመጠው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቅዶ የእስክንድርያ ምዕመናን በአንድ ቃል « ጻድቁን፥ ትጉሁን፥ እውነተኛ ክርስቲያኑን፥ ገዳማዊን አትናቴዎስን ስጡን፥ ፓትርያርካችን እርሱ ነው» በማለት በአንድ ቃል ጮኸውን ነው።

የኒቆሞድያ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚዶለተው ዱለት ግን አትናቴዎስን እንዴት አድርጎ ማስወገድ እንደሚቻል ማጠንጠን ነበር፤ የመጀመሪያው አርሳንዮስ የሚባል አንድ ጳጳስ በአስማት አስገድሎአል የሚል ክስ ነበር የቀረበበት። እርሱን ለማውገዝ በጢሮስ ጉባኤ ተጠራ፤ በዙሪያው እርሱን ለማውገዝ አሰፍስፈው የነበሩት አርዮሳውያን ጳጳሳት ነበሩ፤ ክስ ብቻ ሳይሆን የተገደለው ጳጳስ እጅ ብለውም አንድ የተቆረጠ እጅ አምጥተው ገድሎት በእጁ ያሟርትበታል ብለው በአትናቴዎስ ፊት ሲያስቀምጡ፥ ቤቱ በጩኸት ተቃጠለ፤ አትናቴዎስ ግን ምንም ሳይነዋወጥ « ለመሆኑ ይህ እጅ የአርሳንዮስ ለመሆኑ እርግጠኛ ናችሁ?» አላቸው። « አዎ! በሕይወት ሳለ በሚገባ እናውቀዋለን» ብለው መለሱለት። ከዚያ አትናቴዎስ ተከትሎት ወደመጣው አገልጋዩ መለስ ብሎ በዓይኑ ጠቀሰው፥ ያን ጊዜ በእድሜ የሸመገለ አባት ሰዎች ይዘው ወደ ጉባኤው ገቡ፤ ያን ጊዜ አትናቴዎስ « ለመሆኑ ይህ ማንነው? አርሳንዮስ ነው?» በማለት ጠየቃቸው። ሁሉም በአድናቆትና በጸጥታ ተዋጠ፤ ምክንያቱም ገድሎታል ተብሎ የተከሰሰበት አባት አርሳንዮስ በፊታቸው ቆሞ ነበር። በመቀጠል ጥያቄውን አቀረበ « እጁን አጥቶአል ያላችሁት ይህ ሰው ነው? ብሎ ጠየቀ። ቀስ ብሎ የሽማግሌውን የአርሳንዮስን እጅ ከፍ አድርጎ አሳያቸው፤ የአርሳንዮስ እጆች ሁለቱም በመልካም ሁኔታ ላይ ነበሩ። ፤ አትናቴዎስ ቀጠለ « እንደምታዩት አርሳንዮስ የተገኘው ከነሁለት እጆቹ ነው፤ አሁን ከሳሾቼ ሦስተኛው እጅ ከየት ቦታ እንደተቆረጠ ያሳዩኝ!» አላቸው። የሚያስገርመው እንዲህ ሐፍረት በከሳሾቹ ላይ ቢያጋጥማቸውም ሌላ ክስ ከየትም ፈልገው በዚያው በጢሮስ ባደረጉት ጉባኤ አትናቴዎስ ከመንበሩ እንዲሰደድ ወስነው ነበር፤ የሚያስቀው አትናቴዎስን ያሳደደውን ጉባኤ የመሩት፥ በጎልጎታ አዲስ የተሠራውን ቤተ ክርስቲያን ለመመረቅ በአንድነት ከንጉሡ ጋር ተያይዘው ነበር የሄዱት፤

የአትናቴዎስ ጥፋት ምን ነበር? ለእውነት መቆሙ ነበር። ለክርስቶስ እውነት፤ ኑፋቄ ሆኖ የተገኘበት ደግሞ ለቁስጥንጥንያ ፖለቲካ አለመመቸቱ ነበር፤ ኑፋቄው የፖለቲካ ስለሆነ በኑፋቄ ፖለቲካ መወገዝ ነበረበት፤ ታሪክ እንደሚነግረን አትናቴዎስ አብዛኛውን የሊቀ ጵጵስና የአገልግሎት ዘመኑን ያሳለፈው በስደት ነበር።

ግላዊ ሕይወት፥ ግላዊ ነጻነትና እና የአዲሱ ዘመን ተግዳድሮት፤ ለውይይት መነሻ አሳብ

ከሰሞኑ አፈትልኮ የወጣው ምሥጢራዊ ሰነድ እንዳመለከተው ከሆነ፥ በዚህ በአገረ አሜሪካ የሚገኘው የብሔራዊ ጸጥታ ድርጅት (National Security Agency) የዜጎችን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ በተለይም በኤሌክትሮኒክስ መልክ የሚካሄደውን የመረጃ ልውውጥ እንደሚከታተል ወይም እንደሚሰልል ነው። ይህ ስለ አገር ጸጥታ በሚያስቡ ወገኖች ዘንድ ትልቅ ራስ ምታት ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ የግለሰብን ነፃነትና መብት ለማስከበር ደፋ ቀና ከሚሉት ጀምሮ ስለ ሃይማኖት ነፃነት እስከሚያስቡ ድረስ፥ በግለሰቦች ሕይወት ውስጥ የመንግሥት ሚና ምን ያህል መሆን አለበት የሚል ከፍተኛ ክርክር አስነስቶአል። አንዳንዶች አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ከሆነው የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ አንጻር መንግሥት ምንም አማራጭ እንደሌለው ሲናገሩ፥ ሌሎች ደግሞ ይህ አይነቱ እጅግ የተንሰራፋ ሥልጣን ፍጻሜው ምን ይሆናል ይላሉ።

ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓይነቱ ውይይት ላይ ድምጽ ሊኖራት እንደሚገባ እሙን ነው። ለምሳሌ ሃይማኖታዊ ነጻነትን የሚጋፋ ነው ወይ? በአበ ነፍስና በተነሳሒው መካከል የሚኖረውን ምሥጢራዊ ግንኙነት የሚደፍር ነው ወይ? በአሁኑ ወቅት ካለው የጥድፊያ ኑሮ አንጻር አንዳንድ ጊዜ የምክር አገልግሎት በኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ልውውጥ ሲከናወን ይታያልና።

ያም ሆነ ይህ በአገርና በሕዝብ ላይ ጉዳት የሚያመጡትን አሸባሪዎች ለመያዝ  የሚደረገው ጥረት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ሁሉ የግለሰቦች መብት በምን መንገድ መከበር እንዳለበት ሰፊ ውይይት ሊደረግ ይገባል ለማንኛም ግን እጅግ በማደንቀው በቴክኖሎጂ መዝናኛ እና ንድፍ ባለሙያዎች ስብሰባ ላይ ታዋቂው የቴክኖሎጂ አታቲJuan Enriquez  ያስቀመጠውን ንግግር በማስተዋል ማድመጥ ይገባል፤

ዩአን የሚለን ነገር ቢኖር፥ በድረገጽም ሆነ በሌላም የዲጂታል መገናኛ ዘዴዎች የምንለዋወጣቸው ነገሮች የእኛን ዘመን አልፈው የሚኖሩ ናቸው፤ ጥያቄው ያን እያሰብን ነው ወይ የምንነጋገረው፤ ብዙዎቻችን ዛሬ ማንም አያየውም ያልነው ግላዊ ነጻነቶች (private activities) ነገ የአደባባይ ምሥጢሮች ናቸው። ነገ ስንል ከሞትን በኋላ አይደለም። ቃል በቃል ነገ። ተወያዩበት። 

Tuesday, June 18, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት ( ስድስተኛ ክፍል)

    READ IN PDF
   ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም። ብርሃን ዘእምብርሃን አምላክ ዘእምአምላክ ዘበአማን። 
  ዘተወልደ ወአኮ ዘተገብረ ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ። ዘቦቱ ኲሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ ዘበሰማይኒ ወዘበምድርኒ። 
    

ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ከአብ ጋር የሚተካከል። ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለእርሱ ግን ምንም የሆነ የለም በሰማይም ሆነ በምድርም ሆነ 

በክፍል አምስት ትምህርታችን የግዕዙን አቀማመጥ ተከትለን   ቤተ ክርስቲያን ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ጌታ እንደተባለና ኢየሱስ እና ክርስቶስ የሚሉት ስሞቹ የሚያመለክቱት ምን እንደሆነ። ዛሬም ከዚያው በመቀጠል ዘለዓለማዊነቱንና ፈጣሪነቱን የሚናገሩትን ቃላት እናብራራለን። 

1. ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን፤ 

አርዮስ ከወደቀበት ስህተት አንዱ የወልድን ዘለዓለማዊነት መካድ ነው። በእርሱ እምነት ተወለደ እና ተፈጠረ የሚሉት አንቀጾች አንድ ስለሆኑ « ወልድ ያልነበረበት ጊዜ አለ።» በማለት ያስተምር ነበር  ። ሆኖም በኒቅያ የተሰበሰቡ አባቶች የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት አድርገው በሥጋ የተገለጠው ወልድ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ ጋር እንደነበረ፥ ተቀዳሚ እና ተከታይ የሌለው የአብ ልጅ እንደሆነ አስተምረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ወልድ ከሥጋዌ በፊት ማለት ሰው ከመሆኑ በፊት በቅድምና በዘለዓለም ከአብ ጋር እንደነበረ በግልጥ ያስተምረናል። ዮሐንስ ስለዚህ ሲናገር  « በመጀመሪያ ቃል ነበረ።» ይለናል። ዮሐንስ 1፥1። ይህ ቃል ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር ጋር የነበረ መሆኑንም ሲነግረን « ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» ይለናል። ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእመቤታችን ከመወለዱ በፊት ነዋሪ መሆኑን ሲናገር « አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ።» ወይም « አብርሃም ሳይወለድ እኔ ነኝ» በማለት አስተምሮአል። ዮሐንስ 8፥58።  

ስለ ጌታ ኢየሱስ ዘላለማዊነት የነቢያትን ምስክርነትም እናገኛለን። በትንቢተ ኢያሳይያስ ላይ ከቅድስት ድንግል ስለሚወለደው ሕፃን ሲናገር «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።» በማለት በሥጋ የተገለጠው አምላክ « የዘላለም አምላክ» እንደሆነ ገልጦአል።( ኢሳይያስ 9፥6። )  ዳዊትም ስለ ጌታ ዘለዓለማዊነትና፥ በሞት ላይ ድል አድራጊ ስለመሆኑ ስለትንሣኤውና ስለ ዘለዓለማዊ ክህነቱ በተነገረበት በመዝሙረ ዳዊት ላይ « ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ>> በማለት ተናግሮአል። መዝሙር 109፥3። ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ማለት በሌላ አነጋገር ከጊዜያት በፊት የነበረና ጊዜያትን የፈጠረ ማለት ነው። ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንደተናገረው «  የጊዜያት ባለቤት ለጊዜ አይገዛም።»። 

Tuesday, June 11, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (አምስተኛ ክፍል



ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ የምትመሰክራቸው እውነቶች 

በኒቅያ የተሰበሰቡት አባቶቻችን በአርዮስ የቀረበላቸውን የስህተት ትምህርት ፊት ለፊት በእግዚአብሔር ቃል ሲቃወሙት በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ተከትላ የምታስተምረውን ትምህርት በሚገባ መግለጥ ነበረባቸው።  በሚቀጥሉት ክፍሎች የምናገኛቸው ሐረጎችና ቃላት አባቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምራቸው እውነቶች ጠቅለል አድርገው የገለጡበት ክፍል ነው። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በመያዝ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ አምላክነቱን አስተምራለች ዋጋም ከፍላበታለች።  

1.  በአንዱ ጌታ እናምናለን።
(ወነአምን በአሐዱ እግዚእ፤) 
መጽሐፍ ቅዱስ በሥጋ የተገለጠውን እግዚአብሔር ወልድን ከሚጠራበት ስሞች አንዱ ጌታ ብሎ ነው። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችም « በአንዱ ጌታ» ብለው ተናግረዋል።   ጌትነቱን የምንናገረው በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ነው። « በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። » (1 ቆሮንቶስ 12፥3) በአፋችን ጌትነቱን መናገራችን የደኅንነታችን ምክንያት ነው። « ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና » ሮሜ 10፥9። የአባቶችን ነገረ መለኮት በምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቅ የተመሰገነው ቶማስ ኦዴን እንዳሳሰበን ክርስቶስን በምድር ሲመላለስ ብቻ ጌታ ብንለው ኖሮ ምናልባትም አስተማሪ ወይም አለቃ መሆኑን ማስተዋወቂያ ነው። ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ ጌታ መባሉ በአሁኑ ዓለምም በሚመጣውም የእግዚአብሔር መንግሥት እርሱ ገዢ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሐምሳ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ « እናተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።» በማለት የተናገረው። (ሐዋ ሥራ 2፥6 ) ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በነገረ ጥምቀት ትምህርቱ እንዳለው « እርሱ ጌታ ነው፤ ጌትነቱም ደረጃ በደረጃ ያገኘው ሳይሆን በባሕርዩ ጌታ በመሆኑ ያገኘው ክብር ነው።» 

ጌታ ኢየሱስ ስንል ምን ማለታችን ነው? በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት ጌታ ኢየሱስ የሚለው ቃል ዋጋ የሚያስከፍል ቃል ነበር። ለሮም ግዛት (Roman Empire) በሰዎች ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት ጌታ የነበረው ቄሣር ነበር። በመሆኑም ቄሣር ይሰገድለት ይመለክ ነበር።  በብሉይ ኪዳን የሰብአ ሊቃናትን ትርጕም (ሰብትዋጀንት) ከተከተልን ከስድስት ሺ ጊዜ በላይ ያህዌ የሚለውን የእብራይስጥ ቃል « ጌታ» ተብሎ ተተርጉሞአል። ስለሆነም ጌታ ኢየሱስ ማለት ከቄሣር ተቃራኒ አድርጎ የሚያስቆም « ፓለቲካዊ አቋም» ብቻ ሳይሆን፥ ይህ ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ሙሴን የተናገረው « እኔ ነኝ » ያለውና ነቢያቱን የላከው መሆኑን ነው። ይህ « እኔ ነኝ » ማለት አቻ ወይም ተቃራኒ አልባ ብቸኛ አምላክ ማለት ነው።በጥንት አማርኛ የተጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ጸሎተ ሃይማኖት ትርጓሜ ስለዚህ ቃል ሲናገር «በሐንድ ጌታ ምን አሰኛቸው፥ ሌላ ጌታ አለን ያሉ እንደሆን። ጌታስ መኰንንም፥ ካበላ ካጠጣ ጌታ ይልዋል። እርሱ ግን አጋዙን ቀድሞም ከሰው ያላመፃው፥ ኋላም ለሰው ያያሳልፈው፥ በባሕርዩ በጠባይዕ ገዢ በሐንድ አምላክ ነአምናለን አሉ።» ይለናል።  

  1. ኢየሱስ ክርስቶስ  
 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሥጋ የተገለጠው ቃል የተጠራባቸው ብዙ መጠሪያዎች ቢኖሩም በዋናነት የሚታወቁት ሁለቱ ናቸው፤ እነርሱም ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ናቸው።  ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ስሞች ያላቸውን የነገረ መለኮት አንድምታዎች በሚገባ በመተንተን ከጻፉ ቀደምት ጸሐፊዎች መካከል « የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት» (the father of church history)  ተብሎ የሚታወቀው አውሳብዮስ ዘቂሳርያ ዋናው ነው። አውሳብዮስ ስለ ጌታ ስሞች ሲያብራራ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነገሮች ይነግረናል። አንደኛው ኢየሱስ እና ክርስቶስ የሚለው ስም ከጥንት ጀምሮ በነቢያት የተነገሩና በመላእክት የተበሠሩ ስሞች ናቸው። ሁለተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አምላክነት የሚያሳዩ ናቸው ሦስተኛው እነዚህ ስሞች የጌታን አዳኝነት የሚያመለክቱ ናቸው።   ለዚህ ዋና ምሳሌ አድርጎ የሚያነሣልን ሙሴን ነው። ሙሴ እስራኤልን በመሪነት ሲያስተዳድር ከእግዚአብሔር በተቀበለው ትእዛዝ መሠረት ከሾማቸው የአገልግሎት ሹመቶች መካከል ዋና የሚባሉት ሁለት እንደሆኑ ይጠቅስልናል፤ እነዚህም ሊቀ ካህናቱን አሮንንና ራሱን ሙሴን የተካውን ኢያሱን የሾመበት ነው። አውሳብዮስ እንደሚለን « « በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ» በማለት እንዳዘዘው ቃል የሰማያዊ ነገሮችን አምሳልና ምልክቶች፥  በመጠቀም ክርስቶስ የሚለውን ስም የተለየ ታላቅነት እና ክብር ያለው ስም እንደሆነ እንዲታወቅ በማድረግ የመጀመሪያው ሙሴ ነው። (ዘፀአት 25፥40)ከሰዎች ሁሉ ከፍ ያለውን  የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህን በገለጠበት ወቅት " ክርስቶስ" ወይም " የተቀባ" ብሎ  ጠርቶታል። በእርሱ እይታ ከሰዎች ሁሉ ክብር ከፍ ባለው በዚህ የሊቀ ካህንነቱ አገልግሎት  ሊቀ ካህኑ የክብርና የከፍታ ምልክት ይሆንለት ዘንድ ክርስቶስ የሚለውን ስም ሰጥቶታል። (ሌዋውያን 4፥5፡16፤ 6፥22) » 
  
ለኢያሱ ሲነግረንም፥ ራሱ « ኢያሱ» የሚለው ስም ኢየሱስ ከሚለው ስም ጋር እንዴት ዓይነት ግንኙነት እንዳለው ሲነግረን ኢያሱ « ወላጆቹ ባወጡለት በሌላ ስም አውሴ በመባል ነበር የሚታወቀው። ሙሴ ግን ከነገሥታት ዘውድ የሚበልጠውን፥ ገንዘብ የማይገዛውን እጅግ ክቡር የሆነውን ስም ሊሰጠው ኢየሱስ (ኢያሱ) ብሎ ጠራው።ከሙሴ በኋላና አምሳላዊው አምልኮ ለሰዎች ሁሉ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ከተፈጸመ በኋላ በእውነተኛው ንጹሕ በሆነው እምነት ላይ በመሪነት የተቀመጠው የነዌ ልጅ ኢያሱም የአዳኛችንን ምሳሌ ተሸክሞ ነበር።  » ይህ የአውሳብዮስ ትንተና መልክአ ኢየሱስን በጻፈው የቤተ ክርስቲያናችን ደራሲ በግልጥ ተቀምጦአል
   « አክሊለ ስምከ እንዘ ይትቄጸል በርእሱ፤ 
   « አኅጉረ ፀር ወረሰ ኢያሱ፤» 
       የስምህን አክሊል በራሱ ላይ አድርጎ 
      የጠላትን ሀገሮች ኢያሱ ወርሶአል።
      
ኢየሱስ የሚለው ስሙ 
      
ይህ የአውሳብዮስም ሆነ የመልክአ ኢየሱስ ደራሲ ትንተና የሚያሳየን ኢየሱስ የሚለው ስም የእግዚአብሔር ሕዝብን ከማዳን ጋር የተገናኘ ስም መሆኑን የሚያመለክት ነው። ምክንያቱም በእብራይስጥ የሹኣ፥ ኢያሱ ወይም ኢየሱስ የሚለው ስም በእብራይስጡ « ያሕዌ መድኃኒት ነው» የሚል ትርጉም አለው።  ማቴዎስ ወንጌሉን በተለይ ለአይሁድ የጻፈ እንደመሆኑ፥ በአይሁድ ዘንድ ተስፋ የተነገረለትን የዚህን ስም ትርጉም በመልአክ እንደተነገረው በጽሑፍ አስፍሮታል። የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ሲነግረው « ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።  » ነበር ያለው። ማቴዎስ 1፥21። አውሳብዮስም ሆነ ከእርሱ በኋላ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የመልአኩ ቃል ያስተዋሉት፤ (ወንጌላዊውም ጭምር ማለት እንችላለን) የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ የነገረው ስም የእግዚአብሔር ስም መሆኑን ነው። እርግጥ ነው፥ በትንቢት፥ በምሳሌና በጥላ ቀድሞ ለተነሡት « አዳኞች» ኢያሱዎች ተሰጥቶአል። (ለምሳሌ ዘካርያስ 3፥1 ላይ የተጠቀሰውን ከምርኮ በኋላ እስራኤልን የመራው ሊቀ ካህናቱን ኢያሱን ያስታውሷል።) 

Tuesday, June 4, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት አራተኛ ክፍል

 Read in PDF
ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም። 
ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።

  

መግቢያ 

በነገረ መለኮት ትንታኔው የሚታወቅ አንድ ሊቅ ሲናገር የሃይማኖት ስህተቶች ሁሉ የሚጀምሩት የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ባለመረዳት ነው ብሎአል። በመሆኑም የጸሎተ ሃይማኖት መሰጠትንም ሆነ ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ ያለውን ጊዜ ተከትለው የተደረጉትን ጉባኤያት ብንመለከት በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚሰነዘሩት የስህተት ትምህርቶችን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ልንገልጣቸው ቶማስ አኵናስ የተባለው ሊቅ ይነግረናል። 

• ክርስቶስ ሰው ብቻ ነው የሚሉ፤ 
ለምሳሌ ፎጢኖስ የተባለው « ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፤ ነገር ግን መልካም ሰው ነው። በመልካም አነዋወሩና ሕይወቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማድረጉ በማደጎ (adoption) የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ተጠርቶአል» በማለት አስተምሮአል። ያ ብቻ አይደለም የክርስቶስ ሕልውና የሚጀምረው ከማርያም ከተወለደ በኋላ ነው በማለት ክርስቶስ በጊዜ የተወሰነ እንደሆነ አስተምሮአል። የእግዚአብሔር ቃል ግን እነዚህ አስተሳሰቦች ሐሰት እንደሆኑ በግልጥ ይመሰክራሉ። ዮሐንስ በወንጌሉ « እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለው አንድ ልጁ እርሱ ተረከው» በማለት ወልድ በቅድምና ከአብ ጋር እንደነበር ይናገራል። ዮሐንስ 1፥18፤ ኢየሱስም ራሱ « አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ» ብሎ ሲናገር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከመወለዱ በፊት ከአብርሃም በፊት መኖሩን ነግሮናል። ዮሐንስ 8፥58። 

• ክርስቶስ ራሱ አብ ነው የሚሉ፤ 
በዚህ ስህተቱ የታወቀው ሰባልዮስ የተባለው ሰው ነው። ሰባልዮስ ጌታ ቅድመ ዓለም መኖሩን ያምንና ነገር ግን በሥጋ የተገለጠው ቅድመ ዓለም የነበረው አብ ነው ብሎ ያስተምር ነበር። በእርሱ ትምህርት አብና ወልድ ሁለት አካላት ሳይሆኑ አንዱ አብ ነው በተለያየ መንገድ የተገለጠው። አሁንም የሰባልዮስን ስሕተት የእግዚእብሔር ቃል በግልጥ ይቃወመዋል። ጌታ ራሱ « የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁም» በማለት ከአባቱ እንደተላከ» በዮሐንስ 8፥16 ላይ ገልጦአል። 

• ልዩ ፍጡር ነው የሚሉ፤ 
አርዮስ የተባለው የስሕተት አስተማሪ ስለጌታ ያስተማረው ትምህርት ከቅዱሳት ጋር የሚቃረን ነበር፤ አንደኛ ክርስቶስ ፍጡር ነው። ሁለተኛ፥ ከዘለዓለም ያልነበረና ከሌሎች ፍጡራን ልዩ አድርጎ እግዚአብሔር የፈጠረው ነው ። ሦስተኛ፥ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ ስላይደለ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም እውነተኛ አምላክ አይደለም በማለት ያስተምር ነበር። አሁንም የአርዮስን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ሲሽርበት ጌታ « እኔና አብ አንድ ነን» በማለት በባሕርይ ከአባቱ ጋር አንድ መሆኑ ሲገልጥ እናያለን።  

እነዚህ ከላይ ያያናቸው በየዘመኑ ከተነሡት ለናሙና ያነሣናቸው ስህተቶች ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በክርስቶስ ላይ ለሚሰነዘሩት ስህተቶች መሠረቶች ናቸው። « የኑፋቄ አዲስ የለውም» የሚባለው ለዚህ ነው። ሆኖም ቶማስ አኵኖስ ይህ ሁሉ በየጊዜው የሚነሣው ስህተት  ወንጌላዊው ዮሐንስ  በወንጌሉ መክፈቻ ላይ ያስቀመጣቸው ዐረፍተ ነገሮች « በመጀመሪያ ቃል ነበር» የፎጢኖስን « ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» የሰባልዮስን፥ « ቃልም እግዚአብሔር ነበረ» የአርዮስን ስህተት ይደመስሰዋል ብሎአል ።   

ኢየሱስ ማንነው? 

በጊዜው  በሥጋ ያዩት የሃይማኖት መሪዎች፥  የሕዝብ አስተዳዳሪዎች፥ ደቀ መዛሙርቱ እና ሌላውም ሕዝብ  በአንድነት የጠየቁትን ጥያቄ እርሱ ማንነው? የሚል ነው። እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው በማለትና  በመጠየቅ ስለ አዳኛችን ስለመድኃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥልቀት እናጠናለን።

ሽባውን ሰው « ኃጢአትህ ተሰረየችልህ» ሲለው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ያሉት « ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?  ብለው ያስቡ ጀመር።» ሉቃስ 5፥21። እንደገና ኃጢአተኛዋን ሴት « ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል» ሲላት በማዕድ ከርሱ ጋር ተቀምጠው የነበሩት « ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?» ብለው ነበር። ሉቃስ 7፥48-49።  ዮሐንስን ያስገደለው ሄሮድስም  « ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው?  » በማለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማየት አጥብቆ ይሻ እንደነበረ ሉቃስ ይነግረናል? ሉቃስ 9፥9። ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባና ከተማዋ ስትናወጥ ሕዝቡ « ይህ ማነው?» በማለት ነው የጠየቁት። ደቀ መዛሙርቱም በብዙ ቦታ ስለጌታ የበለጠ ለማወቅ ፈልገው በፍርሃት ዝም እንዳሉ እናያለን? ሉቃስ 9፥45።   
በእነዚህ ሁሉ ሰዎች እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከሁን በተነሳውም ትውልድ ይህ ማነው የተባለውን፥  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በኒቅያ የተሰበሰቡ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች የገለጡበትን መንገድ ለመረዳት በወንጌል ላይ ጌታ ስለራሱ የተናገረውን መረዳት ይገባል።